Saturday, 17 September 2022 13:18

ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መረጃ መሰረት በ1 አመት ውስጥ በአለምአቀፍ ደረጃ ከ4 ጽንስ መካከል አንድ ጽንስ እንደሚቋረጥ ይገመታል። ከዚህም ውስጥ 25ሚሊዮን ጽንስ ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ የሚቋረጥ ነው። የአለም የጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ በአለምአቀፍ 45% ይይዛል። ከፍተኛውን መጠን 97% በመሸፈን በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቀዳሚ ናቸው። ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሚሆኑት 4 ምክንያቶች ውስጥ ይካተታል:: ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ፣ ኢንፌክሺን፣ ልጅ ከተወለደ በኋላ በሚፈጠሩ የተለያዩ እክሎች እና ደህንነትቱ ባልተጠበቀ መንገድ ጽንስ ማቋረጥ መንሴዎች ናቸው። ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ የእናቶች ሞት መንስኤ በመሆን በአለማቀፍ 13%ሲሆን ከሰሀራበታች በሚገኙ ሀገራት ደግሞ 50% በመሆን ተቀምጧል።
ጽንስ ማቋረጥ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በጤና ተቋማት መሰጠት ያለበት ሲሆን በባህላዊ መንገድ ወይም ከህክምና ተቋም እና ከባለሙያ ወጪ በተለያዩ ቦታዎች የሚደረግ ጽንስ ማቋረጥ ደግሞ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ይባላል። ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት በአንድ ሀገር በህግ በተደነገገው መሰረት በጤና ተቋም ይሰጣል። በተለያዩ ሀገራት ህግ መሰረትም አገልግሎቱን ለማግኘት ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል።
አለምአቀፍ የስነተዋልዶ ጤና ማእከል [world reproductive health center] መረጃ እንደሚያሳየው በአለም ላይ 5 አይነት ጽንስ የማቋረጥ ህጎች ወይም የሀገራት አሰራ ሮች ይገኛሉ።
ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት በተገልጋዮች ጥያቄ ወይም ፍላጎት ብቻ ይከናወናል። ይህም እንደየ ሀገራቱ ቢለያይም አብዛኛዎቹ ሀገራት ያለቅድመ ሁኔታ አገልግሎቱን የሚሰጡት እስከ12 ሳምንት[3ወር]
በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ13 ሀገራት ይገኛል። የእናት እና የጽንሱን የተለያዩ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት አገልግሎትን ለማግኘት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች በህግ ተደንግገዋል።
የእናትን ህይወት ከሞት ለመታደግ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሀገራት 41 ናቸው። በመውለጃ እድሜ ላይ የሚገኙ 358 ሚሊዮን ሴቶች በነዚህ ሀገራት ይኖራሉ። እነዚህም የአለምን 22% ይሸፍናሉ።
ሙሉበሙሉ ጽንስ ማቋረጥ የሚከለክሉ ሀገራት ይገኛሉ። እነዚህም 24 ሲሆኑ በየትኛውም ሁኔታ ጽንስ ማቁረጥ ህጋዊ እውቅና የለውም።
የአለምን የህዝብ ቁጥር በቀዳሚነት የምትሸፍነው ቻይና በእናት ጥያቄ መሰረት እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ የህዝብ ቁጥር ያላት ህንድ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት ይሰጣሉ።
ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት በአውሮፓ አህጉር በሚገኙ 39 ሀገራት አገልግሎቱን ፈልገው ጥያቄ ላቀረቡ ሴቶች ይሰጣል። በሌሎች 12 የአውሮፓ ሀገራት ደግሞ ከ18 እስከ 24 ሳምንት የሆነ ጽንስ በህክምና ተቋም መቋረጥ የሚችል ሲሆን እንዲሁም የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላ የእናት ጤና ወይም ህይወት አደጋ ላይ ከሆነ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት ማግኘት ይቻላል፡፡  
በደቡብ አሜሪካ የተወሰኑ ሀገራት ያለ ቅድመ ሁኔታ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ሲፈቅዱ 9 ሀገራት ደግሞ ቅድመሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ። ደቡብ አሜሪካ ደህንነቱ የጠበቀ ጽንስ ማቋረጥን ፍቃድ ያልሰጡ ሀገራት በብዛት እንደሚገኝባት መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተመሳሳይ ከአፍሪካ አህጉር ፍቃድ የማይሰጡ ሀገራት በብዛት ይገኛሉ። ከ54 ሀገራት ቱኒዝያ፣ ኬፕቨርዲ እና ደቡብ አፍሪካ ያለቅድመ ሁኔታ በእናት ጥያቄ መሰረት ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት ይሰጣሉ። ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ።
በኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታዎች በህግ ተቀምጧል።  ጽንስን ማቋረጥ በህግ የተፈቀድባቸው ሁኔታዎች፡-
ሀ) በመድፈር ወይም በዘመድ መካከል በተደረገ የግብረ ስጋ ግንኙነት ምክንያት ጽንሱ የተገኘ ከሆነ፤
ለ) የእርግዝናው መቀጠል በእናቲቱም ሆነ በጽንሱ ህይወት ወይም በእናቲቱ ጤንነት ላይ አደጋ የሚያስከትል ሲሆን ወይም የልጁ መወለድ በእናቲቱ ጤንነት ወይም ህይወት ላይ አደጋ የሚያመጣ ሲሆን፤
ሐ) ጽንሱ ሊድን የማይችል ከባድ የአካል ጉድለት ያለው[ዲፎርምድ] ሲሆን ወይም
መ) አንዲት እርጉዝ ሴት የአካል ወይም የአእምሮ ጉድለት ያለባት በመሆኗ የሚወለደውን ህጻን ለማሳደግ የህሊናም ሆነ የአካል ዝግጅት የሌላት ሲሆን ነው።
ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት በጤና ጣቢያ እና ሆስፒታል ይሰ ጣል። ከ3ወር በታች ለሆነ ጽንስ በጤና ጣቢያ እንዲሁም እስከ 6 ወር ጽንስ በሆስፒታል አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ጽንስ ለማቋረጥ የሚያገለግሉ መድሀኒቶችን ያለባለሙያ እርዳታ በቤት ውስጥ የሚጠቀሙ መኖራ ቸውን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። አዋላጅ ነርስ ዘምዘም አብዱልቃድር እንደሚናገሩት ጽንስ ለማቋረጥ የሚወሰደው መድሀኒት 90% እንዲቋረጥ ቢያደርግም የተቀረው በባለሙያ እገዛ የሚከናወን ነው። እንዲሁም ይህ መድሀኒት እንደተፈለገው ጽንሱን ላያቋርጥ ወይም ከተጠበቀው በላይ ደም እንዲፈስ ሊያደርግ ስለሚችል የህክምና ባለሙያ ክት ትል ያስፈልገዋል።
በአርሲ ዩኒቨርስቲ አዋላጅ ነርስ የሆኑት አቶ ኢሰሙ ባዩ ጽንስ ለማቋረጥ መድሀ ኒቶችን ከህክምና ተቋም ውጪ ከመውሰድ በተጨማሪ “ጽንሱን ያቋርጣል ብለው ያሰቡትን መንገድ በሙሉ እነርሱን የሚጎዳ ቢሆንም እንኳን ይጠቀማሉ” ብለዋል። አዋላጅ ነርስ ኢሰሙ እንደሚናገሩት ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ ድርጊት ሴቶች የሚፈጽሙት ከአቅም በላይ የሆነ የኢኮኖሚ ወይም ማህበራዊ ጫና ሲያጋጥ ማቸው መሆኑን በተለያዩ ጥናቶች የተረጋገጠ ነው። ስለሆነም “እንደ የህክምና ባለ ሙያ ትኩረት የምናደርገው የታካሚዎችን ችግር በመረዳት አገልግሎቱን መስጠት ላይ ነው” ብለዋል አዋላጅ ነርሱ። በተጨማሪም ከጤና ተቋም ውጪ ደህንነቱ ባልተ ጠበቀ መንገድ ጽንስ ለሚያቋርጡ ሴቶች መድሀኒት የሚሸጡ አንዳንድ የመድሀኒት ቤቶች ጉዳዩ ህገወጥ እና ወንጀል መሆኑን ተገንዝበው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል አዋላጅ ነርስ ኢሰሙ ባዩ።
አዋላጅ ነርስ ዘምዘም አብዱልቃድር በበኩላቸው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ የእናትን ህይወት ሊቀጥፍ የሚችል በመሆኑ ሴቶች ከዚህ ድርጊት ሊቆጠቡ እንደሚገባ ተናግረዋል። አክለውም የጤና ተቋማት እና ባለሙያዎች አገልግሎቱ ለሚያስፈልጋቸው ሴቶች ሙያዊ እርዳታ የማድረግ ሙያዊ ግዴታ እንዳለባቸው አስታውሰው “ያለ ፍራቻ ሴቶች ወደ ጤና ተቋማት ይምጡ” በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። በኦሮሚያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ቢሮ የሚሰሩት አቶ ኤፍሬም ረጋሳ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ እና የእናቶችን ሞት አስቀድሞ ለመከላከል ሰዎች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቅሚ እንዲሆኑ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።



Read 11100 times