Saturday, 10 September 2022 20:52

የፀጥታው ምክር ቤት በጦርነቱ ውስጥ እጁን እንዲያስገባ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል
       - የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በኢትዮጵያ ለ10 ቀናት ይቆያሉ ተብሏ


         በኢትዮጵያ ዳግም ያገረሸው ጦርነት ቀጠናውን እንዳያበጣብጥ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት መርማሪ ኮሚሽን ጠየቀ።
ኮሚሽኑ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ዳግሞ ያገረሸው ጦርነት ወደ ሌሎች አገራት ተዛምቶ ቀጠናውን እንዳያበጣብጥ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብሏል።የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥና ጦርነቱ ተስፋፍቶ ቀጠናውን እንዳያናጋ የፀጥታው ምክር ቤት የመከላከል እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀው ኮሚሽኑ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ምክር ቤቱ ጉዳዩን ዋንኛው አጀንዳው እንዲያደርገውም አሳስቧል።
የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ተገቢነት ያለው መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን አቁመው ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።
በተያያዘ ዜና፤ ከቀናት በፊት አዲስ አበባ የነበሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የህውሃት ታጣቂ ሃይሎችን ከመንግስት ጋር ለማደራደር የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ላይ ናቸው ተብሏል። ባለፈው እሁድ ነሐሴ 29 ቀን2014 ዓ.ም አዲስ አበባ የገቡት ልዩ መልዕክተኛው እስከ መስከረም 5 ቀን 2015 ድረስ እንደሚቆዩም ተገልጿል።
ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን አቁመው የሰላም ንግግርና ድርድር እንዲጀምሩ የሚያሳስብ መልዕክት ይዘው መምጣታቸው የተነገረላቸው ልዩ መልዕክተኛው፤ በቆይታቸው ከመንግስት ባለስልጣናትና ሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር እንደሚወያዩ ተጠቁሟል።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የፕሬዚዳንት ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ አምባሳደር ማይክ ሀመር ባለፈው ግንቦት ወር ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሸሙወዲህ ለሁለት ጊዜያት ያህል ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ከአውሮፓ ህብረት አቻቸው አኔት ዌበር፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሃናቴት እና ከካናዳና ጣሊያን አምባሳደሮች ጋር በመሆን ወደ መቀሌ አቅንተው ነበር። የማይክ ሐመር የመቀሌ ጉዞ በሁለቱ ወገኖች  መካከል የሰላም ድርድር እንዲጀመር ያደርጋል የሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፤ ህውሃት ነሐሴ 18 ቀን2014 ዓ.ም የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ ዳግም ጦርነቱን በመቀስቀሱ ሳቢያ የሰላም ተስፋውን አጨልሞታል።



Read 11339 times