Saturday, 20 August 2022 13:58

የመንግስት ያለህ የሚያሰኘው የትግራይ ችግር!!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

 “ከትግራይ እወጣለሁ ብለህ ስታስብ ጎረቤት እንዳይሰማ ይደረጋል፡፡ ጎረቤት ጠቋሚ ነው፡፡ አላማጣ ስልክ እደውላለሁ ብለህ ነው የምትወጣው፡፡ እስከ አላማጣ ትራንስፖርት አለ፤ መቶ ሃምሳ ብር፣ ከአላማጣ ዋጆ ሃምሳ ብር ነው፡፡ ዋጆ ከደረስሁ በኋላ “ዛሬ ይቅርብሸ ለመከላከያ የሚያስረክቡ ደላሎች ተነቅቶባቸው ዋጃ ላይ እየተገረፉ ነው”  ተብዬ ነበር፡፡ ልወጣ ፈልጌ ስለነበር አልተቀበልኳቸውም፡፡ ሁለት ያልተነቃባቸው ደላሎች ስለነበሩ ከእነሱ ጋር አገናኙን፡፡ “የምወስዳችሁ ሕይወቴን ሰጥቼ ነው፤ ስለዚህ ድምጽ እንዳታሰሙ” አለን፡፡ ከእኛ ጋር የመጡት ሁለቱ አማርኛ አይችሉም፡፡ አንዷ የጥልፍ ሥራ ሙያ አላት፡፡ እዚያ ሥራ የለም፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ያኖራል እንጂ ኑሮ ውድ ነው፤ አንድ ጣሳ ስንዴ ሃምሳ ሁለት ብር ነው። ገብስ የተደባለቀበት አንድ እንጀራ የሚሸጠው ሃያ ብር ነው፡፡ ቡና ሩብ ኪሎ 180 ብር ነው። አንድ ኪሎ ስኳር 200 ብር ነው፡፡ ህክምና የለም፡፡ ትምህርት የለም፡፡ ከሕፃናት መዋያ እስከ ስድስተኛ ተከፍቷል፡፡ ከ7ኛ ወደ ትግል ይገባል፡፡ ስወጣ የተነገረኝ “የሕውኃት  ልዩ ኃይልና ፋኖ ካገኘሽ ለደላላውም ለአንቺም መጥፎ  ነው፡፡ መከላከያ ቀጥታ ካገኘሽ ግን ምንም አትሆኝም” ተብያለሁ፡፡ ዋጆ ላይ የሕወኃት ተላላኪ የሆኑት ይታወቃሉ፡፡ ፊትህ ላይ የመውጣት ፍላጎት እንዳለህ የሚያሳይ ስሜት ከታየብህ፣ ቀርበው “እኔም መውጣት እፈልጋለሁ” ይሉሃል፡፡ አዎ ካልካቸው አለቀልህ፡፡ ደላላውን ከአገኘነው በኋላ ከደላላው ቤት ዋልን፡፡ ለሊት ከሰባት ሰዓት በኋላ ጉዞ ጀመርን፡፡  ከአራት ደላሎች አንዱ አስተባባሪ ነው፡፡ “ስትራመዱ ኮቴያችሁ እንዳይሰማ” ተባልን፡፡ “ከሕወኃት ልዩ ሃይል ካምፕ ደርሳችኋል፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ” አሉን፡፡ መንገዱ መስኖ አለበት፤ ጭቃ ነው፤ ጭቃ ውስጥ ትገባለህ፡፡ ልክ ወደ አረብ አገር ነው የምትሄድ የሚመስለው፡፡ ፋኖ ይገኝበታል የተባለውን አካባቢም   ለሊት 9 ሰዓት ላይ አለፍነው ነው፡፡ ድሮ በነፃነት ወጥተህ የምትገባበት አገር (እንባዋ እየተናነቃት)፣ የጠላት አገር እንደሆነ ተደብቀህ ስትገባ ያማል (እያለቀሰች)፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊነቴን መፋቅ ወይም መደምሰስ አልፈልግም፡፡ ኢትዮጵያ ባዕድ አገር ስትሆንብኝ  ልቤ ተሰበረ፡፡
መከላከያ አለበት በተባለው አካባቢ ስንደርስ እስኪነጋ ድረስ ተቀምጠን ጠበቅናቸው፡፡  የመከላከያ ልብሳቸውን ሳይ ልቤ ተረጋጋ፡፡ እነሱ መታወቂያችንን አይተው፣ ሻንጣችንን ፈትሸው ተቀበሉን፡፡ ቆቦ የገባነው በኦራል መኪና ነው፡፡ የቆቦ ሰዎች “አራት ኪሎ ከእንግዲህ አይገኝም” ሲሉን፣በእነሱ ምክንያት እኛ ስንሰደብ በጣም አዘንኩ፡፡ ያችን የጓጓሁላትን ኢትዮጵያን አታገኝም ስባል በጣም ከፋኝ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይሻለኛል ብለህ ወጥተህ እንዲህ ሲሆን ትንሽ ይከብዳል፡፡ የቆቦን ሕዝብ አልፈርድበትም፤ እነሱ ሲገቡና ሲወጡ “አራት ኪሎ እንገባለን” እያሉ ይናገሩ ነበር፡፡--”
(ከትግራይ ወደ አማራ ክልል የገባች
 አንድ ሴት የተናገረችውና በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ)
ሰሞኑን ስለ ትግራይ ከተሰሙት ዜናዎች መካከል አንዱ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተዋጊ የሰው ኃይል ለማግኘት እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ይገኝበታል፡፡ ድሮ በከበሮና በጭፈራ ለውጊያ ይመለመል የነበረው የትግራይ ወጣት፣ አሁን የእሱን መንፈስ ማነሳሳት ቀላል ሆኖ አልተገኘም፡፡ የቀድሞ ተዋጊዎች በውጊያ ሜዳ የደረሰባቸውን ጉዳት እያሳዩ፤ “የእኔን መሳሪያ የሚቀበለኝ ማነው?” እያሉ እንዲማጠኑ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ስሜቱን ያልቀሰቀሰውን ደግሞ የትህነግ አርማን አጥፈው “በል ይህን ተራምደህ እለፍ” ይሉታል፡፡ የትህነግን አርማ ረግጦ ማለፍ ደግሞ የሚያስከትለው እጣ ሞት መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ያለው እድል ከፈጣኑ ሞት የሚዘገየውን ሞት መምረጥ ነው፡፡
በቀረበው ጥሪ መሰረት ወደ ውጊያ ያልገባ ሰው ነገ የሚጠብቀው፣ በገዛ መንደሩ ባይተዋር መሆንና ለማንኛውም አገልግሎት ወደ ዳር መገፋት እንደሚሆን አስቀድሞ እየተገለጠ ነው። በዚህ ጉዳይ የዶ/ር ደብረፅዮን አገዛዝ ጥብቅ አዋጅ ያወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
እነ ደብረፅዮን በቆሰቆሱት ጠብ ወዲህ ከኢትዮጵያ መንግስት፣ ወዲያ ከኤርትራ መንግስት ማንኛውም እንቅስቃሴያቸው በክትትልና ቁጥጥር ሥር እንዲገባ አስገድዷል። ክትትልና ቁጥጥሩ ወደ አካባቢው ለሕይወት አስፈላጊ ነገሮች በመደበኛው መንገድ እንዳይደርስ አድርጓል፡፡ በነገሩ የሌሉበት ንፁሃን ዜጎች መከራውን ለመሸከም ተገድደዋል። በእነሱ ጠብ ሕዝቡ ፍዳውን እያየ ነው፡፡ የትግራይን ሕዝብ መከራ የሚረዳለት እንዳጣም እገነዘባለሁ፡፡
ለሕዝብ መከራና ሥቃይ በተረፈውና  ራሳቸው ጎትተው ባመጡት ጠብ፣ እነ ደብረፅዮን “በከበባ ላይ ነን፤ ከበባውን ሰብረን መውጣት አለብን” በማለት ከሞት የተረፈውን የክልሉን ሕዝብ እንደገና ለሞት ለመዳረግ ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውም እየተሰማ ነው፡፡ በወልቃይት በአፋር፣ በሰቆጣና በወልዲያ ግንባር ሠራዊት እያስጠጉ መሆናቸውም ተሰምቷል፡፡ ሁኔታው ያሰጋው የአማራ ክልልም ተከታዩ እርምጃው ከመከላከል ወደ ማጥቃት እንደሚሸጋገር አሳውቋል፡፡
አንድ የደሴ ከተማ ነዋሪ፤ “የትሕነግ የደጀን ጦር ያለው ከኋላ ሳይሆን መሐል አገር ነው” ያሉትን አስታውሳለሁ፡፡ የእሱ የደጀን ጦሮች በየቦታው ያደራጃቸው እንደ ኦነግ ሸኔ፣የቅማንት፣ የጋምቤላና የቤኒሻንጉል አይነት ታጣቂዎች ናቸው፡፡ መንግስት በነዚህ ቡድኖች ላይ በቅርብ መውሰድ የጀመረው እርምጃ ይበል  የሚያሰኝ ነው፡፡
ሁለት ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በአፋር ክልል ወደ ትግራይ ሊገባ የነበረ ከፍተኛ ገንዘብ መያዙ ተገልጧል፡፡ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ብር የሚሆነው ገንዘብ የተያዘው ደግሞ ወደ ትግራይ የሰብአዊ እርዳታ ጭኖ እየተጓዘ በነበረ ከባድ መኪና ላይ ነው፡፡ የአለም ምግብ ድርጅት ተሽከርካሪዎች በእንዲህ አይነቱ ወንጀል ተሰማርተው ሲገኙ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ እስከ መቼ ዝም ይባላሉ? ተጠያቂ የሚሆኑትስ እንዴት ነው? መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡
የፌደራል መንግስቱ ዛሬም በትህነግ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እንደተበለጠ ነው፡፡ ትህነግ “የትግራይ ጂኖሳይድ” እያለ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጆሮ ሲያደነቁር፣መንግስት  የማይካድራን፣ አፋር ውስጥ የጋሊኮማን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ማንሳትና ማስታወስ ተስኖታል፡፡ ይባስ ብሎ እራሱን እንደ ወንጀለኛ ሲያቀርብም እየታየ ነው።
በመግቢያዬ ላይ ስለጠቀስኳት ከትግራይ ወደ አማራ ክልል በስንት ስቃይ ስለገባችው ሴት ጉዳይ ልመለስ፡፡ ልጅቱ ወጣት እንደሆነች እገምታለሁ፡፡ “የጓጓሁላትን ኢትዮጵያ አታገኚያትም ስባል ልቤ ተሰበረ” የሚለው ንግግሯ፣ የእኔንም ልብ የሰበረ ጉዳይ ነው። የእሷ ጩኸትና እንባ፣በዚያ ክልል የሚኖሩ ወገኖቻችን ጩኸትና እንባ ማሳያ ነው፡፡ የእሷ ብሶት የሁላችንም ብሶት ነው፡፡ የእኔ ልብ ከእሷ ጋር ያነባል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ለትግራይ ሕዝብ የሚደርስለት መቼ ነው? አጥብቄ እጠይቃለሁ፡፡
ትሕነግ እስከ መቼ ነው የትግራይን ሕዝብ መያዣ አድርጎ ሲደራደርበት የሚኖረው? የመንግስት ያለህ የሚያሰኝ  የትግራይ ችግር!!


Read 3332 times