Saturday, 10 September 2022 21:15

“አይ ሀቭ ኤ ድሪም!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

“--እምዬ ኢትዮጵያን ክፉ ከሚያስቡባት በላይ፤ ክፉ ከሚመክሩባት በላይ፣ ክፉ ከሚሸፍጡባት በላይ፣ ክፉ ሴራ ከሚጎነጉኑባት በላይ፣
ቀንና ሌት ውድቀቷን ከሚመኙላት በላይ ያድርግልን!--”
       
       እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለአዲሱ ዘመን ዋዜማ አደረሳችሁማ!
ቅዳሜና ዋዜማ ግጥም አሉና አረፉት!
ስሙኝማ...ይሄ ኮንዶሚኒየም የሚባለው ነገር እኮ ስንት ውለታ አለው መሰላችሁ! ልክ ነዋ...በፊት እኮ በተለይም በዓል ዋዜማ ቀኖች በየቤቱ ሱናሚዎች የሚነሱበት ነው፡፡ እኔ የምለው ዓመቱን ሙሉ ያለፍንበትን መንገድ እያወቅነው፣ የፈረንካዋን ነገር እያወቅን በበግና በምናምን ግዥ የሚፈጠረው አንዳንዴ ቅልጥ ያለ ረብሻ ግርም የሚል ነው፡፡ የኮንዶሚኒየም አንዱ ነገር እንደ ልብ በግና የመሳሰሉትን እንስሳት ማሰሪያ በቂ ስፍራዎች የሉም፡፡ እኛ ደግሞ በግየው ሳይቀላቀል ራሱን ችሎ እንዲታሰር ነው የምፈለገው፡፡ ልክ ነዋ...በኋላ ተቀላቅሎ ሌሊቱን ምን ጠባይ እንደሚያስተምሩት ምን ይታወቃል! ለምሳሌ የሆቴል ክፍል ስንከራይ “ሲንግል ነው ደብል?” እንደምንባለው፣ ‘ለበጋችን’ ሲንግል ማሰሪያ ቦታ ነዋ የምንፈልገው! ደግሞስ የዘንድሮን በግ ማን ያምናል!
“አንተ! ዘንድሮም በግ ሳይገዛ እንዲሁ ባዶ ቤት ልንውል ነው!”
“ምኑ ነው ባዶ ቤት? ጠቦት የሚያክል ዶሮ እያስካካብኝ ባዶ ቤት ትያለሽ!”
“ምን ለማለት ፈልገህ ነው!”
እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ይቺ “ምን ለማለት ፈልገህ ነው!” “ምን ለማለት ፈልገሽ ነው!” የምትለው ነገር...አለ አይደል...ለሆነ ነገር ማብራሪያ ምናምን መጠየቂያ መሆን አልነበረባትም እንዴ? የሆነ ስብሰባ ላይ ወይ ስሙ ‘ስብሰባ’ የሆነ ነገር ላይ ተናጋሪው ሰውየ ወይ እራቀቃለሁ ብሎ፣ ወይ ዋና ሳያውቅ ዘሎ ባህር ውስጥ እንደሚገባ ሰው ተስፈንጥሮ የማያውቀው ነገር ውስጥ ገብቶ ሊያጨናብራችሁ ሲሞክር... “አሁን የተናገርከው አልገባኝም፡፡ ምን ለማለት ፈልገህ ነው?” ምናምን መባል፡፡ ግን ነገርየዋ አሁን ማብራሪያ መፈለጊያ መሆኗ ቀርቶ ነገር መፈለጊያ ሆናለች፡፡ እናላችሁ...ሀሳብ ለማቅረብ ያህል....ስንት ፈረንጅ “ሀርምለስ፣” የሚላቸው ገር፣ ገር ቃላት ከዕለት ዕለት ወደ ዘለፋነት አነጋገር እንደተለወጡ ጥናት ይደረግልንማ! በተለይም በቦተሊካው መንደር፡፡
እናማ...እሷየዋ “ምን ለማለት ፈልገህ ነው!” ስትል... አለ አይደል... “ጠቦት የሚያህል ዶሮ ያልከውን ዘርዝረህ አስረዳኝ፣” ማለቷ አይደለም፡፡ ጠብ እንጂ!
“ማለቴ ቆንጆ ዶሮ መርጠሽ ስለገዛሽ...”
“አንተ ግን በአንተ ቤት አሽሙር መናገርህ ነው!”
“ኸረ እባክሽ እኔ እንደ እሱ አስቤ አይደለም!”
“እኔ ለአንተ ደደብ ነኝ አይደል! ምንም የማላውቅ...”
“ኸረ እባክሽ፣ ኸረ እባክሽ...”
“ራስህ ኸረ እባክህ! ደግሞ ኸረ እባክሽ ይለኛል እንዴ!”
“አሁን ምን ክፉ ነገር ተናገርኩና ነው!”
እሱ እኮ “ቆንጆ ዶሮ መርጠሽ ስለገዛሽ...” ምናም ያለው መለሳለሱ ነበር እኮ!
“ስማ... እኔ ልጂት አንተ ጠቦት አልከኝ፣ ምን አልከኝ...”  በቃ በዚህ መልኩ ይቀጥላል፡
“ታዲያ በዶሮ ብቻ እንቁጣጣሽን ልንውል?!”
“አይ የቴሌቪዥን የበዓል ፕሮ...”
“በቃ! በቃ! ሰይጣኔን አታምጣው!”
እኔ የምለው... የዘንድሮዎቹ ወጣቶች ይቺ “ሰይጣኔን አታምጣው!” የምትለውን ነገር ያውቋታል እንዴ! አሀ...ልክ ነዋ፣ የንዴት ላሊጋ ነች እኮ፡፡
በዚህ ሰሞን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፈ የአንድ ሰንጋ ስዕል ስናይ ነበር፡፡ መሸጫ ዋጋው ሁለት መቶ ሠላሳ ሺህ ብር፡፡ የሚገርም እኮ ነው፡፡
ደግሞላችሁ... ዘንድሮ ከአንደበታችን የማይጠፋ አንድ ጉዳይ የኑሮ መወደድ ነው፡፡ “በዚህ የኑሮ ውድነት አንድ እንጀራ ሙሉ ለምሳ “ትጨርሳለህ!” በሚባልበት ዘመን፣ ሰዋችን እንደሁ በበዓላት ሰሞን ከተማዋን ምንም አይነት ችግር የሌለባት ነው የሚያስመስላት፡፡ (ስሙኝማ...የእኛን ሀገር ኤኮኖሚን ለመተንተን የፈረንጆቹ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ሁሉ “ግራ ገብቷቸዋል...” የሚል ነገር አንዳንዴ ተጽፎ እናያለን፡፡ እውነት ነው ወይስ በየሰበቡ “ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ምናምነኛ እንደምንለው የራስን ጀርባ ቸብ፣ ቸብ ማድረጊያ ነው?)
የምር ግን አንዳንድ ጊዜ በሆነ ፍልስፍና ምናምን አይነት ጭቅጭቅ ምክንያት ሳይሆን አንድ፣ ሁለት ቀናት “አሁን ደመቅሽ አበባዬ!” ተባብለን አስራ አንድ ወር ደመና አጥሎቶብን ከመክረም አንድ ሁለቷን ቀን እንደው ትርፍ ትርፉን ነገር ተወት አድርገን፣ ከኤኮኖሚ አንጻር የበዓል አከባበራችንን ሰብሰብ ማድረግ ብንችል እንዴት ይሆን ነበር!
ከብረው ይቆዩ ከብረው
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሠላሳ ጥጆች አስረው
የሚለው የአዲስ ዓመት ዘፈን አሁን ከእነ ግጥሙ አለ እንዴ!  አሀ...‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ የሚሏቸው አይነት ነገሮች አሉበታ! ለምሳሌ “በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው...” የሚለውን ስንኝ የሆነ ፍሬሽና አለቆቹን ‘ኢምፕሬስ’ ማድረግ የሚፈልግ ቦተሊከኛ...አለ አይደል... “ይህ ግጥም  የቤተሰብ ምጣኔ አስፈላጊነት ላይ ጥቁር ጥላ የሚያጠላ...” ምናምን የሚል ቡትለካ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ሌላኛው ደግሞላችሁ በሌላኛው ላለመበለጥ “...ወንድ ልጅ ወልደው...የሚለው የሾቭኒስቶች መፈክር...” ምናምን ሊል ይችላል፡፡ ዘመኑ እንዲህ ነዋ!
በነገራችን ላይ፣ ማስተካከያ... ሰውየው ‘ሾቭኒስቶች’ የሚለውን ቃል አይጠቀምም፡፡ ልክ ነዋ...እንደዚህ አይነት ጠለቅ ያለ...የቦተሊካ ዲስኩር ብዙም አንሰማማ! የምር ግን... እንግዲህ ጨዋታም አይደል...በዘንድሮ ቦተሊካችን ያኛውን ወገን ‘መሬት ላይ ለማንጠፍ’ እንደ ካርታው ጆከር ሁሉም ቦታ አገልግሎት የምትሰጠው አንድ ሀረግ ብቻ የሆነች አይመስላችሁም...“የድሮ ስርአት ናፋቂ!” የምትለው! ትንሽ አርትኦት ምናምን ተሠርቶባት ከመጣችም ግፋ ቢል “የአጼዎቹ ስርአት ናፋቂ!” ሆና ብትመጣ ነው፡፡ ኸረ እባካችሁ... ቢያንስ ናፋቂ የምትለዋ ነገር ስልችት እያለች ስለሆነች የዝውውር ገንዘብ የማይከፈልባቸው ሌሎች ቀረብ የሚሉ ቃላት ፈልጉማ!
“ስማ ያ ሰውዬ ነገረ ሥራው ምንም ደስ አላለኝም፡፡”
“ስለ የትኛው ሰውዬ ነው የምታወራው?”
“ያ እንትና ነዋ!”
“ምነው፣ ምን አደረገ?”
“አቋሙ ሁሉ ትክክል አይደለም፡፡”
“የምን አቋሙ?”
“የፖለቲካ በለው የሁሉ ነገር አቋሙ የድሮ፣ የድሮ አይነት ነው፡፡ እንደውም አንዳንዴ ሳስበው አምስተኛ ረድፈኛ ይመስለኛል፡፡” ኢሮ! ማጨብጨብ ይሄኔ ነው፡፡ አሀ...አምስተኛ ረድፈኛ ምንም ይሁን ምን ዋናው ነገር በድሮ ስርአት መዝገበ ቃላት ውስጥ የነበረ ስለሆነ ለ“ናፋቂ...” እንደ አምሳያ ቃል ሊያገለግል ይችላል፡፡ አሀ...ወይ “ሽምብራ ወጥ፣” ወይ “የተሰነገ ቃሪያ” ብለን ባዘዝን ቁጥር “የድሮ ስርአት ናፋቂ...“ መባል ሰለቸና! ቂ...ቂ...ቂ...  
ይህን ዛሬ ጠቅልሎ የሚወጣውን ዓመት የሚመስል ሌላ ዓመት መቼም ቢሆን መልሶ አያምጣብን! 
ጠላቶቻችንን ከእነ ተንኮላቸው፣ ከእነ ሸፍጣቸውና ከእነ ሴራቸው እዛው በሩቁ ገድቦ ያስቀርልን!
ጠባይ ለጎደለው ሰናይ ባህሪይ፤ ደግነት ለጎደለው ትህትና፣ ሰብአዊነት ለጎደለው ልቡና ይስጥልን!
እኛ በየከተማውና በየገጠሩ እንደፈለግን እንድንሆን ቀን ተሌት ህይወታቸውን እየገበሩ እኛና ሀገራችንን እየጠበቁን ያሉ ወገኖቻችንን ሁሉ፣ ፈጣሪ የሰማይ ቤትን ለእነሱ ወለል አድርጎ ይክፈትላቸው፡፡ ውለታቸው በምድር ተከፍሎ ሊያልቅ አይችልምና!
እምዬ ኢትዮጵያን ክፉ ከሚያስቡባት በላይ፤ ክፉ ከሚመክሩባት በላይ፣ ክፉ ከሚሸፍጡባት በላይ፣ ክፉ ሴራ ከሚጎነጉኑባት በላይ፣ ቀንና ሌት ውድቀቷን ከሚመኙላት በላይ ያድርግልን!
አዲሱን ዓመት የማርቲን ሉተር ኪንግን የማይሞቱ ቃላት ለመዋስ... “አይ ሀቭ ኤ ድሪም!” የምንልበትና ህልሙንም እውን ለማድረግ የምንታትርበት ዓመት ያድርግልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1431 times