Saturday, 27 August 2022 12:15

“ደብረታቦርን በደብረ ታቦር ከተማ”

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    ደብረ ታቦር ከተማ ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ባለታሪክ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ በአፍሪካ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ የተመሰረተባትና ጋፋት ላይ አፄ ቴዎድሮስ ሀገራቸውን ከጠላት ለመከላከል መድፍ የፈበረኩባት ጭምር ናት-ደብረ ታቦር፡፡
ከአዲስ አበባ በ665 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የምትገኘው የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና መቀመጫ ደብረ ታቦር፤ በርካታ ባህላዊ፣ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች ያሏት ቢሆንም፣ ባላት ሀብት ልክ ያልተጎበኘች፣ ያልተዘመረላትና ሀብቷንም ወደ ገበያ በማውጣት ረገድ ገና ብዙ የሚቀራት ከተማ  ናት፡፡
የሆነ ሆኖ ደብረ ታቦር በስሟ የሚጠራውን የደብረ ታቦር በዓል (ቡሄ)፤ “ደብረታቦርን በደብረ ታቦር” በሚል ማክበርና ልዩ ትኩረት መስጠት ከጀመረች እነሆ ዘንድሮ አራተኛ አመቷን አስቆጥራለች፡፡
የደብረታቦር ዩኒቨርስቲና የደብረታቦር ከተማ በጋራ የሚያሰናዱት ይሄው የቡሄ በዓል ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ ነሀሴ 12 እና13 ቀን 2014 ዓ.ም ተከብሯል።
የዛሬ አመት ደብረታቦር ከተማ በጦርነት ስትታመስ፣ ሰው ሲገደል፣ መሰረተ ልማት ሲወድምባት እንዲሁም ህዝቧ በጭንቀትና በመከራ ውስጥ ማሳለፉን ያስታወሱት የደብረታቦር ዪኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶ/ር)፤ ያ ሁሉ መከራ  አልፎ በዚህ መልኩ የደብታቦርን በዓል ማክበር መቻላችን በእጅጉ ያስደስታል ብለዋል።
“ደብረታቦርን በደብረ ታቦር”በሚል የቡሄ በዓል በከተማዋ እንዲከበር ሀሳብ ያመነጩት በፓርላማ የደብረ ታቦር ህዝብ ተወካይና የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ የሆኑት ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) እንደነበሩ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህ ሀሳብ ከጊዜ ወደ ጊዜ  እያደገና ቅርጽ እየያዘ እንዲቀጥል በማድረጉ በኩል የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶ/ር) የአንባሳውን ድርሻ ስለመውሰዳቸውም ተመስክሮላቸዋል።
ዘንድሮም መላጣውና ገላጣው ቡሄ ከነሃሴ 12 ጀምሮ በድምቀት ተከብሯል። በተለይ በመጀመሪያው ቀን (ነሐሴ 12) በአለቃ ተክሌ የባህል ጥናት አዳራሽ፣ ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሃ ግብር፣ የአማራ ክልል ያለው አጠቃላይ የቱሪስት መስህብ  በዓይነትና በቁጥር ተተንትኖ ለታዳሚ የቀረበ ሲሆን “ይህን ሁሉ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል ያለው ተግዳሮትና መፍትሄውስ” በሚለውም ላይ ውይይት ተደርጓል። በዚሁ አዳራሽ ውስጥ ከቀረቡትና አድናቆት ከተቸራቸው መርሃ ግብሮች መካከል “ትርክት ከሚያባላን ታሪክ ይፈውሰን” በሚል ርዕሰ በመምህር ታየ ቦጋለ የቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ አንዱ ሲሆን፤ መምህር ታዬ ታሪኮችን ከነማስረጃቸው አስደግፈው ትርክቶች ከሚያባሉን ታሪኮች ቢፈውሱን ይሻላል እንጂ ከዚህ ውጪ ያለው ለማንም አይጠቅምም” ሲሉ መላው ኢትዮጵያውያንን መክረዋል።
መምህር ታዬ አክለውም በዋልታ ቴሌቪዥን በቀጥታ ስርዓት መርሃ ግብሩን ይከታተል ለነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ እስካሁን ሆን ብለው አገር አፍራሽ  ሃይሎች በሚያናፍሱት የውሸት ትርክት ንጹሃን በየአካባቢው ደማቸው እየፈሰሰ፣ ንብረታቸው እየወደመና እየተፈናቀሉ መሆናቸውን አስታውሰው፤ አሁንም ቢሆን እነዚህ አገር አፍራሽ ትርክቶችን በተመለከተ ማስረጃ አለኝ የሚል አካል ይምጣና እንዴት ውሸት እንደሆኑና በሀሰተኞች እንደተፈበረኩ በማስረጃ እሞግታለሁ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከአዳራሹ መርሃ ግብር በኋላ አመሻሹ ላይ የተለያዩ የአደባባይ ትዕይንቶች የቀረቡ ሲሆን በከተማዋ እምብርት ላይ በተገነባው የአፄ ቴዎድሮስ ሀውልት ስር (አፄ ቴዎድሮስ አደባባይ) የልጃገረዶች የቡሄና የአሸንዳ ጨዋታ፣ የወንድ ወጣቶች ሆያ ሆዬ፣ የመዘምራን የመዝሙር ትርኢት ለተመልካች ቀርበዋል።
በዋናው የቡሄ እለት ደግሞ በርዕሰ አድባራት ወገዳማት ታቦር ኢየሱስ ከጠዋቱ 2፡00 ጀምሮ የቡሄ ሃይማኖታዊ በዓል ከነሙሉ ክብሩ በዝማሬ፣ በተክሌ ዝማሬ፣ በልጃገረዶች ጨዋታ፣ በወንድ ወጣቶች የጅራፍ ግርፊያና በተለያዩ አስደሳች ሁነቶች ተከናውኗል። ይንን የቡሄን በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊት በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
ከታቦር ኢየሱስ የቡሄ በዓል አከባበር ቀጥሎ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ በአለቃ ተክሌ አዳራሽም በርካታ መርሃ ግብሮች የተከናወኑ ሲሆን፤ በሙሉዓለም የባህል ማዕከል ኪነት ቡድን የቀረቡ ጥኡመ ዜማዎች፣ ስለቡሄ ምንነትና አከባበር ደግሞ ዩኒቨርስቲው የአለቃ ገ/ሃና የባህል ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ቀሲስ እርጥባን ደሞዝ፣ የብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ (ዶ/ር) እጅግ አስተማሪና ጥልቅ ጥናቶች ቀርበዋል።
በተጨማሪም ደብረ ታቦር “የብርሃን ከተማ” የሚል ስያሜ ይሰጣት የሚል ሀሳብ የቀረበ ሲሆን፤ “ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር” የሚለውን ሀሳብ ያመነጩት ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)፤ “የቡሄ እናት” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ይህን ሀሳብ በጥንካሬ በማስቀጠል እዚህ ያደረሱት የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶ/ር) ደግሞ “የቡሄ አባት” የሚል ስያሜን አግኝተዋል።
በአጠቃላይ አራተኛው “ደብረታቦርን በደብረ ታቦር ከተማ” እጅግ በሞቀ ሁኔታ ተከብሯል። ደግሞ የዓመት ሰው ይበለን!!

Read 1245 times