Saturday, 10 September 2022 20:54

“ዓመቱ ኢትዮጵያ ምንም ብትደረግ የማትፈርስ መሆኗን ያየንበት ነው” ፖለቲከኛ የሸዋስ አሰፋ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በመጀመሪያ ለመላው ኢትዮጵያዊያን በጭንቅም ውስጥ ቢሆን እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ። 2014ን እንደ ፖለቲከኛ ከፖለቲካዊ ሁኔታው ነው የምመለከተው። ዓመቱ እንደ ሀገር ከፈረሱ ጋሪውን ለማስቀደም የሞከርንበት ነው። ምን ማለቴ መሰለሽ… ቅድሚያ ለችግሮቹ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሳንሰጥ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ችግሮቻችን ከኋላ ወደፊት ለመፍታት የሞከርንበት ነው። 2012ም፣ 2013ም እንደዛው ነበር።
በእኔ እምነት ፖለቲካው ሲቃና ነው ኢኮኖሚው፣ ማህበራዊ ህይወታችንም ሆነ ሃይማኖታዊ ጉዟችን በትክክል የሚሄደው። እኛ ለዘመናት የታገልነውን ዘውግን ወይም ዘርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ እሳቤን በቆራጥነት ካልገታነው በስተቀር እንደ ሀገር ሁሉ ነገራችንን ነው የሚያቆመው የሚል እምነት ነው ያለን። እናም 2014 ይህንን ዋናውን ችግር አልፈን፣ ሌሎች ተከትለው የሚመጡ በሽታዎችን ለመፍታት የሄድንበት ዓመት ነውና በዚህ መልኩ ነው የምገልጸው።
ስለዚህ በ2015 ዓ.ም ሀገራዊ ምክክሩን የእውነት አድርገን መጀመሪያ መፈታት ያለበትን ማለትም ሁሉ ቦታ ላይ እየገባ ችግር የሚፈጥርብንን ፖለቲካውን ፈትተን ወደ ሌሎች የምንሄድበት   ዓመት እንዲሆን ነው ምኞቴ።  በሌላ በኩል 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ብዙ ነገር ቢሞከርባትም እንኳን የማትፈርስ ሀገር መሆኗን ያሳየችበት  ዓመት ነው። አየሽ ኮሮና ቫይረስ ነበረ፣  ወረራ ነበረ፣ የውጪ ጣልቃገብነት ነበረ፣ አንበጣ ነበረ፣ የጎርፍ አደጋና በጣም በርካታ ፈተናዎች  ነበሩ።
ታዲያ ይንን ሁሉ ልንሻገር የቻነው ኢትዮጵያ የተሰራችበትና እንደ ሀገር  የተሸመነችበት ድርና ማግ የዋዛ ባለመሆኑ ነው። በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላምና የጤና ይሁንልን ለማለት እወዳለሁ። መልካም አዲስ ዓመት።

Read 10936 times