Monday, 05 September 2022 00:00

እውነታን መገንዘብ፣ የመንፈሳዊነት ምሶሶ ነው

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

  ለጥበበኞች ሁሉ የቸገረ የሕልም ምስጢር ለወጣቱ ሊቅ ለዳንኤል ብቻ እንደተገለጠለት ትረካው ይነግረናል። “በሌሊት፣ ለዳንኤል፣ በራዕይ ተገለጠለት። ዳንኤልም፣ የሰማይን አምላክ አመሰገነ። እንዲህም አለ።”… በማለት ትረካው ይቀጥላል።
ጥበብና ኀይል የእርሱ ነውና፤
የእግዚሔር ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ።
ጊዜንና ወቅትን ይለውጣል፤
ነገሥታትን በዙፋን ያስቀምጣል፤
ደግሞም ያወርዳቸዋል።
ጥበብን ለጠቢባን፤
ዕውቀትንም ለሚያስተውሉ ይሰጣል።
የጠለቀውንና የተሰወረውን ነገር ይገልጣል፤
በጨለማ ያለውን ያውቃል፤
ብርሃንም ከእርሱ ጋር ይኖራል።
የአባቶቼ አምላክ ሆይ፣ አመሰግንሃለሁ፤ አከብርሃለሁም፤
ጥበብንና ኀይልን ሰጥተኸኛልና።”…
ግሩም ነው - “የዳንኤል የቅኔ ጥበብ”። አንዷን ቁምነገር ብቻ አንጠልጥለን፣ ሌላውን የዳንኤል ቃል ግን፣ ሰምተን እንዳልሰማን ብናልፍ፣ የጥበብ ቃሉን እናረክሰዋለን።
ዳንኤል፣ ቡራኬ በማቅረብ ከላይ ይጀምራል። በኋላም ምስጋናውን ከታች ይገልፃል። ከላይም ከታችም፣ ተመሳሳይና ተቀራራቢ አባባሎችን ተጠቅሟል።
ከመሃል ደግሞ፣ መነሻውንና ማሳረጊያውን የሚያገናኙ ዋና ዋና ቁምነገሮችን አስፍሯል፤ ሦስት ቁምነገሮችን።
ሀ. የተፈጥሮ ዑደትንና እውነታን፣ በአዎንታ መቀበልና መገንዘብ፣ የጥበብ መሠረት ነው። ይነጋል፣ ይመሻል። ክረምትና በጋ ይፈራረቃል። በሰው ሥልጣን ስር አይደሉም።
ዳንኤል፣ በቅድሚያ ዘላለማዊ የተፈጥሮ ዑደትን ይጠቅሳል። እውኑ ዓለም፣ ከተፈጥሮውና ከዑደቱ አይዛነፍም። የእውኑ ዓለም ተፈጥሮ፣ የሁሉም ነገር መሠረት ነው፤ ዘላለማዊ እውነታ ነው። ዳንኤል፣ ይህን በጥልቀት የተገነዘበ ይመስላል።
እውነታን፣ በፀጋ፣ በ”አዎ”ንታ መቀበልን አስቀድሟል (የጊዜ ዑደትንና የወቅት ፍርርቆሽን)። ዝናብ የሚበዛበት ጊዜ አለ። የዝናብ እጥረት የሚባባስበት ጊዜም አለ። ይህን ተገንዝቦ፣ አስቀድሞ መዘጋጀት ነው - የጥበበኛው መፍትሔ። በዮሴፍ ዘመን የነበረ ፈርዖን፣ እንዲህ አይነት ሁኔታ ነበር የገጠመው። ደግነቱ፣ እንደ ዳንኤል፣ ዮሴፍም፣ ይህን ዘላለማዊ እውነታ አሳምሮ የተገነዘበ ጥበበኛ ነው።
ዮሴፍ፣ “የዝናብና የድርቅ ዓመታትን ለማስለወጥ እንፀልይ” አላለም። “በዝናባማ ዓመታት ብዙ ለማምረት፣ የችግር ዓመታትን የሚያሻግር ብዙ እህል ለማከማቸት እንትጋ” የሚል ነበር፤ የዮሴፍ ምክር። ደግሞም ይቻላል። አርቆ ማስተዋልና ተግቶ ማምረት፣… “በሰዎች ሥልጣን ስር” ናቸው።
የክረምትና የበጋ፣ የዝናባማ ዓመትና የድርቅ ዓመታት ፍርርቆሽ ግን፣ በሰው ሥልጣን ስር አይደሉም።
ተፈጥሯዊ ዑደቶች፣…
በምኞት ብዛት ወይም በፅድቅ ምክንያት የምናገኛቸው ውጤቶች አይደሉም። በምኞት እጥረት ወይም በኀጥያት ሳቢያ የሚመጡብን መዘዞችም አይደሉም።
በቃ፣ የተፈጥሮ እውነታዎች ናቸው። ቀንና ሌሊት ይለዋወጣሉ፤ ወቅቶች ይፈራረቃሉ። “በሰው ሥልጣን ስር” አይደሉም።
ለሌሊት፣ ጧፍና የኤሌክትሪክ አምፖል መስራት፣… ለበጋ ወቅት፣ ግድብና መስኖ መገንባት ይቻል ይሆናል። እነዚህ፣ “በሰው ሥልጣን ስር” ናቸው።
ለእነዚህም ግን፣ በቅድሚያ፣ እውነታውን በአዎንታ መቀበልና መገንዘብ የግድ ነው።
የመጀመሪያውና መሠረታዊው የዳንኤል ነጥብ ይሄ ነው።
ለ. ንጉሥ ይመጣል፤ ንጉሥ ይሄዳል። ይሄ የሰው ስራ ቢሆንም፣ በእለታዊ ምኞት፣ በግል ምርጫ የሚወሰን ጉዳይ አይሆንም።
ዘንድሮ በእውን የምናያቸው የአገር ባህሎችና የመንግሥት ሥርዓቶች፣ የአምና የካቻምና ውጤቶችና መዘዞች ናቸው። ከዚህ አባባል ውስጥ፣ ሁለት ገፅታዎችን መገንዘብ እንችላለን።
በአንድ በኩል፣ መንግሥታዊ ሥርዓት ወይም አገራዊ ባህል፣ በራሳቸው ጊዜ አይበቅሉም። ለክፉም ለደጉም፣ የሥርዓት ወይም የባሕል ውጤቶችና መዘዞች የሚመነጩት፣ ከካቻምና የሰዎች ውሳኔ፣ ከአምና የሰዎች ተግባር ነው። እናም፣…
ከረዥም ጊዜ አንፃር ስናያቸው፣ የአገር ባህልና ሥርዓት፣ “በሰው ሥልጣን ስር ናቸው” ማለት ይቻላል።
በሌላ በኩል ግን፣ “የአገር ባህሎችና ሥርዓቶች”፣… በእለታዊ ውሳኔ አማካኝነት የምናመጣቸው ውጤቶች ወይም የምናስቀራቸው መዘዞች አይደሉም። የቱንም ያህል ብንመኝ፣ የቱንም ያህል ብንፀልይ፣ በአንድ ጀምበር ተቦክተው፣ ተጋግረው፣ ለጉርሻና ለድግስ አይደርሱም። እናም፣…
የአገር ባህልና ሥርዓት፣ ከእለታዊ ኑሮ አንፃር ስናያቸው፣ “ከሰው ሥልጣን ውጭ ናቸው” ማለት ይቻላል።
ለዚህም ይመስላል፣ ከተፈጥሯዊ እውነታ በመቀጠል፣ ዳንኤል፣… የአገር፣ የመንግሥት፣ የሕግ፣ የባህል፣ የሕዝብ ጉዳይን የጠቀሰው። ከሰው ሃሳብና ተግባር የሚመነጩ ናቸው። ግን ደግሞ፣ ከተፈጥሮ ዑደት ጋር የሚያመሳስል ገፅታ አላቸው።
የብዙ ሰዎችና የረዥም ጊዜ ውጤቶች ናቸው - ለክፉም ለደጉም። ወደፊት፣ ቀስ በቀስ ልንገነባቸውና ልናፈርሳቸው፣ ልናሻሽላቸውና ልናበላሻቸው እንችላለን። ነገር ግን፣ የአንድ ጀምበር ወይም የአንድ ሰው ሥራዎች አይደሉም።
የአገር ባሕል ወይም የመንግሥት ሥርዓት፣ የቀድሞ ውርስ ናቸው - የብዙ ዓመታት ውጤት ወይም መዘዝ። ዛሬ ተነስቶ፣ ወደ ኋላ ተመልሶ፣ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን ሊቀይር የሚችል ኀይል የለም። ይሄ፣ ከተፈጥሯዊ እውነታዎች ጋር ያመሳስላቸዋል።
ግን ደግሞ፣ የአገር ባህልና የመንግሥት ሥርዓት፣ የነገ እርሻዎች ናቸው። እየለመለሙ ወይም እየጠወለጉ፣ እየተሸረሸሩ ወይም እየተጠገኑ ሊሄዱ ይችላሉ።
የአገር ባህልና የመንግሥት ሥርዓት፣… ሕግና ድንበር የምንላቸው ነገሮች በሙሉ፣ ነባር ውርሶች ናቸው። ወደ ኋላ ተመልሰን ልናበላሻቸው ወይም ልናሳምራቸው አንችልም።
ወደ ፊት፣ አዲስ የሚጨመርና የሚቀነስ፣ አዲስ የሚመጣና የሚሄድ፣ የሚፀና ወይም የሚፍረከረክ፣ የሚበረታ ወይም የሚዳከም ይኖራል። ነገሥታት ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ፤ ይወርዳሉ። የአገሩ ባህልና ሥርዓቱ ተለውጧል ማለት ግን አይደለም።
የባሕልና የሥርዓት ጉዳዮች፣ የረዥም ጊዜ ውቅር ስለሆኑ፣ በአንድ ውሳኔ፣ በአንድ ድርጊት ተጎትተው የሚመጡና ተገፍተው የሚሄዱ ነገሮች አይደሉም። ከንጉሥም አቅም በላይ ናቸው።
የሥልጣኔ ባሕልና የብልፅግና አኗኗር፣ በአንድ ዓመት፣ በአስር ዓመት ብን ብሎ አይጠፋም። በአንድ ንጉሥ አላዋቂነትና ስንፍና ሳቢያ፣ የአገር ሕልውና በአንድ ጀንበር አይፈርስም። የሥልጣኔ ጉዞ በአንድ አዳር አይቋረጥም (አገር ሊዳከም፣ ጉዞውም ሊቀዛቀዝ ቢችልም)።
የጭፍንነት በሽታ በጊዜ ካልተስተካከለ፣ ለበርካታ ዓመታት እየተስፋፋና እየተዛመተ፣ የአገሩን ስልጣኔ ሊያዳክምና የኋሊት ሊያንሸራትት ይችላል። ለጊዜው ግን፣ በአላዋቂዎችና በሰነፎች እጅ ውስጥም፣ ነባሩ ሥልጣኔና የብልፅግና ኑሮ፣… ለጊዜው፣… እንደቀድሞው ይቀጥላል።
በዚያው ልክ፣ የአገር ኋላቀርነት፣ በአንድ ጥበበኛ አስተማሪ፣ በአንድ አስተዋይ ንጉሥ አማካኝነት፣ ቀስ በቀስ የመሻሻል እድል ይኖረዋል። ነገር ግን፣ በአንድ ዓመት በአስር ዓመት ውስጥ፣ ኋላቀርነት ወደ ሥልጣኔ፣ ድቅድቅ ጨለማው ወደ ደማቅ ብርሃን ዘልሎ አይሻገርም።
ወደ ቁልቁለት የሚያንደረድር አገራዊ ወይም ዓለማቀፋዊ የውድቀት ቅኝት በተስፋፋበት ዘመን፣ ጥበበኛ አስተማሪና አስተዋይ ንጉሥ የቱንም ያህል ቢተጉ፣ አገራቸውን ከቁልቁለት ጉዞ ማዳን ሊያቅታቸው ይችላል።
ለጊዜው፣ ውድቀትን ለማስቀረት መጣጣራቸው አይቀርም። አንዳንዴ ግን፣…
ለዓመታት የተጠራቀመው ናዳ፣ ከአቅም በላይ ይሆንባቸዋል። ዓለማቀፍ ማዕበል ሲመጣም፣ የማምለጫ እድል ያሳጣቸዋል። ንጉሥ ኃይለሥላሴ፣ አገራቸውን ከአለማቀፍ የኮሙኒዝም ማዕበል ማዳን አልቻሉም - ለተወሰኑ ዓመታት መከላከል ቢችሉም።
የምኞት፣ የፀሎት፣ የጥረት ጉድለት ባይኖር እንኳ፣ ቁልቁል መንጋጋት የጀመረውን ናዳ ማስቀረት አይቻልም። ተቋቁሞ ለመግታት መሞከር ተገቢ ነው። ወደ ኋላ ተመልሶ፣ ናዳውን ማስቀረት ግን አይቻልም።
በዓለማቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣ ማዕበል፣ ለበርካታ ዓመታት እየገነገነ የቆየ የጥፋት ባሕል፣… በዛም አነሰ፣ የውድቀት መዘዞችን ማስከተሉ አይቀሬ ነው። ነገ የሚከሰቱ አንዳንድ ነገሮች፣ የዓምና የካቻምና መዘዞች፣ ወይም የአምና የካቻምና ፍሬዎች ናቸው። ሊያመልጡን አይችሉም። ልናስቀራቸው አንችልም። አስቀድሞ ማወቅ ግን ጥሩ ነው - የምንችለውንና የማንችለውን ለይተን አስቀድመን ለመዘጋጀት።
የረዥም ጊዜና የብዙ ሰዎች ውጤት ወይም መዘዝ፣ ሁሌም አለ። በአንድ ጀምበር፣ በአንድ ውሳኔ፣ የአገር ባሕል፣ የአገር ሥርዓት አይቀየርም።
ንጉሡ እንኳ፣ ከሱ በኋላ የሚመጣውን ንጉሥ በእርግጠኛነት መሰየም፣ አቅጣጫውንም እንዳሻው መወሰን አይችልም። ዓለማቀፍ የአስተሳሰብ ቅኝት፣ በአንድ ሰው እለታዊ ምኞት፣ ወይም አንድ ንጉሥ በሚያውጀው አስቸኳይ አዋጅና ትዕዛዝ አማካኝነት የሚሽከረከር አይደለም።
እጅግ ኀያል የሆነ መንግሥት እንኳ፣ ዓለማቀፍ አስተሳሰብን እንዳሻው መቀየር አይችልም።
ነገሥታት ይመጣሉ፤ ነገሥታት ይሄዳሉ።
በርካታ የባሕልና የሥርዓት ጉዳዮች፣ ገና ድሮ በተከፈተላቸው ቦይ ይጓዛሉ።
ወደ ፊት አዲስ ቦይ መክፈት እንጂ፣ ወደ ኋላ ተመልሰን፣ የድሮውን ቦይ “እንዳልተፈጠረ” ማድረግ አንችልም።
ይሄ ሁለተኛው ቁምነገር ነው - በዳንኤል ቅኔ ውስጥ የተገለጠ እውነት። ይሄን የእውነታ ገፅታ ከልብ መረዳት፣ “የማኅበረሰብ ሥርዓትን፣ የታሪክ ጉዞን በቅጡ የመገንዘብ ጥበብ” ልንለው እንችላለን።
ሐ. የግል ማንነትና የግል ሃላፊነት፣ የግል ጥረትና የስራ ፍሬ፣ የግል ብቃትና የሰብዕና ክብር። እነዚህ በሰው ሥልጣን ስር ናቸው። በዘፈቀደ የሚገኝ ጥበብና ክብር የለም።
ሦስተኛው ቁምነገር፣ “ብዙ ሰዎች” ማለት፣ “ብዙ ግለሰቦች” ማለት መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። ግለሰቦች፣ ብዙ ሰዎችን በማስተማር ወይም በማምታታት፣ በረዥም ጊዜ ትልቅ ውጤት ወይም ከባድ መዘዝ የማምጣት አቅም አላቸው።
በዚያ ላይ፣ ጥበብና እውቀት፣ እንደ ተፈጥሮ ዑደት፣ ወይም እንደ አገራዊ ባህል አይደሉም። በግለሰብ ሥልጣን ስር ናቸው - ጥበብና እውቀት።
ዳንኤል፣ የእግዚሔር ስም ይባረክ፣ ብሎ ከተነሳ በኋላ፣ አምላክ ሆይ አመሰግንሃለሁ ብሎ ወደ ማሳረጊያ የሚደርሰው፣ እነዚህ ሦስት የእውነታ ገፅታዎችን በመገንዘብ ነው።
እግዚሔርን ማክበርና ማመስገን ማለት፣ ሦስቱን የእውነታ ገፅታዎች በምልዓት መገንዘብ ማለት ነው ብንል አይሻልም?
አንዲት ቅጥያ ብቻ ይዞ የሚያንጠለጥል ሰው፣ በአላዋቂነት ይሳሳታል። ዳንኤል፣ “ጥበብንና ኀይልን ሰጥቶኛልና” በማለት ብቻ፣ እግዚሔርን ያከበረ ሊመስለው ይችላል። ጥበብና እውቀት፣ እንዲሁ ያለ ጥረት ለዳንኤል በዘፈቀደ የተሰጠው ከመሰለን፣ በጣም ተሳስተናል። የዳንኤል ሀሳብ እንደዚያ አይደለም።
ጥበብን በጥረት ማግኘት እንደሚቻል ስለተገነዘበ ነው፣ ዳንኤል፣ በዚህ ምክንያት፣ ምስጋናውን የሚገልፀው።
ጥበብን መሻትና አስተዋይ መሆን፣ የእያንዳንዱ ሰው የተፈጥሮ ፀጋ ነው፣ የእያንዳንዱ ሰው የስነምግባር ምርጫና ሃላፊነት ነው።
ይህን ዘላለማዊ እውነታ ባለመገንዘብ፣ እግዚሔር ጥበብንና እውቀትን ሰጠኝ ብሎ አይናገርም - ዳንኤል።
“ጥበብን ለጠቢባን፣ ዕውቀትን ለሚያስተውሉ ይሰጣል” በማለት ነው ምስጋናውን የሚገልፀው።
“የሰማይ አምላክን አከብራለሁ፣ ጥበብን ሰጠኝ፣ ምስጢርን ገለጠልኝ”፣… “ጥበብን የሚሰጥ፣ ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ አለ” ብሎ ዳንኤል የሚናገረው፣ በዚህ የሃላፊነት ስሜት ነው። ለሚያስተውል ሰው፣ እውቀትን ይሰጠዋል ይላልና።
እያስተዋለና እያገናዘበ የሚተጋ ሰው፣ የግል ሃላፊነቱን በፅናት የሚፈፅም ሰው፣ ጥበብን ያገኛል። እንደዚህ ይመስላል - የዳንኤል መንፈስ። አይመስልም?

Read 9725 times