Saturday, 17 September 2022 13:05

“አሁንም አይደል ወደ ማታ...”

Written by  (ዳሰሳ) -በድረስ ጋሹ-
Rate this item
(4 votes)

 የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን መጽሐፍ እንካ  ብላ፤ ሂደህም ለሰው ልጆች ሁሉ ተናገር |ህዝ ፫:፩| እንዲለን እንደሰማንም...
ዮናኒ፣ ቅብጢ አልያም ጳርቴ ያልሆነ ...አማርኛ እንጅ!  ከሰው መርጦ ለሹመት ፣ከእንጨት መርጦ ለታቦት ፤ከቃልም መርጦ ለጽሕፈት ልንለው የምንችለው ዓይነት (“አሁንም አይደል ወደ ማታ”...) የሚል መጽሐፍ አሁን ቅርብ ከሔኖክ ደመቀ ደርሶናል። 139 የገፅ ብዛት ያለው መጽሐፉ ሁለት ዘውጎችን እንደ አምድ ተጠቀሟል -_ግጥሞችንና አጫጭር ታሪኮችን! የዘውጎች መቀላቀል በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ይፈቀዳል ወይ ቢሉ የግል ዕይታዬን ከመሰንዘር አልቆጠብም። የመጽሐፉን ርእስ ብዘነጋም በአገራችን ዘውግ የተቀላቀለበት መጽሐፍ አንብቤ አውቃለሁ። ወደ ውጭ ጎራ ያልን እንደሆነ haibun (ፕሮስ እና ሃይኩን የሚያጣመር ከጃፓን የተገኘ ፕሮሲሜትሪክ ጽሑፋዊ ቅርጽ ነው)። John Ronald Reuel Tolkien (J.R.R Tolkien እንግሊዛዊ ጸሐፊ፣ ገጣሚ፣ ፊሎሎጂስት፣ የከፍተኛ ምናባዊ ስራዎች ደራሲ በመባል የሚታወቀው በ The Hobbit እና The Lord of the Ring በተባሉ ድርሰቶቹ ውስጥ ግጥምን ስንግ ሲያደርጋት ይስተዋላል። John Winslow Irving አሜሪካዊ-ካናዳዊ ደራሲ፣ አጭር ልቦለድ ጸሐፊ እና የስክሪፕት ጸሐፊ ሲሆን በ The World According to Garp በተሰኘው አራተኛ ልብ -ወለዱ ውስጥ አጫጭር ታሪኮችን አካቷል። ወዲያም እልፍ ያልን እንደሆነ fantasy and paranormal romance author የሆነችው Larissa Hinton በ Everblossom መጽሐፏ በአበባ የሕይወት ዑደት ማለትም [bud, blossom, and seed _ቡቃያ ፣አበባ እና ዘር ] መሪ ሃሳብ ዙሪያ የተደራጁ የግጥምና የአጫጭር ልቦለዶች ታሪክ(አንቶሎጂ) ጀባ ብላናለች። ከብዙ በጥቂቱ ለመጠቆም የፈቀድኩት የሔኖክ ደመቀ መጽሐፍ ዘውግ ማቀላቀሉ ለእኔ (በግሌ) ችግር እንዳልፈጠረብኝና የተለመደም የነበረም መሆኑንን ለመጠቆም ነው።
መጽሐፉ  እና  5E’s
Excitement
(The way the person first becomes aware of and is attracted to the experience.)
አሁንም አይደል ወደ ማታ...ቀልቤን የሳበው መጽሐፍ ነው። ይህ እንዲሆንም ምክንያት ነበረው። የፀሐፊውን ቀዳሚ ሥራዎች የማንበብ ዕድሉን ከማግኘቴ በላይ መጽሐፉ የመጣበት ልዩ ቅርጽ ነው። በግጥምና በአጫጭር ታሪኮች (በአንቶሎጂ መልክ) የመዋቀሩ ጉዳይ ስቦኛል። ወረቀቶችን ገልበጥ ባደረግኩ ቁጥር ልዩ ነገር አያለሁ። ፓስት ካርድ ስቶሪዎች፣ አጫጭር ታሪኮች ( 3500-7500 ቃላት ) እና ጥቂቶችም በፍላሽ ፊክሽን (53-1000 ቃለት) አልፎም ደግሞ ሐሳቡ  በግጥም ረድፍ የተሰደሩ መሆናቸው ደስታን ፈጥሮልኛል። ደስታዬም ወደ መግባት ....
    2.   ENTRY
               (Entering into the experience,  crossing from one context to another)
   በድርብ ቃል የተመሰረቱ መክስተ-አርዕስቶቹ የሚተው አይመስሉም። በበዛብህ ልሳን ‘ዝ ጽሑፉ ከመ ወይን ጣዕሙ ‘እያሉ የሚያስቀጥሉት ...ከፍላሹ አልያም ከአጭር ታሪኩ አልፎ ስለሚገኘው የሚጓጉለት ነገር እንዲኖር በወፍ በረር ቃኝቼ ላነበው አመንኩ። ያመነ ያነበበ እንዲድን...
ሌሊሳ ግርም ‘ምሥጋናዬን ሰጥቼ ያልቅብኛል ብዬ አልፈራም። የሚያስፈራኝ የምሥጋናዬን ስሞች አሰልፌ መዘርዘር ጀምሬ፤ መጨረስ እንዳያቅተኝ ነው። ደግሞስ ምሥጋና የሚገባው ሁሉ እኔ እስክሰጠው ለምን ይጠብቃል ራሱ ይውሰድ እንጅ’ ይላል- በ የንፋስ ሕልም መጽሐፉ። ወደ አሁንም አይደል ወደ ማታ መጥቼ የሔኖክ  ምሥጋና በሥም ዝርዝር ሲዳረስ ባየው... የጃርስእዎዬን እና የወዳጆቼንም  ሥም ባገኝ፣ የወንድም ጌታ አባት ባሴንም ሥጦታ ደርሶት ብመለከት...ወደ ውስጥ እንድገባ ፈቀድኩ ...(ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል ይሉትን ብሂል እዚህ ሻርኩት። ሳየው ያምራል ስበላው እንዴት ይሆን በማለት ወደ ዝንቅ ዛንታ...
   3. ENGAGEMENT
       ( The main activities that capture the attention of the participant. )
ከመ ያርእዮሙ ብርሃኖ ለእለ ይነብሩ ውስተ ጽልመት ወጽላሎት ሞት ከመ ይርትዕ እገሪነ ውስተ ፍኖተ ሰላም። [ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል። የሚለውን  |የሉቃስ 1:79| ለአሁንም አይደል ወደ ማታ... መስጠት ቢያምረኝ ይቻለኛልን?]
ጀመርኩ....
፩.በዝንቅ ዛንታ:
ወሊሱ ሐምሌ፣ከዓመት ዓመት ይፀፀትበትን፣ በስሙም ይጠራበትን ‘እኝ እኝ’...አይድኔው በማይ መሞቱን፣ በአቧራ የተሸፈነው ድንጋይ በዝናብ መጥራቱን፣ ድንጋዩም መልሶ አቧራን መናፈቁን...ሁሉም አጥፊውን እንዲወድ ይፈረድበትን ...።
ወዛደሩ በወባ ወረርሽኝ ስላጣት ተራዲኢ...ትለይበቱን ቁንዲ፣ ገባሪም ተገባሪም ስለመሆኗ፣ ስለአሚናይቱ-ስለ ክፉ ህልሙም፣ እርስትን ሲል ትንሽ ወንድሙ የጎድን ስለጣለበት ‘የሥጠኝ ሐሳብ’...እሱም ስለመተው፣ ሲረገጥ አሜን ፣ሲገፋ በጄ ብሎ ስለመኖሩ፣ የተከፋ ተደፋን፣  ቅብዝብዙ ሰብዕ ሲያልፍ መሬት በእቅፏ  ስለመያዟ...ስለ ትኅትነዋ፣ ከምሥጋናም ከፍ ያለ_አኮቴት ስለመቸሯ...
፪.በግርድፍ ስልጠት
ሌላው ፍጡር _የምናቡ! ወዛደርም የሆነው  _ለሚወዳቱ፣ ለልብስ ተኳሽቷ፣ ስለ ሥራው ተማሮ ስለሚያወራቷ፣ ስለምትሰማውም ሴት፣ ስለምትመክረው፣ አይዞህታዋን ስለምትቸረውም አይተን...።
እንዲሁም ለማይቀናው ጉብጠትን ሊነግሩት፣ ለማይስተካከል መዛነፉን ሊያወሱት ይገባል ባይ መነሳቱ፣ ሊደምቁበት ሲሰጥ ምልዑነት ከእግዜር መቅረቷን መሳቱ፣ በዚህም ዘውዴ ብሎ የሚመካባት_ወዛደሩ መሳቱ፣ ለዓመጽ መጣደፉን፣ ወደ እምቢተኝነት መጉረፉን...ዘውዱን በጥይት ሲያጣ፣ የሸክም ሁሉ ልቻልህ ባዩ_ፍጡር..መንቃቱን ...።
... “ጸጸት አይወረስም። ባልሰራችሁት የምታዝኑበት ሳይሆን፤ ካልሰራችሁት የምትማሩበት ይሁን” እንዲል ባይሮን ፑልሲፈር
፫.በብካዬ ዳታ
ልጆቹን አሰቃቂ፣ ሚስቱን አስበርጋጊ ስለሆነ _ወታደር፣ ሐሳቧን ልትደመጥ ስለምትሻ ልጃቸው፣ ወደ መምህሯም ሄዳ የሚሰማትን ስለምታወረዋ የልጅ አዋቂ አይተን...
በእጅ ያለ ወርቅ ከመዳብ መቅለሉን፣ የነገሮችን መክበድ ስንርቅ ማወቃችንን፣ እዝን ለቸገራት ባለ ድምጽ ...ሰሚ ያጣችዋን ህጻን ...አፈጣጠሟ ሞት ስለሆነችው...ስለዛች እንቁ ልጅ ይዘክራል።
“ያጣነው እንደምናጣው ፍፁም እንኳን ለቅጽበት ዕድሜ በስጋት ያላሰብነውን ነው...ነፃነታችንንም እንዲሁ”
፬.አሁንም አይደል ወደ ማታ...
በጠጀ ሳር ንዑስ ክፍል በፊታውራሪዎች ዘንድ ስለ ተፈጠረ አለመግባባት፣ አለመግባባትም ስለ አመጣው መዘዝ፣ ጥቋቁር ፍየሎች ስለሚመሰልባቸው ንግርት ..
በጡንጁት ንዑስ ክፍል ኗሪ ሁሉ በበዳዩ ፍላጻ የቀረለትን የበዳይነቱን እውነትነት ማመሳከሪያ ጠባሳውን የሸፈነ እንደሆን፣ድንገት የለሌው መኖር እንደሌለ፣ የሆነው ሁሉም የታሰበ እንዳልነበረ..ይቅርታውን ይቅር ስላለችዋ ብርቅ ሴት፣ ሰው መቅረብም ስለምትፈረዋ...ወጣትነትን መኖር ስለ ፀፀት የመጎናበስ ዝግጅት እንዳለው...
በጦስኝ ንዑስ ክፍል በጓደኞቿ ግፊት ተደፍራ ድርብ ልጅነትን ስለያዘች እናቱ፣ ሴቶችን እንዲሸሽ ሰበብ ስለማግኘቱ፣ ሕይወትም ብክንና ስለመሆኗ፤ብክንናም ማሰብን ተንተርሶ ስለመምጣቱ...።
፭.በፍዝ ይባቤ
‘አስበ..ሲያስብ..አሰባት’ ይለው ቃል አለው። በአንሶላ በብርድ ልብሱ፣ በአልጋ በትራሱ ስለታተመችዋ ውቡ፣ የሕይወት እንዲህ ኑሩኝ ብሂል፣ ቅፅበታትን በዘላለም የመቀበልን ልምድ፣ በጥበቃ ስርቻ ውስጥ ራሱን የደበቀ ሰው እንደሚታይ ..
፮.በድኩም ሁነት
ጆሮዎች አሉታን የሰሙ እንደሁ፣ ሴቷ የባሏን ጓደኛ ሰምታ እንደሁ፣ የሰማችው ጥርጣሬ ሆኖም እንደሁ፣ ባሏም ጓደኛዋን (ጓደኛቸውን) ጠርጥሮት እንደሁ፣ ፍቅርም እንዲሁ ጥርጣሬ ነክቶት እንደሁ...ንፋስ የገባው ገለባ ይሆን ዘንድ እንዴት አይችል...ማመን ያለብህን ሳታምን ስትቀር፣ ያመንከው እንደሚያስትህ ልብ ያላልክ እንደሆን፣ ጥርጣሬ ወደ እውነት የሚያስኬድ እንጅ ራሱ እውነት እንዳልሆነ ያልተረዳህ እንደሆን፣ መጮህ እየዳዳህ በአቅም እጥረት እንዳትችል መሆንህን...።
፯.በሥሙር ራሮት
ሰው ከዓይን እርግብግብታም በላይ፣ ከእርምጃውም ብዛት በላይ በደልን መፈጸሙን ሲታዘብ፣ እንደ ገበቴ ውኃን...ሲሄድ ሲከተላትን ሲያደምጥ _ግንበኛው! የፈለጠውም ድንጋይ ሲፈናጠር፣ ፍንጣሪው የማታውቀውን ስትጠብቅ በኖረችዋ እግር ባት ሲገባ፣ ከአይዞሽ እስከ ጥየቃም ሲከታተላት፣ ስትድንም፣ ሲግባቡም _ሲጋቡም!
፰.በግሱስ ዝማሜ
የአበባን ከፀሐይ ጋር መቃጠር ልብ ይል ዘንድ ስላልታደለው ግሱስ፣ የቀን ዘባተሎውን ስለሚረሳባት ገነቱ ፣...በትዝታ ስለተሞላ አፍቃሪ፣ ዛሬን በበድኑ ትናንትን በመንፈስ ኗሪ ስለሆነውም ...ሁለት ልብ ስለጎደላት ከተማ ፣ይኼ ደንታቸው ሳይሆን ስለሚያረግዱት ዝማሜ፣ ቦታ ይሰጡት ዘንድ እጁን ስለሚዘረጋ ተማጻኝ...ገነቱን_የልቡን መርጋት ስለሚናፍቀውም...
፱.አንድ አንዳንዶች..
የመተላለፍ ወይም የመተጣጣት ልምዷን ስለአካበተችዋ ሕይወት፣ ከፍታዋን እንጅ እውነቷን ስላልተረዳት የጎማ ሲሳይ ፍቅሩ፣ ያለው አልነበረው  የነበረውም እንደሌለው የሚያሳስበው ቀን፣ በአንድ እሱ ስለተተውት አንዳንዶች ፣ ከአንዳንዶችም አንዷ ፍቅሩ ስለመሆኗ _የመቸንከሩ ምክንያት፣ ከአንድ እሱም ከአንዳንዶችም መሐል ጉድለት መኖሩን ልብ እንዳለ፣ በትዝታ ስለከበደችው ሴት፣ ሞት ቢገድላትም እንኳ ትዝታን ሊነፍገው ባለመቻሉ አቅም እንደሌለው የለፈፈበት...
፲.በገፀ-እርታታ
ከደረሱበት ሁሉ ጥበቃ እንዳለ፣ በመድረስ እሰየሁ ሲሉ በማጣት የመረታትን ኃይል ስለማጤን፣ የሳቅን መልክ የሞትን ድምፅ ስለሚያስበው ስለእሱ፣ ከኮርኔስ ከጣሪያው ምሥሏን ስለሚያየው፣ ፍቅሩን ሲነጥቀው ዝም ስላለው ...ዝምታውን አምላኩ የተቀየመው ስለመሰለው፣ ውጉዝ ከመ አርዮስን ስለሚለምነው...
፲፩. በክህደት ክብ
ከፀሐፊነት ወደ ልቡ ስለተጠራችዋ ሴት፣ መካድ የልብን እውነት የሚያዛምድበት እውነት ስለመኖሩ፣ በክህደት ስለሚናጥ ሰብዕ፣ በሕይወት ሊክዷቸው ስለሚገቡ ነገሮች ይደረድሩበት ስለተተወ የክህደት ክብ ...
፲፪. በመወደቅ ዝና
ስም ስላተጋው ዝና፣ በዝንጋታ ሽንቁር መሐል ስለምትገባ ስንፍና፣ ከዝነኝነት ጋር ስለምትመጣዋም ድካም፣ ዝቅ ካለ ጋር ዝቅ ማለትን፣ ስለወደቀው አላዛዐር በጌታው ስለመነሳቱም፣ የዝናም ኸሉ ዝና የሰው ልብ ውስጥ በመልካም ስብዕና መርመስመስን መምረጥን፣ ወደ ልብ መውደቅን ከዋጋ ሁሉ ዋጋ ማድረግን ...

...ሌሎች ሌሎችንም ...
 EXIT
      ( The clear end of the designed experience .)
ጥበበ ንነግሮሙ ለጠቢባን |ለጥበበኞች ጥበብን እንነግራቸዋለን እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ | የቻልኩትን ነግሬ...ያልቻልኩትን ለሚችሉት ትቻለሁ...
ተደስተን እንደገባን፣ ገብተንም እንደቀሰምን አንቀርም። የወጣው አይገባም፤ የገባውም አይወጣም የሚለን የለም። እንዲሁ ወደ ሕይወት ይመጡትን ሸክፈን እንወጣ ዘንድ ግድ ይለናል። እኔ እፍታዬን በፎርሙላይክ መልክ ስለተዋቀረው የግጥም ገፁ አነሳለሁ። እረስቼዋለሁ እንኳ ስል...እንደረሳሁሽ ልነግርሽ እያሰብኩሽም አይደል? እንዲል ሔኖክ። ጨርሻለሁ እንኳ ብላችሁ ስለመጽሐፉ እያሰብኩም አይደል? ...ለዚህም መጽሐፍ አይረሳም። በግጥም ገፀቹ ውብ የሚባሉ አሉ። ቀልቤን የልብ ወለዶቹ ለዛ መስረቃቸው...ግጥሙ ላይ ፍላጎቴ እንዲቀንስ መገደዴን ግን አልክድም።
 EXTENTION
( A physical or digital object that the participant can take wit them to ‘extend’ the experience. )
ይህን መጽሐፍ አስታውሰው ዘንድ ፣ሌላም ጊዜ እመለስበት ዘንድ ልዩ ነገሮችን ሸክፊያለሁ። የሐሳብ ቅፍለት ፊተኛ ቢሆንም ኋለኛውን ሳረዳው ሸብረክ እንዲል አምናለሁ። ስለ መለየት፣ ስለ ሞት፣ ስለ በደል፣ ስለ ጸጸት፣ ስለ ጥበቃ፣ ስለ ተማጽኖ ፣ ስለ ጥርጣሬ፣ ስለ ትዕቢት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሕይወት፣ ብዙ ‘ስለ’ዎች እንዳይረሱ በልቤ ጽላት ላይ ታትመዋል። እንድናደንቅ ብቻ ሳይሆን እንድንረግምም ማስታወስን ቸሮናል ...።
በExcitement የሰርግ ጥሪ ወረቀት እንደደረሰው ሰው፣ የጥሪ ጽሑፉን ጌጥ ገና አይተው እንደሚደሰቱት ሆንኩ፣ በENTRY ሽክ ብለው ለብሰው ወደ ሰርግ እንደሚሄዱት፣ በር ላይ ቆመው የውስጡን ድባብ እንደሚቃኙትም የምሥጋና በር እና መክስተ-አርዕስት  ላይ ተበገርኩ፣ በ ENGAGEMEN ወደ ሰርጉ ገብተው እንደሚደሰቱት፣ እንደሚጨፍሩትም ወደ ጽሑፉ ገብቼ ከሐሳቦቹ ጋር ተጫወትኩ _የልቤን አወጋሁት፣ በ EXIT ሰርጉ ሲያልቅ ደህና ሰንብቱ እንደሚሉት፣ የገቡትም እንደሚወጡት፣ በምርቃት ጉበኑን እንደሚሻገሩትም በ’አልረሳውም’ ቃሌ ወጣሁ፣ በ EXTENTION የሰርጉ ትርዒቶች በዓይነ ህሊና እንደሚመጡ፣ ሁሉም ነገር ትዝ እንደሚል እኔም ስለመጽሐፉ እንደዛ አደረገኝ።
በመጨረሻም  ...አሰብኩ ..እያሰብኩ ...አሰብኩት...
ይህ መጽሐፍ በሕይወት ዑደት ውስጥ  እንደ ቡቃያ፣ እንደ አበባ እንደ ዘርም ይሆንበት ያልተራደፈ ጊዜ አለው። በተለያዩ ሐሳቦች ዙሪያ የተደራጁ የግጥምና የአጫጭር ልቦለዶች ታሪክ ነው።  ጠንካራ የቅዠት፣ የፓራኖርማል እንዲሁም አንዳንድ የፍቅር አካላት አሉት። ከደራሲያን መጽሐፍት (አንዳንዶቹ ቀደም ብለው የታተሙ እና አንዳንዶቹ ያልታተሙ) የገጸ-ባሕሪያት ገጽታም አሉ።የዚህን አንቶሎጂ አጫጭር ልቦለዶች ስንመለከት፣ እነዚህ ታሪኮች እጅግ በጣም አጭር መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል። አጭር ልብ-ወለድ ሰናነብ በውስጡ ያሉትን ነገሮች (Plot,Characterization ,Theme, Setting, Point of veiw) ልንፈልግ እንችላለን። እነዚህ ታሪኮች እኛ የምንፈልጋቸውን ነገሮች በሙሉ እንዳይኖራቸው ያዘነብላሉ።
እያንዳንዱ ታሪክ ማለት ይቻላል ትኩረት የሚስብ ነው። የበለጠ እንድፈልግ ይተወናል። እስከ ፲ ያሉት አርዕስት በተለይ በጥሩ ሁኔታ የተፃፉ እና የተወለወለ ስሜት ሆኖ ይሰማል። ገፀ-ባህሪያቱ መድረኩ ላይ ሲያንቀሳቅሱ፣ ገፀ ባህሪያቱ ራሳቸው ከመንቀሳቀስ ይልቅ ተገደው ተሰምቷቸው ነበር። ብዙ ታሪኩን እንዲፈልግ ሊያደርጋቸው ይችላል። ፀሐፊው ትኩረት የሚስቡ ዓለሞችን፣ ገፀ-ባህሪያትን እና ሁኔታዎችን የመገንባት  ችሎታ እንዳለው ማመላከት አስፈላጊ ነው።
አሁንም አይደል ወደ ማታ...የግጥም እና የስድ ንባብ ድብልቅ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ለስላሳ ፍሰት አጥቼበታለሁ ። አንቶሎጂ  ሲታሰብ ፍሰት ዋና እንደሆነ ይሰማኛል። ላሪሳ መጽሐፏን ስታዋቅር ቡቃያ፣አበባ እና ዘርን የዕድገት ደረጃዎች መምረጧ ለፍሰት ነው። የሶፊያ ታኩር የመጀመሪያ ታሪክ የግጥም መድብል|  Somebody Give This Heart a Pen| ከስልታቸው፣ ከርዝመታቸው ወይም ከጭብጣቸው አንፃር ሁሉም ልዩ የሆኑ የግጥም መድብል ነው። ክምችቱ በአራት ክፍሎች የተከፈለ ነው፡ ‘አደግ (grow)’ ፣ ‘ቆየት (wait)’፣ ‘ሰበር (break)’ እና ‘እንደገና እደግ (grow again)’ በሚል  መዛግብት መገንባቷ ፍሰቱን ለማስጠበቅ ነው።
አሁንም አይደል ወደመታ ህመም ላይ የተራቀቀ ጽሑፍ (ምጥ) እንደሆነ ይሰማኛል። ኀዘንን ተላብሶ የተጻፈ መሆኑ የተስፋ ጽሑፍ ለሚፈልጉ፣ የደስታ ስሜት ለሚሹ ላይሆን ይችላል |ደስ የሚል ኀዘንን ማጣጣም ካልወደዱ በቀር| ገና በርዕሱ ስለመለየት እና ስለሞት ብሎ መጀመሩ ትራጀዲውን የመዘገቡ ሁናቴ ታስቦበት የተደረገ እንደሆነ ያሳምናል።
የተበተነ እንጨት ይሰበሰብ ዘንድ እጅ ይሻል፣ የተሰበሰበ እንጨት ይታሰር ዘንድ ልጥ ይሻል፣ ጽሑፍም ከመዝራት እስከ መሰብሰቡ ይህኑ ይከውናል። የተጻፉትም ያልተጻፉትም፤ የታሰቡት ያልተሰቡትም ...ያልኩትም ያላልኩትም ሁሉም ስለመኖር ነው።


Read 808 times