Sunday, 25 September 2022 00:00

መንግሥትና ሁለተኛው የአማራ ትውልድ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

ትሕነግ መራሹ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን የመንግስት ሥልጣን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጨብጦ ለአንድ ወር ጊዜም አገሪቱን መራ። የመሳሪያ ትግል  ያደርጉ የነበሩና መቀመጫቸውን  በኢትዮጵያ ወስጥ አድርገው የፖለቲካ ትግል ያካሄዱ የነበሩ ልዩ ልዩ ፓርቲዎች እንዲሁም የአንድ ወሩን ጊዜ በመጠቀም ራሳቸውን በፖለቲካ ቡድን ያሰባሰቡ የብሔረሰብ ድርጅቶች የተሳተፉበት የሽግግር መንግሥት መስራች ጉባዔ፣ ሰኔ 19 እና ሰኔ 20 ቀን 1983 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሄደ።
የሽግግር መንግስቱን ምክር ቤት በማቋቋምና ቻርተሩን በማጽደቅ መንግሥቱን መሰረተ። በምክር ቤቱ ከነበሩት ሰማኒያ ሁለት ወንበሮች አርባውን በመያዝ ትሕነግ/ኢሕአዴግ የፈለገውን ለማድረግ የሚያስችለውን ሁኔታ አደላደለ። የሽግግሩ መንግስት የጦር ኃይል የትሕነግ  ጦር እንዲሆን በማስወሰንም፣ በወቅቱ ይብዛም ይነስ የታጠቀ ጦር የነበራቸውን ድርጅቶች ሽባ አደረጋቸው። በዚህ የሽግግር መንግስት ውክልና  ካላገኙት ብሔረሰቦች አንዱ አማራ ነበር።
አማራ በዚያ በብሔርተኛነት መንፈስና ስሜት በሚመራ የመንግሥት ምሥረታ ላይ አለመኖሩ የተለየ አልነበረም። እንደ እሱ ውክልና ያላገኙ፣ ድምጻቸውን የሚያሰማላቸው ወኪል  ያልነበራቸው ብሔረሰቦች ብዙዎች ነበሩ። የከፋው ችግር በሽግግር መንግስቱና የሽግግር መንግስቱን በሚያንቀሳቅሱት ኃይሎች ለአማራው “ነፍጠኛ” የሚል ስም ተሰጥቶት በመንግስትና በፖለቲካ ድርጅቶች የፕሮፓጋንዳ ኢላማ ሆኖ፣ በየአካባቢው ሰበብ እየተፈለገ እንዲታሰር፣ ሀብትና ንብረቱን እንዲቀማ፣ አካሉ እንዲጎድልና እንዲገደል መደረጉ ነው።
ከሽግግር መንግሥቱ በኋላ አዳዲስ የፖለቲካ ቡድኖች እየተመሰረቱ ወደ ፖለቲካ ትግሉ እየገቡ መሆኑን የተመለከቱ ሰዎች፤ “የኢትዮጵያ አንድነት” የተባለ ፓርቲ ለመመስረት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። መገናኛቸውን ቀጨኔ ወ/ሮ አልማዝ ኃይለ ማርያም ቤት አደረጉ። የፓርቲውን ፕሮግራም እየነደፉ፣ መተዳደሪያ ደንብ እያዘጋጁ ባሉበት ጊዜ በሐረርና በአርሲ በአማራው ላይ ተከታታይ ጥቃቶች ተፈጸሙ። በተለይ በአርባ ጉጉ ከፍተኛ ነበር። ይህን በቅርብ የተከታተሉት ከናዝሬት ቀኛዝማች ነቅዓ ጥበብ በቀለና ሌሎችም ወደ አዲስ አበባ አቀኑ። አማራው በዘሩ ተለይቶ እየተጠቃ ነው፤ልንደርስለት አይገባም ወይ የሚል ጥያቄ አነሱ። የመላ አማራ ሕዝብ ድርጅት ተመሰረተ። ጭልጥ ብሎ ብሔርተኛ ድርጅት እንዳይሆንም “ማንም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምንና የድርጅቱን ፕሮግራም የተቀበለ የድርጅቱ አባል መሆን ይችላል” የሚል አንቀጽ በድርጅቱ መመስረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ እንዲካተት ተደረገ።
በዚህ አንቀጽ መሰረት ኦሮሞዎች፣ ትግሬዎች፣ ጉራጌዎች፣ ጋሞዎች  ወዘተ-- ጥቂት ቢሆኑም የድርጅቱ አባል ለመሆን ችለው አገልግለዋል። የቦሌ ክፍለ ከተማ መኢአድ ኮሚቴ ገንዘብ ያዥ  ሴት ትግሬ እንደነበሩም አስታውሳለሁ።
ይሁን እንጂ የእነሱ መኖር መኢአድን “ትሕነግ በቀደደው መንገድ እየሄዳችሁ ለአላማው መሳካት  እየሰራችሁ ነው” ከሚለው ክስና ወቀሳ ሊታደገው አልቻለም። መአህድ (የአሁኑ መኢአድ)  እስከታች ገበሬ ማኅበር ድረስ ወርዶ በማደራጀት ረገድ ከሌሎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሻለ ስራ የሠራ ቢሆንም፣ ተቃውሞውን የሚያሳይበት መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ ከመጥራትና መግለጫ ከማውጣት ያለፈ ስላልነበር፣ የተጠበቀውን ያህል ፈጽሟል ለማለት  ይቸግረኛል።
ይህም ሁሉ ሆኖ በ1997 ዓ.ም በተደረገው አገር አቀፍ የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ፣ ለቅንጅት እንቅስቃሴ ስኬት መሰረት ሆኖ ያገለገለው የመኢአድ የማደራጀት ስራ እንደሆነ ወዳጅም ጠላትም የሚመሰክረው ጉዳይ በመሆኑ መጠቀስ ይኖርበታል።
ሌላው ሊሰመርበት የሚገባው በሲዳማ፣ በአማራ፣ በወላይታ፣ በጌድኦ፣ በኮንሶ፣ በጋምቤላ ወዘተ በሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ በትህነግ ኢህአዴግ መንግሰት የተፈጸመ ቢሆንም፣ እንደ አማራ ሕዝብ ያለማቋረጥ ግፍና በደል የተፈጸመበት ሕዝብ አለመኖሩ የታወቀ ነው። ከ2010 መጋቢት ወዲህ ደግሞ እየተባባሰ ሄዷል፡፡
አማራ በዘሩ ምክንያት የጥቃት ኢላማ በሆነበት ጊዜ መኢአድን የመሰረቱ ወገኖች የመጀመሪያዎቹ ትውልዶች ሲሆኑ፣ ችግሩ እየባሰ መጥቶ በክልሉ ባለውና ከክልሉ ውጪ ባለው ሕዝብ ላይ ህልውናው አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ የተነሱት ፋኖዎች በሁለተኛ ትውልድነት የሚታዩ ናቸው። ከእሱ አንዱ ሰሞኑን ባሕር ዳር ላይ የተያዘው ፋኖ ዘመነ ካሴ ነው።
አቶ ዘመነ የትሕነግ ኢህአዴግን መንግስት ከስልጣን ለማውረድ ታጥቆ የተነሳው፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር አባልና ከድርጅቱ አመራር አንዱ እንደነበረም ይታወቃል። ወደ አገር ቤት ከተመለሰ በኋላም ብዙ ጊዜ ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየው በፋኖ ስልጠና ላይ መሆኑም ይነገራል፡፡
“አማራ ሲሏችሁ አትፍሩ አትሸማቀቁ። ኢትዮጵያዊ ነን ስንል እናንተ አማራ ናችሁ ይሉን ነበር። አማራ ነን ብለን ስንነሳ ኢትዮጵያዊ ናችሁ ይሉናል። ትናንት በአርባ ጉጉ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ አይሆኑ ስንሆን፣ ኧረ በሕግ አምላክ ባቀናነው አገር በእኩልነት አብረን እንኑር ስንላቸው ከንፈር እንኳ የማይመጡልን ሰዎች፣ ስንደራጅ ስለ ኢትዮጵያዊነት ሊያስተምሩን ይነሳሉ። ለበላይ ዘለቀ፣ ለንጉሥ ሚካኤል፣ ለአፄ ምኒልክ ልጅ ኢትዮጵያዊነትን ለማስተማር ማሰብ ትርፉ ትዝብት ነው። አሁን አዴፓ ነን፣ አብን ነን ሳንል በፖለቲካ አስተሳሰብ ሳንከፋፈል የገጠመንን የሕልውና አደጋ ሰብረን መውጣት አለብን” በማለት ፋኖ ዘመነ፣ በአንድ የፋኖ ምርቃት ላይ ያደረገው ንግግር፣ ብዙ ድጋፍ እንዳስገኘለት ይታመናል።
“በክልሉ የወንጀል ተግባራት ተበራክተዋል። በመሳሪያ የታገዘ  ዘረፋ እየተካሄደ ነው። ሕገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውር በዝቷል።” ሕግ የማስከበር ስራ መጀመር አለብኝ፣ በማለት የአማራ  ክልል መንግስት ከወር በፊት ትጥቅ ለመመዝገብና ህገ-ወጥ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት በተነሳ ጊዜ፣ ፋኖ ዘመነ በፈቃዳቸው እጃቸውን ከሰጡት ወይም በሃይል ከተያዙት ውስጥ አልነበረም። በፈቃዱ እጁን ያልሰጠው በክልሉ መንግሥት አመራር ላይ እምነት ስላልነበረው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ። እንደሚወራው ለእርቅ ተብሎ ተጠርቶ ይሁን ወይም የፖሊስ ኮሚሽኑ እንደገለጠው በህዝብ ጥቆማ ተይዞ፣ ሰውየው በሰላም በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉ መልካም ነው ባይ ነኝ - ነገም ሌላ ቀን ነውና።
ሁለተኛው የአማራ ትውልድ የተፈጠረው፣ በአማራ ላይ ዘር-ተኮር ግድያ እየበዛ በመምጣቱ ነው። ሃይልን በሃይል ለመመለስ መደራጀት ብቻ ሳይሆን መታጠቅም የግድ አስፈላጊ ነው ብሎ ያመነ ትውልድ ነው። መንግስት ፋኖን እንደ ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች አገር ለማፍረስ የተነሳ ቡድን አለመሆኑን ሊረዳው ያስፈልጋል። አማራው ላይ የሚደርሰው ጥቃትና በቀል እስከተወገደ  ድረስ  መሳሪያውን አስቀምጦ ወደ መደበኛው ኑሮው መመለስ መቻሉን መገንዘብ ይኖርበታል። ፋኖን የመንግስት ክንድ ለማድረግ መንግስት አጥብቆ መሥራት  አለበት።
ቤት እየተቃጠለ አትጩህ ማለት አይቻልም። ፋኖ ስለ አማራ እየጮኸና እየተዋደቀ ያለ ሃይል ነው። መንግስት ፋኖን፣ ፋኖ መንግሥትን ለመረዳት ያብቃቸው ጸሎቴ ነው።
ማሳሰቢያ፡- ይህ ጽሁፍ፤ የጸሐፊው እንጂ የዝግጅት ክፍሉ አለመሆኑን ላስገነዝብ እወዳለሁ።

Read 2368 times