Saturday, 17 September 2022 13:21

22ኛው የዓለም ዋንጫ 71 ቀናት ይቀሩታል

Written by  ግሪም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ሆኖበታል፡፡ 20 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡ ለስምንት ስታድየሞች ግንባታ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጥቷል፡፡  ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ኳታር ይገባሉ ላኢብ  ልዩ ምልክት፤ Hayya Hayya ኦፊሴላዊ መዝሙር
          በኳታር የሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ 71 ቀናት ቀርተውታል፡፡ ዓለም ዋንጫ የዓለምን ትኩረት የሚስብ ታላቅ የስፖርት መድረክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት በራሽያ የተካሄደውን 21ኛው የዓለም ዋንጫ ከዓለም ህዝብ 3.2 ቢሊዮን የሚሆነው ታድሞታል፡፡  ዓለም ዋንጫ በየአራት ዓመቱ በሚካሄድበት ወቅት የመላው ዓለም  አጀንዳ ሆኖ ለወራት  ይሰነብታል፡፡ ከዓለም ዋንጫው በፊትና በኋላ ያሉት ወራት በውድድሩ ድባብ ውስጥ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡
ኳታር ለዓለም ዋንጫው በታሪክ ከፍተኛው በጀት የመደበች ሲሆን መስተንግዶው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ  ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኝ ተጠብቋል፡፡
በኳታር 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ  በአጠቃላይ የወጣው በጀት  ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡  ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት የተካሄዱትን 21 የዓለም ዋንጫዎች ለማዘጋጀት በድምር የወጣውን በጀት ሁሉ ይበልጣል፡፡ በ1994 እኤአ 15ኛው የዓለም ዋንጫን  አሜሪካ 500 ሚሊዮን ዶላር፤በ1998 እኤአ 16ኛው የዓለም ዋንጫን ፈረንሳይ 2.3 ቢሊዮን፤ በ2002 እኤአ 17ኛው የዓለም ዋንጫንደቡብ ኮርያና ጃፓን 7 ቢሊዮን፤በ2006 እኤአ 18ኛው የዓለም ዋንጫን ጀርመን 4.3 ቢሊዮን፤ በ2010 እኤአ 19ኛው የዓለም ዋንጫን ደቡብ አፍሪካ 3.6 ቢሊዮን፤ በ2014 እኤአ 20ኛው የዓለም ዋንጫን ብራዚል 15 ቢሊዮን እንዲሁም በ2018 እኤአ 21ኛው የዓለም ዋንጫን ራሽያ 11.6 ቢሊዮን ዶላር በጀት በማውጣት ታላቁን የስፖርት መድረክ አስተናግደዋል፡፡ ኳታር በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛውን በጀት ያወጣቸው ከ7 በላይ አዳዲስ ስታድዬሞች በመስራት እንዲሁም አዲስ አየር ማረፊያ ፤ አዲስ የባቡር ሜትሮ ትራንስፖርት ፤ አዳዲስ አውራ ጎዳናዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ሆቴሎች በመገንባት ነው፡፡
 22ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ በኳታር 5 ከተሞች  ስምንት ስታድየሞች ተገንብተዋል፡፡ ለእነዚህ ዘመናዊ የስፖርት መሰረተልማቶች  ከጅምሩ 4 ቢሊዮን ዶላር ቢበጀትም የሁሉም ግንባታ ሲጠናቀቅ ወጭው እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡  80ሺ ተመልካች የሚይዘው ሉሴይል አይከኒክ ስታድየም በሉሴየል ከተማ፤ 60ሺ ተመልካች የሚይዘው አል ባየት ስታድዬም በአል ክሆር ከተማ፤ 40ሺ ተመልካች የሚይዘው ስታድዬም 974 በዶሃ ከተማ፤ 40ሺ ተመልካች የሚይዘው በአልትሁማማ ስታድየም ዶሃ ከተማ፤ 45416  ተመልካች የሚይዘው ካሊፋ ኢንተርናሽናል ስታድየም በአል ራያን ከተማ፤ 45350 ተመልካች የሚይዘው ኤዱኬሽን ሲቲ ስታድየም በአል ራያን ከተማ እንዲሁም 40ሺ ተመልካች የሚይዘው አል ጃንውብ ስታድዬም በአል ዋክራህ ከተማ ይገኛሉ፡፡
22ኛው የዓለም ዋንጫ በወጣበት ከፍተኛ ወጭ የሚስተካከለው እንደሌለ ሁሉ በስታድዬም መግቢያ የትኬት ዋጋም የምንግዜም ውዱ ዓለም ዋንጫ እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡  የስታድዬም መግቢያ ትኬት ከ4 ዓመታት በፊት ራሽያ ባስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ከነበረው ዋጋ ኳታር ላይ በ46 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የ22ኛው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜን ለመመልከት የስታድዬም መግቢያ ትኬት ዋጋው 1607 ዶላር ወይንም 5850 የኳታር ሪያል እንደሆነም ታውቋል፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት ራሽያ ባዘጋጀችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ የዋንጫ ጨዋታውን ለመታደም የስታድዬም መግቢያ የትኬት ዋጋ 1100 ዶላር ነበር፡፡ በመክፈቻው ጨዋታ ርካሹ የስታድዬም መግቢያ ትኬት 302 ዶላር ሲሆን ከ4 ዓመታት በፊት 220 ዶላር ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫው አዘጋጆች ከ2.45 ሚሊዮን በላይ የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች መሸጣቸውን ቢያስታውቁም  ፊፋ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የትኬት ሽያጩ 3 ሚሊዮን እንደሚደርስ ገምቷል፡፡ከኳታር ጎረቤቶች ሳውዲ አረቢያና ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ የሚነሱ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በትኬት ግዢው ከፍተኛውን ብዛት ያስመዘገቡ ሲሆን ሌሎቹ የዓለም ዋንጫ ታዳሚዎች አሜሪካ፤ ሜክሲኮ፤ እንግሊዝ፤ አርጀንቲና፤ ብራዚልና አውስትራሊያም የሚወክሉ ናቸው፡፡
ለ22ኛው የዓለም ዋንጫው ከመላው ዓለም በመሰባሰብ ኳታር የሚገቡ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ከ1.2 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆኑ ተገምቷል፡፡ እነዚህን እንግዶች ለማስተናገድ በትልልቅ ሆቴሎች ከ130ሺ በላይ የመኝታ ክፍሎችና ከ60ሺ በላይ የመኖርያ አፓርትመንቶች መዘጋጀታቸው ተወስቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ኳታር ለእንግዶቿ በቂ የማረፊያና የመስተንግዶ አገልግሎት እንደማይኖራት የሚተቹ በርካታ ዘገባዎች ተሰራጭተዋል፡፡ የአገሪቱ መንግስት ግን ከሆቴሎች እና ከአፓርትመንቶች በተጨማሪ ሁለት ግዙፍ የመዝናኛ መርከቦችን እንዲሁም በረሃው ላይ ከ1100 በላይ ድንኳኖችን በመጣል የአግር ኳስ አፍቃሪዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
ኳታር የዓለም ህዝቦች መናሐርያ ናት ብሎ መግለፅ ይቻላል፡፡  የህዝብ ብዛቷ 2.9 ሚሊዮን ሲሆን 90 በመቶ ድርሻውን የሚይዙት ወይም ከ1.7 ሚሊዮን በላይ በስደት ኳታር ውስጥ ገብተው የሚኖሩና የሚሰሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ በስታድዬሞቹ ግንባታ ላይ የኳታር ዜግነት የሌላቸው ከ33ሺ በላይ ስደተኛ ሰራተኞች  ተቀጥረው የሰሩ ሲሆን ብዙዎቹ ከባንግላዴሽ፤ ከህንድ፤ ከኔፓልና ከፊሊፒንስ የተገኙ ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ  የዓለም ዋንጫው በመካከለኛው ምስራቅ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲካሄድ የወሰነው ከ12 ዓመታት በፊት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የ22ኛው የዓለም ዋንጫ ልዩ ምልክት ወይንም ማስኮት La’eeb ላኢብ በሚል ስያሜ ይፋ ሆኗል፡፡ የውድድሩ ልዩ ምልክትን ለዓለም ህዝብ የሚገባና የማይረሳ ሆኖ ለማቆየት በፊፋና አዘጋጅ አገር የሚደረገው ጥምረትም እንደባህል ሊቀጥል ችሏል፡፡ ላኢብ  በጣም ጥሩ የኳስ ችሎታ ያለውን ተጫዋች የሚወክል ነው። በአረቡ ዓለም ባህላዊ አለባበስ ኬፊዬ የተሰራ ገፅታው ላይ አንጸባራቂ ስብዕናው ይስተዋላል፡፡ የዓለም ዋንጫው ኦፊሴላዊ መዝሙር “Hayya Hayya,” አንድ ላይ ይሻላል ወይንም “Better Together,”  በሚል ርእስ የተሰራ ነው፡፡ አሜሪካዊቷ ትሪንዳድ ካርዶና ፤ ናይጄርያዊው ዳቪዶ እና ኳታራዊቷ አይሻ  በጋራ አዚመውታል፡፡ በአር ኤንድቢና በሶል የሙዚቃ ስልቶች የተሰራው ዜማን ፕሮዲውስ ያደረገው በመድረክ ስሙ ሬድዋን ተብሎ የሚታወቀው ሞሮካዊው ናዲር ካሃያት  ሲሆን  አሳታሚው ደግሞ ዩኒቨርሳል ነው፡፡Read 11143 times