Saturday, 17 September 2022 12:55

ከሰላም ድርድር በፊት ህወሓት ትጥቅ መፍታት አለበት ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ታጣቂው የህወሓት ቡድን  የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ዕለት መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር በሚካሄድ የሰላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ ነኝ ማለቱን ተከትሎ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከማንኛውም የሰላም ድርድር በፊት ቡድኑ ትጥቅ መፍታት እንዳለበት አቋማቸውን ገልፀዋል።
“ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሚችለው የኢትዮጵያ ሉአላዊነት በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ ሊሆን ይገባል” ሲል በመግለጫው ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ “ህወሓት ለሰላማዊ ድርድር ተስማምቻለሁ ብሎ ጥያቄ ማቅረቡ መጥፎ ባይሆንም፣ በተለመደ ባህሪው የሰላም ድርድሩን እንደ ጊዜ መግዣ ወስዶ ጥቃት ለመክፈትና ለጥፋት ዝግጅት እንዳይጠቀምበት እንሰጋለን” ብሏል። መንግስትና ህዝብ ይህንኑ በመረዳት አስፈላጊውን ዝግጅትና ጥንቃቄ እንዲያደርጉም በአፅንኦት አሳስቧል- ኢዜማ። “ከዚህ በኋላ በአማራና አፋር ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ከዛሬ ነገ ጥቃት ደረሰብን፣ ንብረታችን ተዘረፈ፣ ሰላማችን ደፈረሰ፣” ልጆቻችን ተደፈሩ፣ ተቋሞቻችን ሊፈራርሱ ነው እያሉ በስጋት ውስጥ እንዳይኖሩ ሀገራችንም የሉአላዊነትና የህልውና ስጋት ተጋርጦባት እንዳትቀጥል በየትም ቦታ በህወሓት የሚመራ ምንም ዓይነት የታጠቀ ሃይል አለመኖር እጅግ ወሳኝ ተግባር መሆኑን በአጽንኦት ለማሳሰብ እንወዳለን።” ብሏል- ፓርቲው።
ማንኛውም የሰላም ውይይትና ድርድርና ቢኖር እንኳን የሃገር ህልውና አደጋ ላይ በወደቀ ቁጥር ከፊት ተሰልፎ የሃገርን ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የሚዋደቀውን ሃይል ለሁለተኛ ዙር መስዋዕትነት በማይዳርገው መልኩ መከወን ይገባዋል ያለው ኢዜማ፤ “ይህ ሊረጋገጥ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ በህወሓት የሚታዘዝ ምንም ዓይነት የታጠቀ ሃይል በየትም ቦታ እንዳይኖር በማድረግ ብቻ ነው” ብሏል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ፤ ህወሓት ድርድርና ሰላማዊ የግጭት መፍቻ አማራጮችን በድጋሚ የጦርነት ማራመጃና የሽብር ማሳለጫ መሳሪያ አድርጎ እንዲጠቀም ሊፈቀድለት አይገባም ብሏል- በመግለጫው።
አለመግባባቶች ሁሉ በሰላም መፈታት አለባቸው የሚል ፅኑ አቋም እንዳለው የጠቆመው አብን፤ ነገር ግን “ህወሓት የድርድርና የሰላም አማራጮችን የጦርነት ማራመጃና የሽብር ማሳለጫ መሳሪያ  የሚያደርግበትን አግባብ በፅኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።
“የኢትዮጵያና የመላው ኢትዮጵያውያንን ዘላቂ ሰላም፣ ጥቅምና ህልውና ማረጋገጥ የሚቻለው የሽብር ቡድኑ ህልውና የሚከስምበትን የጦር፣ የኮሙኒኬሽን፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ስልቶች በተሟላ ሁኔታ ስራ ላይ በማዋል ብቻ ነው” የሚል እምነት እንዳለውም አብን አስታውቋል።
“የፌደራሉ መንግስት ከሽብር ቡድኑ ህወሓት ጋር ሰላም ለማውረድ በሚያደርገው ጥረት፣ የሽብር ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ከማስፈታት ያነሰ ግብ እንዳይዝና የሽብር ቡድኑን ህልውና ለማክሰም የሚያስችሉ ሁሉንም አማራጮች አሟጦ እንዲጠቀም” አሳስቧል- አብን በመግለጫው።
በሌላ በኩል በጉዳዩ ዙሪያ የጀርመን የአማርኛ ድምፅ ዶቸ ቬሌ ያነጋገራቸው አንድ የአማራ ብልፅግና ከፍተኛ አመራር በሰጡት አስተያየት፤ ከሁሉ በፊት በሽብርተኝነት የተፈረጁት ሁሉ እጃቸውን ለመንግስት መስጠት አለባቸው ብለዋል።የጀርመን ድምጽ ካነጋገራቸው የአማራ የክልል ነዋሪዎች አንዱ፣ ህወሓት ለሰላም ድርድር ሲለመን፣ አፍሪካ ህብረትን እንደማያምንና እነ አሜሪካንና እንግሊዝ እንዲደራድር እንደሚፈልግ ሲገልጽ መቆየቱን አስታውሰው፤ ድርድር የሚካሄድ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ለህግ መቅረብ አለባቸው፤ ትጥቅም መውረድ አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።


Read 12549 times