Saturday, 03 September 2022 13:57

ኔፓል እንደ ቆንጆ ሴት!

Written by  -ድረስ ጋሹ-
Rate this item
(4 votes)

[...ምድር እሳት ትተፋ ፣ ሰማይ ዋእዩን ያወርደው ጀመር። ላዩ ነዲድ ታቹ  ወበቅ ፣ ቀኑ ቃጠሎ ሌቱ ብርድ ሆነ። የእሳቱ ላንቃ ከልብሴ ወደ አካሌ ተዛመተ። ከታች ያለውን ስንኝ እንደ ዳዊት ልደግም ቃተትኩ...
 አበሻ ቀሚሴን እሳት ፈጀው ማታ ፤
እሳት ዳር ቁጭ ብዬ ስቋጥር ስፈታ።
... የእይታዬን መዳረሻ ደመና ሲጋርደው ፤እራመድበትን መንገድ ሸረኛ ሲጎርደው...በሐሳብ መንጎዴን ቀጠልኩ። በእግር ያልደረሱትን በሐሳብ ይጓዙታል። በእውን ያልጨበጡትን በህልም ይቧጥጡታል። ከደቃቅ ገባሮች እስከ ትላልቅ ወንዞች፣ ከዕደ-ጥበባት እስከ ፋብሪካ ውጤቶች ...ብዙ ‘ ከ ...እስከ’ ዎችን ማተርኩ።  ዕጣ ፈንታዬን ለህልም ዳርኩት ... ዕድል ክፍሌን ከሐሳብ አዋሰብኩት። ሐሳብ አማጥኩ። ሐሳብ ወለድኩ።
እነሆኝ...
[[...የጎረምሳ ዓይን ቢወረወር ወደ ጡት፣ እይታውን ቢቆለምመው ዳሌ ነበር። ዓይኔ ወደ ተራራ ...ዓይኔ ወደ ተፈጥሮ መባከኑ ግን ለምን ነው ?....ሕይወት የተራራ አምሳል ...ሲወጧት አቀበት፣ ሲወርዷት ደግሞ ቁልቁለት፤ ለአንድ ተራራ ሁለት ስም ፣ ለአንድ ሕይወትም እንዲሁ:: ከቡድን ፎቶግራፍ ውስጥ ቀድሜ የማየው ራሴን ነው። ከብዙ ደስታዎች መሐል ችግሬን ማየቴ ለዚህ ነው። ችግሬ ሕይወት...ሕይወት ተራራ!
[[...ዓይኔ ተራራ አየ። ተራራ ሕይወት ፤ሕይወትም እሱን አልኩ። ተራራው የኔፓል ነበር። የቆንጅየዋ ኔፓል  ዳሌ ዓይኔን ሳበ። ተማረኩ። የጊዜን እና የቦታን ክልል ጥሳ ነደፈችኝ። አገርም እንደ እናት ይናፍቃል ወይ ሲሉ አውቃለሁ። አገርም እንደ ሴት ይፈቀራል ወይ? ብዬ ላለመቀጠሌ እንዴት ልተማመን። ከቁሜ ኩምሽሽ፣ ከሽብርኬ ልውስ አልኩ። ደግሜ ደጋግሜ አየኋት... አሐዱ ፣ክልኤቱ ...ሰለስቱ!!
[[...ልቤ ወደ ውጭ ሃገራት ተጓዘ። ሐሳቤ ቀድሞ ነበር። ዳሩ መንገድ ዳር የተጎለተ ፍቅር አደናቀፈኝ። በደቃቅ ከተጻፉት ያገር ስሞች መካከልም ወደቅኩ። ተጋድሜ ዓይኔን  በሕንድ እና በቻይና መካከል አንከላወስኩት። ድንገት የኔፓል አጎጠጎጤ  ቀንጣፋ ሆነብኝ። ላልፍ ስል የሚጎትት ፣ልራመድ ስል የሚስብ ...እንደዛ ዓይነት ነገር ተፈጠረ!...በደቡብ እስያ የምትገኝ በጣም ውብ የአገር ኮረዳ ፣ ወደብ የለሽ ሀገር እንደሆነችም ቃኘሁ። የተለያዩ የሂማሊያን መልክዓ ምድሮች፣ አስደናቂ ተራሮችና አስደናቂ ቦታዎችን የያዘች ኔፓል፤ የገነት ቁራጭን እንዴት አላፍቅር?...አልውደድስ?
 ሽፋሽፍቴን ሳላቅቅ፣ ዓይኔን ከፈት ሳደርግ፣ ልዩነቷ በውልብታ ይመጣብኛል። ለምን?...ተከተሉኝ ላስቃኛችሁ....
[[ ፩... በልጆች የቴሌቪዥን ጣቢያ ዓይኔን አሳስሜ ሳለ፣ 10 ጥያቄ ሰማሁ። ከሁለቱ በቀር መልሱ ሁሉ ኔፓል ነበር።  ኔፓል የሂማላያ አገር ናት። የተኳኳለች ሙሽራ ትመስላለች። ሚዜዎቿ ...እያጀቧት...እየዘመሩላት የምትኩነሰነስ ልጃገረድን ታሰንቃለች። ተራሮቹ ፣ኔፓል፣ ቡታን፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ፓኪስታንን ጨምሮ በአምስት አገሮች መካከል ይጋራሉ። ከአለማችን 10 ከፍተኛ ቦታዎች  8ቱ ኔፓል ውስጥ ታጭቋል ፤ኤቨረስትን ጨምሮ...ኦ ኔፓል!...በአንችስ ፍቅር ወደቀ ልባል!
  ኦ! ኔፓል...ኦ! አገር..ኦ! ማማር
[[ ፪....በአለም ላይ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ብሄራዊ ባንዲራ የሌላት ብቸኛ ሀገር መሆኗስ አይደንቅም?...(ከተለመደው ክብ እንጀራ ውጭ አራት ማዕዘን አይተህ ታውቃለህ?...የለም!)። የኔፓል ብሔራዊ ባንዲራ በሁለት ባለ ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ባላቸው ባንዲራዎች የተዋቀረ ነው። መላው ዓለም አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ባንዲራ ቅርጽ ቢኖረውም ሀሳቡ አልተለወጠም። ቀይ ቀለም ያለው የበስተጀርባ ቀለም እና የሰንደቅ ዓላማው ጥቁር ሰማያዊ ድንበር በኔፓል ጥበብ እና ማስጌጫዎች ውስጥ ተወዳጅ ቀለሞች ናቸው። በሰንደቅ ዓላማው የላይኛው ክፍል ላይ  ስምንት ጨረሮች ያሏት ነጭ ጨረቃ አለች:: በታችኛው ክፍል ደግሞ አሥራ ሁለት ጨረሮች ያሉት ነጭ ፀሐይ ታያለህ። ሁለቱ ምልክቶች ከሉዓላዊው መንግሥት ሥርወ-ነገሮች ጋር የተቆራኙ ናቸው፤ እናም ሀገሪቱ እንደ ፀሐይና ጨረቃ ተመሳሳይ ረጅም ዕድሜ እንዲኖራት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል ...ኦ ኔፓል!...ስለአንቺስ ብዙ ልባል!  
  ኦ! ኔፓል...ኦ!ቦታ...ኦ!ፍቅር
[[ ፫...የኔፓል ማህበረሰብ የገባው እንደሆነ ሰማሁ። የሚከተሉት ሃይማኖት በብዛት ሂንዱይዝም እና ቡድሂዝም ነው። የቡድሃ የትውልድ ቦታ መሆኗን ልብ ይሏል። በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ጥል የለም። ብዙ ጎሳ አለ፤ የጎሳ ግጭቶች ግን አይስተዋሉም። በዩኔስኮ ከሰባት በላይ ቅርስ ያስመዘገበች የቱሪስት መዳረሻ መሆኗ ደስታን ያጭራል። ዘፈናቸው በታሪክ የተዋቀረ እና ልብ ኮርኳሪ ዋሽንት የታከለበት መሆኑ የመንፈስ እርካታ የሚሰጥ ነው።
በተራራ የተዋበች የአገር ኮረዳ ፣በወንዞች ፣በሀይቆች ፣ በጫካዎችና በውብ መልክዓ-ምድር የተሰራች፣ ተግባቢ  ኗሪ ያጀባት፣ የዱር አራዊቶች ያደመቋት ወይዘሮ እንዴት አትወደድ?
  ኦ! ኔፓል...ኦ!አየር...ኦ!ምቾት
[[ ፬...ኔፓል በየትኛውም የውጭ ወረራ ስር ያልነበረች ሀገር ነች። የነጻነት ቀንን አታከብርም። በቅኝ ግዛት ታሪክ ውስጥም  አልነበረችም። በዓለም ሪከርድ ድንቅ ደረጃ ያላቸው ... የኤቨረስት ተራራ ከባህር ጠለል በላይ 8,848.48 ሜትር ከፍታ ያለው የአለማችን ከፍተኛው ጫፍ፣ የቲሊቾ ሀይቅ ከባህር ጠለል በላይ በ4,800ሜ ከፍታ ያለው የአለማችን ከፍተኛው ሀይቅ፣ የሼይ-ፎክሱንዶ ሐይቅ በ145 ሜትር ጥልቀት ያለው የዓለማችን ጥልቅ ሐይቅ ፣ በአለም ላይ ያለው ጥልቅ ገደል “Kali Gandaki Gorge” ከአናፑርና I 5,571m ያነሰ መሆኑ፣አሩን ሸለቆ በምድር ላይ ከፍተኛው ሸለቆ ፣ሆቴል ኤቨረስት ቪው በዓለም ላይ ከፍተኛው ሆቴል መሆናቸው ይታወቁላታል።
   ኦ! ኔፓል...ኦ!አገር...ኦ!ሰላም
 ኔፓልን በሐሳብ ጎበኛችሁ?...በቂ ነው።
...ሐሳብ ፈረሰኛ አይደለም። እርካብ፣ ልጓም ቀረ  ኮርቻ ጠፋ አይልም፡፡  እኔም እርካብ ስጎትት፣ ኮርቻ ሳነጥፍ አልቆየሁም፤ ሐሳብ ...ነጎድኩ ...ዋለልኩ ... አራት ማዕዘን እንጀራ የማየት ያህል ነቃሁ። ባልተመደ መልኩ ...ባልታየ መንገድ ዓይኔን ለትዕይንት፣ አፌን ለቅኝት ከፈትኩ። ተሳካልኝ ብዬ አልቆምኩም።
ስኬት መዳረሻ ሳይሆን ጉዞ እንደሆነ ጅብራን አረዳኝ። ለጉዞ ወጣሁ። ፊቴን ወደ ኢትዮጵያ አዞርኩ። የሚናገሩላት እያለ የምናገረው ጠፋኝ።
....አምስቱ የስሜት ሕዋሶቼ ተራ በተራ ተቃኙ። እንደ ክራር ዜማ አወጡ፡፡ ባለትክሻው ሊጨፍር ተነሳ፤አንካሳው ምድር ቀለለችው፡፡ እፎይ አልኩ። ተገዝግዞ ዜማ ፣አምጦ ልጅ ፣አስቦ ጽሑፍን ለምደናል፡: ዓይነ ህሊና በጽሑፈ ልቡና ሲመራ፣  አበባ ቢቄላ በባዶ እግሩ የሮጠበት ሮም፣ ማንዴላ የተማረበት ት/ቤት፣ አና ፍራንክ የተደበቀችበት ቴራስ ሳይቀር ይታያል ፤ኔፓልም እንዲሁ !
....መላዕክት ይዞት የመጣ የራእይ ደብዳቤ ሕልሜ ውስጥ ነበር። ከፍቼ ማንበብ አልቻልኩም። ልቤ ያመነው “ኔፓል እንደ ቆንጆ ሴት “ እንደሚል ገመትኩ። ግምቴ ፈር የሳተ አይመስለኝም።
የጃርት ሕልሟ ዱባ ይሉት ብሂል ያረጋግጥልኛል። ሕልሜ  አገር...አገርም ተራራ..ተራራም ሕይወት ...ለአንዱ አቀበት ለአንዱ ቁልቁለት ...ለዚህም ኔፓልን ለተምሳሌትነት አሳጫት።

Read 1621 times