Saturday, 27 August 2022 10:46

ሜሪ ጆይ በ5 ዓመታት ውስጥ 100 ሱቆችን ሊገነባ ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ከሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል

          ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ 100 ሱቆችን በመገንባት፣ በለጋሾች ላይ ብቻ ተመስርቶ የነበረውን ገቢውን በራሱም ለመደገፍ መወሰኑን አስታወቀ። ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ የሜሪ ጆይ ውጥን እውን ይሆን ዘንድ የሱቆቹን ብራንዲንግ፣ የፕሮሞሽንና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ባለፈው ማክሰኞ በካፒታል ሆቴል ስምምነት ተፈራርሟል።
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በፊርማ          ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ሜሪጆይ ባለፉት 28 ዓመታት ከአጋር ድርጅቶችና ከኢትዮጵያዊያን ሀብት በማሰባሰብ በአዲስ አበባ፣ በሲዳማ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ 112 ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለችግር የተጋለጡና በድህነት ውስጥ ላሉ ወገኖች ትኩረት በመስጠት፣ በአጠቃላይ ጤና፣ በኤችአይቪ ኤድስ መከላከል፣ በስነ-ተዋልዶ ጤና፣ በድህነት ቅነሳ፣ ከስደት ተመላሾችን መልሶ በማቋቋም፣ በህጻናት ተሳትፎና ማብቃት፣ እንዲሁም ለችግር የተጋለጡ አረጋዊያንን በግለሰቦች ስፖንሰርሽፕ ድጋፍ፣ በቋሚነት በመርዳት የተቀናጀ የልማት ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ የሀገሪቱ ችግሮች ምክንያት የለጋሾች ቁጥር ማነስና የተረጂዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ፣ ሜሪ ጆይ የራሱን ስራ በመስራት ገቢ ለማመንጨት ማቀዱን የገለጹት ሲስተር ዘቢደር፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 100 ሱቆችን ሰርቶ ገቢ ለማመንጨት እንዲችል ህጉ በሚፈቅደው መሰረት “ ሜሪ ጆይ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር” የተሰኘ የንግድ ድርጅት መቋቋሙን ተናግረዋል።
በቅርቡም የመጀመሪያዎቹ ሶስት ሱቆች በአዲስ አበባ የሜሪ ጆይ ጽ/ቤቶች ባሉባቸው አካባቢዎች እንደሚከፈቱ ሲስተር ዘቢደር ጨምረው አስታውቀዋል፡፤
በአምስት የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ትምህርትን በጥራት እያስተማረ የሚገኘው “ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ” ትልልቅ የቢዝነስ ኩባንያዎችን በማቋቋም ዝናን ባተረፉ ባለሙያዎች የተመሰረተ ሲሆን በሜሪጆይ የሚደገፉ 100 ሰዎችን በየቀኑ በመመገብ፣ ሌሎችን በማስተባበር 170 ሰዎችን እንዲመገቡ በማድረግና የኮሌጁ አንዱ ከፍተኛ አመራር 25 ልጆችን በግላቸው በማተማር የሜሪጆይ የጀርባ አጥንት በመሆን እየሰራ ይገኛል። አሁን ሜሪጆይ ከለጋሾች ድጋፍ ከመጠበቅ ይልቅ የራሱን ሀብት ለማፍራትና ለበለጠ ስራ መነሳሳቱን ተከትሎ በተለያየ መልኩ ለመደገፍ ስምምነት መፈራረሙ እንዳስደሰታቸው በኮሌጁ የምርምር ህትመትና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት  ጌታቸው ዋጋው (ዶ/ር) ተናግረዋል። ም/ፕሬዚዳንቱ የሱቆቹን አጠቃላይ የግንባታ ሂደት ከሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ የሚጠበቀውን ድጋፍና የሱቆቹን የአዋጭነት ሁኔታ በተመለከተ ባቀረቡት ጥናት፤ ሜሪጆይ በዓመት በትንሹ ከእያዳንዱ ሱቅ 1ሚ ብር ቢያተርፍ ከ100 ሱቆቹ 100 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ይችላል ካሉ በኋላ ይህም ሜሪጆይ ለጋሾች ላይ ብቻ ተመርኩዞ የነበረውን ገቢውን በመጠኑ በመቅረፍ ያለ ስጋት የልማት ስራውን እንዲሰራ ያግዘዋል ብለዋል።
የሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አንተነህ እውነቱ በበኩላቸው፤ የኮሌጁ አመራሮች ቢዝነስን በመመስረትና ለውጤት  በማብቃት የተመሰከረላቸው ባለሙያዎች እንደሆኑ አስታውሰው፤ ሜሪጆይ የሚያስገነባቸውን 100 ሱቆች በፕሮሞሽን በብራንዲንግ፤ በማማከርና በቴክኒክ ድጋፍ ውጤታማ በማድረጉ በኩል ኮሌጁ ሚናውን እንደሚወጣ ተናግረዋል። አቶ አንተነህ አክለውም ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ በተለይ ለሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎቻቸው የቢዝነስ ፕላን ውድድር በማዘጋጀትና አሸናፊዎቹ የቢዝነስ ሀሳቦች እውን እንዲሆኑ የፋይናንስና የቦታ አቅርቦት በማመቻቸት እየሰራ ሲሆን፤ ሁለተኛው የቢዝነስ ፕላን ውድድርም በቅርቡ እውን እንደሚሆን አብራርተዋል።
የባንኩን ቅርንጫፎች በጠንካራ እንስቶች ስም በመሰየም የሚታወቀውና አንዱን ቅርንጫፉን በሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ስም የሰየመው እናት ባንክ፤ ለሜሪጆይ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ሱቆች ግንባታ የ200 ሺ ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በቀጣይም ሜሪጆይን ለመደገፍ እንደሚሰራ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት በእናት ባንክ የኮርፖሬት ሰርቪስ ም/ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ገነት ሀጎስ ተናግረዋል።
ሜሪጆይ ኢትዮጵያ ከ28 ዓመት በፊት በ1986 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በተቀናጀ የጤና፣ የበጎ አድራጎትና የልማት ስራው እስካሁን 1.6 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉም ተገልጿል።

Read 11783 times