Saturday, 27 August 2022 11:15

አቡበከር ናስር ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፕሮፌሽናሊዝም ተስፋ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

  በደቡብ አፍሪካ PSL ሊግ ሁለት ጨዋታዎችን ተቀይሮ በመግባት ለሜመሎዲ ሰንዳውንስ 86 ደቂቃዎችን የተጫወተው አቡበከር ናስር  የአገሪቱን ሚዲያዎች ትኩረት ስቧል፡፡
የሜመሎዲ ሰንዳወንስ ምክትል አሰልጣኝ ሩላኒ ሞኮዬዋና ስለእሱ በሰጡት አስተያየት በአስደናቂ ተጨዋቾች በመከበቡ በቶሎ ለውጥ ማሳየት ይችላል፡፡ ለሁሉ ነገር አዲስ ተጨዋች ስለሆነ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንዲረጋጋና ሙሉ ብቃቱን እንዲያሳይ ደጋፊዎች ትእግስተኛ ሆነው መጠባበቅ እንዳለባቸውም ገልፀዋል፡፡  አንዳንድ ዘገባዎች አቡበከር በቋንቋ የተነሳ ችግር ውስጥ መግባቱን ያወሱ ቢሆንም ሰሞኑን የተሰራጩ መረጃዎች ተጨዋቹ ሜዳ ውስጥ ከአሰልጣኞች ጋር እንዲግባባ ክለቡ አስተርጓሚ መመደቡን አትተዋል። እንደ ደቡብ አፍሪካው ኪኮፍ መፅሄት ዘገባ አቡበከር ናስር በቀጣይ ጨዋታዎች በሜዳው ውስጥና ከሜዳ ውጭ መነጋገርያ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
አቡበከር ናስር ለሜመሎዲ ሰንዳውንስ የመጀመርያውን ጨዋታ ያደረገው በቲ ኤስ ጋላክሲ 1ለ0 በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ ነበር፡፡ በጨዋታው ከቤንች ላይ ተቀይሮ በመግባት ለደቂቃዎች ቢጫወትም ውጤቱን የሚቀይር ብቃት ውስጥ አልነበረም፡፡ በሁለተኛው ጨዋታው አሁንም ተቀይሮ በመግባት  ደቂቃዎችን የመጫወት  እድል አገኘ፡፡ ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ተጋጣሚውን ካይዘር ቺፍን 4ለ0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ  በጨዋታው ምርጥ ብቃቱን በማሳየትና አስደናቂ ግብ ማስቆጠር ችሏል። የደቡብ አፍሪካ ሊግን  የሚያደምቅና ወደ አውሮፓ ለመሻገር ተስፋ ያለው ተጨጠዋች ሆኖ በመጠቀስ የአፍሪካን የስፖርት ሚዲያዎች ማነጋገሩን ቀጥሏል። የሜመሎዲ ሰንዳውንስ አሰልጣኞች ከተለያዩ ሚዲያዎች  ባደረጓቸው ውይይቶች በክለባቸው እንደአቡበከር አይነት አዳዲስ ተጨዋቾች በልምምድና ጨዋታዎች ብቃታቸውን አያሻሉ በመሄድ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ እምነት አለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ነ22ኛ ዓመቱን የያዘው አቡበከር በሜመሎዲ ሰንዳውንስ 28 ቁጥር ማሊያ ለብሷል፡፡
በተያያዘ አቡበከር ናስር በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የክለቦች የሊግ ውድድር በመጫወት 5ኛው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከእሱ በፊት ፍቅሩ ተፈራ፤ ጌታነህ ከበደ፤ ፍስሐይመር በጋሻውና መሀመድ ኢብራሂም በ6 የተለያዩ ክለቦች መጫወት ችለዋል። በተለይ ፍቅሩ ተፈራ በሁለቱ ታላላቅ ክለቦች ኦርላንዶ ፓይሬትስና ሱፕር ስፖርት ዩናይትድ ከመጫወቱም በላይ ለሁለት ጊዜያት የደቡብ አፍሪካ ሊግን በማሸነፍ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበ ነው፡፡ ጌታነህ ከበደ ደግሞ በቢድቬስት ዌስትና በፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ 19 ጨዋታዎችን በማድረግ በደቡብ አፍሪካው ሊግ 6 ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡
አቡበከር ናስር ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመሻገሩ በፊት በኢትዮጵያ ቡና የስፖርት ክለብ እስከ 2025 እኤአ የሚቆይበት የኮንትራት ውል ነበረው፡፡ ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ሊያዛውረው ከፈለገ በኋላ በውሰት ለሌላ ክለብ በመስጠት ሊያጫውተው አስቦ ነበር፡፡ ስለዚህም ለስድስት ወራት በቡና ስፖርት ክለብ  ውስጥ ቆይታ አድርጓል፡፡ የእንግሊዘኛ ቋንቋውንም በዚህ ወቅት ለማሻሻል አስተማሪ ተቀጥሮለት ሁሉ ተሰርቷል። በመጨረሻም ቡና የስፖርት ክለብ በፕሮቶሪያ ለሚያደርገው ቆይታ ወጭውን ከሸፈነለት በኋላ ለሁለት ሳምንታት በሜመሎዲ ሰንዳውንስ ቆይታ አድርጎ በ250ሺ ዩሮ የዝውውር ሂሳብ ለደቡብ አፍሪካው ክለብ ሙለሙሉ ሊፈርም ችሏል፡፡ ከሜመሎዲ ባሻገር ካይዘር ቺፍ የሚፈልገው ሌላው የደቡብ አፍሪካው ክለብ ነበር፡ ኪክኦፍ መፅሄት እንደዘገበው የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ሽሚያ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በአልጄርያና በግብፅ ክለቦች ይፈለግ እንደነበር ሲሆን፤ የጆርጅያ ክለብ እና በስፔን ዝቅተኛ ዲዚዮን ያሉ ክለቦች ሊወስዱት ሙከራ እንዳደረጉም አውስቷል፡፡
አቡበከር ወደ ደቡብ አፍሪካው ክለብ ከመዛወሩ በፊት ከ2014 እስከ 2016 እኤአ በሃረር ከተማ በመጫወት የክለብ ህይወቱን ጀምሯል፡፡ ከ2016 ጀምሮ ደግሞ ለስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በመጫወት አሳልፏል፡፡ በቡና ቢ ቡድን መጫወት ከጀመረ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዋና ቡድን ተቀላቅሏል፡፡ ከ23 በላይ የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን በማድረግ 29 ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡ በ2021 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ በ24 ጎሎች ያሸነፈ ሲሆን ሌሎች የምርጥ ተጨዋች ሽልማቶችንም ተቀዳጅቷል፡፡
አቡበከር ናስር ባለፉት 3 ዓመታት በዓለም ዋንጫ ፤ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች፤ በወዳጅነት ጨዋታዎች፤ ዋና ውድድሮች ለብሄራዊ ቡድን 21 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ 5 ጎሎችንም ከመረብ አሳርፏል። በብሄራዊ ቡድን ማሊያ ካገባቸው ጎሎች ሁለቱም በወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ያስቆጠራቸው ሲሆኑ በባህርዳር ስታድዬም  በኡጋንዳና በማላዊ ላይ ነው፡፡ ሌሎች ሁለት ጎሎችን ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በባህርዳር ስታድዬም በማዳጋስካር ላይ እንዲሁም በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ዚምባቡዌ ላይ በሃራሬ ስታድዬም አስቆጥሯል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ክለብ ሜመሎዲ  ሰንዳውንስ በአገሪቱ ከፍተኛ የክለቦች ውድድር  ከ15 ጊዜያት በላይ ዋንጫዎችን አሸንፏል፡፡ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና የአፍሪካ ሱፕር ካፕንም ያሸነፈ ምርጥ ፕሮፌሽናል ክለብም ነው፡፡ ሜመሎዲ ሰንደውንስ በደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ በ11 ሚሊዮን ዶላር የዋጋ ተመን ሃብታሙ ክለብ ሲሆን፤ዋና ባለቤቱ ፓትሪስ ሞትሶፔ ታዋቂ የደቡብ አፍሪካ ቢሊዬነርና የማዕድን ኢንቨስተር ናቸው። መቀጫውን በፕሪቶሪያ፤ ቲስዋኔ ያደረገው ክለቡ ከተመሰረተ 52 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በሜመሎዲ ሰንዳውንስ የ46 ተጨዋቾች ስብስብ አብዛኛዎቹ ደቡብ አፍሪካዊ ቢሆኑም ከምስራቅ አፍሪካና ከደቡብ አሜሪካ ጭምር ፕሮፌሽናሎች ተሰባስበዋል። ከኢትዮጲያ፤ ኬንያ ፤ ኡጋንዳ፤ ኡራጋይ፤ ቺሊና ቦሎቪያ የመረጡ ተጨዋቾች በቡድኑ ይገኛሉ፡፡

Read 31678 times