Saturday, 27 August 2022 12:45

ሆያ ሆዬ በየዓይነቱ

Written by  ቡሄ (ፊጋ)
Rate this item
(1 Vote)

   ቡሄ (ፊጋ)

ክፈት በለው ተነሣ
ያንን አንበሳ (2)
ክፈት በለው በሩን
የጌታዬን (2)
ሆያ ሆዬ ሎሚታ
ልምጣ ወይ ወደማታ
ሆያ..ሆዬ… አብዬው መሬ
ሆያ ሆዬ…ሆ (2)
ድንጋይ ለድንጋይ -(ሆ)
ትዘላለች ጦጣ- (ሆ)
እኔ አለቅም ዛሬ (ሆ)
ነብሴ ብትወጣ! (ሆ)
    ሆያ ሆይ ሎሚታ
    ልምጣ ወይ ወደማታ
ሆያ ሆዬ-ሆ (2)
ሆይ የኔ ጌታ (ሆ)
ሲቀመጥ ያምር (ሆ)
ሲቆም ይረታ (!)
    ሆይሽ ሆዬ ጉዴ
    ጨዋታ ነው ልማዴ!
ሆያ ሆዬ…
የኔማ ጌታ- አጣ ከሚሉኝ
በቁርበት ጠቅልለው ገደል ይጣሉኝ
የኔማ ጌታ-(ሆ)
ብትሰጠኝ ስጠኝ-(ሆ)
ባትሰጥ እንዳሻህ-(ሆ)
ከጎረቤትህ- (ሆ)
ካነሰ ጋሻህ!
ሆያ ሆዬ ጉዴ
ዝና ወዳዴ!
እንንዳው ላ-ሙን… እንንዳው
ላሙን?... እንንዳው
ደባ ደባው-ን!... እንንዳው
ላሙን?- እንንዳው
ሆያ ሆዬ ጉዴ
ዝና ወዳዴ!
    ሆያ ሆዬ ሆ
    ሆያ ሆዬ ሆ
የኔ … እ-መ-ቤ-ት-”ሆ”
የፈተለችው-”ሆ”
የሸረሪት ድር-”ሆ”
አስመሰለችው!-ሆ!
ለዚያች ለማሪያም-”ሆ”
እዘኑላት-”ሆ”
ዓመት ተመንፈቅ-”ሆ”
አለቀላት! ሆ
    ሆያሆይ ሎሚታ    
    ልምጣ ወይ ወደማታ!
ሆያ ሆዬ- አብዬው መሬ (2)
የወንዜው -ነብር…”የወንዜው”
ነብር?... “የወንዜው”
ሊበላኝ ነበር… “የወንዜው”
ጋሽዬ ባይኖር… “የወንዜው”
ጌትዬ ባይኖር… “የወንዜው”
(ምርቃ)
    ክበር በስንዴ ክበር በጤፍ
    ምቀኛህ ይርገፍ!
    የነጭ ጤፍ ዘርፋፋ
    የወለዱት ይፋፋ!
ዓመት ዓውዳመት-ድገምና
የጌታዬን ቤት ድገምና
ወርቅ ይፍሰስበት- ድገምና
የእመቤቴን ቤት- ድገምና
ወርቅ ይፍሰስበት- ድገምና
ክበር በስንዴ ክበር በጤፍ
ምቀኛህ ይርገፍ
የነጭ ጤፍ ዘርፋፋ … የወለዱት ይፋፋ!
አስዮው ቤሎማ- “እሆሆ አሃሃ”
የቤሎማ ጥጃ- “ኦሆሆ አሃሃ”
ይዟታል ቁንጫ- “ኦሆሆ አሃሃ”
ታሥረን እንንጫጫ “ኦሆሆ አሃሃ”
***
እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ከምንጃር ድረስ የሚመጡ ሆያ-ሆዬ ጨፋሪዎች ነበሩ - ከምንጃር ተነስተው በውልንጭቲ በኩል የሚመጡ አሉ! ከፊሎቹ ደግሞ በኤጀሬ በኩል በሞጆ አድርገው ናዝሬት ይገባሉ። የነዚህኞቹ መነሻቸውም በሙክዬ በኩል ነው።
በየደረሱበት እንደኛ እንደ ከተሜዎቹ ሙልሙልና ሳንቲም ሳይሆን፤ ድፎ ዳቦ፣ ሙክት፣ ወይፈን አንዳንዴም በሬ ተሸልመው ነበር የሚመጡት! በየመንገዱ እያረዱ እየበሉ ነው ወደ እኛ፣ ወደ ናዝሬት የሚደርሱት። ይህ የጭፈራ ሂደት በጅራፍ ጩኸት፣ አንዳንዴ በጠመንጃ ጥይት ድምጽ የታጀበ ሲሆን፤ የሰው ብዛት እጅግ በርካታ ነው። አልፎ አልፎ ድንኳን ይዘው የሚመጡ አሉ። በተረፈ ግን በሀብታም ቤት ደጃፍና ግቢ ይደግሳሉ። ጠላ በእንሥራ(ዎች) ይቀርብላቸዋል። በየደረሱበት ቤት ቤተሰብ ናቸው!! ይህ ሂደት እስከ እንቁጣጣሽና አልፎ ተርፎም እስከ መስቀል ይቀጥላል። ማታ ጅብና ማንኛውንም አውሬ  በችቦ ነው የሚያባርሩት። ናዝሬት ከገቡ በኋላ እኛ ቤት ግቢ ሲያርፉ ትዝ ይለኛል። ግቢውን ጢም አድርገው ይሞሉታል። ከምንጃር ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ጨፋሪዎች ከወደ ጮሬም ይመጣሉ።
እኛ ግቢ የሚገናኙበት ጊዜ ነበረ!
ጨፋሪዎቹ እንደኛ እንደ ናዝራዊዎቹ ልጅ - እግሮች ሳይሆኑ፤ ጎረምሶችና ወጠምሻ፣ ወጠምሻ ኮበሌዎች ናቸው። በሚመገቡበት ጊዜ አሞራና ጭልፊት ካስቸገራቸው በዱላ ቅዝምዝምና በረዣዥም ወንጪፎች ያባርሯቸዋል። አንዳንዴም ይተኩሱባቸዋል!!


Read 750 times