Saturday, 10 September 2022 21:02

በአዲሱ ዓመት ለአገሬና ለወገኔ የምመኘው!!

Written by  ሃና.ገ
Rate this item
(0 votes)

ባለፉት አራት ዓመታት አገራችን ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ ስትሸጋገር ነው የከረመችው፡፡ በዚህ ሂደትም ብዙ ሺዎች ተገድለዋል፤ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሃብት ንብረታቸውን አጥተዋል፤የሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂ ሆነዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በብዙ ቢሊዮን ብሮች የሚገመቱ መሠረተ ልማቶችም ወድመዋል፡፡
በተለይ በአማጺው የህወሓት ቡድን በ2013 ጥቅምት መገባደጃ ላይ የተከፈተው ጦርነት በሁለት ዙር ብዙ የህዝብ እልቂትና የንብረት ውድመት አስከትሏል፡፡ ለዚህ ነው በአማጺው ቡድንና በመንግስት መካከል ሊደረግ በሂደት ላይ የነበረው የሰላም ድርድር ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት የቆየው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አማጺው የህወሓት ቡድን ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ዳግም ለሦስተኛ ጊዜ በቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ፣ የሰላም ተስፋው ተጨናግፎ፣ ጦርነቱ ተባብሶ የቀጠለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
 በዚህም የተነሳ አዲሱን ዓመት በአሳዛኝ ሁኔታ የምንቀበለውና የምናሳልፈው በጦርነት ውስጥ ሆነን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ዘንድሮን ጨምሮ ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ በመከራና በሰቆቃ ውስጥ ለሚገኘው ኢትዮጵያዊ ወገኔና ፈተና ላልተለያት ውዲቷ አገሬ በአዲሱ ዓመት የምመኝላቸውንና ተስፋ የማደርገውን ልገልጽ እወዳለሁ - እንደ አንድ ዜጋ፡፡ እነሆ ሳይበረዝ ሳይከለስ ከሃሳቤ እንደወረደ፡-
አዲሱ ዓመት በአገራችን ጦርነትና ግጭት የሚቆምበትና ሰላምና ዕርቅ የሚወርድበት እንዲሆን ከልቤ እመኛለሁ፤ ተስፋም አደርጋለሁ!!
አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያውያን የሚገፋፉበትና የሚቃቃሩበት ሳይሆን የሚተሳሰቡበትና የሚተባበሩበት  እንዲሆን እመኛለሁ፤ ተስፋም አደርጋለሁ!!
አዲሱ ዓመት የተበደሉ የሚካሱበት- ያዘኑ እንባቸው የሚታበስበት የፍትህና ርትዕ ዘመን  እንዲሆን እመኛለሁ፤ ተስፋም አደርጋለሁ!!
አዲሱ ዓመት ለሰው ልጅ ህይወት ዋጋ የምንሰጥበት - ነጻነትና ዲሞክራሲ  የሚስፋፋበት ዘመን  እንዲሆን እመኛለሁ፤ ተስፋም አደርጋለሁ!!አዲሱ ዓመት የፖለቲካ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በምክክርና በውይይት መፍታት የምንጀምርበት ይሆን ዘንድ  እመኛለሁ፤ ተስፋም አደርጋለሁ!!
አዲሱ ዓመት በአንድ ልብና መንፈስ፣ ብልጽግናን አልመን፣ ለሥራ የምንነቃቃበትና የምንተጋበት  እንዲሆን እመኛለሁ፤ ተስፋም አደርጋለሁ!!
አዲሱ ዓመት መንግስት ሙሉ ጆሮውንና ልቡን ለህዝቡ ሰጥቶ በቅንነት  የሚያገለግልበት ዘመን  እንዲሆን እመኛለሁ፤ ተስፋም አደርጋለሁ!!
እርግጥ ነው እኒህ ሁሉ በጎ ምኞቶችና ተስፋዎች በተዓምር ብቻ እውን አይሆኑም፡፡ ከሁሉም በፊት ጥልቅ መሻትን ይጠይቃሉ፡፡ ከዚያም በትጋት መሥራትን፡፡ እኔ ደግሞ የኢትዮጵያ ዓምላክ እውን እንደሚያደርጋቸው አምናለሁ፡፡ ለዚያም ከልቤ እጸልያለሁ፡፡ እናንተም ጸልዩ፡፡
     ኢትዮጵያንና  ህዝቦቿን ፈጣሪ  ይባርክ!!



Read 1155 times