Saturday, 27 August 2022 12:24

ሻደይ እና አሸንዳን ከአሸባሪ ጋር

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

   በዚህ መጣጥፍ በባህል ዙሪያ ላይ ለማተኮር አሰብኩና ሳሰላስል አንድ ወቅታዊ ባህላዊ ክብረ በዓል ትዝ አለኝ - አሸንዳ እና ሻደይ፡፡ “አሸንዳ” እና “ሻደይ” የተለያዩ ማህበረሰባዊ ጨዋታዎች ናቸው፡፡ “አሸንዳ” በትግራይ ክልል በሚገኙ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች የሚከበር የሴቶች የጨዋታ በዓል ሲሆን፤ “ሻደይ” ደግሞ በሰሜን ወሎ የሚከበር የሴቶችና የወጣቶች ጨዋታ ነው፡፡ የሻደይ ጨዋታ በሰሜን ወሎ በተለይም በላስታ “አሸንድዬ” በሚል ስያሜ፣ በቆቦ “ሶለል” በሚል ስያሜ፣ በዋግ አውራጃ ደግሞ “ሻደይ” በመባል ይታወቃል፡፡ የትግራዩንና የወሎውን ጨዋታዎች ከታሪካዊ አመጣጣቸው በመጀመር በተናጠል እንያቸው፡፡
አሸንዳ በትግራይ - ከአሸባሪ ጋር!
አሸንዳ በትግራይ ክልል በሚገኙ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች በየዓመቱ ከነሐሴ 07 - 23 ቀን የሚከበር የሴቶችና ልጃገረዶች ባህላዊ የጨዋታና የጭፈራ በዓል ነው። የአሸንዳ በዓል መሰረታዊ ይዘቱ እና አከባበሩ በመላው ትግራይ ተመሳሳይ ቢሆንም በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የተለያዩ ስያሜዎች አሉት። ለምሳሌ በእንደርታና በክልተ አውላሎ ወረዳዎች “አሸንዳ” እየተባለ ሲጠራ፤ በአጋሜ (በአዲግራት ከተማና አካባቢዋ) “ማሪያም” ይባላል፡፡ በአክሱም አካባቢ ደግሞ “ዓይኒ-ዋሪ” ይባላል፡፡
የዛሬን አያርገውና በየዓመቱ የአሸንዳ በዓል ሲቃረብ በትግራይ የሚገኙ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች በቡድን በቡድን ሆነው በዓሉን እንዴት ማክበር እንዳለባቸው መወያየትና መነጋገር ይጀምራሉ። ዝግጅቶቹ በአብዛኛው የሚያተኩሩት በበዓሉ እለት ልጃገረዶቹ ምን መምሰል እንዳለባቸው የሚደረግ ምክክር ነው። ዛሬ በትግራይ ምክክሩ ከወያኔ አስተዳደር አምልጠን እንዴት ወደ ወሎ እንግባ የሚል እንደሚሆን አስባለሁ፡፡
የአሸንዳ አመጣጥን በተመለከተ
መብራህተን ገ/ማሪያም የተባለ ጸሐፊ በትግራይ የአሸንዳ ባሕላዊ በዓል ታሪካዊ አመጣጥን በተመለከተ የተለያዩ መላምቶች መኖራቸውን ገልጿል። የሃይማኖት ምሁራን ከሚሰጡት አስተያየት ውጭ እስካሁን ድረስ “አሸንዳ ሃይማኖታዊ መነሻ አለው” የሚለውን መላምት የሚደግፉ ጥናቶች የሉም ብሏል መብራህተን። ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሳ የተባሉ የሃይማኖት ሰው ግን አሸንዳ በየዓመቱ ነሐሴ 15 ቀን የሚከበርበት ምክንያት ክርስቲያናዊ አመጣጥ ስላለው መሆኑን በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ሲገልጹ ተደምጠዋል። እንደ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ከሆነ፤ አሸንዳ ከቅድስት ማርያም ዕርገት ጋር የተያያዘ መሆኑንና በየዓመቱ ነሀሴ 15 ቀን የሚከበረውም የቅድስት ማርያም የዕርገት ቀንን ለማሰብ ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ የልጃገረዶች ብቻ እንዲሆን የተደረገው ለምንድነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሳ፤ “ሴቶች ቀኑን የሚያከብሩት ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ከመወለዷ በፊት ሴቶች ከወንዶች የበታች ተደርገው የሚታዩና የተናቁ ነበሩ። ከቅድስት ማርያም ልደት በኋላ ግን በወንዶች ክብርና እውቅና ተሰጥቷቸዋል” ብለዋል።
እዚህ ላይ አንዳንዶች የሚያነሱት ጥያቄ፤ “አሸንዳ ሃይማኖታዊ በዓል ከሆነ ታዲያ እንደ ትግራይ ሁሉ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለምን አልተከበረም?” የሚል ነው። ለምሳሌ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ የዳበረና የላቀ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት አለ። በጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ባሉ ማህበረሰቦች ግን አሸንዳ አይከበርም፡፡
ሰላም ባለኸይ እና ሙሉብርሃን ባለኸኝ የተባሉ የመቀሌ ዩንቨርስቲ ምሁራን “The Art, Aesthetics and Gender Significance of Ashenda Girls’ Festival in Tigray, Northern Ethiopia” በሚል ርእስ በትግራይ የሚከበረውን አሸንዳ በተመለከተ ባደረጉት ጥናት፤ “የአሸንዳን አመጣጥ በተመለከተ ባደረግነው ጥናት ሁለት አማራጮችን ልንጠቁም እንወዳለን” ካሉ በኋላ “እነሱም፡- 1) አሸንዳ የአዝመራ መሰብሰቢያን እና የወቅቶችን መቀያየር አስመልክተው አረማውያን የሚያከብሩት ባህል ነው አሊያም 2) አሸንዳ በአረማውያን ልማድ መሰረት ወጣቶች ለመተጫጨት የሚያከብሩት ባህል ነው” የሚል መላምት (ሃይፖተሲስ) አስቀምጠዋል።
የአሸንዳ ዜማዎች - ማህበራዊ ሂሶች
እንደ ጄንግ እና ሳንቶስ (2004) ያሉ የማህበረሰብ ጥናት ተመራማሪዎች “ባህላዊ ወግና ልማዶች በማህበረሰቦች መካከል ማንነትንና አንድነትን በማጎልበትና በማጠናከር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ” ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ በትግራይ የአሸንዳ በዓልን የሚያከብሩ ልጃገረዶች እና ወጣት ሴቶች ከእናቶቻቸውና ከታላላቆቻቸው የሰሙትን ግጥሞችና ዘፈኖች በቃል በመውረስ ብቻ ሳይሆን በአካባቢያቸው የሚያዩዋቸውን ሁኔታዎች የሚመለከቱ ግጥሞችን በመፍጠር ያዜማሉ፡፡ በዜማቸውም የተለያየ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ያስተላልፋሉ።
በአሸንዳ በዓል ላይ የትግራይ ልጃገረዶች እና ወጣት ሴቶችም እራሳቸውን ወደ ማህበራዊ ተቺነት በመቀየር ግለሰቦችን በመተቸትና አስተያየት በመስጠት በማህበረሰባዊ ጥፋታቸው የተነወሩ ሰዎችን ይገስጻሉ። የእነሱ ትችት የሚያተኩረው በብዙ የማህበራዊ ህይወት ዘርፎች ላይ ሲሆን፤ በተለይም በህብረተሰቡ ውስጥ በግለሰቦች እና በቡድን ማህበረሰባዊ መስመሮችን በተላለፉና ማህበራዊ ወግና እሴቶችን በጣሱ፣ በህዝብ የተጠላን ነገር በፈጸሙ ሰዎች ላይ ያተኩራል። ማንም አይተርፍም፡፡ ግለሰቦች፣ ማህበረሰቦች፣ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች፣ ታዋቂ ሰዎች ወዘተ ሁሉም ይተቻሉ፡፡
ዘንድሮ ግን የትግራይ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች እንኳን አደባባይ ወጥተው መንግስትን ሊወቅሱ፣ አጥፊዎችን ሊተቹ ቀርቶ ከእናታቸው ጓዳ አይወጡም፡፡ ከወጡ በሀሺሽ በናወዙ የወያኔ ጀሌዎች ይደፈራሉ። አሊያም ያለ ፍላጎታቸው እየታነቁ ለጦርነት ይማገዳሉ። እንዲያውም ብዙዎቹ በአሁኑ ወቅት ክላሽ ተሸክመው በየበርሃው፣ በየጢሻው፣ በየተራራውና በየሜዳው እየተንከራተቱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
አፄ ዮሐንስ 4ኛ በአሸንዳ ልጃገረዶች የሚዘፈኑትን ማኅበራዊ ትችቶች የሚያዳምጡ ሰዎችን ወደ በዓሉ ስፍራ ይልኩ ነበር ይባላል፡፡ ንጉሡ በሚመጣላቸው መረጃ መሰረት፤ በዘመነ ስልጣናቸው ይፈጸም የነበረውን ጥፋት ለማረም ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ዛሬ እነ ንጉስ ደብረ ጽዮን እንኳን የሚተቻቸውን ቀና ብሎ የሚያያቸውን ሰው በህይወት አያሳድሩትም፡፡ እናም ዛሬ የትግራይ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች በአሸባሪ አስተዳደር ውስጥ ሆነው አሸንዳን በአደባባይ ሳይሆን በየቤታቸው ጓዳ በትዝታ እያሰቡት እንደሆነ ይታመናል፡፡
“ሻደይ” – “አሸንድዬ” – “ሶለል” ጨዋታ በሰሜን ወሎ
በወሎ ዩንቨርስቲ መምህርት የሆኑት ዶ/ር አፀደ ተፈራ “የሻደይ ጨዋታ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር” በሚል ርእስ ባዘጋጁት የምርምር ጽሑፍ፤ በትግራይ “አሸንዳ” የሚል ስያሜ ያለው የልጃገረዶችና የወጣት ሴቶች የጨዋታ በዓል በዋግ “ሻደይ”፣ በላስታ “አሸንድዬ”፣ በቆቦ “ሶለል” እንደሚባል ገልጸዋል።
ዶ/ር አፀደ ጥናት ያደረጉት በዋግ ኽምራ የሻደይ ባህላዊ ጨዋታ ክዋኔና ፋይዳ ላይ ሲሆን፤ የሻደይ ባህላዊ ጨዋታ የፎክሎር ዘርፎች በሆነው በሀገረሰባዊ ባህል ስር የሚመደብ ነው ብለዋል። እንደሚታወቀው “ፎክሎር” ማለት የአንድ ማህበረሠብ ባህል፣ እምነት፣ ስርዓተ-አምልኮ፣ አመጋገብ እና ልማድ ወዘተ የሚገለፅበት የእውቀት ዘርፍ ነው፡፡ “ፎክሎር” ማህበረሰብ በባህልም ሆነ በዘልማድ የሚተገብረው የሰዎች መንፈሳዊና ቁሳዊ ተግባር ነው የሚል ትርጉምም አለ፡፡ “ፎክሎር” ማለት የተለያዩ እምነቶችን፣ ልማዶችንና ባህልን ከትውልድ ወደ ትውልድ የምናስተላልፍበት መንገድ ነው የሚሉ ምሁራንም አሉ፡፡
ዶርሰን የተባለ የሥነ-ሰብ ተመራማሪ “ፎክሎር”ን በአራት አበይት ዘርፎች ይከፍለዋል፡፡ እነሱም፡- ፌስቲቫልና ክብረ-በዓል፣ መዝናኛዎችና ጨዋታዎች፣ ሀገረሰባዊ መድኃኒት እና ሀገረሰባዊ ሃይማኖት ናቸው። ከላይ ከቀረቡት ትርጓሜዎች ስንነሳ ሻደይም ሆነ አሸንዳ በ“ፎክሎር” ውስጥ የሚጠቃለል ማህበረሰባዊ እሴት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
የጨዋታው ቅድመ ዝግጅት፣ ሂደትና ፋይዳ
በዋግ “ሻደይ”፣ በላስታ “አሸንድዬ”፣ በቆቦ “ሶለል” ተብሎ በወጣት ልጃገረዶች የሚከበረው በዓል በከተማ ከነሀሴ 16 – 18 ቀን (ለሦስት ቀናት)፣ በገጠር ደግሞ ከነሀሴ 16 – 21 ቀን (ለስድስት ቀናት) የሚካሄድ ጨዋታ ነው፡፡ ወጣት ወንዶች ሴቶችን ለመጠበቅና የትዳር አጋርን ለመምረጥ በዚህ ጨዋታ ላይ እንደሚሳተፉ ይታወቃል፡፡
ሻደይ፣ አሸንድዬም ሆነ ሶለል በቡድን የሚከናወን ጨዋታ በመሆኑ ቅድመ ዝግጅት የሚፈልግ ጨዋታ ነው፡፡ በመሆኑም፤ በዓሉ ከሚከበርበት ዕለት አንድ ሣምንት ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት የቡድን ምስረታ ምክክር ተደርጎ ቡድን ይመሰረታል፡፡ ሌላው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጊያጌጥ ወይም መዋብ ነው፡፡ በዓሉ ቆነጃጅት ሁሉ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ አዲስና የፀዳ ልብስ ለብሰውና ተኳኩለው የሚታዩበት እለት በመሆኑ፤ ወጣቶቹ ለውበት ማድመቂያ የሚሆናቸውን ነገር ሁሉ ያሰባስባሉ። ያላት የራሷን፤ የሌላት ደግሞ ተውሳ አጥባ ታዘጋጃለች። የጌጣጌጥ ዓይነቶችም ከዘመድ አዝማድ ይሰባሰባሉ፡፡ ሹሩባ መሰራት ሌላው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ነው፡፡
የሻደይ ጨዋታ በሚከበርበት እለት የቡድን አባላት ይሰበሰቡና ጨዋታቸውን ከመጀመራቸው በፊት አለቃ ይመርጣሉ፡፡ አለቃዋን የሚመርጡበት መስፈርት በእድሜ ትልቅ መሆን፣ ታማኝነት፣ ውበት እና የጨዋታ ችሎታ ናቸው፡፡ የቡድኑ አለቃ ሁለት ተግባራትን ታከናውናለች፡፡ አንደኛ፤ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ትይዛለች፡፡ ሁለተኛ፤ ችሎታ ያላት ከሆነቺም በአቀንቃኝነት ትጫወታለች፡፡
የሻደይ ልጃገረዶች ለሦስት ቀናት ጨዋታቸውን በየግለሰቡ ቤት ያካሂዳሉ፡፡ ብር የሚሰጣቸው ይሰጣቸዋል፡፡ የማይሰጥ “ተቀድማችኋል” ይላል፡፡ “ተቀድማችኋል” ማለት ለሌላ ቡድን ሰጥተናል ማለት ነው፡፡ … በዚህ መልኩ ቀኑን ሙሉ ሲጫወቱ ይውላሉ። በማግስቱም “ነገ ኑ” ወዳሏቸውና በእለቱ “አበባ ጥለናል” በማለት ወዳለፏቸው ሰዎች ቤት በመሄድ ገንዘብ ያልተቀበሉባቸውን ቤቶች ያዳርሳሉ፡፡ በሦስተኛው ቀን ከሰዓት በኋላ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ጨዋታቸውን ያጠናቅቃሉ። ወደ ማታ ላይ የቡድኑ አባላት ይሰባሰባሉ፡፡ ያሰባሰቡትን ገንዘብ ስለመከፋፈል ይመክራሉ። ይከፋፈላሉ፡፡
በገጠር ደግሞ በየቤቱ በመዞር የሚያዋጡት ወይም የሚያሰባስቡት እንደ ከተማ ገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ ዱቄት እና  ክክ፣ በርበሬ፣ ቅቤ፣… የመሳሰሉትን ማጣፈጫዎች ያሰባስባሉ። ዱቄቱን አቡክተው እንጀራና ዳቦ ይጋግራሉ። ያሰባሰቡት ማጣፈጫ አነስተኛ ከሆነ ከየቤታቸው በማዋጣት ጨማምረው ወጥ በመስራት ከእናቶች ጋር ተሰባስበው ይበላሉ ይጠጣሉ፡፡
በአጠቃላይ፤ የሻደይም ሆነ የአሸንዳ ጨዋታ በርካታ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ጨዋታው ማህበረሰባዊ እምቅ እሴትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል ትልቅ መድረክ መሆኑ፣ በቤት ውስጥ ተወስነው የሚውሉ ሴቶችን ለአጭር ጊዜም ቢሆን ወደ አደባባይ ወጥተውና ነጻነት ተጎናጽፈው እንዲጫወቱ የሚፈቀድበት መሆኑ፣ ሴቶች ከመቼውም በበለጠ ተውበውና ደምቀው ከመታየታቸውም በላይ ከቤት ወጥተው የማያውቁት ወጥተው በአደባባይ ስለሚታዩ ለትዳር የሚፈላለጉ ወጣቶች የሚጠያየቁበትን አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑ፣ ጨዋታው ከልዩነት ይልቅ አንድነት ጎልቶ የሚታይበት መሆኑ፣ ጨዋታው ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶች መዝናኛ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑና ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በጨዋታው ባይሳተፍም በተመልካችነት ደስታውን በመግለጽ ስነ-ልቦናዊ እርካታ የሚያገኝበት መሆኑ ዋና ዋና ፋይዳዎቹ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡
የሻደይም ሆነ የአሸንዳ ጨዋታ ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም በተንከባካቢነትና በጠባቂነት የሚያሳትፍ፣ የወደፊት የትዳር ጓደኛ ምርጫም የሚከናወንበት፣ በርካታ ቁሳዊ ባህሎች የሚተዋወቁበት፣ የማህበረሰብ ማንነት ጎልቶ የሚታይበት ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡ ይህ ጨዋታ ድምቀቱንና ውበቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ፋይዳው ዘርፈ ብዙና የጎላ በመሆኑ ለመስህብነቱ ሀገር አቀፋዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ትኩረትና ጥበቃም ያሻዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡Read 12082 times