Print this page
Saturday, 03 September 2022 14:39

ጄኔራል ሙሆዚና፤ የቤተሰብ ፖለቲካ በአፍሪካ

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(1 Vote)

 “--በቤተሰብ የመተካካቱ ጉዳይ ጊዜ ያለፈበት ሥርዓት ቢመስልም፣ ሀገሮቹ ግን አንፃራዊ እርጋታ ይታይባቸዋል። በሰላም ወጥቶ የሚገባ፣ ማን መራው ማን፣ ግድ ላይሰጠው ይችላል። ዲሞክራሲ የሚባለውም ሁሉም ቦታ ሲሰራ አልታየም።--”
        
       ባለፈው ሳምንት የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ፣ ሜጀር ጄኔራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ፣ አዲስ አበባ መጥተው ከባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተዋል። የደህንነትና ወታደራዊ ተቋማትን እንዲሁም የአባይ ግድብንም ጎብኝተዋል። የቡድኑ መሪ ግን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴታ እንደሆኑ ተነግሯል። ዜናዎችም ከእሳቸው ጋር ቃለምልልስ በማድረግ ነው የተሰሩት።
ሜጀር ጄኔራል ሙሆዚ የሀገሪቱ ምድር ጦር አዛዥ ቢሆኑም፣ ሰሞኑን ኢትዮጵያን የጎበኙት በዛ ሃላፊነታቸው ነው ለማለት ያስቸግራል። ሁለቱን ሀገሮች በወታደራዊ ደረጃ በክፉም ሆነ በደግ እንዲህ የሚያቀራርብ ነገር መኖሩ ያጠራጥራል። እንደዛም ቢሆን ወይ ፕሬዚደንቱ አሊያም መከላከያ ሚኒስትሩ ነበር የሚመጡት። እርግጥ ሕወሓትን ደግፈው ማህበራዊ መገናኛ ላይ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል ቢባልም፣ በግልፅ የታወቀ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን የሚያሳይ ማስረጃ አልታየም። እንደዛ ቢሆን ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ድፍረቱ ይኖራቸዋል ተብሎ አይታሰብም።
በግልፅ የሚታየው ግን ሰውዬው ዩጋንዳ ውስጥ የፈጠሩት ተፅዕኖ በመጉላቱና አባታቸውን ሊተኩ ስለሚችሉ የሥራ ልምድ ማግኛና መተዋወቂያነቱ ነው። ሙሴቬኒ የ77 ዓመት እድሜ ባለፀጋ በመሆናቸው ከሄዱ ቅርስ ጠባቂ ያስፈልጋል - ከልጅ የሚቀርብ ከየት ይገኛል። እስካሁን ሕገ መንግሥቱን እስከለተሞታቸው ሥልጣን ላይ እንዲያቆያቸው አድርገው ሲያሻሽሉት ኖረዋል። በዚህም የእድሜያቸውን እኩሌታ እካባቢ ኖረውበታል። ሀገሪቱ ነፃነቷን ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ ሲቀያየሩ የነበሩት መሪዎች ጊዜ በሙሉ ቢጨፈለቅ እንኳ የሳቸውን ቆይታ የሚገዳደር የለም። ዩጋንዳውያን ‘ማማ ጃኔት’ የሚሏቸው ባለቤታቸውም የቀዳማዊ እመቤትነትን ድንበር ተሻግረው አሁን የትምህርት ሚኒስትር ናቸው። ሥልጣኑ ላይ ቤተሰቡ ተንሰራፍቷል።  ሰሞኑን ኬንያ ውስጥ በተደረገው ምርጫ ራይላ ኦዲንጋ ለአምስተኛ ጊዜ ሲወዳደሩ፣ ይባስ ብሉ በተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መደገፋቸው፣ ኬንያውያንን ‘የውርስ ሥልጣን’ ይብቃ የሚል እሮሮ እንዲያሰሙ አድርጓቸዋል። ኡሁሩ የመጀመሪያው የኬንያ ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ ልጅ መሆናቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል።
እኛ ሀገር ከንጉሣዊው ሥርዓት በዃላ ፈላጭ ቆራጭነቱ እንደተጠበቀ ቢሆንም፣ በመሪዎች ደረጃ ሥልጣን ለልጅ ለማውረስ የቋመጠ አልታየም። የኮሎኔል መንግሥቱና የመለስ ልጆች ዶ/ር ትእግስትና ሰምሃል አልፎ አልፎም ቢሆን በአደባባይ ሃሳባቸውን በመግለፅ ቢታወቁም፣ ወደ ሙሉ ጊዜ ፖለቲከኛነት የገቡ የመሪ ልጆች በአገራችን አይታዩም።
በ1980ዎቹ አጋማሽ በአንዳንድ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች፣ ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው የሚመስሉ  የኢትዮጵያው መለስ፥ የኤርትራው ኢሳያስ ፥ የዩጋንዳው ሙሴቬኒ፥ ወደ ሩዋንዳም እነ ፖል ካጋሜ ብቅ ባሉ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ቢል ክሊንተን፤ ‘ምርጥ የአመራር ዝርያዎች’ ብለው አሞካሽተዋቸው ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል ሁሉም ከገለበጧቸው ሰዎች በላይ መቆየታቸው ብቻ ሳይሆን፤ በአማካይ ለሰላሳ ዓመታት ያህል ሥልጣኑ ላይ ከርመዋል። በየሃገሮቹ ያለው አብዛኛው ትውልድ ከነሱ በስተቀር ሌላ መሪ አያውቅም። አንዳንዶቹ ጭራሽ ልጆቻቸውን ሊተኩ ዳር ዳር እያሉ ነው። የዩጋንዳው ግልፅ ሲመስል፣ የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂም ይህንን ጎዳና የመከተል አዝማሚያ ያሳያሉ። አብርሃም የተባለው ልጃቸውን አልጋ ወራሽ ለማድረግ እየታተሩ ነው ሲሉ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን አምተዋቸዋል። ለሃሜቶቹ መንግሥት የሚሰጠው የከረረ ማስተባበያ ነገሩን ይበልጥ ተዓማኒ ያደርገዋል።  አብርሃም ድምፁን አጥፍቶ ወደዚህ አገር ብቅ ማለቱ አልቀረም።
ይህ የቤተሰብ ፖለቲካ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች እያንሰራራ መጥቷል።
አንኳር አንኳሮቹ
ባለፈው ዓመት ከአማፂያን ጋር የሚደረገውን ጦርነት ግንባር ድረስ ሄደው እያስተባበሩ ሳሉ የተገደሉት የቻዱ መሪ ኢድሪስ ዴቢ፣ ለማየት ባይታደሉም ያቀዱት የተሳካ ይመስላል። የዓማፂያኑ ዓልሞ ተኳሽ ነጥሎ ይምታቸው ወይ እዛው ከጄነራሎቻቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ይገደሉ እስካሁንም መነጋገሪያ ነው። ኢድሪስ ዴቢ ድፍን ሰላሳ ዓመት የቆዩበት ሥልጣን አልበቃ ብሏቸው እስከለተ ሞት ለመምራት ሕገመንግሥቱን ከልሰውታል። በተጨማሪም ልጆቻቸውን በሀገሪቱ ቁልፍ ተቋማት ላይ ሾመው ነበር። ታዲያ እዛ ግንባር ሄደው ድንገት በቀሩ ጊዜ በሕገመንግሥቱ መሠረት የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እሳቸውን መተካት ነበረባቸው። “ሀገሪቱ ጦርነት ላይ ባለችበት ወቅት በመለዮ ለባሽ እንጂ በተራ ዜጋ መመራት የለባትም። በዚህ ሁኔታ ህገ መንግሥታዊ ግዴታዬን ለመወጣት ይቸግረኛል” የሚል መግለጫ እንዲሰጡ ተደርጎ፣ የ37 ዓመቱ ማማት ኢድሪስ ዴቢ የአባቱን ዙፋን እንዲወርስ ተደርጓል።
የ80 ዓመት እድሜ ባለፀጋ የሆኑት የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ኦቢያንግ ንጉየማ፣ ልጃቸውን ቴኦዶሪንን የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አድርገው ለዋነኛው ቦታ ካዘጋጁት ዓመታት ተቆጥረዋል። በአውሮፓና አሜሪካ በቅንጡ አኗኗሩ፤ ውድ ተሽከርካሪዎችን በመሰብሰብ ይታወቃል። የድሃ ሀገሩን ህዝብ እየዘረፈ ያከማቸው ሀብት ነው በሚል በተደጋጋሚ በፈረንሳይና በአሜሪካ ንብረቶች ቢወረሱበትም፣ አባቱን የመተካቱ ሁኔታ የማይቀር ይመስላል።
የቶጎ ፕሬዚደንት የነበሩት ናሲምቤ ኢያደማ፣ በጊዜያቸው ለረጅም ዘመናት በመምራት ክብረወሰን ጨብጠው ነበር። ቶጎን 38 ዓመታት መርተው ለህክምና ወደ አውሮፓ እየተጓዙ አውሮፕላን ውስጥ ጭጭ ባሉበት ሰሞን አንዳንድ ጫጫታ ቢነሳም፣ አቧራው ሲሰክን፣ ልጃቸው ቦታው ላይ ቁጢጥ ብሏል። ይኸው ከ17 ዓመታት በዃላም የሚነቀንቀው አልተገኘም።
ወደ ታች ስናመራ የኮንጎ አማፂዎች ሞቡቱ ሴሴሴኮን ካባረሩ በሁዋላ፣ ሎረ ደዚሬ ካቢላ መሪ ነበሩ። ሥልጣኑ ላይ አራት አመት ሳይደፍኑ በድንገት ከጠባቂያቸው አንዱ እዛው ቤተ መንግሥት ውስጥ ጥይቱን ጨርሶባቸዋል። ከቀናት በዃላ እሳቸውን የተካው ልጃቸው ጆሴፍ ካቢላ፣ ሃያ አመት ያህል መርቶ፣ የዛሬ ሶስት አመት አካባቢ ከመድረኩ ራሱን አግልሏል።
በማዕድን ሀብት የበለፀገችው ጋቦንን ለረጅም ዘመናት የመሯት ኦማር ቦንጎ ኦዲምባ ናቸው። በ73 ዓመታቸው ባርሰሎና በሚገኝ ሀኪም ቤት ከማረፋቸው በፊት ቦታውን ለልጃቸው አሰማምረውት ነበር። አርባ አመት ከመሩ በዃላ፣ ‘እንደኛ ቤተሰብ ለሀገራችን የሚያስብ የለም’ አይነት ልጃቸውን አሊ ቦንጎን ተክተዋል።  ይኸው 13ኛ ዓመቱን ተያይዞታል። 
አንጎላን 40 ዓመት ያህል የመሩት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ፣  ከሚታወሱበት አንዱ ሴት ልጃችው ኢዛቤል ዶስ ሳንቶስን የአፍሪካ ቁንጮ ሀብታም ማድረጋቸው ነው። ፎርብስ የተባለው የባለፀጋዎችን ገቢ የሚዘግበው መፅሔት፣ በአንድ ወቅት የሴትየዋን ሀብት ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ ገምቶታል። አባት አንጎላ ውስጥ አትራፊ የተባለ ነገር በሙሉ ወላ ሲሚንቶ ፋብሪካ፥ ወላ ስልክ፥  አልማዝ፥ ባንክ ሁሉንም ሰጥተው ቢሊየነር አደረጓት። ወንዶቹም ሥልጣኑ አካባቢ ነበሩ። ነገር ግን ባለቀ ሰዓት ታማኝ ለሚሉት የኤምፒኤልኤ (የብልፅግና አቻ) ካድሬ ሥልጣኑን ሲያስረክቡ ነገር ተባላሸ። ሰውየው የቤተሰቡን አባላት ገዝግዞ ጣለ። ሴትየዋም አንዴ እንግሊዝ፣ አንዴ ፖርቱጋል ታዩ እየተባለ ቁም ስቅላቸውን አይተዋል። አሜሪካ ደጅ እንዳይደርሱም ፈቃድ ተነፍጓቸዋል። አሁን ድምፃቸውን አጥፍተው  ዱባይ ይኖራሉ። አሳዛኙ ነገር ባለፈው ሀምሌ መግቢያ ላይ ባርሰሎና በሚገኝ ሀኪም ቤት (ድሮ ኦማር ቦንጎ የመከሯቸውን አስታውሰው መሆን አለበት) ሕይወታቸው ያለፈው የዶስ ሳንቶስ አስከሬን፣ የአተካራ ምንጭ ሆኖ ባለፈው እሁድ ነው የተቀበሩት። መንግሥት ለጀግኖች በተዘጋጀው ቦታ በክብር ይረፉ ሲል፣ ልጆች ደግሞ “ለቀብር አንጎላ ብንገባ እንያዛለን፤ በአባታችን አስከሬን ከኛ በላይ ማንም ሊያዝ አይችልም” የሚል ሙግት ውስጥ ነበሩ። በመጨረሻ አንዱ የስፔን ዳኛ፣ አስከሬኑ ለሶስተኛዋ ባለቤታቸው ተሰጥቶ አገሩ እንዲገባ ወስኗል።
በደቡብ አፍሪካ ተከብበው ያሉት ሌሴቶና ኢስዋቲኒ (የቀድሞዋ ስዋዚላንድ) እንዲሁም የሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮ ድሮም በንጉሥ ስለሚተዳደሩ ሥልጣንን ለልጅ ለማውረስ ሕጋዊ መሰረት አላቸው።
ሌሎችም እንደ ሊቢያው ጋዳፊና የግብፁ ሆስኔ ሙባረክ፣ ልጆቻቸውን ለዙፋን አዘጋጅተው ነበር፤ ህዝባዊ ማዕበል ባይቀድማቸው ኖሮ።በቤተሰብ የመተካካቱ ጉዳይ ጊዜ ያለፈበት ሥርዓት ቢመስልም፣ ሀገሮቹ ግን አንፃራዊ እርጋታ ይታይባቸዋል። በሰላም ወጥቶ የሚገባ፣ ማን መራው ማን፣ ግድ ላይሰጠው ይችላል። ዲሞክራሲ የሚባለውም ሁሉም ቦታ ሲሰራ አልታየም።

Read 2973 times