Saturday, 27 August 2022 11:41

ሰማይ መልቲ ሚዲያ” የንባብ ባለውለታዎችን ሊሸልም ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

መቀመጫውን በሀዋሳ ከተማ ያደረገው ሰማይ መልቲ ሚዲያ በሀዋሳ ከተማ ለንባብ ማደግ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን ነሀሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ሊሸልም ነው። የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኢዮብ ፅጌ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት የመርሃ ግብሩ ዓላማ ሰማይ መልቲ ሚዲያ ባለፈው ዓመት ባዘጋጀው “ሐዋሳ ታነብባች” የንባብ ማበልጸጊያ መርሃ ብግር ላይ የተሳተፉ ተቋማትንና ግለሰቦችን፣ የወረቀት ውድነቱን ተቋቀዉመው በ2014 ዓ.ም   መፅሐፍ ያሳተሙ ደራሲያንን፣ ለንባብ ማደግ አስተዋጽኦ ያደረጉ የጥበብ ማህበራትን፣ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆችን፣ ረዥም ጊዜ የቆዩ መጽሐፍት ቤቶችንና ሌሎችንም ከንባብ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ ያላቸውን  አካላት ማመስገንና እውቅና  መስጠት ነው ብለዋል።
በዚህ የእውቅናና የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ግጥሞች፣ ሙዚቃ፣ ንባብን ስለማሳደግ ውይይት ሌሎችም መርሃ ግብሮች የሚቀርቡ ሲሆን፣ በተለይ የከተማዋ ከንቲባ አንብበው ከወደዱት መፅሀፍ ማራኪ አንቀጽ እንዲያነብቡ በማድግ የከተማው ወጣት ለንባብ እንዲነቃቃ ያደርጋሉም ብዋል-አቶ ኢዮብ።
ከዚህም በተጨማሪ የከተማዋ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መመሪያ ሃላፊዋ ወ/ሮ ደጊቱ ጫሊ የንባብ ባህል መዳበርን ተከትሎ “ሰማይ መልቲ ሚዲያ” ላነሳው ሃሳብ እውቅና በመስጠትና  ሁኔታዎችን በማመቻቸት ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ላደረጉት ያልተቆጠበ ድጋፍና አስዋጽኦ በልዩነት እውቅና እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል። በመርሃ ግብሩ ላይ ተጋባዥ እንግዶች፣ ደራሲያን፣ ገጣሚያንና የጥበብ ሰዎች እንደሚታደሙም ታውቋል።

Read 21817 times