Saturday, 17 September 2022 12:53

በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት አዳዲስ ትምህርቶች ተካትተዋል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(7 votes)

     በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት አዳዲስ
የፊታችን ሰኞ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚጀመረው የዘንድሮው ዓመት ትምህርት፤ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት እንደሚተገበር ተገለጸ። በትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አመለወርቅ ህዝቅኤል እንደገለጹት፤ ሰኞ የሚጀመረው የአዲሱ ዓመት ትምህርት ከ1ኛ-8ኛ ክፍል ሙሉ ትግበራ ሲሆን፤ ከ 9ኛ-10ኛ ክፍል የሙከራ ትግበራ በተመረጡ 80 ት/ቤቶች ይጀምራል።
በተለይም ከ1ኛ-8ኛ ክፍል ያለው ትምህርት ማንኛውም ዕድሜው በዚህ ደረጃ ያለውን ትምህርት ለመማር የሚችል ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት እንዲገባ የሚያስገድድ ሲሆን ግዳጁ ወላጅ፤አሳዳጊ፤መንግስትና ማንኛውንም አካል እንደሚመለከት ሀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረገብ ፤አገር በቀል እውቀትና ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ ትምህርቶች እንደተካተቱበት የገለፁት ሀላፊዋ፤የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ትምህርት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ 7ኛ ክፍል እንደሚጀምርም ጠቁመዋል።
ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር የሚጣጣሙ የተማሪዎች መማሪያና የመምህራን  መፃሕፍት መዘጋጀታቸውንና በህትመት ሂደት ላይ ያሉም መኖራቸውን የገለፁት ሃላፊዋ መምህራንም ከሚያስተምሩባቸው መፅሀፍት ጋር ትውውቅ ማድረጋቸውንና ስልጠና መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ምን ያህል ተማሪ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሀላፊዋ ሲመልሱ፤ እንደ ሀገር የተቀመጠ ቁጥር መኖሩን በተለይ በአዲሱ የትምህርት አዋጅ መሰረት ከ1ኛ-8ኛ ክፍል ባለው ትምህርት ሁሉም ተማሪ ወደ ት/ቤት እንዲመጣ የሚያደርግ አስገዳጅ ህግ መቀመጡንና ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው የሚያስቀሩ ችግሮችን (የት/ቤት ምገባን ጨምሮ ሌሎችንም) በማሟላት ትምህርት በነፃ በማቅረብ በርካታ ተማሪ እንጠብቃለን ያሉ ሲሆን እስካሁን በርካቶች መመዝገባቸውንና ቀሪዎቹ ጥቂት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የቀድሞው ስርዓተ ትምህርት ከባድና ለተማሪ የማይመች ነው በሚል መሻሻሉን በተመለከተ ትምህርቱ ቀላል እንዲሆን መደረጉ በተማሪዎች እውቀትና ክህሎት ላይ ችግር አይፈጥርም ወይ በሚል ላነሳነውም ጥያቄ፤ “በየትኛውም ዓለም ቢሆን ሥርዓተ ትምህርት እየተሻሻለ በጥናት ያሉበት ክፍተቶች እየታዩ ከዘመኑ ጋር እንዲሄድ እየተደረገ ይቀረፃል” ያሉት ወ/ሮ አመለወርቅ፤ አሁንም የተደረገው ጥናትና ማሻሻያ የከበደውን የማቅለልና የመለወጥ ጉዳይ አይደለም ብለዋል።  ይልቁንም የቀድሞው ሥርዓተ ትምህርት ክፍተቶቹና ጉድለቶቹ ምን ምን ነበሩ የሚል ጥናት መካሄዱንና ፍኖተ ካርታው ሲዘጋጅ ከ 3.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጥናቱ መሳተፋቸውን ጠቁመው፤ በጥናቱ ከተገኙ ጉድለቶች መካከል የይዘት መታጨቅና የአግባብነት መጓደል ዋነኞቹ ሲሆኑ ሌሎች ችግሮች ተገኝቶበት መሻሻሉንና አንድ ተማሪ በትምህርት ደረጃውና ሂደቱ ማግኘት ያለበትን እውቀትና ክህሎት አግኝቶ እንዲወጣ በሚያስችለው ሁኔታ መስተካከላቸውን አብራርተዋል። በአደረጃጀት ደረጃም አዲስ ነገር መደረጉን የገለፁት ሀላፊዋ፤ ቅድመ መደበኛ፤ መደበኛ (ከ1ኛ-6ኛ) ፤ ከ 7ኛ-8ኛ (መለስተኛ) እና ከ 9ኛ-12ኛ  (ሁለተኛ ደረጃ) በሚል መደልደሉን ገልፀው በአጠቃላይ አዲሱ የትምህርት ዘመን  መልካም በሆኑ አዳዲስ አሰራሮችና አደረጃጀቶች ታጅቦ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
በጦርነቱ ከ 4ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መጎዳታቸውን የገለፁት ወ/ሮ አመለወርቅ፤ ከነዚህ መካከል 1 ሺህ 300 ያህሉ ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውንና ሙሉ ለሙሉ የወደሙት ድጋሚ የሚገነቡት የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር አጥንቶ ባቀረበው አዲሱ የኢትዮጵያ ት/ቤቶች ዲዛይን መሰረት እንደሆነ አብራርተው፣ እስካሁን በአማራና በአፋር በሚገኙ ስድስት ት/ቤቶች ላይ መሰረት ድንጋይ መጣሉንም ተናግረዋል ፡፡ እነዚህ ት/ቤቶች በዲያስፖራ ትረስት ፈንድና በሜንሽን ፎር ሜንሽን ድጋፍ ግንባታቸው መጀመሩንም ነው ሀላፊዋ ጨምረው የገለፁት።
ትምህርት ሚኒስቴር ስድስቱን ጨምሮ ሌሎች 200 ት/ቤቶችን በራሱ ለመገንባት እቅድ ይዟል ያሉት ሀላፊዋ፤ እስከዚያው ግን ተማሪዎቹ ከትምህርት ውጪ መሆን ስለሌለባቸው በሌሎች አማራጮች ወደ ት/ቤት እንዲመለሱ ከክልሎች ጋር በመነጋገር ሀላፊነት ወስደው በዚህ ላይ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ጉዳት ደርሶባቸው ነገር ግን ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት መስጠት የሚችሉትን ት/ቤቶች በሚመለከት የክልል የትምህርት ቢሮዎች ሀላፊነት ወስደው እየሰሩ ነው ብለዋል ፡፡

Read 13805 times