Saturday, 03 September 2022 14:30

“ማዕከሉ ባዛርና ኤግዚቢሽኖችን ራሱ ማዘጋጀቱን ይቀጥላል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  “አዲስ ዓመት ብሩህ ነው፤ ተስፋ አለ፡፡ ምንም ውጣ ውረድ ቢኖር፣ ይሄን ባዛርና ኤግዚቢሽን ዞር ዞር ብሎ በማየት ስሜትን ማነቃቃት
ያስፈልጋል፡፡ መኪና የት አቆማለሁ ብላችሁ ሳትጨነቁ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ጎብኙ፤ ተዝናኑ፤ ቀኑን ሙሉ ዲጄ አለ፡፡ ከ11 ሰዓት በኋላ ደግሞ ባንዶች ሙዚቃ ያቀርባሉ፡፡--”

         የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅና የማርኬቲንግ መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ተክሉ አባተ፣ ዘንድሮ ለአዲስ ዓመት ራሱ ማዕከሉ ባዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም በአጠቃላይ በመሥሪያ ቤታቸው የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ሰሞኑን ከአዲስ አድማስ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-


       የዘንድሮ የእንቁጣጣሽ ኤግዚቢሽንና ባዛር ምን ይመስላል?
ድርጅታችን እስካሁን ድረስ ኤግዚቢሽንና ባዛሮችን፣ ኩነቶችን ለሚያዘጋጁ ተቋማት ወይም ሶስተኛ ወገኖች ነበር በጨረታ አወዳድሮ የሚሰጠው፡: ከገና 2014 ጀምሮ ግን የትንሳኤ በዓልንና የአዲስ ዓመትን ባዛር በራሱ አቅም እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ ይህም በነጋዴውና በሸማቹ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም ድርጅታችን በራሱ ሲያዘጋጅ ትርፍን ከገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከነዋሪው እርካታ አንጻርም ነው የሚያየው፡፡ ከዚህ ቀደም በፕሮግራም አዘጋጆች የነበረው ከፍተኛ የዋጋ ጫና፣ ሸማቹም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በመፍጠሩ የዋጋ ማሻሻያ አድርገናል፡፡ ይሄን ተከትሎ ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ ነው፣አብዛኛዎቹ ቦታዎች ተይዘው ያለቁት፡፡ በተጨማሪም፤ ዘንድሮ የሚታየውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ለማርገብ በማሰብ፣በተለይ የበዓል ፍጆታዎችን ለማህበረሰቡ  በቅናሽ ለማቅረብ  36 የሚጠጉ ቦታዎችን ለሸማቾችና ለህብረት ስራ ማህበራት፣ እንዲሁም ለጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በነፃ እንዲጠቀሙበት አመቻችተናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እስካሁን ሰባት የሚደርሱት ገብተዋል፤ እስከ በዓል መዳረሻ ደግሞ ቀሪዎቹ ይገባሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ቦታ በነፃ የተሰጣቸው ማህበራት ምን ያህል የዋጋ ማሻሻያ አድርገዋል? አንዳንዴ ባዛሮች ላይ የዋጋ ቅናሽ እንደተደረገ ቢነገርም፣ እውነቱ ግን ከወትሮውም የበለጠ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ ያጋጥማል፡፡ ከዚህ አንጻር  የዋጋ  ቁጥጥር ታደርጋላችሁ?
ከሌላ ቦታዎች አንፃር መጠነኛ የሆኑ የዋጋ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ዋጋውን መቆጣጠር ባንችልም፣ ቦታውን በነፃ ስለሰጠናቸው፣ ሌላው ነጋዴ ከሚሸጠው ያነሰ እንዲሸጡ  ተነጋግረናል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታም ሸማቹ ከእነዚህ ማህበራት በብዛት ሲገዛ አያስተዋልን ነው፤የዋጋ ቅናሽ በማድረጋቸው፡፡  
ማዕከሉ ለምንድን ነው አሰራሩን ቀይሮ ኤግዚቢሽንና ባዛር ራሱ ማዘጋጀት የጀመረው?
ይሄ ማዕከል  ፕሮግራሞችን እንደሚያዘጋጅ በአዋጅ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት አመራሮች የሚከተሉት የራሳቸው አሰራር ይኖራል፡፡ እኛ ግን እንደመጣን  የተሳታፊውን ማህበረሰብ ሀሳብ በመውሰድ መረጃ አሰባሰብን፡፡ ባገኘነው መረጃ መሰረትም፤ ተከታታይ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ መቆየቱ ተግዳሮት እንደሆነና ይህም በተዘዋዋሪ በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አረጋገጥን፡፡ ይህን እንዴት መፍትሄ እናበጅለት በሚለው ዙሪያ እየመከርንበት ሳለ፣ የገና 2014 ዓ.ም ባዛርን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ዋጋ ያቀረበልን ኤቨንት አዘጋጅ፣ በወቅቱ በነበረው ሀገራዊ ሁኔታ ሳቢያ፣ ፍቃድ ያገኘው በዓሉ አስር ቀናት ብቻ ሲቀረው ስለነበር፣ ፕሮግራሙን ማዘጋጀት አልቻለም ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ተቋማችን ፈጣን ውሳኔ በመስጠት በዘጠኝ ቀናት ውስጥ የመጀመሪያውን ኤግዚቢሽንና ባዛር ራሱ አዘጋጀ፡፡ እናም ኤግዚቢሽኑ ውጤታማ ነበር፡፡ የነጋዴው ማህበረሰብም ከዚህ በኋላ እናንተ እንድታዘጋጁት እንፈልጋለን የሚል ሀሳብ በሰጠን መሰረት፣ አሁንም እየሰራን እንገኛለን፡፡
ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ከዚህ ቀደም በግል ድርጅቶች ሲዘጋጁ ብዙ ጎብኚዎችን ለመሳብና ትርፋማ ለመሆን ሲሉ ዝግጅቱን ለማድመቅና ማራኪ ለማድረግ ብዙ ይጥራሉ፤የማስተዋወቅ ስራዎችም በስፋት ይሰራሉ፡፡ እናንተስ?
 የአዲስ ዓመት ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ከሌላው ጊዜ በተለየ በጣም ብዙ ማሻሻያዎችን አድርገናል፡፡ የመጀመሪያው በጣም ባለቀ ሰዓት ላይ  ያዘጋጀነው ስለነበር፣ የማስተዋወቅ ስራ ለመሥራት በቂ ጊዜ አልነበረንም፡፡ አሁን ግን ብዙ ልምድ ወስደን ቀደም ብለን ነው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እንዲሁም በመኪና በመዘዋወር የማስተዋወቅ ስራውን የጀመርነው፡፡ እዚህ ያለው ደግሞ ከዚህ በኋላ ነው ይበልጥ እየደመቀ የሚመጣው፡፡ ይሄ ወቅት ማህበረሰባችን  ለመሸመት ብቻ ሳይሆን ጎብኝቶ፣ ራሱንና  ልጆቹንም አዝናንቶ የሚሄድበት ነው፡፡ ኤግዚቢሽኑ  ትልቁ የበዓል ድምቀት እንደመሆኑ በጉጉት የሚጠበቅም ነው፡፡
አሁን አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ፤ ጦርነት፣የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት አንጻር፣ ኤግዚቢሽኑ ከወትሮው ሊቀዘቅዝ ይችላል ብላችሁ አልሰጋችሁም?
ኤግዚቢሽን ማዕከል በዓይነቱ ብቸኛው ተቋም ነው፤ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የከተማው ነዋሪ  ምርትና አገልግሎት ለመሸመት ብቻ ሳይሆን ለመዝናናትም ጭምር ስለሚመጣ፣ በዓል በዓል የሚለው ድባብና ግርግሩ፣ በተለይ ከአስራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው የሚታየው፡፡  በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፣ ማህበረሰባችን ለምዶታልና ይመጣል፡፡ ባሉት ቀጣይ ቀናትም የበለጠ እየደመቀ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዓል ነው..መጪው የትምህርት ጊዜ ነው፤ ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት መሣሪያዎችን ይገዛሉ፤ ልጆቻቸውን ያዝናናሉ … ቤታቸውን በአዲስ ነገር ያስውባሉ፤ ይሄ በየዓመቱ  ተለምዷል…. ተስፋ ሰንቀን እንደ አዲስ የምነንሳበት አዲስ አመት ስለሆነ፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ ይደምቃል፤ማህበረሰቡም ይጠብቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ብቸኛው የባዛርና ኤግዚቢሽን ማዘጋጃ ሥፍራ መሆኑ የራሱን ተወዳዳሪነትና የተጠቃሚውን የማማረጥ ዕድል አይጎዳውም?
ኤግዚቢሽን ማዕከል ብቸኛው ላይሆን ይችላል፡፡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አቅጣጫ የተሰጠበትና በሲኤምሲ አካባቢ እየተገነባ የሚገኝ አዲስ “አፍሪካን ኮንቬንሽን ሴንተር” የተሰኘ ማዕከል ሲጠናቀቅ ይከፈታል፡፡ እዛም ላይ እኛ ትልቅ ባለድርሻ ነን፡፡ የዚህ ተቋም መኖር አማራጮችን ለተጠቃሚ ያመቻቻል፤ ጤናማ የሆነ ፉክክርም ይፈጥራል፡፡  
ወደፊትም ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት ትቀጥላላችሁ ማለት ነው ---?
አዎ በማዘጋጀቱ እንቀጥላለን፤ምክንያቱም ከመግቢያ ትኬት ጀምሮ ከፍተኛ የዋጋ ማሻሻያዎችን አድርገናል፡፡ የማህበረሰቡን እርካታ አስጠብቀን መሄድ እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ ማዘጋጀቱን እንቀጥልበታለን፡፡ በዓመት ውስጥ በርካታ ኹነቶች አሉን፡፡ ያንን የሚያዘጋጁ ተባባሪ አዘጋጆችም አሉ፤እነሱም ይቀጥላሉ፡፡ ሆኖም የአዲስ ዓመትን፣ የገናንና የፋሲካን ባዛር ማዕከሉ ማዘጋጀቱን ይቀጥልበታል፡፡ ነገር ግን በማኔጅመንት በኩል የመንግስትና የባለድርሻ አካላት ጥቅም ተነክቷል ይሻሻል ከተባለና ከተገመገመ ደግሞ ለሦስተኛ ወገን እንሰጣለን፡፡
በመጨረሻ የአዲስ ዓመት ምኞትዎን መግለጽ ይችላሉ---
አዲስ ዓመት ብሩህ ነው፤ ተስፋ አለ፡፡ ምንም ውጣውረድ ቢኖር፣ ይሄን  ባዛርና ኤግዚቢሽን ዞር ዞር ብሎ በማየት ስሜትን ማነቃቃት ያስፈልጋል፡፡ መኪና የት አቆማለሁ ብላችሁ ሳትጨነቁ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ጎብኙ፤ ተዝናኑ፤ ቀኑን ሙሉ ዲጄ አለ፡፡
ከ11 ሰዓት በኋላ ደግሞ ባንዶች ሙዚቃ ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ወደ ማዕከሉ እንዲመጣ እጋብዛለሁ፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላምና የብሩህ ተስፋ ይሆንልን ዘንድ እመኛለሁ፡፡

Read 4953 times