Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 20 October 2012 09:50

“መስመሮች ሁሉ ተይዘዋል!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ብዙ ነገር በኔትወርክ ተጨናነቀሳ! የምር… “መስመሮች ሁሉ ተይዘዋል…” የሚለው ነገር ለሞባይል ብቻ መሆኑ ቀርቶ በብዙ ነገር ‘ኔትወርክ ተጨናንቆ’…አለ አይደል… “መስመሮች ሁሉ እየተያዙ…” ተቸግረናል፡፡
እናማ…“ኔትወርክ ተጨናንቋል…” እንዴት አሪፍ ኮድ እየሆነ መሰላችሁ፡፡ በቃ…አለ አይደል…ተናጋሪውና አድማጩ የሚተዋወቁበት ኮድ በሉት፡፡
ለምሳሌ እሱዬው እንትናዬን ይቀጥርላችኋል፡፡ እሷዬዋም፣

“አምስት ሰዓት ቀደም ብለህ ደውልልኝና እዛ ቦታ እንገናኛለን…” ትለዋለች፡፡ እናላችሁ… እሱዬውም ሰዓቱ ሲደርስ ይደውልና “እዛው ነሽ! ልምጣ እንዴ!” ይላታል፡፡ (በነገራችን ላይ “ልምጣ እንዴ!” ከምትለው የሁለት ቃላት ጥያቄ ጀርባ ያሉትን ጥያቄዎችና… “ያው እንግዲህ አስቸገረኝ ያልሽው ቁርጥማት ምናምን ትቶሻል አይደል!” የሚሉት ስውር መልእክቶች ግንዛቤ ይግቡማ!) 
ይሄኔ ምን ልትለው ትችላለች መሰላችሁ…“እኔ ልደውልልህ ኔትወርክ ተጨናንቋል…” አሪፍ አይደል! “አካባቢው በሰው ተሞልቷል…” ማለት የለ፣ “የአጎቴ ሚስት አውቶብስ ፌርማታው አጠገብ ቆማለች…” የለ፣ “የወንድሜ ጓደኛ ከሩቅ ሆኖ ጫማ እያስጠረገ እያየኝ ነው…” ብሎ ለሰው መጋለጥ የለ…በቃ “ኔትወርክ ተጨናንቋል፡፡”
እናላችሁ፣ እንግዲህም ጨዋታም አይደል……ዘንድሮ ብዙ ነገሮች ላይ ‘የኔትወርክ መጨናነቅ’ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ በቀጥተኛውና ‘አገር ባወቀው’ መንገድ የሚሄድ ሁሉ እንደ ድንጋይ ዘመን ሰው የሚታይበት ጊዜ ሆኖላችኋል፡፡ ጥሩ የሚባል ነገር፣ መልካም የሚባል ነገር፣ አሪፍ ነገር ያለበት ነገር ሁሉ በኔትወርክ ተጨናንቆ ታገኙታላችሁ፡፡ ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ኔትወርኩን ካጨናነቁትተ መሀል የምታውቁተ ሰው መቼም ማግኘት አለመቻላችሁ፡፡ እኔ የምለው…ጥያቄ አለን፡፡ አሪፍ፣ አሪፍ ነገሮች ሁሉ በዕድርም፣ በዕቁብም በ“አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች…” ኢንተርቪውም በማናውቀው ‘ፖፑሌሽን’…ኔትወርኩ የሚጨናነቅበት…እኛ የማናውቃትና እኛ የማናውቃቸው ‘ዘመድ አዝማዶቻችን’ የተሰበሰቡባት ‘ኤስኮርት’ አገር አለችን እንዴ! ልክ ነዋ…“ይሄ እኮ እንትና ነው…” “ያቺ ጥግ ላይ ያለችው እከሊት ናት…” ማለት ሲያቅተን ምን እንበል!
እናላችሁ… ብልጦቹ ‘ሀከሮች’ (ያው ‘ሰብረው’ አይደል የሚገቡት!) ‘ኔትወርኩን’ እያጨናነቁብን ከወጪ ቀሪውም እያረረብን…አለ አይደል… ጦም እያደርን ነው እላችኋለሁ፡፡
ሥራ ፍለጋ በዋና በቀለበት መንገድ ሄደው የሚያመለክቱ… ነገርዬው በ“ካዛንቺስ ሃያ ሁለት በአቋራጭ…” አይነት ነገር ‘ኔትወርኩ ተጨናንቆ’ ትርፉ በሌለ ገንዘብ የፎቶ ኮፒ ወጪ ማብዛት ብቻ እየሆነ ችግር የሚፈጠርበት መአት ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ነገርየው ሁሉ እንዲህ ከሁሉም ጨዋታ ውጪ ሲያደርጋችሁ…በቃ፣ “ምነው ያኔ ኔትወርክ ቅብጥርስዮ ምናምን የሚሉት ነገር የሌለበት ዘመን በመጣ…” ለማለት ምንም አይቀራችሁ፡፡
ስሙኝማ…የኋላ ዘመንን ነገር ካነሳን አይቀር፣ ጊዜ መለወጡን ያላወቅን ሰዎች ግራ እየገባን ነው፡፡ መቼም እዚች አገር ላይ…አለ አይደል…ምንም ነገር ‘በበፊት ጊዜ እኮ…’ ብላችሁ የሆነ ነገር ስታነሱ ያው የተለመዱት እርግማኖች ነበሩ፡፡ አሁን፣ አሁን በብዙ ነገር ‘ማጣፊያው እያጠረ’ መጣ መሰለኝ መለስ ብሎ አንዳንድ ነገሮችን በ‘መልካም ጎናቸው’ ማንሳት መጀመሩ ሸጋ ነገር ነው፡፡ (እኔ የምለው…እንደ ሦስተኛው ዓለም ‘ቦተሊካ’ ቀሺም ቲራቲር አለ! የምር! ነገርዬው…አለ አይደል…“ከእኛ በፊት የነበረው ሁሉ ውጉዝ ከመአርዮስ ስለሆነ አፍርስልኝ! አጥፋልኝ! ደህና አድርገህ ውቀጥልኝ!…” አይነት ነገር እየሆነ ነገርዬው ሁሉ “የእንትን ነገር ሁልጊዜ አበባዬ…” ይሆንላችኋል፡፡ ልክ… “አሁን ደበበ ሰይፉ ምኑ ገጣሚ ነው!” የሚሉ የግጥም ሲንግል የለቀቁ ገጣሚዎች አይነት፡፡
እናላችሁ… ካነሳን አይቀር፣ የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጥ የለ…ልጄ… ቀይ ወጥ መጋበዝ አሪፍ የነበረበት ዘመን ነበር፡፡ የምር የበፊት የምግብ ቤቶች ቀይ ወጥ እኮ ወደ ጓሮ አሥሬ አያንደረድርም፡፡ ያኔ ቀይ ወጥ፣ በቃ ቀይ ወጥ ነበር! እንደ ዘንድሮ ሪሚክስ ቀይ ወጥ አልነበረም፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) ትናንት ቋንጣ ፍርፍር የበሉ ጊዜ ሲሄዱ የተዉአት አንድ ሁለት የሥጋ ቅንጣቢን በዛሬው ቀይ ወጥ ውስጥ ሪኮግናይዝ ሊያደርጉ ይችላሉ! እንዲህ ‘ስትሬንጅ’ ዘመን ላይ ደርሰናል እላችኋለሁ!
በነገራችን ላይ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ለምግብ ውጪ የሚያዘወትሩ ሰዎች የሚበሉበትን ቦታ በጥንቃቄ መምረጥ ያለባቸው ዘመን ነው፡፡ በየጓዳው ደስ የማይሉ ነገሮች ይሠራሉና! ስለጣፈጠ ብቻ አሪፍ ነው ማለት አይደለም፡፡ አንድ ወዳጄ ለጁስ የሚያዘወትረው ቦታ ድንገት ወደ ጓዳ ብቅ ሲል ሊጣሉ የሚገባቸው የፓፓያ ፍሬዎች ለጁስ በእጅ ሲቦኩ ተመልክቶ አንድ ሰሞን በዛ በኩል ማለፍ እንኳን አስጠልቶት እንደነበር አጫውቶኛል፡፡
እናማ ዘንድሮ ልጄ…ብቻ እንኳንስ ሶፍት በብር፣ በብር መንገድ ላይ ተገኘ እንጂ ተበልቶ በአሥራ አምስተኛው ደቂቃ ሆድ ውስጥ የደቡብ አሜሪካው ‘ኸሪኬን ምናምን…’ የሚመስል አይነት ረብሻ ይጀምራል፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ዘንድሮ ከተማዋን የሞሉት ሸላዮች ቀይ ወጥ ምን እንደሆነ ያውቃሉ! የእኔ ቢጤው የዘመን ባቡር በካቻምናው ጣቢያ ላይ እንደቆመ የቀረበት፤ “ምሳ ብጋብዝሽ ምን ይመስልሻል?” ይላል፡፡
“በጣም ደስ ይለኛል፡፡”
ከዛ የሆነ ሌሊት ለብሶት ባደረው ልብሱ የሚታዘዝ አሳላፊ በሽ በሽ የሆነበት ምግብ ቤት ይገባና ያጨበጭባል፡፡ እናላችሁ…እንትናዬዋ እሱዬው የዘንድሮ አራድነት ኔትወርክ ተጨናንቆበት ገና በር እያንኳኳ መሆኑን አላወቀች “የሚያዝልን ክትፎ ኖርማል ይሆን ስፔሻል!” እያለች የራሷን ካልኩሌሽን ትሠራለች፡፡ (በነገራችን ላይ…የእኔ ቢጤ ‘የውሀ ቀለም ቅቦች’ እኮ በባዶ ኪስም ‘የተረፋቸው’ የሚመስሉበትን ጥበብ ተክነዋል፡፡)
እናላችሁ…አሳላፊው ሲመጣ…አለ አይደል…“ስማ እስቲ እዚህ ጋ ሁለት ቆንጆ ቀይ ወጥ!” ይላል፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ… መጀመሪያ ለእሷዬዋ ቀይ ወጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡
አንዴ ከተረዳችና ድንጋጤዋ ትንሽ ቀለል ካለላት በኋላ ምን ትዝ ይላታል መሰላችሁ… ገና ስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ስታልፍ አክስቷ “ጠላትሽ ካጠገብሽ ነው የሚመጣውና ዝም ብለሽ ማንንም ጓደኛ አታድርጊ…” ያሏት ትዝ ይላታል፡፡እግረ መንገዴን……የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… በፊት እኮ ስም እየተጠቀሰ “እሱን ጓደኛህን ጠንቀቅ በለው፡፡ የሚያጠፋህ እነሱ ነው…” ምናምን የሚባል ምክር ነበር፡፡ ዘንድሮ እንዲህ የሚል መካሪ ጠፋሳ!
እኔ የምለው ጦር ማስቲካ አሁንም አለ እንዴ! ማንም ማስተካ ማኘክ ያለበት ሁሉ፤ ነገር እያኘከ የማስቲካዎቹ ስምም እየጠፋን ነው፡፡ እነ እንትና በድቡልቡል ማስቲካ ስንቱን አድቦለቦላችሁት! ቂ…ቂ…ቂ….
ደግሞላችሁ…አለ አይደል…አራዶቹ በ‘ቦክሰኛ ኬክ’ ግብዣ ስንት… ጓንት የማይደረግበት… እጅ በቡጢ መልክ የማይጠቀለልበት…ተጋጣሚዎቹ በሁለት እግሮቻቸው ቀጥ ብለው የማይቆሙበት ፍልሚያ ይካሄድ ነበር፡፡
እናላችሁ… ቦክሰኛ የተጋበዘች እንትናዬ… አይደለም ራሷ እንትናዬዋ፣ ቤተዘመዶቿ የምስራቹን የሰሙት ዘመድ አዝማዶቿ ሁሉ ሲመርቁት ሊከርሙ ይችላሉ፡፡
ያኔ “ቦክሰኛ ኬክ” ማለት እኮ የዛሬው ስፔሻል ክትፎ ሲደመር ዋይን ምናምን አይነት ግብዣ እንደ ማለት ነው፡፡ (ከግብዣው በኋላ ያሉት ትዕይንቶች ላይ ስር ነቀል ለውጥ መኖር አለመኖሩን ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡)
እናላችሁ… ለሌላ እንኳን ባይሆን ለኔትወርክ ሲል ዘመን በኋላ ማርሽ በሄደ ሊያሰኙን የሚችሉ ነገሮች እየበዙብን ነው፡፡ በሁሉም ነገር ‘መስመሮች ሁሉ ሲያዙብን…’ አይደለም ትናትን ከትናንት ወዲያንስ የማንመኝሳ!
“መስመሮች ሁሉ ተይዘዋል!” ከሚለው መሳቀቅ ይጠብቃችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

Read 4124 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 09:58