Saturday, 27 August 2022 11:47

የግንቦት 7 ልዩ ኮማንዶ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ወያኔዎችን ምን እንዳስጨነቃቸው አላውቅም። ያደረጉትን ለምን እንደሚያደርጉትም አልገባኝም። ከቤተሰቦቼ መሃል ከአባቴ በስተቀር ሌላ ማንም እስር ቤት እንዳይጎበኘኝ አድርገዋል። ጉብኝቱንም በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ብቻ እንዲሆን ወስነዋል። የተሰጠን ጊዜም ግማሽ ሰዓት ብቻ ነው።
ማንም ሌላ እስረኛ እንዲህ አይነት ገደብ የለበትም። አባቴ ሊጎበኘኝ ሲመጣ እንደሌላው ጎብኚ ከሌሎች ጠያቂዎች ጋር አልቀላቀልም። እኔም ከሌሎች እስረኞች ጋር ተቀላቅዬ አልጎበኝም። አባቴና እኔ የማንገናኘው የቃሊቲው አስተዳዳሪ ቢሮ ውስጥ መሆኑን ቀደም ብዬ ተናግሬለሁ። በየሳምንቱ አባቴን ለማግኘት ስንቀሳቀስ ሃምሳ ሜትር እርዝማኔ የሌለው መንገድ፣ መኪና ቀርቦልኝ እንደምወሰድም ጠቅሻለሁ።
ከሁሉ ያልገባኝ ነገር በመኪና መወሰዱ ሳይሆን የሚደረገው ጥንቃቄ ነው። መሳሪያ የያዘ ወታደር መኪናው ውስጥ አብሮኝ መግባቱ የተለመደ አሰራር ሊሆን ይችላል። እስረኛ ያለአጃቢ ስለማይንቀሳቀስ። ከዚህ አልፎ ግን እኔ በምንቀሳቀስበት ቀንና ሰዓት መንገዱን በሙሉ ከእስረኛ ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከቃሊቲ ፖሊሶች ማጽዳት ለምን እንደፈለጉ ወይም እንደተገደዱ ነው አልገባ አለኝ።
ቅዳሜ ቀን ቃሊቲ በጣም ብዙ እንቅስቃሴዎች የሚታይበት ቀን ነው። ብዙ እስረኛ በቤተሰብ የሚጠየቀው ቅዳሜ ቀን ነው። እስረኛውም ገንዘብ የሚያገኘውም የሚያጠፋውም ቅዳሜ ነው። አሳሪዎቼ ብቻ ከነገሩኝ ተነስቼ ሳይሆን አንድ ቅዳሜ እኔም በመኪና ስወሰድ ያየሁት ነው። ትርምስ ነው። ወደ ላይ ወደ ታች የሚሉ ሸቀጥ የያዙ በወታደሮች የታጀቡ ሴትና ወንድ እስረኞች አይቻለሁ። ፖሊሶች ምግብ የሚበሉባቸውና ቡና የሚጠጡባቸው ዳስ ነገሮች በፖሊሶች ተሞልቶ አይቻለሁ። ይህን ያየሁት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ከዛ ቀን ውጭ በምንቀሳቀስበት ወቅት በምሄድበት መንገድ ወፍ ዝር እንዳይል ይደረጋል። መኪናው ወደ አስተዳደሩ ቢሮ እስከሚዞር በርቀት ዋናውን የግቢውን በር ማየት እችላለሁ። በዛ መንገድ ላይ እንኳን እስረኛ ፖሊስም እንዳይታይ ተደርጎ ነው የሚያንቀሳቅሱኝ። አንዳንድ ጊዜ ከታሰርኩበት ግቢ በራፍ ላይ እንድቆም ተደርጎ መንገዱ በሙሉ መጽዳቱን ብርሃኔ ጠይቆ ነው መኪና ላይ የምጫነው።
በዚህ ጉዞ አልፎ አልፎ ብርሃነና ሌሎች ፖሊሶች የሚጨቃጨቁበት ሁኔታ ይፈጠራል። መንገዱ ጸድቷል ተብሎ ስንወጣ ከሆነ አሳቻ ስፍራ ብቅ ብቅ የሚሉ ፖሊሶች ነበሩ። እኔን ለማየት እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። ወደ መኪናው እያዩ የሚጠቋቆሙበትን ሁኔታ አይቻለሁ። ብርሃነ እነዚህን ፖሊሶች ወደ ወጡበት እንዲመልሱ ትእዛዝ ይሰጣል። እነሱም በፈቃደኝነት እሺ ብለው አይመለሱም። ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸውም በዝግታ እያጉረመረሙ ይመለሳሉ።
ሴት ፖሊሶች ተሰብስበው ቡና የሚጠጡበትን በቆርቆሮ የተሰራ ዳስ አልፈን ነው ወደ አስተዳደሩ ቢሮ የምንሄደው። አንድ እለት ብርሃነ እዛ ክፍት ዳስ ውስጥ ቡና ይዘው የሚያያቸውን ፖሊሶች በተመለከተ፣
“እኛ ወደዚህ ስንመጣ ነው እንዴ የእነዚህ ሴቶች የቡና ሱስ የሚቀሰቀሰው፤አሁን ስንወርድ እኮ  ቦታው ባዶ ነበር።” አለ። መኪና የሚነዳው የብርሃነ አገር ሰው ሴቶቹን በተመለከተ የሰጠው ኋላ ቀር አስተያየት አስደነገጠኝ። ከእነዚህ ቡና ከሚጠጡ ሴት ፖሊሶች መሃል በድፍረት ወታደራዊ ሰላምታ የምትሰጠኝ አንዲት ፖሊስ ነበረች። ማንም ቢያያት አትፈራም። እንዴት ዝም ይሏታል እያልኩ፣ በፈገግታ ሰላምታዋን ተቀብዬ አልፍ ነበር።
እኔንም ለማንቀሳቀስ ወያኔ በሚያደርገው ጥንቃቄ በመገረም ጉዳዩን በዝርዝር ለእንግሊዝ መንግስት ጎብኝዎቼ ነገርኳቸው።
“የግንቦት 7 ልዩ ኮማንዶ ከቃሊቲ መንጭቆ ያወጣኛል ብለው ይሰጋሉ መሰለኝ፤ ሲያንቀሳቅሱኝ ከምክንያት ያለፈ ጥንቃቄ ያደርጋሉ” አልኩ። በመሃከላችን ተቀምጦ የነበረው የደህንነት ሰው ተናደደ።
ጥንቃቄ የሚደረገው ስጓጓዝ ብቻ አይደለም። ከውጭ ሰው አምጥተው እታሰርንበት ግቢ ውስጥ የሚያሰሩት ነገር ካለ፣ “እቤት ውስጥ ግቡ” እንባላለን። ስራው እስኪያልቅ ይቆለፍብናል። ሽንት ቤትና እጅና እቃ መታጠቢያው ገንዳ አካባቢ የሚሰራ ስራ ካለም እንዲሁ ይቆለፍብናል።
ቃሊቲ ከገባሁ በኋላ ብዙ ጊዜ የተለያዩ የጤና መታወኮች ገጥመውኛል። መጀመሪያ ሰሞን የቃሊቲ እስር ቤት ሃኪሞች እንዲያዩኝ አልተፈቀደላቸውም ነበር። ለተብርሃን ተፈልጋ መጥታ ነው፤ እንደገና ለተቀሰቀሰብኝ ኪንታሮት በሽታ መድሃኒት የሰጠችኝ። እሷ ስትመጣ አሰፋና ዳዊት እቤት ውስጥ ይዘጋባቸዋል። ለተብርሃን ምርመራ የምታደርግልኝ ግቢው ውስጥ እደጅ ነው። የኪንታሮት ምርመራ ደጅ ማድረግ አልቻለችም። የነገርኳትን ብቻ ሰምታ መድሃኒት አዘዘችልኝ።
ከለተብርሃን በኋላ አስናቀች የምትባል የጤና መኮንን ተተካች። አስናቀች የቃሊቲ ሃኪም ናት። ስሟን ያወቅሁት ከተዘጉበት ክፍል በቀዳዳ አሾልቀው ካዩዋት ቁራኛዎቼ ነው። አስናቀች የትግራይ ተወላጅ አይደለችም። እንደ ለተብርሃን ሩህሩህ መሆኗ ያስታውቃል። ከበሽታዬ አልፋ እንደ ለተብርሃን ስለ ሌላ ነገር ግን አታናግረኝም። እንኳን ለሌላ ወሬ ከህክምና ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ለመናገርም ድፍረት ያላት አትመስልም። ፖሊሶቹን፤ “ከዚህ ዞር በሉ፤ ሃኪምና በሽተኛ ብቻቸውን መሆን (ፕራይቬሲ) ያስፈልጋቸዋል” አትላቸውም። “ለምንድነው እዚህ ካፊያ እያካፋ፣ እውጭ ምርመራ የማደርግለት” አትልም።
ቃሊቲ ከአምስት ጊዜ በላይ ጥርሴን በጣም ታምሜአለሁ። በህመሙ የተነሳ ፊቴ በተደጋጋሚ ክፉኛ አብጧል። ተስቦ፣ ቁርጠት፣ ተቅማጥ፣ የመሳሰሉት የጤና መታወኮች በተደጋጋሚ ገጥመውኛል። አንድ ሰሞን  ጉንፋን ደንበኛው አድርጎኝ ነበር። ሁሉም በሽታ በህመም ማስታገሻና በጸረ ባክቴሪያ መድሃኒት እንዲታለፍ ተደርጓል።
ጥርሴ እንዲነቀልልኝ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቤአለሁ። የሰማኝ አልተገኘም። የሚታዘዝልኝንም መድሃኒት በአንዴ ለመስጠት ፈቃደኛ  አይደሉም። ሰአቱ በደረሰ ቁጥር ጠዋት፣ ምሳ ሰዓትና እራት ሰዓት ላይ እየተቆነጠሩ ይሰጡኛል። ይህ አሰራር ቀድሞ ያልነበረ አሰራር ነው። ማታ ማታ እነ አብርሃም በሩን ቆልፈው ከሄዱ ለኔ ብለው አይመለሱም። በዚህ የተነሳ የህመም ማስታገሻ መድሃኒት ታዞልኝም መድሃኒቱ በእጄ ስለማይሰጠኝ እየተሰቃየሁ ማደር እጣዬ ነው።
እኔን ውጭ አውጥቶ ከሌላ ሃኪም ጋር ማገናኘት የማይታሰብ ነው። ቁራኛዎቼ ለትንሹም ለትልቁም ቃሊቲ ወደ አለው የጤና ክሊኒክና በአካባቢው ወዳለ ጤና ጣቢያ ይወስዳሉ። ከዛም አልፎ እስከ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና አግኝተዋል። ምንም ያህል ቢያመኝ ይህንን መብት ወያኔዎች ለኔ አልሰጡም።
አስናቀችም አንድም ቀን የሃኪምነት የሥነምግባር ግዴታዋን ተጠቅማ “ሌላ ቦታ ተወስዶ ይመርመር” የሚል ጥያቄ አቅርባ አታውቅም። የደረት ማዳመጫውንና የደም ግፊት መለኪያውን ይዛ መጥታ እዛው ጸሃይ ወይም ዝናብ ላይ የምታደርገውን አድርጋ ትሄዳለች። የደም ግፊቴን ስትለካ ግን ግፊቱ በትንሹም ቢሆን ከፍ የሚያደርግ ነገር ታስከትልብኝ እንደነበር ሳትረዳ ተለያየን።
ሌላው ከወያኔ ጥብቅ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ የተነፈግኩት መብት ጸጉር የመስተካከል መብት ነው። እኔ ይህን መብት እንዳልጠይቅ በታፈንኩበት ወቅት ቦርሳዬ ውስጥ ያገኟትን የጸጉርና የጢም ማስተካከያ ተሰጥቶኛል። የራሴ ማስተካከያ ባይኖረኝ ኖሮ በጠርሙስ ይላጩኝ ነበር? ወይም ማስተካከያ ይገዙልኝ እንደነበር የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው።
ቃሊቲ እንደገባሁ በዚህ ጸጉር ማስተካከያ ዳዊትና አሰፋን ጠይቄ ጸጉሬን እንዲያስተካክሉኝ ማድረግ ጀምሬ ነበር። በዛውም እነሱንም ተራ በተራ በዚሁ ማስተካከያ አስተካክላቸዋለሁ። እርስ በርስ በመጨቃጨቃቸው የተነሳና ጠባያቸውም እየተበላሸ ስለሄደ ሁለቱንም ማስተካከሌን አቆምኩ። እንዲያውም “ደጁን ማያ ሰበብ ይሆናችኋል። እነ ብርሃነ እየወሰዱ ሌላ ጋር እንድትስተካከሉ ያድርጉ” አልኳቸው። አሳሪዎቻቸውም ሳይወዱ በግድ እነአሰፋን ሌላ ዞን እየወሰዱ ማስተካከል ጀመሩ። ተስተካክለው እስኪጨርሱ ሌላ እስረኛ ማስተካከያው ክፍል እንዳይገባ ይደረግ ነበር። እነ ዳዊት ለአስተካካዮቹ አንድ ቃል እንዳይተነፍሱ ብርሃነ ወይም በሪሁ እዛው ተቀምጠው፣ ጠብቀው ሲጨርሱ ይዘዋቸው ይመለሳሉ።
ቁራኛዎቼ የትም ቦታ ሲወሰዱም በሻምበል በሪሁ ወይም በሻለቃ ብርሃነ ታጅበው ነው። ለህክምና እንደሚወሰደው እንደሌላው እስረኛ፣ ከሌላው እስረኛ ጋር ተቀላቅለው በአንድ መኪና አይሄዱም። የሚንቀሳቀሱት ለብቻቸው አንድ መኪና ተመድቦላቸው ነው።
ቤተሰብ ጥየቃም ሲሄዱ በሪሁ ወይም ብርሃነ ሳያጅቧቸው አይሄዱም። በተለይ የአሰፋ ቤተሰቦች የሚመጡበትን አስቀድመው ስለማይናገሩ እነ ብርሃነ ተፈልገው እስከሚገኙ ቤተሰቦቹ ለረጅም ሰዓታት የሚጉላሉበት ጊዜ ነበር። ዳዊት በሶስት ዓመት ዘመዶቹ ሊጎበኙት የመጡት አንድ ጊዜ ብቻ ስለሆነ ችግር አልነበረበትም። አንዷንም ጊዜ ቢሆን ዘመዶቹ ብዙ ተንገላተው የደም እንባ አንብተው ነው ሊያገናኙት የቻሉት። አሰፋና ዳዊት ከምግብ ጠባቂዎች ጋር በቀጥታ እየተገናኙ ምግባቸውን እንዳይቀበሉ የተደረገው ከመጋቢዎች ጋር እንዳያወሩ ተፈርቶ ነው።
ይህንና ሌሎችም ፈጽመው ቅጥ ያጡ ቁጥጥሮች ለማድረግ ወያኔ ለምን እንደተገደደ እስከ ዛሬ ለኔ ሚስጥር ነው።
(ከአንዳርጋቸው ጽጌ “የታፋኙ ማስታዎሻ” መጽሐፍ የተቀነጨበ፤2012 ዓ.ም)

Read 2325 times