Saturday, 10 September 2022 20:53

“አብዛኛው ህዝብ በምሬት የሚያነሳው ዓመት ሆኖ ነውያለፈው” አርቲስት ያሬድ ሹመቴ-

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የሚያሳዝነው ነገር እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ትተናል። ምክንያቱም ሁላችንም አይደለንም በሰላም እየደረስን ያለነው። እንግዲህ የተጠናቀቀውን ዓመት ፈጣሪ የሰጠን ባርኮ ነው። ዓመታትን እግዚአብሔር ባርኮ ነው የሚሰጠው። እውነት ለመናገር ዓመቱ ብዙ የተሰጋበት  ዓመት ነበር። የተሰጋለትን ያህል ባይሆንም በከፍተኛ ደረጃ የወገኖቻችን እልቂት የታየበት፣ ድርቅና ረሀብ ሀገራችን ውስጥ ተከስቶ በቦረና አካባቢ ሰውም ከብቱም ያለቀበት፣ በጦርነት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖቻችን የተሰቃዩበት፣ ጦርነቱ ከአንዴም ሁለት ጊዜ አገርሽቶ በርካታ ቦታዎች ላይ ብዙ ሰው ያለቀበት ብሎም ንብረት የወደመበት፣ የትግራይ ወገኖቻችን ይሙቱ ይኑሩ ሳናውቅ ከበርካታ ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጋር ተነጣጥለው የቆዩበት፣ በጦርነቱ ቤተሰብ ለሁለት ተከፍሎ ልጅ ከእናት፣ አባት ከሚስት የተነጣጠለበትና ይኑሩ ይሙቱ ሳይታወቅ ሁሉም ነገር ድፍን ብሎ የኖርንበት ዓመት ነው። በተለይ የትግራይ ወገኖቻችንን ማሰብ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉም ምስኪን ህዝብ ነው። የትግራይም ህዝብ እንደዚሁ በጣም ምስኪን ህዝብ ነው። እነዚህ ምስኪን የትግራይ እናቶች ከልጆቻቸው ሳይሆኑ፣ ልጆቻቸውም እናቶቻቸውን ሳያዩ የቆዩበት ክፉ ዓመት ነበረ። ይህ በእርግጥ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተፈጠረ ሀቅ ነው።በእኛ በኩል ደግሞ የሚቆጠር ሀብት ከህዝብ አሰባስበን ወገኖቻችንን ለመታደግ በጣርንበት ወቅት ከኢትዮጵያውያን አጋርነትን፣ ንፁህነትን፣ ለጋሽነትን፣ ሩህሩህነትንና መልካምነትን ያየንበት ቢከሰትም እግዚአብሔርን ያየንበት ዓመት ነው።
በሌላ በኩል የኑሮ ውድነቱ ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ጣሪያ የነካበትና በዚህም ህዝብ የተንገሸገሸበት ዓመትም ነበረ። በግል ደረጃ የተወሰኑ ስኬቶች ሊመዘገቡ ይችላሉ። ነገር ግን 2014 ዓ.ም አብዛኛው ህዝብ በምሬት ሚያነሳው ዓመት ሆኖ ነው ያለፈው። 2013 ዓ.ም ላይ ሆነን 2014ን ስንቀበል ዓመቱ ከፍተኛ እልቂት የሚፈጸምበት እንደሚሆን ተገምቶ ነበር። ምንም እንኳን ብዙ እልቂትና መከራ ቢከሰትም፤ እግዚአብሔር በተባለው መጠን አላደረገብንምና ማመስገን አለብን።
በ2014 ሌላው የተጎዳነው ወደ አድዋ የምናደርገው ዓመታዊ ጉዞ (ጉዞ አድዋ) ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋረጠበት ዓመት መሆኑ ነው። አያቶቻችን አድዋ ሄደው የተዋጉት፣ አድዋ ሁሉም ድል ሆኖ እንዲቀጥልና ዓለም እስካለች የአድዋ ድል ደማቅነቱ ቀጥሎ እንዲረጋገጥ መሆኑ ነው። በአሁኑ ወቅት ግን የአድዋ ልጆች የትግራይ ወገኖቻችን ከሶስተኛ ወገን  ጥቃት በደርስባቸው እንኳን ለመከላከል በማንችልበት ሁኔታ ላይ ሆነን መቆየታችን በጣም ሆድ የሚያባባና ከባድ ሀዘንን የሚያሳድር ነው።
በዚህ ሁሉ መሃል በጣም የምደሰተው ደግሞ ይሄ ሁሉ የታየው ግፍና መከራ ህዝብን ምን ያህል እንዳስመረረውና እንዳንገሸገሸው በቁርጠኝነት የሳየበትና ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ለመውጣት እንደሚፈልግ ያረጋገጠበት የተነሳበት ዓመት በመሆኑም ጭምር ነው። ህዝብ ሰላም መቀራረብና ፍቅር የሚፈልግ መሆኑን በግልጽ ያሳበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል።
በ2015 ዓ.ም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት በፍቅር የጋራ ቤቱን ለማቆምና ምሶሶውን ለማጠንከር በጋራ ሚቆምበት እንዲሆን ነው የምመኘው። ባለፈው ጦርነት ህዝብ ተጎድቷል፤  በሁለቱም ወገን ያለው ህዝብ ተክዷል። ስለዚህ ይሄ ህዝብ መካስ አለበት። መካስ ካለበት ደግሞ ወደ ሰላም፣ ወደ አንድነትና ወደ ፍቅር መምጣት አለብን። እኔ በበኩሌ 2015ን ባርኬ ነው የምጀምረው እንዲያው የምጠራጠረው ነገር እንኳን ቢኖር ከአፌ አላወጣውም፤ ዓመቱ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሁሉ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ።ከእስካሁኑ  መከራ አንጸር ይሄ ጦርነት መቀጠል የማይገባው ነውና ፖለቲከኞችም በጋራ ልብ ነገሩን ማስተካከል አለባቸው። የጋራ ልብ የሌለው ፖለቲከኛ ካለ ግን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ሰላም ወዳዱ ህዝብ ሰላሙን በገዛ እጁ ለመመለስ አጥፊዎችን የቀጣበት የራሱ ተዓምራዊ መንገድ ስላለው ምንም ጥርጥር የለውም ጦርነቱም ይቆማል፤ ሰላምም ይወርዳል፤ ሀገራችንም ሰላም ትሆናለች የሚል እምነት አለኝ። በድጋሚ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን።

Read 10909 times