Saturday, 17 September 2022 13:04

‘አሮጌ’ ዓመት እና ‘አሮጌ’ ሀሳብ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ እንኳን አደረስከኝ፣ እንኳን አደረስከን!
አንድዬ፡- ከየት ወደየት ነው ያደረስኳችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡- እንዴ አንድዬ!
አንድዬ፡- ጥያቄዬን መልስልኛ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ አሮጌ የሚባል ዓመት አለ እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አን...አንድዬ...
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ ጭራሽ አንደበትህ እየተዘጋ መጣ እንዴ! እኔ እኮ አሮጌው የሚባል ዓመት ምን አይነት እንደሆነ ስላልገባኝ ነው የምጠይቅህ፡፡ ነው ወይስ መጠየቅ የለብኝም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ እንደሱ አላልኩም!
አንድዬ፡- ታዲያ መልስልኛ፡፡ አሮጌ ዓመት የሚባለው ምን አይነቱ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡- በቃ ያለፈ ነዋ አንድዬ! ማለቴ ያለፈ አገልግሎቱ ያበቃ ዓመት ማለት ነዋ፡፡
አንድዬ፡- አገልግሎቱ ያበቃ ያልካትን አባባል ወድጄልሀለሁ፡፡ አገልግሎቱ ያበቃ ማለት በቃ የማይጠቅም አሽቀንጥረህ የምትወረውረው ለማለት ነው፡፡ አይደል፣ ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪን ሀበሻ፡- እ..እንደዛ ነገር ነው አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- አሁን መጣህልኝ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ ስለዚህ አሮጌው ዓመት ከህይወታችሁ ወጥቷል ማለት ነው፡፡ ማለትም አሮጌ ልብስ ከተጣለ ተጣለ ነው፡፡ አሮጌ ዓመት ደግሞ ከተጣለ ተጣለ ማለቴ ነው፡፡ አጠፋሁ እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡- ኸረ በጭራሽ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ለምሳሌ አንተ አሮጌ ሱሪ ኖሮህ አገልግሎቱ አበቃ ብለህ ስትጥለው መልሰህ ስለሱሪው አታስብም አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡- በጭራሽ አንድዬ፣ በጭራሽ!
አንድዬ፡- እንደዛ ከሆነ እናንተ ሰዎች ከስንትና ስንት ዓመት በፊት አሮጌ ብላችሁ የጣላችሁትን ዓመት እንደገና እያነሳችሁ ካልተናነቅን የምትባባሉት ለምን እንደሆነ እስቲ ንገረኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ለምን እዋሻለሁ እኔ በእሱ መልክ አስቤው አላውቅም፡፡
አንድዬ፡- ግን አሮጌ ያላችሁትን ዓመት አሽቀንጥረን ጥለነዋል ያላችሁትን ዓመት እያነሳችሁ በእሱ መተናነቃችሁን ታምንልኛለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አዎን አንድዬ፣ በደንብ ነው የማምነው፡፡
አንድዬ፡- ስለዚህ ዓመት አለፈ ይባላል አንጂ አሮጌ አይባልም አይደል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አ... አዎን አንድዬ፡፡ አሁን እየገባኝ ነው፡፡
አንድዬ፡- አየህ ምስኪን ሀበሻ፣ አሁን የተናገርከው እኔን ላስደስት ብለህ ነው እንጂ አምነህበት አይደለም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ኸረ አምኜበት ነው አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ተው፣ ተው ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ ግዴለም እኔ አልቀየምህም፡፡ አንተን ተቀየምኩ ማለት እኮ አብዛኛውን ሰው ተቀየምኩ ማለት ይሆናል፡፡ ለምን ብለህ ጠይቀኛ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ለምን አንድዬ?
አንድዬ፡- ምክንያቱም በጣም ብዙ ሰው የሚያደርገውና የሚናገረው የሚያምንበትን ሳይሆን ሌላውን ለማስደሰት ብሎ ነው፡፡ ግን እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ጠይቀኝ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- እንደው አሮጌ ሀሳብ የሚባል ነገር ሊኖር እንደሚችል አስባችሁ ታውቃላችሁ፡፡ 
ምስኪን ሀበሻ፡- እንዴታ አንድዬ እንዴታ! እንደውም ወደ ኋላ ጎትቶ ያስቀረን እኮ አሮጌ ሀሳብ ነው፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ እንዲህ ግልጽ ሲሆን እኔንም ቀለል ይለኛል፡፡ አለበለዛ ወደ ምድር ስትመለስ የሆኑት ሰዎችን ሰብስበህ ውግዘት፣ መግለጫ ልታወጣብኝ ትችላለህ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ ኸረ...
አንድዬ፡- ግዴለም ለቀልድ ያህል ነው፡፡ ግን ምስኪኑ ሀበሻ ውግዘትና መግለጫ እንደምትወዱ አትክደኝም፡፡ አይደል አንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡- እ...እሱማ አንድዬ....
አንድዬ፡- ተመልሶልኛል፡፡ እና ምስኪኑ ሀበሻ በደንብ አስረዳኛ፡፡ አሮጌ ሀሳብ የምትሉት ምን አይነቱን ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡- በቃ ያለፈውን ነዋ፣ አንድዬ፡፡ ይሄ አንዳንዶች ማንሳት የማይሰለቻቸው የትናንት፣ የትናንት ወዲያ ነገሮች ማለት፡፡
አንድዬ፡- ስለዚህ ሀሳብ አሮጌ የሚያሰኘው በዋነኛነት የትናንት የትናንት ወዲያ መሆኑ ነዋ! ልክ ነኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ እኛ እኮ አዲስ ሀሳብ ለመፍጠር ስንታትር የአሮጌውን ዘመን ያለፈበት ሀሳብ እያመጡብን ነው የተቸገርነው፡፡
አንድዬ፡- የሌላውን ስትገለብጡ እንጂ አዲስ ነገር ለመፍጠር ይህን ያህል ስትታትሩ ባላይም አባባልህ ክፋት የለውም፡፡ ግን ምስኪኑ ሀበሻ ማውራት ሌላ መሥራት ሌላ መሆኑን ታምንልኛለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- በደንብ እንጂ አንድዬ፣ በደንብ እንጂ!
አንድዬ፡- ጎሽ ዛሬ ሁሉን ነገር እያመንክልኝ አስደስተኸኛል፡፡ ሌላ ጥያቄ ባስከትል ነዘነዘኝ አትለኝም አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡- ምን ቆርጦኝ አንድዬ! እንደውም በጣም ደስ ይለኛል፡፡
አንድዬ፡- ይሄ መዳፋችሁን እያጋጫችሁ ይመችህ፣ ይመችሽ እንደምትባባሉት እኔንም ይመችህ በለኛ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ...
አንድዬ፡- እሺ ምስኪኑ ሀበሻ፣ አሁን ላሊበላ፣ አክሱም የመሳሰሉት ሁሉ የምትኮሩባቸው ቅርሶች ናቸው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ትክክል አንድዬ፡፡ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንሄድባቸው መኩሪያዎቻችን ናቸው፡፡
አንድዬ፡- ግን እኮ ምስኪኑ ሀበሻ እየኮራችሁ ያላችሁት በትናንት አሮጌ አእምሮዎች የተፈጠሩ የአሮጌ ሀሳቦች ውጤቶች ነው፡፡ እየሰማኸኝ ነው ምስኪኑ ሀበሻ? ቅርሶቹን የፈጠሩት እኮ የትናንት ወዲያ አእምሮዎች ናቸው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- እሱማ ልክ ነው አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- አሁን ደግሞ ብዙዎቻችሁ ወደ ቀድሞ ማንነታችን መመለስ አለብን የምትሉት ነገር አላችሁ...
ምስኪን ሀበሻ፡- ሁላችንም ባንሆን...አዎ አንድዬ..
አንድዬ፡- ግዴለም፣ ብዛታችሁ አያጨቃጭቅም፡፡ ወደ ቀድሞ ማንነታችን ማለት ወደ ትናንት ሀሳቦች መመለስ ማለት አይመስልህም?
ምስኪን ሀበሻ፡- እ..እ...
አንድዬ፡- ግራ አጋባሁህ አይደል! ግዴለም አትመልስልኝ፡፡ ግን ትናንትናንና ከትናንት ወዲያን አሮጌ ብላችሁ ዛሬ አንዲት አዲስ ነገር መፍጠር ሳትችሉ፤ ፈረንጅን መኮረጅ ስልጣኔ እየመሰላችሁ ከእከሌ ልምድ፣ ከእክሌ ተሞክሮ እያላችሁ በየመድረኩ ስትዘባነኑ የትናንትናና የከትናንት ወዲያ ሀሳቦችን አሮጌ ለማለት የትኛው የሞራል ከፍታ አላችሁና ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡- አን...አንድዬ ይህን ያህል አስቆጣንህ እንዴ!
አንድዬ፡- መቆጣቴ አይደለም፡፡ ግን ግብዝነታችሁ ማለቂያ አጣ፡፡ እናንተ ገና አንዲት ወንዝ የምታሻግር ሀሳብ ሳትፈጥሩ የቀድሞዎቹን መሳደብ፣ መራገም፣ ማንቋሸሽ...ብቻ ተወው ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ ግን ይሄ አሮጌ ዓመት የምትሉትን ነገር እስቲ አስቡበት፡፡ ምናልባት አሮጌ ያላችሁት ዓመት ውስጥ ገና ጫፉን ያልነካችሁት አዳዲስ ሀሳብ የሚያየው አጥቶ ተከማችቶ ሊሆን ይችላል፡፡ በል በሰላም ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 1280 times