Saturday, 03 September 2022 14:30

የሚገለጽ ተአምር ካለ...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

    “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ በዚህ አሳዛኝ በሆነ ወቅት ለሁላችንም አርቆ ማስተዋልን፣ ተልቆ ማሰብን፣ ንጹህ ልቡናውን ይስጠንማ! የሚገለጽ ተአምር ካለ፣ ይህኛው ተአምር በእኛው እጅ ነውና! በተረፈ የእሱ ጥበቃ አይለየን! --”
         
     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ እንዴት ነህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አለሁ አንድዬ፣ መኖር ከተባለ አለሁ፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ ምነው! ምነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን አጠፋሁ አንድዬ?
አንድዬ፡- በአዲስ ዓመት ዋዜም ሌላ ጊዜ እንደምትለው፤ እንዲህ አድርገኸን፣ እንደዚህ ብለኸን እያልክ ልትወቅሰኝ ነው እንዴ የመጣኸው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ በጭራሽ አንድዬ! በጭራሽ!
አንድዬ፡- ጎሽ አረጋጋኸኝ፡፡ እኔ ደግሞ ምን አይነት ስጦታ ይዘኸልኝ መጣህ ብዬ ስጓጓ ልታሳፍረኝ ነው ብዬ ነበር፡፡ ምነው ፊትህ ቅጭም አለ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን መሰለህ...አንድዬ፣ ስጦታ ስትለኝ...
አንድዬ፡- ለአንተ ስጦታ ለማምጣት አቅሙ የለኝም ልትለኝ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እሱ ሳይሆን ደግሞ ለአንተ ስጦታ ምን...ምን...
አንድዬ፡- ምን አይነት ስጦታ ላመጣ ነው ልትለኝ ነው ወይስ ጭራሽ ስጦታ ምን ያደርግልሀል ልትለኝ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ የምለው ጠፋኝ እኮ!
አንድዬ፡- ይሄን ያህልማ አትጨነቅ፡፡ እዚህ መምጣትህ  ራሱ ለእኔ ስጦታ ነው፤ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አመሰግናለሁ አንድዬ፣ አመሰግናለሁ፡፡
አንድዬ፡- እሺ ምስኪኑ ሀበሻ፤ ዛሬ ልትግረኝ የምትፈልገው የተለየ ነገር አለ ወይስ እግር ጥሎህ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ኸረ እኔ አንተ ዘንድ እግር ጥሎኝ አይደለም የምመጣው፡፡
አንድዬ፡- እየው እንግዲህ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እየው እንግዲህ... እንደው ይሄ ትንሹንም ትልቁንም የምትጠመዝዙት ነገር በቃ ላይተዋችሁ ነው! ግርም የሚል ነገር እኮ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እኛም እኮ ወደን አይደለም፡፡ ቶሎ እኮ ሆድ ስለሚብሰን ነው፡፡
አንድዬ፡- ቆይ፣ ቆይ ለእናንተ ከሌላው የተለየ አይነት ሆድ ነው እንዴ የፈጠርኩት፤ ዘለዓለም ሆድ ባሰን የምትሉት? ምነው ሌሎች እንደእናንተ ሆድ አይብሳቸው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን እናድርግ አንድዬ! እኛም እኮ ሳናውቀው ቀርተን ወይ ተምችቶን አይደለም፡፡ ግን እኮ አንድዬ መከራችን አላልቅ አለ፡፡
አንድዬ፡- እሺ፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ መከራችሁ ያላለቀው ለምንድነው? ንገረኛ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን ልብልህ አንድዬ! እኛም እኮ ግራ እየገባን ነው፡፡ ጠላታችን በዛ አንድዬ፣ ጠላታችን በዛ፡፡ ምንም ነገር ውስጥ የሉበትም ያልናቸው ሁሉ በጎን ሲገዘግዙን፣ እኛስ ማንን እንመን፣ ማንንስ እንጠርጥር!
አንድዬ፡- ቆይማ፣ ምስኪኑ ሀበሻ! እኔ ብዙ ጠላት እንዳለባችሁ አልክድም፡፡ መጀመሪያ ውስጣችሁ እኮ ገና፣ ገና ናችሁ፡፡ እኔ ደግሞ የሚገርመኝ ይኸው ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምኑ ነው የሚገርምህ አንድዬ?
አንድዬ፡- እናንተ፣ እናንተ ናችሁ የምትገርሙኝ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ መቼ ነው እርስ በእርሳችሁ በንጹህ ልብ የምትዋደዱት?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንዋደዳለን እኮ!
አንድዬ፡- ተው፣ ተው እንጂ ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምን መሰለህ...በእርግጥ ሁላችንም ባንሆን፣ ብዙዎቻችን እኮ እርስ በእርስ እንዋደዳለን፡፡ አብረን ማእድ እንቋደሳለን፣ ቡና እናጣጣለን...
አንድዬ፡- ቆየኝ፣ ቆየኝ ምስኪኑ ሀበሻ....አሁን፣ ትንሽ ጠንከር ብዬ ልናገርህ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ተናገረኝ አንድዬ፣ ጠንከር ብለህ ተናገረኝ፡፡ ለእኔም እኮ ትምህርት ይሆነኛል፡፡
አንድዬ፡- እሱን እንኳን ተወው፤ ከዚህ ቀደም ስንት ነገር ነግሬህ፣ እኔ ፊት እሺ ብለህ ተቀብለህ ምድር ስትወርድ እዛው አይደለህ እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ. እሱ በፊት ነበር፡፡ አሁን ግን ያልከኝን ሁሉ በደንብ እፈጽማለሁ፡፡
አንድዬ፡- የአዲሱ ዓመት እቅድህ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አ...አንድዬ...
አንድዬ፡- ስቀልድ ነው እሺ! ደግሞ ይህንን ከቁም ነገር ቆጥረህ እንዳትተረትረው! ስማ... ይልቅ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እንደው ስለ እቅድ አውራኝ፡፡ ከዛ በፊት ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ጠይቀኝ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- እናንተ አዲስ እቅድ ለማውጣት የግድ መስከረም መምጣት አለበት እንዴ! ሁሌ የሚገርመኝ እኮ ነው፡፡ ሲጋራው ውስጥህን እየሰረሰረህ በሚቀጥለው መስከረም ለማቆም በዚህኛው ጥቅምት ቃል ትገባለህ፡፡ ምስኪን ሀበሻ፤ ንግግሬ ሁሉ የእንትን እየመሰለ መጣ እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ በጭራሽ አንድዬ!
አንድዬ፡- እና ጥያቄዬን መልስልኛ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ያው ልምድ ሆኖብን ነዋ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ቆይ፣ ስማኝማ ምስኪኑ ሀበሻ... አልኮሉ ጉበቱን እየበጣጣሰው ያለ ሰው መጠጣቱን ለማቆም አይደለም፣ የአስርና የአስራ አንድ ወር... የአስርና የአስራ አንድ ቀን ቀጠሮ መስጠት ያስፈልጋል እንዴ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ... እንዳልኩህ ለምዶብን ነው፡፡ አንድዬ፣ ደግሞ እንደእውነቱ ቃል እንገባለን እንጂ ብዙዎቻችን  አንፈጽመውም እኮ፡፡
አንድዬ፡- ደግሞ የገባኸውን ቃል አልፈጸምክም የሚላችሁ የለም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- የለም አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ ምስኪኑ ሀበሻ ዛሬ አስደሰትከኝ፡፡ እንዲህ እንዳንተ ሁሉም ስህተቱን ቢያምን እኮ እናንተም፣ ሀገራችሁም ይህ ሁሉ መከራ ባልደረሰባችሁ ነበር፡፡
ደግሞ በዚህ መከራ ውስጥ የእኔ እጅ እንደሌለበት በፊትም ነግሬሃለሁ፣ አይደለም እንዴ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ልክ ነው አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ፖለቲካ ተናገርኩ እንዴ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ ምንም ፖለቲካ የለውም አንድዬ፡፡ ደግሞስ ፖለቲካስ ይሁን፣ ምንስ ይሁን አንተ ሁሉንም ያልተናገርክ ማን ሊናገር ነው!
አንድዬ፡- ዛሬ እያሞጋገስክ አንጀት፣ አንጀቴን እየበላኸው ነው፡፡ የዚህ ዓመት እቅድሀ ምንድነው? ልጠይቅሀ አስቤ ነበር፡፡ ግን ይቅር፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ለምን አንድዬ! ብትጠይቀኝ እኮ እነግርህ ነበር፡፡
አንድዬ፡- እኮ...ትነግረኛለህ ብዬ ነው እኮ የማልጠይቅህ፡ አየህ ለእኔ ፊት ለፊት የሆነ ነገር እፈጽማለሁ ካልከኝ በኋላ ቃልህን ብታጥፍ ሊከፋኝ ይችላል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ በምንም አይነት አንተንማ አላስከፋም!
አንድዬ፡- ስማ በዋዜማው የማይሆን ነገር ተናግረህ፣ እኔንም መስመሩን እንዳታሳልፈኝ፡፡ በል ደህና ሁን፡፡ ደግሞ አዲሱን ዓመት መልካም ማድረግ የምትችሉት እናንተ ብቻ ናችሁ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ በዚህ አሳዛኝ በሆነ ወቅት ለሁላችንም አርቆ ማስተዋልን፣ ተልቆ ማሰብን፣ ንጹህ ልቡናውን ይስጠንማ! የሚገለጽ ተአምር ካለ፣ ይህኛው ተአምር በእኛው እጅ ነውና! በተረፈ የእሱ ጥበቃ አይለየን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 1395 times