Saturday, 03 September 2022 14:12

ከሚመጣው ዓመት ዶሮ፣ እንቁላል ዘንድሮ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዕለታት አንድ ቀን  የቅዳሜ ሹር ለት  ቤተሰብ ተሰብስቦ፣ የፆመ የሚገድፍበት፣ ያልፆመም በግድ ተቀስቅሶ ገበታ የሚቀርብበት ሌሊት፣ አንድ አመለኛና አስቸጋሪ ልጅ፣ እንደ ሁልጊዜው ከሰው ፊት ምንትፍ ያደርጋል፡፡
የዚያን ዕለት ሌሊት በእንግድነት የተገኘ ጥቁር እንግዳ አለ፡፡
አባትና እናት፣ ያ አመለኛ ልጅ ያስቸግራል ብለው በየደቂቃው ስቅቅ ይላሉ፡፡ ዶሮው መጣ፡፡ ለየሰው በቁጥር እየለዩ እናት አወጡ፡፡ አመለኛው ልጅም ደርሶታል፡፡ ግን አመል ነውና ፋንታውን ዋጥ ስልቅጥ አድርጎ በእጁ እመር እያለ፣ የእንግዳውን ዕንቁላል ላፍ አደረገ፡፡
አባት፡-
“ኧረ ይሄ ባለጌ፣ የእንግዳውን ድርሻ ትወስዳለህ?”
እናት
(በምንተፍረት)
“ግዴለም ይብላ ተውት፣ ልጅ አደል? አለኮ፣ለእንግዳው አወጡለት፡፡”
እንግዳውም በሀፍረት ልሳን፡-
“ኧረ ግዴለም አትቆጡት! የእኛ ቤት ልጅ´ኮ ሙሉ ድስቱን ነው አንስቶ ይዞ የሚሮጠው!” አለ
ይሄኔ አባት፤
“አይ ለሱስ ደህና አድርገን ቀጥተነዋል፡፡”
***
በዓላት እንደ ድምቀታቸው ቀላል የኢኮኖሚ ጠባሳ  ሳይተው አያልፉም፡፡ በተለይ ከነሐሴ 12-13ቱ ቡሄ እስከ እንቁጣጣሽ፣ አልፎም እስከ መስቀል፣ እንደየ ብሔረሰቡ የፌሽታ አከባበር ስርዓት የዋዛ ጉዳት አይደለም የሚያደርሱት።
ከበዓላቱ በተጨማሪ ደግሞ መስከረም የትምህርት ቤት መከፈቻ ወቅት መሆኑ፣ የየቤተሰቡን ኢኮኖሚ መጫኑና ኪስን ማጎድጎዱ፣ የየዓመቱ የሂሳብ ስሌት የሚያስታውሰው ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ ለክረምት እረፍት ቤተሰቡን ለማየት ከውጪ የሚመጣው ሰው ብዛት እንኳ የዋዛ አይደለም፡፡ ሁሉም የየትውልድ ቀዬውን ባሕላዊ እሴትና ማዕድ ተቋድሶ ወደመጣበት ይመለሳል፡፡
ከበዓላቱ ሁሉ ግን እንደ መስከረም ደማቅና በፀደይ የተከበበ፤ ጨፍጋጋውን ክረምት ለማሰናበት ፀሐይ ፏ ብላ የምትበራበት፣ የአዲስ ዘመን ብስራት፣ በአየር  ጠባዩ ለውጥ የሚነገርበት፣ ልጆች አበባ ስለው ከቤት ቤት እየዞሩ፣ ለየዘመድ አዝማዱ የሚሰጡበት ወዘተ የለም፡፡
ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ፤
“…ማን ያውቃል እንዳለው፣ ለድንጋይስ ቋንቋ፣
ለሚቆረጥ ዛፍ፣ እንዳለው ጠበቃ ?
ማን ያውቃል?
የመስቀል ወፍና፣ የዐደይ አበባ
 ቀጠሮ እንዳላቸው፣ መስከረም ሲጠባ?!...”
ማለታቸውን ይኸው ለዘመናት እየደጋገምን እንለዋለን፡፡
በአዲስ ዘመንና ወቅት አዳዲስ አበቦች ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ልቦች፣ አዳዲስ ሃሳቦች፣ አዳዲስ ራዕዮች፣ አዳዲስ የህይወት ቅኝቶች፣ እንዲያብቡ ተስፋችን ህልቆ-መሳፍርት የለውም፡፡ አዲስ ዓመት የአዲስ ህልውና መፀነሻና ማደጊያው ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
አንድ የአገራችን ገጣሚ ለእንቁጣጣሽ ለገናና ለጥምቀት በዓል የገጠመው የሚከተለው ግጥም፣ ለየዘመኑ ያገለግላል፡፡ እነሆ፡-
ያበባነቴ አበባ
በአበባነቴ አበባ፣ ማዞሬን ዛሬ ሳስበው፣
እንደቀን-ጥንጥን ተዳውሮ፣ ዛሬ ለሆንኩት ሁሉ
ንጥረ-ነገሩ እሱው ነው!
ትላንትና አላለቀም
የአበባ ጅምር ነው እንጂ፣ ረግፎ መሬት አልወደቀም፡፡
ዘመን ማለት የዕድሜ ቁጥር
የእንቁጣጣሾች ጀማ ነው፣ ያልባለቁ አበቦች ድምር፡፡
ያላለቁ እምቡጦች ቀመር!
የአበባነቴ አበባ ነው፣ የየዕለቱ ዕድሜ ስፍር፡፡
የአምና ጀምበር ጠልቃ አትቀር
በዘንድሮ በኩል ልትሰርቅ፣ ተሻግራም ነገ ልትጨርር
 የአበቅቴን ውል ልታሻግር
ያው ትኖራለች ከኛው ጋር፡፡
ያም ሆኖ፣ የጥንቱ አበባ፣ አሁን/ጠውልጎ እንዳላየው
የየዓመታቱን ጉንጉን ሐር፣ በንቡጥ ቀለም ነው  ምፈትለው!
የትላንት እኔን ሰርቄ
ለዛሬው እኔ አበድሬ
ለነገም ወለድ ቋጥሬ
ከዓመት ወደ ዓመት በቅዬ፣
አድራለሁ አበባ አዙሬ
ሌላው ቢቀር  የቅን-ልቤን፣ ለቅሜ የራሴን ፍሬ!
(ለእንቁጣጣሽ ለገናና ለጥምቀት በዓል) 2014 ወዘተ--
ለማንኛውም የዘንድሮን የመስከረም እንቁጣጣሽና የብርሃነ-መስቀል በዓል በሰላም በፍቅር ያድርሰን!
መልካም አዲስ ዓመት!
መልካም የመስቀል በዓል!
አዲስ አድማስ ጋዜጣ የትፍሥሕት እና የፌሽታ ጊዜ ይመኝላችኋል!!

Read 12102 times