Saturday, 10 September 2022 20:58

በርካታ መከራዎች የታለፉበትና ታላላቅ ስኬቶች የተመዘገቡበት ዓመት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

ተሰናባቹ 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን እጅግ በርካታ መከራዎችንና ታላላቅ ስኬቶችን ያስተናገዱበት ዘመን ነበር፡፡ አሮጌው ዓመት ኢትዮጵያውያን በህወሃት ታጣቂ ሃይሎች በየጊዜው በሚቀሰቀሱ ጦርነቶች ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻቸውን ያጡበት ፣በተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪው ኦነግ ሸኔ የንጹሃንን ደም በግፍ ያፈሰሰበት፣ አያሌ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ የወደቁበት የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች በአማራና በአፋር ክሎሎች የጀመሩትን ወረራ አስፋፍተው እስከ ደብረሲና ድረስ የዘለቁበት፣ ምዕራባውያኑ  ደግሞ የህወሃትን  ሃይሎች በሚደግፉ ተግባራት ላይ ተጠምደው የከረሙበት፣ የዋጋ ግሽበቱ ጣራ የነካበትና የኑሮ ውድነቱ የዜጎችን ናላ ያዞረበት፤ መንግስት ለዓመታት ሲያደርገው የኖረውን የነዳጅ ድጎማ ለማንሳት የወሰነበትና ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የተደረገበት ፈታኝ ዓመት ነበር፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጨት የጀመረበትና 3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀበት፣ በግብርናው ዘርፍ አስገራሚ ስኬቶች የተመዘገቡበት፣ ዓመት ነበር 2014 ዓ.ም፡፡
በአስቸጋሪ የታሪክ ሂደት ውስጥ እያለፈች የምትገኘው ኢትዮጵያ በተሰናባቹ  ዓመት ከገጠሟት ዋና ዋና ፈተናዎች መካከል በህወሃት ሃይሎች በተደጋጋሚ የሚቆሰቁሱት ጦርነቶችና የተባበሩት መንግስታትና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከምዕራብውያን አገራት የሚደርሱባት ጫናዎች ይገኙባቸዋል፡፡ የመንግስታቱ የፀጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ ከ13 ጊዜያት በላይ ለስብሰባ የተቀመጠበትና የምክር ቤቱ አባላት በውሳኔዎች ላይ እርስበርስ መግባባት ሳይችሉ እየቀሩ ስብሰባዎቹ ያለውጤት የተበተነበት ዓመትም ነበር።
ከስንቅና ትጥቅ አቅርቦት በተጨማሪ በተለያዩ መንገዶች በምዕራባውያኑ አገራት የሚደገፈው የህውሃት ታጣቂ ሃይል፤ ወሮ በያዛቸው የአማራና አፋር ክልል ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ንፁሃን ህፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ በግፍ የጨፈጨፈበት፣ በዕድሜ የገፉ እናቶችና መነኩሴዎች ሳይቀሩ የተደፈሩበት፣ ሰዎች በጅምላ ተገድለው የተቀበሩበት፣ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የግፍ ግድያ የተፈፀመበት ዓመት  ያሳለፍነው በተጠናቀቀው 2014 ዓ.ም ነው። የወገኖቹን የግፍ ግድያ በመቃወም ከህውሃት ሃይሎች ጋር ግንባር ለግንባር ተፋልሞ ከነልጁ ለአገሩ መስዋዕት የሆነውንና በደሙ ደማቅ ታሪክ ጽፎ ያለፈውን የሸዋሮቢቱን ጀግና የእሸቴ ሞገስን የጀግንነት ታሪክ የሰማንበትም ዓመት ነበር።
የፌደራሉ መንግስት ከህወሓት ሃይሎች ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ መሆኑን በተደጋጋሚ የገለፀበት፣ ህውሃትም የተዘረጋውን የሰላም እጅ በተደጋጋሚ በማጠፍ ፀረ-ሰላም አቋሙን በተግባር ያረጋገጠበት ወቅት ነው-ያሳለፍነው ዓመት።
አገሪቱ ለዓመታት የዘለቀው የተዛባ የንግድ ስርዓት በተለይም የውጪና ገቢ ንግድ አለመመጣጠን፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የውጭ ንግድ  መቀዛቀዝ፣ ከአጎዋ ተጠቃሚነት መሰረዝ፣ ጦርነት፣ አለመረጋጋትና በመላው ዓለም የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ተደማምረው በፈጠሩት ግሽበት ሳቢያ የኑሮ ውድነቱ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ታይቶ በማይታወቅበት ሁኔታ የናረበትና የዋጋ ግሽበቱ አራት አስርታትን በመሻገር፣ 46.7 በመቶ የደረሰበት ዓመት ነበር-2014 ዓ.ም። በዚህም ሳቢያ መሰረታዊ  የሚባሉ  ሸቀጦች ዋጋ ከዜጎች  የመግዛት አቅም  በላይ የሆነበትና በዜጎች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና ያሳደረበት ዘመን ነበር-ተሰናባቹ 2014 ዓ.ም።
ከነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ ሩዝ፣ ፓስታና መኮሮኒ ከውጪ አገር ሲገቡም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምባቸው ከቀረትና ታክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንዲሆኑ እንዲሁም ስንዴ ከውጪ አገር ሲገባ ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲሆን ተወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ በእነዚህ ሸቀጦች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ ሆኗል። ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ላይ 40 ብር ይሸጥ የነበረው ስኳር በያዝነው ወር ላይ 120 ብር በመድረስ 3 እጥፍ ያህል ጭማሪ አሳይቷል፡፡ እነዚህን ሸቀጦች መንግስት በሸማችና መሰል ተቋማት ለህብረተሰቡ የማዳረሱን ተግባርም ችላ ያለው ይመስላል፡፡
ለአመታት የአገሪቱ አንገብጋቢ ችግር ሆኖ የዘለቀው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዘንድሮም በባሰ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣው የምንዛሪ ተመን፣ የምጣኔ ሀብት  ባለሞያዎችን ስጋት ላይ የጣለና አሳሳቢነቱ የተነገረለት ሆኗል፡፡ በትናንትናው ዕለት ሁሉም ባንኮች አንዱን የአሜሪካን ዶላር በ52 ብር ከ51 ሳንቲም የገዙ ሲሆን በጥቁር ገበያ የአንድ ዶላር ዋጋ ከ70-72 ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ የሰባት ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ አምና በጷጉሜ ወር አንድ ዶላር በባንኮች በ45 ብር ከ60 ሳንቲም ይመነዘር ነበር፡፡
ተሰናባቹ አመት አገሪቱ በርካታ ችግሮችንና ፈተናዎችን ያስተናገደችበት የመሆኑን በርካታ ያህል ስኬቶችንም ያስመዘገበችበትና በድል የተጠናቀቁ ስራዎችን ያከናወነችበትም ዘመን ነው ፡፡ ከእነዚህ አገሪቱ በተጠናቀቀው ዓመት ካሳካቻቸው ታላላቅ ተግባራት መካከል ዋንኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንቸት መጀመርና ሶስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቋ ነው።
ጠቅላላ የግድቡ ግንባታ ስራ 83.3 በመቶ የደረሰው የታላቁ ህዳሴ ግድብ፤ በዚሁ ዓመት መጨረሻም ቀሪ የግድቡን ግንባታ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ተገልጿል- በዚሁ በተጠናቀቀው የ2014 ዓ.ም።Read 13649 times