Saturday, 17 September 2022 13:10

“ያለነጻነት ከመሞት ነጻነትን ይዞ መሞት ይሻላል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ጃንሆይ በምክር ቤት የተናገሩት ዲስኩር


       ከአርባ ዘመናት ይበልጥ ዠምሮ ኢጣሊያ አገራችንን ለመውሰድ ያላትን ምኞት ምን ጊዜም ቢሆን አላቋረጠችም ነበር፡፡ በነዚሁ ዘመናት ሁሉ በልዩ ልዩ አኳኋን ዘወትር ይታይ የነበረው ይኸው ምኞቷ ባለፈው በ1926 ዓመት በክረምቱ ውስጥ በሥራዋ እየተገለጸ መታየት ዠመረ፤ ይኸውም ርግጥ ይሆን ዘንድ ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር ውስጥ አላንዳች ምክንያት የኢጣሊያ መንግስት በወሰኖቻችን አቅራቢያ የጦር መሣሪያ በብዙ ማከማቸት ዠመረ፡፡
ይህንኑ ነገር ሰምተን ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንጠይቅ ብለን ሮማ ላለው ጉዳይ ፈጻሚያችን ትዕዛዝ እንዲያልፍለት አደረግን፤ ይህን የጦር መዘጋጀት ያደረግነው ኢትዮጵያ የኤርትራንና የሱማሌ ቅኚ አገሮቻችንን ለመውጋት አሳብ ስላላት ነው፣ የሚል መሠረት የሌለው፣ ከመዠመሪያው እስከ መጨረሻው ሐሰት የሆነ ምክንያት ምላሽ አድርገው ሰጡ፡፡ ምንም ይህ የተሰጠው ምላሽ ጨርሶ ሐሰት መሆኑን ብንገልጽ፣ ኢጣሊያን ከዚያን ጊዜ ዠምራ የምትከተለው አሳቧ በረዥሙ መርምራ በቆረጠችው ፕላን ነበርና፣ ምንም በፍጹም የወሰነችው አሳቧ እኛን በማጥቃት ለመውጋት ቢሆን ለመከላከያ ነው እያሰኘች፣ የጦር መዘጋጀቷን እየገፋች ከመሄዷም አላቋረጠችም፡
ይህን የመሰለውን ግፈኛ የሆነ አሳብ በዓለም ህዝብ ፊት የሚገባ ነገር አስመስሎ ለማሳየት ለዚሁ የሚጠቅም ምክንያት ማግኘት ለኢጣሊያ የሚያስፈልጋት ነበረ፡፡
ግማሾቹ የኢትዮጵያ አገር የመሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች በሆኑና ግማሾቹ የኢጣሊያ የንግድ አጃንሲያ አሽከሮች በሆኑ በኢትዮጵያ ተወላጆች መካከል ባለፈው በህዳር ወር ውስጥ ጎንደር ላይ በሴት ምክንያት አምባጓሮ ተነሳ። በነዚህ ሰዎች መካከል በራሳቸው ጉዳይ ይህ ጠብ ተነስቶ ደም ቢፈስ አዲስ አበባ ያለው የኢጣልያ ሌጋሲዮን በዲፕሎማቲክ መንገድ በብርቱ በነገሩ ገብቶበት መንግስታችን ሰላም ፈላጊ በመሆኑ የከረረ ጠብ እንዳይነሳ ሲል ኢጣልያኖች የጠየቁት እንዲፈፀምላቸው አደረገ። ከዚህ በኋላ ደግሞ ላሁኑ ጠባችን መሰረት የሆነው የወልወል አደጋ ወደቀ።
ኢጣልያ የኛን ግዛት ቀንሳና ያገራችንን ነጻ ተገዥነትን እንደ ማክበር ሁሉ ጥሳ በ፲፱፻ ዓ.ም በሁለቱ መንግስቶች መካከል የተደረገው ውል የወሰነውን ወሰን (1) መቶ ኪሎ ሜትር ያኽል አልፋ ወልወል በሚባለው ቦታ ላይ ወታደርና ብዙ መሳሪያ አስቀመጠች።
ከእንግሊዝ ሱማሌና ከእኛ መካከል ያለውን ወሰን በመወሰኑ ምክንያት በውል እንደ ተፈቀደላቸው የእንግሊዝ ሱማሌ ጎሳዎች ከብት የሚያግጡበትን ቦታ ሄደው አይተው ለመወሰን ከኢትዮጵያም መንግስት ከእንግሊዝም መንግስት ሰዎች ታዘው ነበር።
እነዚህ መንግስታት ለስራ የላኳቸው መላዕክተኞች የታዘዙትን ስራ በግዛታቸው ላይ ሲሰሩ የሚጠብቃቸው መንግስታችን ስለ ነበር፣ ተከታዮች ወታደሮች ተሰጥቷቸው ነበር። በነዚህም በኢትዮጵያ ወታደሮች እንደምታውቁት ሁሉ በህዳር ፳፮ ቀን አደጋ በድንገት ተጥሎባቸው አርበኞች ወታደሮቻችን በኢጣልያ መትረየስ በታንኩና በአቪዮኑ እየተመቱ መውደቃቸው የኢጣልያ አጥቂዎች ቀድሞ አስበው የፈፀሙት ግፍ መሆኑን እንደሚበቃ የሚመሰክር ነው።
እንደዚህ አድርገው በገዛ ግዛታቸው ላይ ወታደሮቻችንን ወግተው ኢጣልያ የገዛ ሰዎቿ የሰሩትን ግፍ አዛውራ በእኛ ላይ ለማድረግና እኛን ለመውቀስ አሰበች። ወታደሮቻችን ይቅርታ  እንዲጠይቋትና ካሳ እንዲከፍል ከመጠየቅ ደረሰች።ኢትዮጵያም የሚገባትን መብት ህሊናዋ ያውቅላታልና፣ ኢጣልያ ለዘላለም በመካከላችን ሰላምና ወዳጅነት ፀንቶ እንዲኖር፣ በመካከላችንም ጠብ ቢነሳ ይኸው ጠብ በሽማግሌ ስልጣን በሰላም እንዲያልቅ ቃል የገባችበትን በ፲፱፻፳ ዓ.ም የተደረገውን ውል ጠቅሰን ነገሩን በውል ቃል መሰረት ለመጨረስ ጥያቄያችንን ወዲያው አቀረብንላት። ለዚህም ላቀረብነው ጥያቄያችን ምላሹ ፍፁም እንቢታ ሆኖ፣ ኢጣልያ ሳይመረመርና በሚገባው መንገድ ሳይፈረድ ያቀረበችውን ጥያቄ በሙሉ ለማስፈፀም ጥብቅ አሳቧን ገለፀች።
እኛም ክብር ምንም ቢሆን እንዳይነካ ቆርጠን ነበርና፣ አንድ መንግሥት በሙሉ ፈቃዱ ይህን የመሰለውን ጠብ ለተገባው አለመድሎ ለሚፈርድ ለመንግሥታት ዳኛ አቅርቦ ቢፈረድ እንደ ፍርዱ መፈጸም፣ ይህንኑ መንግሥት ከፍ አድርጎ የሚያሳየው እንጂ የሚያዋርደው አለመሆኑን ስለተረዳነው፣ በዚህ ነገር ውስጥ ኢትዮጵያ ጥፋተኛ ሁና የተገኘች እንደሆነ፣ የተፈረደባትን ፍርድ በሙሉ ወዲያው የምትፈጽም መሆኗን በግልጽ አስታወቅን፡፡
ኢጣሊያ ነገሩ በሽማግሌ እንዲያልቅ የማትፈልግ ከመሆኗ የተነሳ ነገሩ በሕግና በሰላም መንገድ እንዲያልቅ ፈቃዳችን ስለ ነበረ፣ ይህነኑ ሰላማዊ መንገድ በመፈለግ ነገሩን ወደ መንግሥታት ማኅበር አማካሪዎች ለማድረስ የሚያስፈልግ ሆነ። ይህንኑ ነገር ወደ መንግሥታት ማኅበር ያደረስንበትን ምክንያት በዝርዝሩ በጽሕፈት አድርገን ለኢጣሊያ ንጉሥና ለኢጣሊያ መንግሥት ሹም ለሙሴ ሙሶሎኒ አስታወቅን፡፡
ባለፈው በጥር ወር የመንግስታት ማሕበር አማካሪዎች በተሰበሰቡበት ጉባኤ ላይ ነገሩ ታይቶ በሽማግሌ እንዲያልቅ አሳቡን ኢጣልያ ሲቀፋት ተቀበለች።
ነገር ግን በዚሁ በጥር ወር ፲፩ ቀን የመንግስታት ማህበር አማካሪዎች የቆረጡትን ቃል ተከትለን ሽማግሌዎቹን ለመምረጥ ተጀምሮ የነበረው የዲፕሎማቲክ ንግግር ያላደረግነውን ጥፋት ለማሳመን እየተጣጣረ፣ የኢጣልያ መንግስት ሚኒስትር ነገሩን እየጎተተው ስለ ሄደ በመጋቢት ወር ውስጥ እንደ ገና ነገሩን ወደ መንግስታት ማሕበር አማካሪዎች ማድረስ የሚያስፈልገን ሆነ።
በውነትም ኢጣልያ በዲፕሎማቲክ መንገድ መንግስታችንን በማይገባ ለመጫን ስትጣጣር፣ ደግሞ ባንድ ፊት በየቀኑ በራዲዮ የሚመጣው ወሬ በየቀኑ ወታደር፣ የጦር መሳሪያ ጥይት ወደ ኤርትራና ወደ ኢጣልያ ሱማሌ ወሰኖቻችን ባለማቋረጥ መላኳን እየሰማን፣ ጦር ይሆናል የማለትን አሳብ በየጊዜው የሚያረጋግጥልን ሆነ።
ነገሩን ሁለተኛ ወደ መንግስታት ማሕበር ከማድረሳችን የተነሳ በግንቦት ፲፯ ቀን ፲፱፻፳፯ ዓመት በርግጡ ሽማግሌዎቹ እንዲመረጡ ተቆረጠ።
ኢትዮጵያ የሚፈረደው ፍርድ በፍፁም በህግ መሰረት አለመድሎ እንዲሆን ምኞቷ ስለ ነበር ከሷ ወገን ሽማግሌ የሚሆኑትን በመንግስታት ህግ በእውቀታቸውና በስልጣናቸው እጅጉን የታወቁ አንድ የፈረንሳይ የህግ ሊቅ፣ አንድ የአሜሪካ ህግ ዐዋቂ ሁለት ሰዎች መረጠች።
  ኢጣሊያም በበኩሏ ከኢጣሊያ መንግሥት ሹማምንት ውስጥ ሁለት የኢጣሊያ ሰዎች መረጠች፡፡
በዚህም ምክንያት ምንም የምንቃወመው ነገር ባይኖር የኢጣሊያ መንግሥት በመምረጡ ክርክሩ በሕግና አድልዎ በሌለበት መንገድ እንዲያልቅ አለመፍቀዱን ማሰብ የሚገባ መስሎ ታየን፡፡ ምክንያቱም ማንም ሰው ቢሆን እንዲከራከርላት በመረጠችው አገሩ ላይ አድልዎ የሌለበት ፍርድ ይፈርዳል ተብሎ የማይጠረጠር ስለሆነ ነው፡፡
የኢጣሊያ መንገድ የመረጣቸው ጨዎች የታያቸውን እንዲፈርዱ ነጻነት የሌላቸው በመሆናቸው ምክንያት ክርክሩ በሽምግልና ዳኝነት እንደማያልቅ የሚያሰጋ ስለሆነ፣ የእንግሊዝ መንግሥት የዓለም መንግሥታት ሕግ ዋና መሰረቱ የዓለም ሰላም መሆኑን ተመልክቶ ደግሞ ዋና ምኞቱ በዓለም ላይ ሰላም እንዲጸድቅ ስለሆነ የመታወቂያ መንገድ ይገኝ እንደሆነ በማለት በበኩሉ መሞከር ጀመረ፡፡ ምንም የውጊያ አውራጃ የኢትዮጵያ መሆኑ በሕግ ረገድ የማያጠራጥር ቢሆን፣  ምንም ኢጣሊያ ተጋፍቶ መጥቶ በርስታችን ላይ ክፉ አደጋ ቢጥልብን፣ የእንግሊዝ መንግሥት ያቀረበው የዕርቅ ሐሳብ እኛ  ከውጋዴ ግዛታችን አንድ ክፍል ቆርሰን ለኢጣሊያ እንድንሰጥና ለዚህም ለውጥ እንግሊዝ የዘይላ በር አንድ ክፍል ከግዛቱ ቆርሶ ለኛ እንዲሰጥ ነበር። የቀረበውን የዕርቅ ሐሳብ ለመመርመር ተዘጋጅተን ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ የዕርቅ ሐሳብ ገና ከመቅረቡ ሙሴ ሙሶሊኒ በፍጹም አልቀበለውም ስላለ በነገሩ እንድናስብበት የሚያስፈልግ ሆነ፡፡
አሁን ጨዎቹ የተመረጡበትን ጉዳይ ለመፈጸም አልተቻላቸውም፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት ያቀረበውን የዕርቅ ሐሳብ የኢጣሊያ መንግሥት ዋና ሹም ባጭሩ ቆረጠው፡፡
ኢጣሊያኖችም መሰናዳታቸውን አላቋረጡም፡፡ የኢጣሊያ መንግሥትም ታላላቁ ሹማምንት በልባቸው ያለው የዕርቅ ሐሳብ የኢጣሊያ መንግሥት ዋና ሹም ባጭሩ ቆረጠው፡፡ኢጣሊያኖችም መሰናዳታቸውን አላቋረጡም፡፡ የኢጣሊያ መንግሥትም ታላላቁ ሹማምንት በልባቸው ያለው ዋናው ሐሳባቸው አገራችንን ለመውሰድ መሆኑን በግልፅ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ የጦርነት ሰዓት እየቀረበ መሄዱ ነው፡፡
ባለፈው ሰኔ ፩ ቀን የኢጣሊያ መንግሥት ዋና ሹም የአፍሪቃ ምስራቅ ተብሎ አዲስ ወደተሰየመው ወደ ኤርትራና ወደ ሱማሊያ በታዘዘው አምስት ሺህ ወታደር ፊት ቆሞ እንደ ልማዱ ለኢጣሊያ ሕዝብ ሲሰብክ፣ የጦር ፈላጊን መንፈሳቸውን ለማነቃቃት ብሎ፣ እናንተ የምትሄዱበት ለታሪካችን በጣም ከፍ ያለ የጀግንነት ነገር ልትጽፉ ነው ብሎ ተናገረ፡፡
ሙሴ ሞሶሎኒ እንደሚሉት፤ ኢጣሊያ የምትፈልገው የእኛን ሕዝብ ለማሰልጠን ነው፡፡
ነገሩ በሰላማዊ መንገድ እንዳያልቅ ለማድረግ ኢጣሊያ ካሁኑ ቆርጣለች፡፡ ሐሳቧ ብዙ ደም ፈሶ የቀድሞውን ያዷን ብድር ለመመለስ ነው፡፡
አረመኔ ሕዝብ እያለች ስሙን የምታጠፋው  የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የሰጠውን ቃል የሚያከብርና የፈረመውን ውል የሚያጸድቅ ሕዝብ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲሆን አትፈልግም፡፡ የመጣውን ግን መከላከሏ አይቀርም፡፡ ባዷ ጊዜም ቢሆን ጠብ አንሺ ኢትዮጵያ አልነበረችም፡፡ ጦርነትም የሆነበት ምክንያቱ ኢጣሊያኖች ወሰን አልፈው በግዛቷ ውስጥ ስለ ተገኙ ነው፡፡ ምናልባት ደግሞ ነገ እንደዚሁ ያደርጉ ይሆናል፡፡
በእግዚአብሔር ቸርነት በአርበኞቿ ዠግንነት የመጣባትን መክታ ምንም በ፲፰፻፹፰ ዓመት ኢትዮጵያ ድል ብትነሳ (ብታደርግ) የሚገባትን ሁሉ አልጠየቀችም፤ የግዛቷ ማስፋፊያ ምክንያት አላደረገችውም፡፡
ከቀን እስከ ቀን የማይቀር መስሎ የሚታየው ጦርነት በደረሰ ጊዜ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ኅሊናው አይወቅሰውም፡፡ ሰላም እንዲጠበቅ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች ላይ ሥልጣን ይኑረኝ የማለት ሐሳብ የላትም፤ በግዛቷ ውስጥ ባለቤት ሁና ስልጣኗና ወሰኗ ሳይደፈር ለነጻነቷ ስትል እስከ መጨረሻው ድረስ ለመከላከል የተዘጋጀች ነች፡፡
ተጋፊ የሆነው የኢጣሊያ ሕዝብ፤ ዘመኑ ያወጣውን የአጥቂነት መሳሪያ ይዞ፣ ስልጣኔ ላስተምራችሁ ነው ብሎ ሲመጣ፣ ለንጉሠ ነገሥቱና ላገሩ ለመሞት የተዘጋጀ አንድነት ያደረበት ሕዝብ ተሰልፎ ይጠብቀዋል፡፡
ወታደር ሆይ፤ በጦርነት ውስጥ አንድ የተከበረና የተወደደ አለቃ ለነጻነታችን ብሎ ሞተ ሲባል አትዘን፤ ተስፋ አትቁረጥ፡፡ ላገሩ የሚሞት ሁሉ ዕድለኛ ሰው መሆኑን ተመልከት  እንጂ፤ ሞት ሳያማርጥ በሰላም ጊዜ ሆነ በጦርነት የፈቀደውን ይወስዳል፡፡ ያለ ነጻነት ከመሞት ነጻነትን ይዞ መሞት ይሻላል፡፡
አባቶቻችን አገራችንን በነጻነት ያቆዩልን ሕይወታቸውን እየሰጡ ነው፡፡ እሱ አብነት ይሁኗችሁ፡፡
ወታደር፤  ነጋዴ፤ ገበሬ፤ ልጅም ሽማግሌም፤ ወንድም ሴትም አንድነት ይደርባችሁ፤ እየተረዳዳችሁ ላገራችሁ ተከላከሉ፡፡
እንደ  ጥንት ጊዜ ልማድ፣ ሴቶችም ወታደሩን በማደፋፈር ቁስለኛ በማስታመም፣ ላገራቸው ይከላከላሉ፡፡ ዕርስ በርሳችን እንድንለያይ ምንም ኢጣሊያ የተቻላትን ሁሉ ብታደርግ፣ ክርስቲያንም ሆነ ወይም እስላም አንድ ሆኖ ይመክታል፡፡
ምሽጋችንና ጋሻችን እግዚአብሔር ነው፡፡ የአጥቂዎቻችን አዲስ መሳሪያ ለኢትዮጵያ ነጻነት ከመከላከላችሁ፣ ከተቀደሰ ሐሳባችሁ አያዘንብላችሁ፡፡
ዛሬ የሚናገር ንጉሣችሁ፤ በዚያ ጊዜ በመካከላችሁ ይገኛል፤ ለኢትዮጵያ ነጻነት ደሙን ለማፍሰስ ተዘጋጅቷል፡፡
ሳንጨርስ ዳግመኛ አንድ የምንነግራችሁ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለሰላም አጥብቀን መጣጣራችን ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም መድከሙን እናሳስባችኋለን፡፡ በዲፕሎማቲክ መንገድ ሰላማዊ የሆነና ለሁለታችንም ክብር ያለበት የመስማሚያ መንገድ መፈለጉን አላቋረጠም።
የኢጣሊያ መንግሥት በፈቃዱ የፈረመውን የወዳጅነትና የሽምግልና ዳኝነት ውል እንዲያከብር እንዲያደርግ የመንግስታትን ማህበር ሁለት ጊዜ ጠይቋል፡፡
ዳግም ጦርነት በፍጹም እንዲቀር ተብሎ የቀረበውን ውል ኢትዮጵያም ኢጣሊያም ከሌሎች መንግሥቶች ጋራ ስለፈረሙ፣ የውሉም መሥራች አሜሪካ ስለ ሆነ፣ አሁን በቅርቡ ለአሜሪካ መንግሥት አስታውቀናል፡፡
ደግሞ አሁን ሆላንድ አገር የሁለታችንም ጨዎች ክርክራችንን ሲመረምሩ፣ የኢጣሊያ ጨዎች ስላስቸገሩ ፓሪስ ያለው ሚኒስትራችን ለሶስትኛ ጊዜ ለመንግስታት ማኅበር እንዲያመለክት አዘነዋል፡፡
እስከ መጨረሻው ድረስ ሰላም እንዲሆን እንጣጣራለን፡፡ ነገር ግን ድካማችንና መልካም አሳባችን ፍሬ ያላገኘ እንደ ሆነ ኅሊናችን አይወቅሰንም፡፡ የኢትዮጵያ  ሕዝብም በእምነት ተባብሮ ላገራችን ነጻነት በእውነተኛው ነገር ለመከላከል እግዚአብሔር የአርበኞቻችንን ሃይል እንዲያጸና ወደ እግዚአብሔር ይዘረጋል፡፡
***
(ማስታወሻ፡- ከጥንት እስከ ዛሬ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማንበርከክ ጠላቶች ሳያሰልሱ ሲነሱባት ኖረዋል፡፡ ሁሌም ኢትዮጵያ እውነትን ይዛ በልጆቿ መስዋዕትነት ነጻነቷን ስታስጠብቅ ነው የኖረችው፡፡ አሁንም ቢሆን እንዲሁ ነው የሚሆነው፡፡)

Read 1125 times