Monday, 29 August 2022 00:00

ትንበያ ለተፈጥሮ ዑደትም፣ ለሰው ግባርም= ነው - በዮሴፍ ትረካ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  በአይሁድ፣ በክርስትናና፣ በእስልምና ሃይማኖቶች ዘንድ የሚታመንበት ነው - የዮሴፍ ትረካ። ሃይማኖታዊው ትረካ እንደሚገልፅልን ከሆነ፣ ዮሴፍ (የሱፍ)፣ የመጀመሪያው የትንበያና የሕልም ጌታ ነው።
ከዮሴፍ በፊት፣ “ሕልም አልነበረም” ለማለት አይደለም። ነበረ። እንዲያውም፣ በዮሴፍ ቅድመ አያት፣ ማትም በአብርሃም ዘመን ላይ ነው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሃይማኖታዊው ጽሑፍ ውስጥ፣ ስለ ሕልም የተተረከው። በአብርሃም ልጅ በይሳቅ ዘመን፣ ከዚያም በኋላ በያዕቆብ ጊዜ፣ የተለያዩ ሕልሞች ነበሩ።
ነገር ግን፣ ከዮሴፍ በፊት የነበሩ የሌሊት ሕልሞች፣ ከዘወትሩ የቀን ንግግሮች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። “ወደ ግብፅ ሂድ”፣ “ወደ ግብፅ አትሂድ”… ዓይነት ንግግሮች ነበሩ የያኔው ሕልሞች። ቀጥተኛ ትዕዛዝ ወይም ምክር እንጂ፣ የትንበያ ሕልም ወይም የባለ ራዕይ ሕልም አይደሉም።
ለነገሩ፣ ያኔ ጥንት፣ ከእለታዊው ኑሮ የዘለለ፣ ብዙም የትንበያ አቅም ባይፈጠር፣ ብዙም የተለየ የራዕይ ሕልም ባይኖር አይገርምም። ጥንታዊው እለታዊ ኑሮ፣ ከእጅ ወደ አፍ ነው። ለሕልም አይመችም። “ሕልም ታየ” ከተባለም፣ ቃል በቃል፣ ከመደበኛ ንግግር የተለየ አይደለም።
ዮሴፍ ነው፣ አዲስ ዓይነት የትንበያ ሕልም ወይም የባለ ራዕይ ሕልም ይዞ የመጣው። ያኔ ነው፣ ምስጢር ያዘለ “የትንበያ ሕልም”፣ ትርጉም የሚያስፈልገው “የባለራዕይ ሕልም” የተፈጠረው።
ከያዕቆብ 12 ወንድ ልጆች መካከል አንዱ ነው - ዮሴፍ። በአባቱ ዘንድ በጣም የተወደደ እንደሆነ ትረካው ይገልፃል። ሌሎች ወንድሞቹ ከሚለብሱት የተለየና የተዋበ፣ ጌጠኛ ልብስ ለዮሴፍ ተሰርቶለታል። ይሄ ለወንድሞቹ አስደሳች አልነበረም።… በእርግጥ የእያንዳንዱ ሰው ሃሳብና ተግባር ይለያያልና፣ ሁሉን በጅምላ መውቀስ የለብንም። ሁሉም ባይሆኑም፣ አብዛኞቹ፣ ዮሴፍን ጠልተውታል ብንል ይሻላል።
አስተዋይነቱንና የጥበብ ዝንባሌውንም የወደዱለት አይመስሉም። ቁመናውና መልኩም፣ የሚያስቀና እንደሆነ፣ በትረካው ተጠቅሷል። የጥላቻቸው ሰበብ ምንም ሆነ ምን፣ ጠምደውታል። በዚህ መሃል ነው፣ የዮሴፍ ልዩ የትንበያ ሕልም የመጣው።
ያየውን ሕልም አይቶ ዝም ቢል ይሻለው ነበር። ግን ዝም አላለም። ዮሴፍ፣ ቅንነትና የዋህነት በተቀላቀለበት አነጋገር፣ ሕልሙን ያወራላቸዋል። እነሱም ይናደዱበታል። ትረካው እንዲህ ይላል (ዘፍ ምዕ 37፣ 5)። (“ነዶ” ማለት አዝመራ በሚሰበሰብበት ጊዜ፣ የታጨደው በጭብጥ በጭብጥ ሲታሰር ነው። ቀጤማ ላይ እንደምናየው ማለት ነው)።
ዮሴፍም ሕልም አየ። ሕልሙንም ለወንድሞቹ ነገራቸው። እነሱም የባሰ ጠሉት። እሱም እንዲህ አላቸው። ያየሁትን ሕልም ይሄውላችሁ፣ ስሙኝ። ይሄውላችሁ፣ እኛ በእርሻ ማሳ ውስጥ፣ ነዶ እያሰርን ነበር። ይሄውና፣ የኔ ነዶ፣ ብድግ ብላ ተነሳችና ቀጥ ብላ ቆመች። ይሄውላችሁ፤ የእናንተ ነዶዎች ዙሪያዋን ሆነው፣ ለኔ ነዶ ሰገዱ” አላቸው።
ወንድሞቹም፣ “በእኛ ላይ ለመንገሥ፣ እኛን ለመግዛት ታስባለህን!” አሉት። ስለሕልሙም ስለንግግሩም፣ ይበልጥኑ ጠሉት።”
…Joseph dreamed a dream and told it to his brothers and they hated him all the more. And he said to them, “Listen… to this dream that I dreamed. And, look, we were binding sheaves in the field, and, look, my sheaf arose and actually stood up, and, look, your sheaves drew round and bowed to my sheaf.”
And his brothers said to him, “Do you mean to reign over us, do you mean to rule us?” And they hated him all the more, for his dreams and for his words.
ዮሴፍ ለምን ለወንድሞቹ ሕልሙን እንደነገራቸው እንጃ። “ሕልሙ”፣ የትንበያ ሕልም እንደሆነ ዮሴፍ አይጠፋውም። ጥበበኛ ነው። ወንድሞቹ እንኳ ነገሩ አልጠፋቸውም። እና እንዲያጨበጭቡለት ነው የሚነግራቸው? ወይስ እንዲሰግዱለት? የዮሴፍ ሕልም፣ ለነሱ የምስራች አይደለም።
እንደገና ሌላ የትንበያ ሕልም ሲያይስ፣ መች ዝም አለ? አሁንም አወራላቸው።
“ይሄውላችሁ፣ ሌላ ሕልምም አየሁ። ፀሐይና ጨረቃ፣ አስራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ” ብሎ ነገራቸው።
ሁለተኛው የዮሴፍ የትንበያ ሕልም፣ ከመጀመሪያው ሕልም ትንሽ ይለያል። መልዕክቱ ግን ይመሳሰላል። ያው፣ እንደ ምሳሌያዊ ዘይቤ ልንቆጥረው እንችላለን። ከዘወትር መደበኛ አነጋገር ይለያል። ውስጣዊ መልዕክት ይዟል። እርግጥ፣ በምስጢራዊ ምልክቶች በጣም የተወሳሰበ አይደለም። ቢሆንም ግን፣ “ትርጉም ያዘለ አገላለፅ ነው”፣ “ፍቺ የሚያስፈልገው ሕልም ነው” ልንለው እንችላለን።
ፀሐይና ጨረቃ፣… የዮሴፍ እናትና አባት መሆናቸው ነው። በእርግጥ፣ ቀደም ሲል፣ የዮሴፍ እናት፣ በወሊድ ጊዜ ሕይወቷ አልፏል። ቢሆንም ግን፣ የሕልሙን መልዕክት አያፈርሰውም። 11 ከዋክብት ደግሞ፣… የዮሴፍ ወንድሞች መሆናቸው ነው። የሕልሙ ትርጉም፣ ወይም የምሳሌያዊው ዘይቤ መልዕክት፣ ከባድ ምስጢር አይደለም። አባቱ እና ወንድሞቹ፣ የሕልሙን መልዕክት ለመገንዘብ አልከበዳቸውም።
ለክፋት ፊት አለመስጠት በጊዜ ነው።
ወንድሞቹ፣ የዮሴፍ ያህል ጥበበኞች ባይሆኑም፣ ሞኞች አይደሉም። የመጀመሪያውን ሕልም የነገራቸው ጊዜ፣ “የነገሩ አዝማሚያ” ገብቷቸዋል። “በእኛ ላይ ለመንገሥ፣ እኛን ለመግዛት ታስባለህን?” ብለውታል - በንዴት። ሁለተኛውን የትንበያ ሕልም ሲነግራቸው እንዴት እንደሚንገበገቡ አስቡት።
ብዙም አልቆዩም። ወንድሞቹ፣ (ሁሉም ባይሆኑም ብዙዎቹ)፣ በቅናትና በጥላቻ ስሜት፣ ከቀድሞውም አስበልጠው ክፉኛ ጠመዱት።
“ያውና፣ ያ የሕልም ጌታ!” እያሉ አላገጡበት። “ያውና፣ ያ ባለ ሕልም መጣ” ብለው አደሙበት። ተመካክረውም፣ በባርነት ሸጡት። እንዲያውም ሊገድሉት ነበር። ለትንሽ ነው የተረፈው። ከሞት ያመለጠው፣ ሁለት ወንድሞቹ፣ በየፊናቸው፣ በዘዴ ሊያድኑት በመሞከራቸው ነው።
መሞከራቸው በጎ ቢሆንም፣ በጣም ዘግይተዋል። መጀመሪያውኑ፣ ለክፉ አድማ መተባበር፣ ከነአካቴውም ለክፉ አላማ “ፊት መስጠት” አልነበረባቸውም። ገና ከመነሻው፣ ጭፍን ጥላቻን በጥንስሱ ቢቃወሙ ነበር የሚቀልላቸው። ጥላቻው ተባብሶ ወደ ክፉ አድማ ከደረሰ በኋላ፣ ያስቸግራል።
ሰዎች የግል ሃላፊነትን ጥለው በመንጋ ተቧድነው በጭፍን መንጋጋት ከጀመሩ በኋላ፣ ነገሩ መላ ያጣል። “አይሆንም” ብሎ ክፋትን በግልፅ “መቃወም” ቀርቶ፣ “ይቅርብን” ብሎ በለዘብታ ማፈንገጥም ያስፈራል።
ሁለቱ የዮሴፍ ወንድሞች፣ ከአድማው ለማፈግፈግ ቢፈልጉም፣ ክፉውን ሃሳብ በግልፅ ለመቃወም አልደፈሩም። በዘወርዋራ መንገድ ነው፣ ዮሴፍን ለማዳን የሞከሩት።
“በእጃችን ከምንገድለው፣ ገደል ውስጥ እንጣለው” አለ ከወንድማማቾቹ አንዱ። ገደል ውስጥ ከተቱት።
ሌላኛው ወንድም ደግሞ፣ “ገደል ውስጥ ከሚሞት፣ በባርነት እንሽጠው” ብሎ ተናገረ። እናም፣ ለባርነት ሸጡት።
ዮሴፍ፣ ወደ ግብፅ የሄደው፣ በዚህ ክፉ አጋጣሚ ነው። ከዚያም ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት የሚገባበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ትረካውን ካሁን በፊት አይተነዋል።
የትንበያ ዓይነቶች - ለግዑዝ የተፈጥሮ ዑደትና ለሰው ተግባር።
በዚያ ዘመን የነበረው የግብፅ ፈርዖን፣ እጅግ የሚያስጨንቅና መንፈሱን የሚያውክ ሕልም አየ። በርግጎም ከእንቅልፉ ተነሳ። ጊዜ አላጠፋም። ሕልም የሚተረጉሙ ጠቢባን (የትንበያ ትንታኔ ባለሙያዎች) እንዲመጡ አዘዘ። ተጠርተውም ከፈርዖን ፊት ቀረቡ።
“ሰባት የሰቡ ከብቶች፣ ከወንዝ ሲመጡ በሕልም አየሁ። ከዚያም ሰባት የከሱ ከብቶች አየሁ። የሰቡትንም ከብቶች በሏቸው። ክሳታቸው ግን አልተለወጠም። ሕልሜን ፍቱልኝ። ትርጉሙን ንገሩኝ” ብሎ ጠቢባኑን ጠየቃቸው።
የአገሪቱ ጠቢባን፣ ብዙ ናቸው። የሕልሙን ትርጉም ሊነግሩት፣ የትንበያ ትንታኔ ሊያቀርቡለት አልቻሉም።
ሕልሙን የፈታለት ግን፣ ከእስራኤል አገር በባርነት ተሸጦ የመጣው፣ ዮሴፍ የተባለው ወጣት ጥበበኛ ነው።
የሳተላይት መረጃ እና የትንበያ ትንታኔ እንደማለት ቁጠሩት። ሕልሙና ፍቺው፣ በጣም የተራቀቀ ባይሆንም፣ “የዘወትር ዓይነት ንግግር” አይደለም። ትርጉም ወይም ትንታኔ ያስፈልገዋል። ሰባት የደለቡ ከብቶች፣… ከዚያም ሰባት ጎስቋላ ከብቶች፣… የተፈጥሮ ዑደት አይመስልም?
ትርጉሙን ዮሴፍ ይናገራል።
ሰባት የአዝመራና የጥጋብ ዓመታት ይመጣሉ።
ከዚያም፣ ሰባት የችግርና የረሃብ ዓመታት ይከተላሉ።
የቀድሞው የአዝመራ ዘመንም፣ ፈፅሞ እንዳልተፈጠረና እንዳልነበረ ይሆናል።
የሕልሙን ፍቺ ለፈርዖን ተናገረ - ዮሴፍ። ግን፣ በዚህ አላበቃም። የመፍትሄ ምክርንም ጨምሮ ለፈርዖን ነግሮታል።
ለሰባት ዓመታት፣ በተከታታይ፣ ምድረ ግብፅ በወንዙ ውሃ አማካኝነት የሲሳይ አገር ትሆናለች? ዝናብ ከሰማይ፣ ወንዙም ከአባይ ምንጭ ይመጣ ይሆናል። በእርግጥም፣ የተፈጥሮ ዑደትን መርምሮ ያወቀ ጥበበኛ፣ ስለ ዝናብና ስለ ወንዝ ውሃ፣ የትንበያ ትንታኔ መስጠት ይችላል። ነገር ግን ተፈጥሮ ዑደት በራሱ ጊዜ ጎተራ አይሞላም። ኪስ አይገባም።
“የአዝመራና የጥጋብ ዘመን ይመጣል፣ ሲሳይም ይሆናል” ሲባል፣ በብልኀት ከተጉበት ብቻ ነው። በራሱ ጊዜ፣ ሲሳይ አይፈጠርም። ይሄ ሃሳብ፣ ከዮሴፍ እንሰማዋለን። ራሱን የቻለ ትንበያ ነው። የተፈጥሮ ዑደትን ሳይሆን፣ የሰው ምርጫንና ተግባርን፣ ውጤቱንና መዘዙን ይተነብያል። በብልሃት ከተጋችሁ ጎተራችሁ ይሞላል። ከሰነፋችሁ ግን፣ በራሱ ጊዜ የሚመጣ ሲሳይ አይኖርም። “እንዲህ ካደረጋችሁ፣ እንዲያ ይሆናል” የሚል ቅርጽ የያዘ ነው - “ሰውን የሚመለከት ትንበያ”።
ደግሞም፣ በትጋት የተገኘው መልካም ፍሬ፣ ካልተጠነቀቁለት፣ ለከርሞ ሳይደርስ ይጠፋል። በጥበብ ከያዙትና ካከበሩት ነው፣ ለነገም ለከነገ ወዲያም የሚበረክተው። አስቀድሞ ማስተዋል፣… ለዛሬ ያዋጣል፤ ለነገም ያዛልቃል። ይሄም ሌላ ትንበያ ነው። “እንዲህ ካደረጋችሁ፣ እንዲያ ይሆናል” - በሚል ቅርፅ። ይህን በተፈጥሮ ዑደት ላይ ከሚቀርብ ትንበያ ጋር አነፃፅሩት።
“ከጊዜ በኋላ፣ ውኃ የሚጠፋበት፣ ወንዝ የሚደርቅበት ዓመት መከሰቱ አይቀርም” ይላል በተፈጥሮ ዑደት ላይ የተነገረው ትንበያ። ማሳ ሁሉ፣ በሃሩር የሚቃጠልበት ጊዜም ይመጣል። ለሰባት ዓመታት ችጋር እየተደራረበ፣ ክፉ የመከራ ዘመን ይሆናል። ያስፈራል። ፈርዖን፣ በሕልሙ ምክንያት ከእንቅልፉ በርግጎ የባነው፣ በጭንቀት የተብሰለሰለው፣ አለምክንያት አይደለም።
እንግዲህ፣ የተፈጥሮ ዑደት ነውና፣… የሲሳይ እድሎችና የመከራ ፈተኛዎች፣ ሁሌም ነበሩ። ሁሌም ያጋጥማሉ። የተፈጥሮ ዑደትና በእውን እየተደጋገመ የታየ ታሪክ ነው። ከታሪክ የተማረ፣ (ማለትም፣ እውነታን ያገናዘበ ሰው)፣ ስለ መጪው ጊዜ ምን ያስባል? ምንስ ያደርጋል?
ያለፉትን ዓመታት መረጃ መመዝገብና መሰነድ ጥሩ ነው። መረጃ ካልተገናዘበ ግን፣ ጥሬ መረጃ ወይም ትዝታ ብቻ ሆኖ ይቀራል።
“የትዝታ ሕልም”፣ ወዳለፈው ዘመን መልሶ የሚወስድ፣ በትዝታ ወይም በሰቀቀን የሚያስጎበኝ ሊሆን ይችላል - እንደ ታሪክ።
የዝናብ ወይም የአባይ ወንዝ ውኃ እንደ ልብ የተገኘበት ጊዜ ነበረ። እናም፣ የአዝመራና የብልፅግና፣ የፍቅርና የሰላም ዓመታትን የሚያስቃኝ፣ አስደሳች ሕልም ይኖራል። የትዝታ ሕልም እንጂ ትንበያ አይደለም።
የውኃ ጠብታ የተወደደበት የታሪክ ጊዜም ነበረ። እናም፣ የረሀብና የስቃይ፣ የሀዘንና የትርምስ ዓመታትን እያሳየ የሚያስበረግግ ሕልም ይኖራል። ይሄም “ሕልም” ነው - የትውስታ ሕልም ቢሆንም።
ነገር ግን፣ ያለፈውን ጊዜ ከማስጎብኘት በተጨማሪ፣ ወደ መጪው ዘመን የሚወስድ፣ ወደ ነገ አሻግሮ የሚያሳይ “ሕልም” ደግሞ አለ። የትንበያ ሕልም፣ የአላማ ራዕይ ብለን ልንሰይማቸው እንችላለን።
ወደ ኋላ ማየትና ታሪክን መቃኘት፣ አንድ ነገር ነው። እንደ እውነተኛ መረጃ ቁጠሩት። መረጃዎችን አገናዝበን የተፈጥሮ ዑደትን መረዳት ስልችል ደግሞ፣ እንደ እውቀት ቁጠሩት። “ማወቅ”፣ ቀላል ነገር አይደለም።
እውቀትን ጨብጠን፣ “የነገን ሕልም ለማየት ስንጠቀምበት” ደግሞ፣ የእውቀት ዋጋና ክብር ይጨምራል።
“የኋላውን አይቶ፣ ያለፈውን ጊዜ አስታውሶ፣… የወደፊቱን መመልከትና መጪውን ጊዜ መቃኘት!” ነው ሕልም።
አንድም፣ መጪውን ዘመን ከወዲሁ አሻግሮ ማየት፣ ዙሪያ ገባውን “መቃኘት”፣… ማለት ነው። የትንበያ ትንታኔ ነው። የተፈጥሮ ዑደትን የሚያሳይ ቀመር ልንለው እንችላለን።
ሁለትም፣ መጪው ዘመን እንዲቃና፣ ከወዲሁ መንገዱን ማስተካከል፣ አሳምሮ “መቃኘት”፣… ማለት ነው። ይሄ፣ የተፈጥሮ ዑደትን ከማወቅ ባሻገር፣ የአላማና የመርህ፣ የሙያና የትጋት ሃላፊነትን ያካትታል።
እንግዲህ፣ ከጥሬ መረጃና ከትዝታ ጀምሮ፣ እስከ እውቀትና እስከ ተፈጥሯዊ ዑደት ትንበያ፣ እስከ አላማና ራዕይ ድረስ፣ የተለያዩ ደረጃዎችን ተመልክተናል። የሕልም ነገር፣ ሰፊና ጥልቅ ነው።
ያየናቸውና የሰማናቸው፣ የተረዳናቸውና ያልተረዳናቸው፣ የተጨበጡልንና አልያዝ ብለው ያስቸገሩን፣…
የተመኘናቸውና የጣልናቸው፣ ያጠፋናቸውና ያፈራናቸው፣ የወደድናቸውና የጠላናቸው፣ ያከበርናቸውና የናቅናቸው፣…
ያረኩንና የመረሩን፣ የተመቹንና ያሳመሙን፣…. ስንቱ ተቆጥሮ ይዘለቃል?
“ሕልም”፣ ከእነዚህ ሁሉ የሚመነጭ፣ የሚጨመቅ፣ የሚጠመቅ “ራዕይ” ነው።
ይሄ ሁሉ ቀላል ነገር አይደለም። የዓመታት መረጃዎችን ይቅርና፣ የአንድ እለት መረጃዎችን ሁሉ መዝግቦ መጨረስ አይቻልም። በእርግጥ፣ ትኩረቱን እየተቆጣጠረ መረጃዎችን የሚያስተውል፣ በአግባቡ እያገናዘበ ቅጥ የያዘ እውቀትን የሚገነባ ትጉህ ጥበበኛ፣… በጣም አይቸግረው ይሆናል። ቢሆንም ግን፣ ቀላል ጉዳይ አይደለም።
አዎ፣ ጥሬ መረጃዎች ያስፈልጋሉ። መረጃዎቹን በማገናዘብ፣ የተጣራ እውቀትን መጨበጥ ደግሞ፣ ተጨማሪ የጥበብ ስራ ነው።
በእርግጥም፣… መረጃ ከእውቀት ጋር በቅጡ ሲዋሃድ፣…
ጥሬ ሕልምም ከትርጉሙ ጋር በጥበብ ሲዛመድ ነው የሚያምረው።
ጥሬ የትዝታ ሕልሞች፣ ወይም የተንጠባጠበ መረጃ ብቻቸውን ምን ይረባሉ?
ቅንጥብጣቢ መረጃ፣ እውቀትን የሚያስጨብጥ ካልሆነ በቀር፣ ብቻውን ዋጋ የለውም።
ሕልምም፣ ውስጠ ምስጢሩ ካልተተረጎመ፣ ወደ ትንበያ ትንታኔ ካላደገ በቀር፣ የሚዳስሱት የሚጨብጡት ትርፍ አያስገኝም።
ነገሩ እዚህ ላይ አያቆምም።
መረጃና እውቀት ቢሟሉስ፣ በተግባር ለኑሮ ካልፈየዱ፤…
ሕልምና ፍቺው ቢዋሃዱስ፣ በእውን ለሕይወት ካልጠቀሙ በቀር፣ ከአላማና ከብሩህ ራዕይ ጋር ካልተዋሃዱ በቀር ምን ያደርጉልናል?
ደግነቱ፣ የፈርዖን ሕልምና የዮሴፍ ፍቺ፣ በተግባር፣ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለማዳን ጠቅሟል። ጥበበኛው ዮሴፍ፣ የቅርቡን በእውን አስተውሎ፣ የሩቁን በምናብ አገናዝቦ፣ መላ ፈጥሯል። ታዲያ፣ “መላ” ወይም “መፍትሄ” በራሱ ጊዜ አይመጣም። “እንዲህና እንዲህ ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህና እንዲህ ካደረጋችሁ ኑሯችሁ ይሰምራል” የሚል ትንበያ ነው - የዮሴፍ መፍትሄ።
በሰባቱ የአዝመራ ዓመታት ውስጥ፣ ብዙ እህል ለማምረትና በመጋዘኖች ቆጥቦ ለማከማቸት መትጋት ይስፈልጋል። ይሄ የመጀመሪያውና ትልቁ መፍትሄ ነው። በብልኃት ከተግታችሁ ብዙ ታመርታላችሁ፣ ብዙ በረከት የእለት ጉርስን ያሟላል፤ ለወደፊትም ጥሩ ስንቅ ይሆናል። በአዝመራ ዓመታት የተኘው ፍሬ፣ በጥንቃቄና በክብር ከያዙት፣ ለችግር ዓመታት ይተርፋል።
ዮሴፍ፣ በጥበቡና በብልሃቱ፣ ፈርዖንም ምክር በመስማቱና ከልብ አምኖበት በመስማማቱ፤ የእልፍ አእላፍ ሰዎች ሕይወት፣ ከረሃብና ከእልቂት ተረፈ።
በባርነት ወደ ግብፅ የመጣው ዮሴፍ፣ በፈርዖን ዘንድ፣ በእጅጉ ተከበረ። ለዘመናት የሚዘልቅ ወዳጅነትን አተረፈ። ከሌሎች ሁሉ የላቀ ሹመትና ሥልጣን አገኘ።
ያኔ ነው፣ ዮሴፍ፣ ከወንድሞቹ ጋር እንደገና የሚገናኝበት እድል የተፈጠረው። ከረሀብ ለመዳን ነው፣ ወደ ግብፅ ምድር የወረዱት - እህል ለመሸመት። በዮሴፍ ጥበብና ምክር፣ በዮሴፍ ብልሃትና ትጋት፣ በግብፅ ምድር ብዙ እህል በመጋዝኖች ተከማችቶ መቀመጡ፣ ለወንድሞቹ ጠቀማቸው።
ወንድማቸው መሆኑን፣ ገና አላወቁም ነበር። ከፈርዖን ቀጥሎ፣ በግብፅ ምድር ሁሉ፣ እጅግ የተከበረ ባለሥልጣን መሆኑን ግን አይተዋል። በዚህ ጊዜም ነው፣ በአክብሮት የሰገዱለት።
ለካ፣ ዮሴፍ በወጣትነቱ ያየው ሕልም፣ የእውነት ሕልም ነበር። ሕልሙ፣ በእውን እንደታለመው ሆነ። ነገር ግን፣ ወንድሞቹ እንዳሰቡት ዓይነት አልሆነም።
ለካ፣ የዮሴፍ ሕልም፣ ወንድሞቹ ላይ ለመንገሥና ለመግዛት አልነበረም። ጥላ ከለላ ሊሆንላቸው እንጂ።
እዚህ ላይ፣ እንዳንሳሳት።
አንደኛ ነገር፣ ሕልም ስላየ ብቻ አይደለም፣ እንደታለመው ለመሆን የበቃው። በመልካም ጥረት ነው፣ ሕልሙ እውን የሆነው።
ሁለተኛ ነገር፣ ክቡር ነገሮችን በመስራት ነው፣ ዮሴፍ የከበረው። ከዚያም የተከበረው። ሰዎች የሚያከብሩት መሆኑ ጥሩ ነው። ግን፣ ባያከብሩትስ? መቼስ ምን ይደረጋል?
በእውቀቱና በጥበቡ፣ በመልካም ስራውና በመልካም ፍሬው የከበረ ሰው፣ ሌሎች ሰዎች ባያከብሩት፣ የነሱ ችግር ነው። ወይ አላዋቂነትና ደንታቢስነት፣ ወይ ጠማማነትና ክፋት ቢጠናወታቸው፣ ኀጥያታቸው በራሳቸው ላይ ነው።
በሌላ አነጋገር፣ “ሰዎች እንዲያከብሩትና እንዲሰግዱለት አልሞ” አይደለም የሚሰራው። መክበር ይቀድማል፣ ከመከበር በፊት። በስራው እንጂ ያለ ስራው ቢያከብሩት ዋጋ የለውማ። በውሸት ላይ የተመሰረተ ክብር፣ ከጉራ የበለጠ ትርጉም አይኖረውም።
በአስተዋይነቱ፣ በጥበቡ፣ በሙያውና በትጋቱ ከበረ። በአክብሮት ሰገዱለት። ባያከብሩትም ግን፣ ለዮሴፍ ብዙም ለውጥ የለውም። ክብሩን አያጎድልበትም፣ አይጨምርለትም። ለነሱስ ለውጥ አለው?
የኋላ ኋላ፣ ዮሴፍ ራሱ፣ እውነተኛ ማንነቱን ሲነግራቸው፣… እንዴት እንዴት እንደሆኑ!
ለዓመታት በውስጣቸው የተቀብሮ የተደበቀ የኀጥያት ጥቁር ጠባሳ፣ ጎምዛዛ የጥፋተኝነት ስሜት፣… ከሸክም የከበደ የፀፀት እዳ፣…
ፊት ለፊት በቅን ልቦና ኀጥያታቸውን ካልተጋፈጡት፣… ነፍሳቸውንም አንፅተው ለማደስ ካልቆረጡ፣ የትም መቼም የሚያመልጡት ቅጣት አይደለም - የክፉ ድርጊት እዳ። በልባዊ ፀፀትና በይቅርታ ነው፣ ነፍሳቸውን እንደገና ለማደስ፣ ጥሩ እድል ያገኙት።
እንግዲህ፣ የዮሴፍ ታሪክ፣ ከሞላ ጎደል፣ በዚህ ነው የሚጠናቀቀው።
እንደማንኛውም ትልቅ ታሪክ፤ የዮሴፍ ታሪክ ሲጠናቀቅ፣ ለሌላ የታሪክ ውጥን፣ አዲስ መነሻ መሆኑ አልቀረም።
መሬት ሁሉ የፈርዖን ሆነ።
ፈርዖኑ፣ በአዝመራ ዓመታት፣ ከአገሬው ሰው፣ ብዙ እህል የሰበሰበውና በመጋዘኖች ያከማቸው፣ በምን ዘዴ ይሆን? በገበያ ዋጋ ገዝቶ ነው? በዘፈቀደና በግዳጅ ነጥቆ ነው? አይመስልም። ምናልባት፣ በታክስ ሊሆን ይችላል። ከረሀብ ዓመታት በኋላ፣ “የ20 በመቶ ታክስ” በዜጎች ላይ እንደተጫነ፣ ትረካው ይገልፃል። ከረሀብ በፊት፣ እህል የተሰበሰበውም በዚሁ መንገድ ሳይሆን አይቀርም።
በመጋዘን የተከማቸው እህል፣ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ግን፣ በግልፅ ተጠቅሷል። ረሀብ የመጣ ጊዜ፣ የፈርዖን መጋዘኖች ተከፍተው፣ እህል ለአገሬው ሰው መሸጥ ጀመሩ። “በነፃ ውሰዱ” ቢል፣ “ደግነት” ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ “መጥፊያቸው” ነበር የሚሆነው። ዓመት ሳይሞላው፣ ሁሉም ነገር በሽሚያ ይራቆት ነበር።
መንግሥት፣ ሽልማቶችን መስጠት፣ የአደጋ ጊዜ ደራሽ መሆን ይችላል። ከዚያ ውጭ ግን፣ የደግነትና የልግስና ነገሮችን፣ ለደጋግና ለለጋስ ሰዎች ትቶ፣… እህሉን በዋጋ መሸጡ፣ ብልኀነት ነው። እህሉ በሽሚያ እንዳያልቅ፣ መጋዘኖቹም ኦና እንዳይሆኑ፣ አገሬውም በረሀብ እንዳይጠፋ ይረዳል። ጊዜያዊ ቢሆንም እንኳ፣ የተሻለ መፍትሔ ነው።
ነገር ግን፣ የ7 ዓመት ረሀብ ቀላል አይደለም። የአገሬው ሰዎች፣ እህል ለመግዛት፣ ንብረታቸውን፣ ከብታቸውን፣ የእርሻ ማሳቸውንም ጭምር፣ ለፈርዖን እስከ መሸጥ ደርሰዋል። በዚህም ሰበብ፣ “መሬት የመንግሥት ሆነ” ማለት ነው። ዜጎች ደግሞ፣ እንደ “ጭሰኛ”።
የመከራ ዓመታትን ከተሻገሩ በኋላ፣ አገሬው ሲያገግም፣ የእርሻ ማሳዎችን ለዜጎች መልሶ መሸጥ ይቻላል። አለበለዚያ ግን፣ ችግር ያመጣል። “መሬት የመንግሥት ነው” ከተባለ፣ ገበሬዎች የመንግሥት ጭሰኛ ይሆናሉ። በእርግጥ፣ ለጊዜው፣ ገበሬዎችን የሚጨፈልቅ ከባድ ሸክም ላይሆን ይችላል። “መሬት የፈርዖን ነው። ገበሬዎችም ከምርታቸው 20 በመቶ ለፈርዖን ይሰጣሉ” ነው የተባለው።
ነገር ግን፣ መሬትን ሙሉ ለሙሉ የሚቆጣጠር መንግሥት፣ ውሎ አድሮ፣ ሕዝቡን ለአደጋ፣ አገሩን ለመከራ ማጋለጡ አይቀሬ ነው። “ክፉ አምባገነንን የሚጣራ ግብዣ” እንደማለት ነውና - “የመንግሥት መሬት”። አገር ምድሩን ሁሉ፣ ሰውና ንብረቱን በሙሉ፣ እንዳሻው በባርነት ረግጦ መግዛት የሚፈልግ ፈርዖን ከመጣ፣… በጣም ይመቸዋል። ደግሞም፣ እንደዚያ ዓይነት ፈርዖን ይመጣል። በሱ ጦስ አገሪቱ ትተራመሳለች።

Read 9367 times