Saturday, 10 September 2022 21:18

ላያስችል አይሰጥም?

Written by  -ከድረስ ጋሹ-
Rate this item
(8 votes)

[..እንደ ዲዮጋን ቅል አንጠልጥዬ መጓዝ ከጀመርኩ ሰነባበትኩ። በጠራራ ፀሐይ ከሰው መሐል ሰው ፍለጋ መባዘኑ ከረመብኝ። ይህች ምድር ለጠንካሮች ናት። እንደ እኔ ዓይነት ደካማ አብሯት አይኼድም። ጃርስእዎ ሞትባይኖር ኪሩቤል በ “ከደመና በላይ” መጽሐፉ፤ “ዓለም የወደዳትን ጥሬ ከብስል ታላምን” ሲል ታዝቧታል።እኔ እታዘብበት ዓቅም የለኝም። እርጅናን በወጣትነቴ የተቀበልኩ ብቸኛ ፍጡር ነኝ።ይህ እንዲሆን ምክንያት አለው።
ሰማይን አንጋጥጬ እንዳላይ አንገቴ ብይድ ሆኗል። ማቀርቀሩ ገንዘቤ ነው። የሕይወትን ጨለማ ገፅ ከእኔ ቀጥሎ ፊዲዮር ዶስቶቭስኪ ነው ሊያውቅ የሚችለው። የሕይወትን ብርኃን አልባ መልክ ከእኔ ቀጥሎ ኤድጋርድ አለን ፖ ነው ሊገልፀው የሚችል። እኔ የጨለማ ውስጥ አካል ሳልሆን ጨለማው ራሱ ነኝ።
አእምሮዬ ከመብረቅ ጉርምርምታ በላይ ይናወጻል። ንውጽውጽታ፣ ኹከት፣ ግርግር አይሆንልኝም። እንደ ሎሬቱ “እሸሸግበት ጥግ አጣሁ” ለማለት ይዳዳኛል። የምይዝ የምጨብጠው፣ የምደገፍ  የምረግጠው ሳጣ ባዶነት ይዋረሰኛል። አይቴ ብሔሯ ለነፍሴ? እላለሁ በጩኸት። ከሞት በኋላ የሚገኘውን ኩነኔ ምድር ላይ ጨረስኩት ፤ከዚህ በላይ ቅጣት ይኖር ይሆን? የሥርቻ ውስጥ መጣጥፌን ለእናንተ ባደርስ “ምጽ” ትሉ ይሆናል ፤ኑሮዬን ብትኖሩት ምን ልትሉ ነው? ያበበ ጽጌሬዳ ተቀጥፎ ቢያገኝ ለሚናደድ ፣የአሸተ በቆሎው ተዘንጥፎ ቢያገኝ ለሚያዝን ፣ ጎተራውን አይጥ ብትቀደው ለሚያባሽ ሰው ...የልብ መቀጠፍን እንዴት እንደማስረዳው አይገባኝም። ራሴን ለመረዳት ስታገል እንደሚረዳኝ እያመንኩ ቀጠልኩ። ያመነ ፣ያነበበ እንዲድን...
[...እንደ ሰው “አበራሁኝ ሻማ ሞቅ አለ ጎጆዬ” ብዬ አውቃለሁ። ኮከበ ጽባሕ ፣ ጸያሔ ፍኖት የሆነች ...የሱፍ አበባ የመሰለች የትዳር አጋር ነበረችኝ። የተጋባንበትን በዓመተ ምህረት ቆጥሬ ልነግራችሁ አልችልም። በዓመተ ውድቀት ከሆነ ግን ጀሯችሁን ስጡኝ። ቁመቷ ዘለግ ፣ ዳሌዋ ጣል ያለች ናት። ዓይኖቿ ሲገለጡ ጨለማን ይገረስሳሉ ፣ጥርሶቿ ሲስቁ ኅዘንን ያስረሳሉ። ለእኔ እንደ ሰውም፣ እንደ መለኮትም ነበረች። ክሊዮፓትራ፣ንግሥተ ሳባ ቆንጆነታቸው ለእናንተ ነው። ለእኔ ማን እንደ ፌኔት? በነግ ከጥልቅ እንቅልፌ ተነስቼ አያታለሁ፤እንደ በረዶ እንዳትሟሟ ሥጋቱ አለ። ከአንገቷ ደገፍ አድርጌ ግንባሯን እስማታለሁ። ዓይን ዓይኗን እያየሁ መንፈሴን አድሳለሁ። ከዕለታትም በአንዱ...ማለዳ ተስቼ...
“ፌኔቴ” አልኳት ።
“ወይዬ የኔ ንጉሥ” አለችኝ፤ በዛ መረዋ ድምጿ።
“ህልሜ ውስጥ አስፈሪ ነገር አየሁ “
“ንገረኝ ስወድህ “
“የቆምኩበት መሬት ተንዶ ሲውጠኝ አየሁ “
“በል ከቁብ አትቁጠረው ንጉሤ!  በፈላስፎች አነጋገር መጽሐፍ ላይ ሰው በህልሙ አፈር ከተጫነው ፣አፈር ሲራጭ ፣በአፈር ብዙ ነገር ሲያደርግ ካደረ፣ የአፈርነቱ ባህርይ አይሏል ማለት ነው። ሌላም ቀን የእሳትነት ፣የውኃነት ፣የነፋስነት ባህርይ ሲያመዝኑ ሌላ ህልም ልታይ ትችላለህ። ስለዚህ እርሳው ለክፉ አይደለም” ብላ አስረሳችኝ።
ህልሜን በአየሁ በማግስቱ የመጀመሪያ ልጃችን አረፈ። የጉድጓድ ውኃ ውስጥ ገብቶ ሞተ። እሷ ጉንጯን መታች ፤እኔም በእንባ እታጠብ ጀመር። ተስፋ የጣሉበት እንዳይበረክት በእሱ አወቅሁ። ለቅሶ የሚደርሰው ሁሉ “ላያስችል አይሰጥም” ይለኛል። በልጄ መጥቷልና እግዜርን ልሞግተው ተነሳሁ። እንደ ፍሬድሪክ ኒቼ ፣እንደ ቮልቴር ጠንከር ያለ ሙግት ያልሆነ ወቀሳዬን ላኩለት።... እኮ! ወጣቶችን ለምን ይገድላል? በአራት እግራቸው የሚድኹ አሮጊቶች ፣ዕድሜ ጠገብ አዛውንቶች ፣ “የእኔን መቀበሪያ ጎመን ልትዘራበት ነው ወይ ያቆየኸኝ?” ብለው ሞት የሚለምኑ የአልጋ ቁራኞች እያሉለት፣ ለምን ዓይኑን ወጣት ልጄ ላይ አሳረፈ? የታገለ አይጣልህ ፣የሮጠ አይቅደምህ ፣ውሎህ ሰላም መንገድህ ቀና ይሁን ብዬ የሸኘሁትን ልጅ በቃሬዛ መልሶ ማሳየት ነበረበት? ...እያልኩ ተነጫነጭኩ ። “እግዚአብሔር በከንፈርህ ካልተናገረ በቀር ሊሰማህ አይችልም” የሚለው የጅብራን ምክር ትዝ አለኝ። ለካ እሱ የክፉ ቃል መስሚያ ጆሮ የለውም ፤መልካሙን እንጅ!
[...የልጄን ኅዘን ሳልወጣው ፣ የሰጠኝን ሳያስችለኝ ለሌላ መከራ ፣ለሌላ መራር ሕይወት ታጨሁ። ለምን እንደታጨሁ አውቃለሁን? እኔ ሩቅብእሲ አይደለሁምን?
ዕለቱ ሐሙስ ነው። የቀን ቅዱስ ይሉታል የተቀደሰላቸው። ወንዝ የሚያሻግር ሰርግ ነበረብን ። እህል ውኃ ይዘን ልንሻገር ከውኃው ገባን። ያላሰብነው ማዕበል ተነሳ። እስከ ጉልበት የማይደርሰው ውኃ እስከ አንገታችን አለበሰን። የሞትን መልክ አየነው። እጁን ለሰላምታ ዘረጋልን። እኔ እንደ ዐፄ ቴዎድሮስ ፎከርኩ። እጅህን ስጥ አለኝ ሞት ፣እጅ ተይዞ ሊወሰድ ...ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ አልኩ። ስቃያችንን ያየ ወጣት ማዶ ቆሞ የምንጨብጠው ማገር ወረወረልን። ፌኔቴን ወደ ኋላ ትቼ እኔ ያዝኩት። እኔ ከማዕበሉ ወጣሁ ፤እሷን ውኃ ወሰዳት። ያኔ ወደ እኔ ጮሃ ተናገረች። ምን ያለች ይመስላችኋል? አታውቁትምና አትገምቱ...
ራስ ወዳድነቴን ያየሁበት፣ የልጅነት ፍቅሬን ያጣሁበት ፣ለዚች ዓለም ሸክምነት የታጨሁበት ዕለት እውን ቅዱስ ነውን?...ዓይኔ እያየ ፌኔትን ውኃ ሲወስዳት የተሰማኝ ስሜት ሊጻፈኝ አልቻለም። ጨለማ እንደዋጠኝ ሳይሆን ጨለማ እንደሆንኩ ብቻ ገብቶኛል።
-ይሁዳ አምላኩን በ 30 ዲናር ሸጠ። ለዚያውም አቅፎ ፣ስሞ...
-አዳም የአምላኩን ትዕዛዝ ጣሰ ሔዋንን ሰምቶ ፣ሔዋንም እባቡን ሰምታ...
-ጴጥሮስ ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ከዳ። አምላኩን አላውቀውም አለ ...
-እኔም ፌኔቴን ከዳሁ። አቅፌ ይዤ ውኃ ውስጥ አስገብቼ ለማዕበል ዳርኳት...ይኸው ጸጸት ፣ሕመም ፣ ተዋረሰኝ ።
የይሁዳ ጸጸት በስቅላት፤ የአዳም ጸጸት በጾም በጸሎት፤ የጴጥሮስም ጸጸት በትህትና ተገለጸ። የእኔን ጸጸት የሚሸከም ቃል ጠፋ። የመጨረሻ ቃሏ ...ጮኻ የነገረችኝ እስካሁን እያመመኝ ነው...
ንዑስ ሕመም
እንደ ዘፋኙ እያነቡ እስክስታ  ለምዷል ትክሻዬ  አልልም ፤እያነቡ መኖር ነውና የተቸረኝ። ሰው ከመላዕክት በላይ መልካም የመሆን ጸጋ ተሰጥቶታል። ሰው ከሰይጣን በላይ ክፉ የመሆንስ ጸጋ የለውም  ትላላችሁ ? ነፍስ ባላወቀ ህጻን አንገት ላይ ቢላ መስደድን ሰይጣን ላያውቀው ይችላል። ይልቅ ሰው የሰይጣንን እጅ ይዞ ያስፈጸመው ይመስለኛል። ፌኔትን ከማግባቴ በፊት ...ከመብራት ምሰሶ  ስር ቆመን መጫወት እናበዛ ነበር። የገነት ተክል የመሰለች ልጅ ፣ እግዜር ታጥቦ የሰራት (ለመሆኑ ሳይታጠብ የሰራው ማንን ነው ግን?) ልጅ ጋር መጫወትን ማን ይጠላል። ከመብራቱ ምሰሶ ስር የተከማቸ ሣር አለ። ከሳሩ የወጣ እባብ በአካሌ ተጠመጠመ። በድንጋጤ ወገቡን ይዤ ወደ ፌኔት ገላ ወረወርኩት። ነደፋት። በብዙ ሰው እርብርብ ፣በሃበሻ መድኀኒት ብርታት ፣በእግዜሩም ፈቃድ ተረፈች።ያኔም ቀኑ ሐሙስ ነበር። ሐሙስ የቀን እርኩስ። እየተከተለ ጦሱን ይጥልብኛል። ራስ ወዳድነቴ ያቆጠቆጠበት ዕለት ነው..ከርሞ የሚያብድ ሰው ዘንድሮ ልብሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል እንዲሉ፡፡
ዓቢይ ሕመም
የመኖሬ ምስጢር እያለ የሚጠራት አፌ፣ ከሞትህና ከውድህ ምረጥ ብባል “በመጨረሻ እስትንፋሴ እወድሻለሁ” ብዬ እንደምለያት የነገራት ምላሴ...የመጨረሻ ጩኸቷ ላይ ታጠፈ ። የምላስ ወለምታ በቅቤ አይታሽም። የሕይወት ማገር ወደ ማዕበሉ ሲወድቅ ተሽቀዳድሜ ያዝኩት። የእሷ መሞት ደንታዬ አልነበረም ? ወይስ የእኔ መትረፍ ነበር ደንታዬ?...በቁሜ እንደ እንጨት ያደረቀኝ ፣ከማዕበሉ መንጥቄ እንዳላወጣት ያሰረኝ ምን ይሆን?...
የእኔና የሰዎች ግፍ ተጠራቅሞ ጎርፍ ሆነ። ጎርፉ ለፌኔት ተረፈ። እኔ በማገሩ ተንጠልጥዬ ወጣሁ። እሷ አንድ ቃል ጮኻ ሄደች። እሱም “ልጆቼን አደራ” የሚል ነበር። ይሄ ነው ትልቅ ሕመሜ።
“አባት ሆይ የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” የሚለው ቃል ታወሰኝ። ለሚገድሉት ቸር የተመኘ አምላክ፣ በሴት ተመስሎ አጠገቤ ነበርን? ልጆቼን አደራ ...ልጆቼን አደራ ....ልጆቼን አደራ ...ይኼ ቃል በዙሪያዬ ተንጫጫብኝ። ጆሮዬን ይዤ እሪሪ ብዬ ጮህኩ ። ገደሉ እያላገጠብኝ ነበር። የጸጸት ድምጼን በቀበሌ መልሶ አሰማኝ። ድምጼ አያምርም ...ተግባሬን ...ድምጼን ሁሉ ጠላሁት። ማገር ሰጥቶ ያተረፈኝን ሰው ሳልሰናበት ብን ብዬ ጠፋሁ።ዘመን ዘመንን ተካ። በልቤ የተደበተው ህመም ቦካ። የኀዘን ልብስ አለበስኩም ፤ኀዘን ራሱን ሆኛለሁ። ውኃ ባየሁ ቁጥር እርጉምነቴ ይታወሰኛል። ለፌኔት ብሞትላት ሞት ያንሰኝ ነበር ። መኖሬ ቀብሯን እንድጎበኝ ብቻ ነው የረዳኝ። ከመቃብሯ ላይ የተከሉት ቁልቋል ጸድቋል ። እኔም ቀብሯ ላይ አጋም ተከልኩ። ለምን ? “ከአጋም ተጎራብቶ የኖረ ሲያለቅስ” እንደሚኖር ብትረዳኝ ብዬ ነው። ከ ጸጸት ጋር የተጎራበተ የሰላም እንቅልፍ የለውም። ጸጸት አጋሙን ፤እኔ ደግሞ ቁልቋሉን ...አልቃሽና አስለቃሽ![...ፌኔት ለሞት እጇን ለምን ሰጠች?  ለእኔና ለልጆቿ መኖር ስትል። ክርስቶስ ለአይሁድ እጁን ለምን ሰጠ?  ለአዳም መዳን ሲል። ሕይወቱን ሰጥቶ ለአዳነ መልሱ ምን ይሆን?...እህህ! መቃብሯ ላይ የበቀሉት ዛፎች ግጥሞች ናቸው።
 በእንባዎቼ አሳድጊያቸዋለሁ። የፌኔትን ደህንነት በዛፎች በኩል አውቃለሁ። ከአጋሙ ቀጥፌ የእግሬን እሾህ አወጣለሁ ፤እሷን ገድዬ እኔ እንደተረፍኩት ሁሉ።ዘመን ዘመንን ተካ። መቃብሯን መኖሪያዬ አደረግኩት። ልጆቻችንን ሜዳ በተንኳቸው። አደራዋን በላሁ። ሕይወቴን ሕጸጽ አጀባት። ዞሮ ማየትን አልፈጠረብኝም።
 እንዳልኳችሁ አንገቴ ብይድ ሆኗል። እኔ ኀዘንተኛ አይደለሁም፤ እኔ ኀዘን ራሱን ነኝ። ወረቀት አውጥቼ ፌኔትን ልጽፋት እታገላለሁ።
ለፌኔት ቃል ይሳሳል፤ ቅኔም ቅኔ አይሆን። ልቤ ከሄኖክ በቀለ ቃል እንዲዋስ መረጠ። “ሰው መስላኝ ታውቃለች ፤መለኮቷ ሚስቴ “ አልኳት። የልቤ ሩብ አልደረሰም።ሁለት ዓመት ዝናብና ጸሐይ ተፈራረቀብን። ፌኔት በአካል ሞታለች ፤በመንፈስ አለች። እኔ በአካል አለሁ ፤በመንፈስ ሞቻለሁ። ዛሬ ለእኔም ለእሷም ስል ለቀብሯ ቤት እየሰራሁ ነው። በቁሟ ጎድቼ በበድኗ ልጠቅማት መሆኑ ነው። “ልጆቼን አደራ “...ለክፉ ሰው እንዴት ትዕዛዝ ይሆናል። ውኃው ሲወስዳት ...ለምን ተውከኝ?...ለምን ካድከኝ? ...ለምን ራስ ወዳድ ሆንክ ? ብትለኝ ምናለበት። ካልጠፋ ክፉ ቃል...መርጣ  “ልጆቼን አደራ” አለችኝ። እየገደሉት ይቅር በላቸው እንዳለው አምላኳ አደረገች። ፌኔት የሰው መለኮት ናት።
እላለሁ.... ለወደዱት ሰው ነፍስ ይሰጡታል ፤ይብላኝ እንጃ ለባለ ዕዳው! ምድር በጥፋት ውኃ እንዳትመታ ቃል አላት ፤ እግዜር የእኔን ክህደት ሲያየው ወዮላት ! መኖር ረጅም ጉዞ ...አባጣ ጎርባጣ ...አቀበት ቁልቀለት...ቀና ጠማማ...ዘብጥና ጉብስ...። ከፌኔት ጀርባ ያለው ሥውር እጅ ኗሪ ነው። የመኖር አካል መሆን፣ የሞት አባል ከመሆን አያስጥለውም። በአካል መኖርን እያታለለ፣ በመንፈስ ከሙት ጋር የዋለ ነው።
እንደ ዘማዊዋ ሴት በእንባ የማጥበው እግር ፣ ይቅር በይኝ እያልኩ የምጎትተው ቀሚስ እንዲኖር ተመኘሁ። ቀሚሱም የፌኔት ፤እግሩም የመለኮታዊቷ ሴት ቢሆን አልኩ። ለመቃብሯ ቤት ሰራሁ።
ልኖር ነው ፤ግን ሞቼ ነው። ላያስችል አይሰጥም ትሉ ይለ?..ለምን እኔን ላያስችል ሰጠኝ?..ጉድጓዴን በእጄ ምሻለሁ ፣ ለመግነዙ አልጨነቅም። ከበቀሉባት ሁለት ተክሎች አጋሙን ነቀልኩ ፤ ከመቃብሬም ራስጌ ተከልኩት። ቁልቋሉንም ነቀልኩ ፤ከመቃብሯም ራስጌ ተከልኩት። ራሴን ወደ አይመለሱበት ሸኘሁ...መቃብሬ ላይ የበቀለው አጋም ...መቃብሯ ላይ ያለውን ቁልቋል ሲወጋና ሲያስለቅስ ይኖራል። አጋሙም እኔ ፤ ቁልቋሉም እሷን ይወክላል።
አልቃሽና አስለቃሽ። ቋሚ ይማርበት ዘንድም ክፉነቴን መቃብሬ ላይ አተምኩ ፤መልካምነቷንም እንዲሁ። እላችኋላሁ ...”ልጆቼን አደራ”...


Read 11103 times