Saturday, 17 September 2022 13:08

አስደማሚው ቅዱስ ገላውዲዮስ ጥንተ ቤተ ክርስቲያን በጎንደር ደብረታቦር

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ከደቡብ ጎንደር ዞን ዋና መቀመጫ ደብረ ታቦር ከተማ በስተሰሜን 50  ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከአማራ ክልል ዋና መቀመጫ ባህርዳር ከተማ በስተምስራቅ 75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል - ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዲዮስ ጥንተ ቤተ ክርስቲያን።
በ1550ዎቹ በአፄ ገላውዲዮስ እንደተገነባ የሚነገርለት ይህ ጥንታዊ ደብር፣ እጅግ ማራኪና በሁሉም አቅጣጫ ለአይን የሚማርክ መልክአ-ምድርን ለማየት የሚያስችል ቦታ ላይ መታነጹ ይበልጥ አስደማሚ ያደርገዋል። ይህን የተመልካችን አይን አፍዝዞ የማስቀረት አቅም ያለው ጥንተ ደብር፣ የአፄ ልብነ ድንግል ልጅ የሆኑት አፄ ገላውዲዮስ ያስገነቡበት ምክንያት ቀጣዩን ይመስላል።
ግራኝ አህመድ አፄ ልብድንግልን ከገደላቸው በኋላ አፄ ገላውዲዮስ የአባታቸውን ገዳይ ግራኝ አህመድን ለመፋለም ግራኝ በር  ወደሚባል ቦታ ይዘምታሉ። በዘመቻው ወቅት የእመቤታችንን የማሪያምን ታቦትና ታቦተ ገላውዲዮስን በፈረስ ጭነው ወደ ዘመቻው ጉዞ መጀመራቸውን በጉብኝታችን ወቅት ያገኘናቸው የጥንተ ቤተ ክርስቲያኑ አባቶች አጫውተውናል። እንደ ቤተክርስቲያኑ አባቶች ገለፃ ከሆነ፤ አፄ ገላውዲዮስ ግራኝ አህመድን ለመፋለም በጉዞ ላይ እያሉ አሁን ቤተ ክርስቲያኑ ከተገነባበት ቦታ ወረድ ብላ በምትገኝ ወንዝ አቅራቢያ ሲደርሱ፣ ታቦተ ገላውዲዮስን የጫነው የአፄ ገላውዲዮስ ፈረስ ከቦታው አልንቀሳቀስም ብሎ ያስቸግራቸዋል።ፈረሱን ለመንዳትና ለማንቀሳቀስ ብዙ ታግለው ያልተሳካላቸው የአፄ ገላውዲዮስ አጃቢዎች የሆነውን ለአፄው ተናገሩ። አፄ ገላውዲዮስ የሆነውን በአይናቸው በተመለከቱ ጊዜ “ይህ ፈረስ አልንቀሳቀስ ያለው በዚህ ቦታ ላይ አንዳች ተዓምር ቢኖር ነው” በማለት በቦታው ላይ ሰራዊታቸውን አስፍረው ማደራቸውንና በዚያም ሌሊት ለፈጣሪያቸው ስለት (ብፅአት) መግባታቸውን ከገዳሙ አባቶች በተጨማሪ ቦታውን ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለማስጎብኘት አብረውን ወደ ስፍራው የተጓዙት በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና የአለቃ ገብረሃና የባህል ጥናት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ መሰረት ወርቁ ገልጸውልናል።አጼ ገላውዲዮስ በዚያ ሰፍረው ባደሩበት ቦታ የገቡት ስለት፣ በጦርነቱ ግራኝ አህመድን አሸንፌ ከተመለስኩ ለቅዱስ ገላውዲዮስ ቤተ ክርስቲያንህን በዚህ ቦታ ላይ  አንጻለሁ የሚል እንደነበር ነው አቶ መሠረት ወርቁ ያወጉን፡፡ አፄ ገላውዴዎስ ስለታቸው ሰምሮ ግራኝ አህመድን አሸንፈው ብቻ ሳይሆን ገድለውም ጭምር በድል ሲመለሱ ይህንን ያማረ ጥንተ ቤተ ክርስቲያን በ1550ዎቹ ማስገንባታቸውን ነው የገለጹልን።አፄ ገላውዲዮስ ከግራኝ አህመድ ጋር ባደረጉት በዚህ ጦርነት ከታቦተ ገላውዲዮስና ከቅድስት ማርያም ታቦት በተጨማሪ አንዲት ንብ አብራ መዝመቷን የሚገልፁት የቤተ ክርስቲያኑ አባቶች፤ አሁንም ያቺ ንብ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደምትኖር፣ እንደማትወልድና እንደማትባዛ ጠቁመው፤ ይህ የእግዚአብሔርን ተዓምር ከምናይበት አንዱ ነው ይላሉ። በዚህ ቤተ ክርስቲያን ሌላም በአስደናቂነቱ የሚገለጽ ታሪክ አለ። በዚያ ወቅት ሰዎች ወደ ቅድስቲቱ ኢየሩሳሌም ሄደው የመቀበር ፅኑ ፍላጎት ስለነበራቸው ይህንን ጽኑ ፍላጎት ያዩት አፄ ገላውዲዮስ፤ ከኢየሩሳሌም አፈር በግመል አስመጥተው ቤተ ክርስቲያኑን ማስደልደላቸውን ይናገራሉ።በዚሁ ጥንተ ቤተ ክርስቲያን ሰው ሲሞት የሚቀበረው እንደሌላው አካባቢ ከቤተ ክርስቲያን ግቢ ውጪ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደሆነ የሚናገሩት አስጎብኚዎቹ፤ በዚህ ግቢ ውስጥ ሰው በተቀበረ በጥቂት ጊዜ ውስጥ አስክሬኑ እንደሚጠፋና አፅሙም እንደማይገኝ ይገልጻሉ። ይኸው እስከዛሬም ድረስ የአካባቢው ሰው በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ እየተቀበረ የመቃብር ቦታው እንደማይሞላና ከዚህ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ሌላ ቦታ ሰው እንደማይቀበር ያብራሩት የቤተ ክርስቲያኑ አባቶች፤ ቦታው ብዙ የፈጣሪ ተዓምራት  የሚታይበት ነውም  ይላሉ።
በጎንደሪያን የኪነ-ህንፃ አሻራ በማራኪ ሁኔታ የተገነባው ይህ ጥንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ከግቢው አጥር ጀምሮ መግቢያ በሩ ብሎም እስከ ዋና ህንፃ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በውበቱና በማራኪነቱ አይን አፍዝዞ የሚያስቀር፣ የጥንት አባቶቻችንን የጥበብ አሻራ አንፀባራቂነት የሚያሳይና ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን የሚችል ሀብት ቢሆንም፣ እስከዛሬ ድረስ እዚህ ግባ የሚባል ቦታውን ወደ ሀብትነት የመቀየር ስራ እንዳልተሰራ  በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል የስነ-ጥበብ ታሪክ መምህር አቶ ጌታቸው ጋሻው ይገልጻሉ፡፡ እስካሁንም ምንም አይነት ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በቦታው ላይ እንዳልተሰራም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ይህን የመሰለ ታሪካዊ ቦታ ላይ ለምን ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር እንዳልተካሄደ ከጋዜጠኞች ለምሁራኑ ጥያቄ ቢቀርብም፣ ለጊዜው ለዚህ ጥያቄ እነሱ መልስ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸውልናል፡፡ እኛ ግን በህንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ውበት፣ በግቢው ስፋትና ውበት፣ በቦታው ልምላሜና በሁሉም አቅጣጫ ያለውን መልክዓ ምድር ለማየት አመቺ ቦታ ስለመገንባቱ ተደንቀን እንዲሁም የአካባቢው አርሶ አደሮች ባሳዩን ፍቅርና የምሳ ግብዣ ተደምመን ተመልሰናል። በመጨረሻም የፌደራል ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የክልሉና የዞኑ የባህልና ቱሪዝም ቢሮና ጽ/ቤቶች ይህንን በቅርብ ርቀት ላይ ያለ ሀብት ለምን ችላ አሉት? ስንል እንጠይቃለን።

Read 1253 times