Saturday, 10 September 2022 20:56

“ያለፈውን ስህተት የማንደግምበት ብሩህ ዓመት እንደሚሆን አምናለሁ” መምህር ታዬ ቦጋለ -

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

2014 ዓ.ም በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና  ሌሎች ዘርፎች በአንድ በኩል ተስፋ ሰጪ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የታዩበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ መፈናቀል የደረሰበትና በተለይ በወለጋ በአካባቢ ዜጎች አሳዛኝ ሁኔታ የተጨፈጨፉበት፣ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የህዝብ እሮሮ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሰማ የሚያደርግ ቢሮክራሲ የገነነበትና ከዚያም አልፎ አንዳንድ ሰዎች “ጊዜ ሰጠን” በሚል ሁኔታ ከፍተኛ የመብት መጋፋት ተግባር ያሳዩበት ዓመት ነው ብል ማጋነን አይሆንም።
በሌላ በኩል ደግሞ በሀገራችን ግዙፍ የሆኑ ፕሮጀክቶች የተጀመሩበትና የተጠናቀቁበት፣ በአጠቃላይ መልካምና መጥፎ ሁኔታዎችን ጎን ለጎን ይዞ የተጓዘ ዓመት ነበር።
ከዚህ በተቃራኒው፣ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተለይ በወሎ ግንባርና በሁመራ  አሸባሪው፣ ተስፋፊውና አረመኔው የትግራይ ወራሪ ቡድን የአማራንና የአፋርን አካባቢ የወረረበት እንዲሁም ብዙ ጥፋቶችን የፈጸመበት ዓመት ሆኖ አልፏል። በዓመቱ እንደ አንድ ትልቅ የከፋ ድርጊት የምቆጥረው ይህንን ነው። ይሁንና መላው ጥምር ጦራችን ማለትም መከላከያው፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ፤ በተመሳሳይም የአፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሻ በአንድ ላይ በመሆንና በመቀናጀት አሁንም በምነጋገርበት ሰዓት ወራሪውንና  አሸባሪውንን ቡድን  ድባቅ  እየመቱ ለረጅም ጊዜ በወራሪው ጭቆና ስር የነበረውን የትግራይን ህዝብ ነፃ ለማውጣት እየገሰገሱ መሆኑ አስደሳች ዜና ነው።
ሌላው ከ2014 ወደ 2015 ዓ.ም ይሸጋገራል ብዬ የማንምነው የብሄራዊ ምክክር ጉዳይ ነው። ምክክር እንደ ሀገር ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት በጣም ሰፊ ሚና የሚጫወት ነውና ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱና የድርጊት ቅደም ተከተል አስቀምጦ መንቀሳቀስ መጀመሩ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ምናልባትም የምክክር ኮሚሽኑ ሥራ ፍሬያማ የሚሆንበት አካሄድ ካለ፣ በህገ-መንግስት ማሻሻያ ላይ ንግግር የምንጀምርበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። በ2015 በጎ ጅምሮች ተጠናክረው፣ ደካማ ጎኖቹ ተሻሽለው ያለፈውን ስህተት የማንደግምበት ብሩህ ዓመት እንደሚሆን አምናለሁ።
2015 ዓ.ም የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤና የመተሳሰብና እርስ በእራሳችን አፍ ከልብ ሆነን ኢትዮጵያን ለማሳደግ ጥራት የጋራ የምናደርግበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ። ዓመቱ ለረጅም ጊዜ በሰቆቃ ውስጥ የቆየውንና በእንባ ለረጅም ጊዜ ተሸፍኖ ያሳለፈውን የኢትዮጵያን ህዝብ ከዚህ ሰቆቃ ማውጣት የምንችልበት መሆን አለበት። በተረፈ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ2015 ዓ.ም አደረሳችሁ። ዓመቱ ሰቆቃ ዋይታ፣ ብጥብጥ መፈናቀልና ሞት የማይከሰትበት እንዲሆን እመኛለሁ።

Read 11111 times