Saturday, 27 August 2022 11:02

መንግስት ወደ ክልሉ የሚገባው እርዳታ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ማስተማመኛ ጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(13 votes)

 የህወሓት ታጣቂ ሃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ ነሃሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ በምስራቅ ግንባር በሚገኙ በሶበር፣ ዞብል እና ትኩልሻ አቅጣጫ ጥቃት መሰንዘራቸውንና ዳግም ጦርነት መጀመራቸውን ተከትሎ፣ መንግስት አፀፋዊ እርምጃ እየወሰደ ነው። የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ ህውሓት የጀመረውን ጦርነት  አቁሞ ወደ ሰላማዊ ንግግር  እንዲመጣ የትግራይ ህዝብ ጫና ያደርግ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው መጋቢት ወር የታወጀውን የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት በማፍረስና ተስፋ የተጣለበትን የሰላም ድርድር በማቋረጥ የህወሓት ታጣቂ ሃይሎች ሰሞኑን የጀመሩት ጦርነት በይፋ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ማፍረሳቸውን አመላካች መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል። ቡድኑ የፈጸመው ጥቃትም ሆነ ጥቃቱን ተከትሎ የሚያወጣቸው መግለጫዎች፣ ቡድኑ አስቀድሞ ለጦርነት ሲዘጋጅ እንደነበር ማሳያ ነው ተብሏል። መንግስት ይህንኑ የህወሓት ታጣቂ  ቡድን ትንኮሳ በተሳካ ሁኔታ እየመከተ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።
ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ ዳግም  ያገረሸው ጦርነት በእጅጉ እንዳሳሰባቸውና ሁለቱም ወገኖች አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህበረት፣ አሜሪካና ብሪታኒያ ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሁለቱም ወገኖች አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉና ለሰላማዊ ንግግር እንዲቀመጡ ጠይቀዋል። “በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት መቀስቀስን ዜና ስሰማ በጣም ደንግጫለሁ” ያሉት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጦርነቱ ቆሞ የሰላም ድርድሩ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስትንና የህውሓት ታጣቂ ሃይሎችን ለማደራደር ጥረት እያደረገ የቆየው የአፍሪካ ህብረትም ጦርነቱ እንዲቆምና ተፋላሚ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄን በመሻት ወደ ጀመሩት ድርድር እንዲመለሱ ጠይቋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ጦርነቱን በቅርበት እየተከታተሉት  መሆኑን ጠቁመው፤ ጦርነቱ ቆሞ ሁለቱም ወገኖች ወደ ሰላማዊ ድርድር ሂደት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። የአወሮፓ ህብረት በበኩሉ፤ ወቅቱ ለሰላም ውይይት የሚደረግበት ጊዜ መሆኑን አመልክቶ ሁለቱም ወገኖች ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። አሜሪካ በበኩሏ፤ የጦርነቱን ዳግም መቀስቀስ አስመልክታ ባወጣችው መግለጫ፤ ጦርነት በሰዎችን ላይ መጠነ ሰፊ ስቃይ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣና ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚያስከትል ነው” ብላለች።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ ጦርነቱ ስጋት እንዳጫረባቸው አመልክተው፤ ሁለቱም ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደጉና ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። ከተጀመረ አምስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው በዚሁ ዳግም ጦርነት ሳቢያ በተለያዩ ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰኑ የአማራና የአፋር ክልል ከተሞች ላይ ውጥረት ነግሷል። ከተለያዩ አቅጣጫዎች የጦር መሳሪያ፣ ጥሬ ገንዘብና አደንዛዥ እጽ በመጫን ወደ ክልሉ ለመግባት የሞከሩ ተሽከርካሪዎችም በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆናቸው ተመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ትግራይ ውስጥ ለሚያካሂደው የእርዳታ አቅርቦት የሚገለገልበት 570ሺ ሊትር ነዳጅ በህወሓት ታጣቂ ቡድን መዘረፉ ተነግሯል።
ታጣቂ ቡድኑ መቀሌ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን ውስጥ በሃይል በመግባት 12 ታንከሮችን 570 ሊትር ነዳጅ ጋር መዝረፉን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሌ ተናግረዋል። ይህ የህወሓት ድርጊት አስፀያፊና አሳፋሪ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ድርጊቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ዘንድ እንዳይደርስ በማድረግ ሚሊዮኖችን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ነው ብለዋል። ቡድኑ የዘረፈውን ነዳጅ በአስቸኳይ እንዲመልስም ጥሪ አቅርበዋል።
የህውሓት ታጣቂ ቡድን ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ የቀረበበትን ክስ በማጣጣል፣ ለድርጅቱ በብድር የሰጠሁትን ነዳጅ ነው መልሼ የወሰድኩት ብሏል።
ከህውሓት  ታጣቂ ሀይሎች ጋር ቀረቤታ አላቸው እየተባሉ የሚታሙት የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ዋና ሃላፊ ሳማንታ ፓወር በበኩላቸው፤ ህውሓት ከመቀሌው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የዘረፈውን 570ሺ ሊትር ነዳጅ በአስቸኳይ እንዲመልስ አሳስበው፤ “ዝርፊያን በመፈጸም ተደራጅዎች ምግብ የማቅረብ ሰብአዊ እርዳታን ማስተጓጎል የጭካኔ ተግባር ነው” ሲሉ ድርቱን ኮንነዋል።
በህወሓት ታጣቂ ቡድን የተፈፀመውን የነዳጅ ዘረፋ ተከትሎ፣ መንግስት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አማካኝነት ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው ሰብአዊ እርዳታ ለታለመለት ዓላማ እያዋለ ስለመሆኑ ማስተማመኛ እንዲሰጠው ጠይቋል። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ በታጣቂ ቡድኑ የተፈጸመውን ዘረፋ በጽኑ እንደሚያወግዘው ጠቁሞ፤ ድርጊቱ ግልጽ ጦር ወንጀልና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋትን የጣሰ ድርጊት ነው ብሎታል። ቡድኑ ከፈጸመው ዝርፊያ ባሻገር ድርጊቱን ለማስቆም የሞከሩ የሰብአዊ እርዳታ ባለሙያዎችን ማሰሩንም መግለጫው አመልክቷል። አያይዞም የተዘረፈው ነዳጅ እንዲመለስ፣ በትግራይ ሃይሎች ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍንና ወደ ትግራይ የሚገባው እርዳታ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ማስተማመኛ እንዲሰጠው ጠይቋል።


Read 11589 times