Monday, 26 September 2022 00:00

በማምለጫ ፍጥነት፤… የመምጠቂያ ብርታት!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 ለማምለጥም ይሁን ለመምጠቅ፣… እንዲሁ በባዶ ሜዳ ሊሆን አይችልም። “ከምን ወደ ምን?” ወይም ደግሞ፣ “ከየት ወዴት?” የሚል ጥያቄ አብሮት አለ። የመነሻና የመድረሻ ጥያቄ ይመጣበታል።
ያለ መነሻና ያለ መድረሻ፣ አጭርም ሆነ ረዥም፣ የማምለጥም ሆነ የመምጠቅ ጉዞ የለም። መነሻን ማወቅ፣ መድረሻን መምረጥ ደግሞ የሰዎች ድርሻ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። “እንዴት?” የሚለው የዘዴና የመንገድ ጥያቄ ይታከልበታል።
እዚህ ላይ ነው፣ “የማምለጫ ፍጥነት” (“escape velocity”) የተሰኘው የሳይንስ ፍሬ ሃሳብ የሚመጣው።
እንግዲህ፣ “ማምለጫ ፍጥነት” ሲባል፣… ከዋጋ ንረትና፣ ከኑሮ ችግር፣ ከኋላቀርነትና ከጦርነት ለማምለጥ ሊሆን ይችላል። እንደ ችግሩ ክብደት፣ እንደ መነሻችን ዝቅታ፣ እንደ አላማችን ከፍታ፣ የዚያኑ ያህል ከባድና ከፍተኛ ብርታትን ይጠይቃል።
ማምለጥ ሲባል፣… ከምድር ተስፈንጥሮ፣ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ዓለማችንን ለመዞር ሊሆን ይችላል (እንደ ብዙዎቹ ሳተላይቶች)። ወደ ጨረቃ፣ ከዚያም ባሻገር ወደ ማርስ ለመድረስ ካነጣጠርን ደግሞ፣ ለጉዞዎቻችን ርቀት የሚመጥኑ ከፍተኛ የማምለጫ ፍጥነቶች ያስፈልጉናል።
ሙሉ ለሙሉ ከምድር የስበት ኃይል ለመላቀቅ የተሰራ መንኮራኩርስ፣ በምን ያህል ፍጥነት ይወነጨፋል? እንዲህ አይነት ፍጥነት ነው፣ ቃል በቃል፣ “የማምለጫ ፍጥነት” የሚል ማዕረግ የሚያገኘው።
የመንኮራኩር የፍጥነት ዓይነቶችን አንድ ሁለቱን እናያለን።
እስከዚያው ግን፣ በምሳሌያዊ ዘይቤ፣ “ከዋጋ ንረት የሚገላግል የማምለጫ ፍጥነት ምን ያህል ነው? ከየትስ ይገኛል?” ብለን ብናስብ አይከፋም። ኑሮ ነዋ።
አዎ፣ ስለ ሳተላይትና ስለ ሮኬት ማሰብ በጣም ተገቢ ነው። ስለ ሕዋ ያልተመራመረ፣ ስለ ዓለማት ምህዋርና ዑደት ያላወቀ ትውልድ፣ አንድ ስንዝር ወደ ስልጣኔ መራመድ አይችልም። ቢሆንም ግን፣ ሰማየ ሰማያትን ስንመለከትና ስናስብ፣ እግራችን ስር እየተደናቀፈ የተጎሳቆለውን ሕይወት መርሳት አይኖርብንም። ከጉያችን ውስጥ ብዙዎችን እያንገበገበ ያለውን እለታዊ ኑሮ መዘንጋት የለብንም።
በሌላ አነጋገር፣ ከምድር ወደ ሕዋ ለመምጠቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከኑሮ ዝቅታ ወደ ኑሮ ከፍታ የሚያሸጋግር የማምለጫ ፍጥነትንም ማሰብ አለብን።
የኑሮ ችግርና ስራአጥነት፣… የዋጋ ንረትና የሃብት ብክነት፣… የመኖሪያ ቤትና ትራንስፖርት እጥረት… ምኑ ተወርቶ ያልቃል? ልናመልጣቸው የሚገቡ ብዙ አስቀያሚ ነገሮች አሉ።
ገሚሶቹ በየጊዜው የሚመጡና የሚያገረሹ አጣዳፊ ውጋቶች ናቸው።
ገሚሶቹ በጣም የከረሙና ስር የሰደዱ ፅኑ ህመሞች ናቸው።
ምንም ይሁኑ ምን፣ ከእነዚህ ሕመሞች ለመላቀቅና ለማምለጥ ማሰብ አለብን።
ከኑሮና ከኢኮኖሚ ጉዳዮች በተጨማሪ፤ የጦርነትና የግጭት፤ የሕገ-ወጥነትና የሥርዓት አልበኝነት፤ የጋጠወጥነትና የጥላቻ፤ የጭፍን እምነትና የዘረኝነት፤ የአሉቧልታና የክፋት በሽታዎችም አሉብን። ለቁጥር ያስቸግራሉ።
የቱንም ያህል ቢበዙ ግን፤ ሁሉም ህመሞች የሁላችንም ጉዳዮች ናቸው። የሰላምና የእርጋታ፤ የሕግና የሥርዓት፤ የጨዋነትና የመከባበር፤ የእውቀትና የስነ-ምግባር፤ የእውነትና የመልካምነት ጉዳዮች ናቸውና።
አዎ፣ ልናመልጣቸው የሚገቡ ነገሮች እንዘርዝራቸው ቢባሉ፣ ለቁጥር ያታክታሉ። ነገር ግን ማምለጫ የሌላቸው፣ በሰው አቅም የማይቻሉ የእጣ ፋንታ እስር ቤቶች አይደሉም።
ታዲያ፣… “መላቀቅ፤ መራቅ፤ ማምለጥ” ሲባል፤… የቁምነገሩን አንድ ጎን አጥርተን ለማየት ያህል እንጂ፤ ለብቻው ነጥለን፣ የህመም ፈላስፋ፣ የህመም ጎረቤትና ቤተኛ ለመሆን አይደለም። “ማምለጥ” የሚል ሃሳብ ላይ ብቻ አፍጥጠን ከቀረን፤ ትርጉም ያጣል።
መጥፎ ነገር ማምለጥ፤… በሌላ ጎኑ፤ ወደ ሌላ ወደ የተሻለ ነገር የመጓዝና የመድረስ ፍላጎትን ያጣመረ መሆን አለበት።
ፍላጎት ወይም ምኞት ብቻ ሳይሆን፤ ጥበብና ዘዴ፤ ጥረትና ፅናትም ጭምር ሊኖረን ይገባል ማለት ነው።
ከውርደት የማምለጥ ጥበብና ጥረት፤ ከዝቅታ የመውጣት ብልሃትና ፅናት፤… በሌላ ጎናቸው ሲታዩ፣ ወደ ክብር የሚያሸጋግሩ፤ ወደ ከፍታ የሚያንደርድሩና የሚያመጥቁ ኃያል ጉልበቶች ናቸው። ወይም ልናደርጋቸው ይገባል።
የማምለጫ ፍጥነት፤ የማድረሻ ፍጥነት ነው። ወይም መሆን አለበት። ወይም፣ መሆን እንዳለበት መርሳት የለብንም።
ከረባዳ ስፍራ ወደ ጉብታ፣ ከዝቅተኛ ቦታ ወደ ከፍታ የሚጓዝ መኪና፤ ዳገቱን ለመውጣት ይንደራደራል። የመኪናውን ጉልበት በማርሽ አስተካክሎና ነዳጅ ሰጥቶ ፍጥነቱን ይጨምራል። ታዲያ፣ ከረባዳው ስፍራ ለመውጣት፣ ከሸለቆው ለማምለጥ ብቻ አይደለም።
ዳገቱን አሸንፎ ከፍታው ላይ የሚያደርስ ጉልበት እንዲሆንለትም ነው - ፍጥነት መጨመሩ።
ድህነትን ለመቀነስና ከችግር ለማምለጥ ብቻ ሳይሆን፤ የስራ ፍሬ እንዲበረክትለት፣ ወደ ተሻለ ኑሮ ለመሸጋገር፤ ወደ ብልፅግና መንገድ ለመግባት መሆን አለበት - የሰው አላማ።
ከጦርነትና ከግጭት ለመገላገል ብቻ ሳይሆን የተረጋጋ ሰላማዊ ኑሮ ለማደላደል መሆን አለበት የሰዎች ሃሳብና ተግባር።
ሕገ-ወጥነትንና ስርዓት አርልበኝነትን የመግራት ጥረት፤… ሕግና ሥርዓትን ለማፅናት የሚረዳ፤ የመከባበርና የመተማመን ባሕል ለማስፋፋት፣ ለዚህም የሚያመች መንገድ ለመጥረግባ ከማቃናት የተወጠነ አላማ ሊሆን ይገባዋል።
ከይብስ ወይም ከትብስ ማምለጥ፤ ወደ ይሻል ወይም ወደ ትሻል ለመሄድ መሆን አለበት።
አለበለዚያ፤ መድረሻ ሳያውቁ መሬት መልቀቅና ለማምለጥ መሞከር፤ ከከንቱ ልፋት የዘለለ ትርፍ አያመጣልንም። ከከንቱ ልፋት የባሰ ኪሳራ ሊያመጣብን ግን ይችላል።
በዘፈቀደ መንደርደርና ሽቅብ መዝለል፤ ገደል ለመግባት ወይም ተመልሶ ለመፈጥፈጥ ሊሆን ይችላል።
የተሻለ ለመገንባት ካልሆነ በስተቀር ነባሩን ማፍረስ፤… አንድም ለመራቆት ነው። አልያም ከፍርስራሽ ስር ለመቀበር ነው።
በአጭሩ ምን ማለት ነው?
ማምለጥ ሲባል፤ ከመጥፎ ነገር ለመላቀቅ፣ ርቆ ለመሄድ፣ ከችግር ለማምለጥ ቢሆንም፤ ጎን ለጎን ወደ ተሻለ ደረጃ መጓዝንና ወደ ከፍታ መድረስን ሊያጣምር እንደሚገባው መዘንጋት የለብንም።
በሌላ በኩል ግን፤ ወደ ከፍታ የመድረስና ስኬትን የመቀዳጀት አላማ እስከያዝን ድረስ፣ “የዛሬ ችግሮቻችንን እንርሳ” ማለት አይደለም።
ህመሙን ያላወቀ አገር፣ ከበሽታ ማምለጥና ጤንነትን ማግኘት አይችልም። መነሻውንና ነባር አቅሞቹንና ችግሮቹን በትክክል ያልተገነዘበ ሰው፣ ወደ አዲስ አድራሻ የመገስገስ እድል አይኖረውም። አላማውም እውን ሊሆን አይችልም።
መነሻችንን እና አቅማችንን ማወቅ፣…
አላማችንንና መድረሻችንን መምረጥ፣…
የኛ የሰዎች ሃላፊነት ነው።
ያለንበት መነሻ፣… በጣም ዝቅተኛ ቦታ ከሆነ፣ እጅግ የከፋ ትርምስና ጉስቁልና፣ ስር የሰደደ የጭፍንነትና የጥላቻ መቀመቅ ውስጥ የምንገኝ ሰዎች ከሆንን፣…
ወደ ከፍታ ለመጓዝ ብዙ ዳገት ይጠብቀናል።
በብርቱ መንደርደር ይኖርብናል።
በየእርከኑ ትንፋሽ እየወሰድን፣ ተስፋ ሳንቆርጥና ሳንታክት፣ እንደገና ወደ ተሻለ ከፍታ ለመሻገር እየደጋገምን የመንደርደር ትጋትና ጽናት ያስፈልገናል።
እንደ መነሻው ዝቅታ፣ እንደ መድረሻው ከፍታ ነው - የማምለጫና የመምጠቂያ ፍጥነት።
አውሮፕላኖች አየር ላይ ለመብረር፣ መሬት ላይ መነሻና መንደርደሪያ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውሱ። ከምድር መነሳትና መብረር የሚችሉት በፍጥነት ሲንደረደሩ ብቻ ነው። ለዚህም ነው፤ ሁለት ኪሎ ሜትር ሶስት ኪሎ ሜትር መንደርደሪያ የሚያስልጋቸው፤ እንደ አውሮፕላኖቹ አይነትና ጭነት። አየር ላይ ከወጡ በኋላም፣ ትክክለኛው “የበረራ ፍጥነት” ላይ መድረስ አለባቸው።
መነሻቸው ግን አየር ላይ አይደለም። መነሻቸው መሬት ነው። በሃይለኛ “ሞተሮች” (ኢንጂኖች) ግፊት ይንደረደራሉ። መፍጠን አለባቸው። ከመሬት መነሳት የሚችሉበት ፍጥነት፣ Take-off speed ይሉታል። የማኮብኮቢያ ፍጥነት እንበለው። ከዚህ ፍጥነት በታች ከሆኑ፣ መሬትን መልቀቅና መብረር አይችሉም።
መሬትን ከለቀቁና ካኮበኮቡም ጉዳቸው ነው። አየር ላይ ደግፎ የሚይዝ ወለል የለም። መተማመኛቸው ሌላ ሳይሆን ፍጥነታቸው ነው። ማለትም ቀስ ብለው መብረር አይችሉም።
የመፍጠን ጉልበት ከሌላቸው ባይንደረደሩና መሬትን ባይለቅቁ ይሻላቸዋል።
በአጭሩ፣ “የማኮብኮቢያ ፍጥነት”፣… ከዚያም “የበረራ ፍጥነት” ያስፈልጋቸዋል - አውሮፕላኖች።
የሮኬት ሰዎች ደግሞ፣ “escape velocity” ይላሉ። በእርግጥ፣ የዚህ ሃሳብ ምንጭ፣ አይዛክ ኒውተን ነው። ኒውተን ካፈለቃቸው እልፍ የሳይንስ ሃሳቦችና ቀመሮች መካከል አንዱ፣ “የማምለጫ ፍጥነት” የተሰኘው ሃሳብ ነው።
ነገሩ ምንድነው? የመሬት ስበት ከምንለው ነገር ጋር የተዛመደ ነው።
ከመቶ ሜትር ከፍታ፣ አንድ ጠጠር፣ ብይ ወይም አሎሎ ቢለቀቁ፣ በመጀመሪያው ሴኮንድ 5 ሜትር ይወርዳሉ። በሁለተኛው ሴኮንድ 15 ሜትር ወደታች ይጓዛሉ።
በሦስኛው ሴኮንድ 25 ሜትር ይወርዳሉ። በእያንዳንዱ ሴኮንድ ፍጥነታቸው በ10 ይጨምራል። ይህ ቁጥር፣ የምድራችንን የስበት መጠን የሚያመለክት ባሕርይ ነው።
የጨረቃ ከዚህ ያንሳል። የፀሐይ ደግሞ እጅግ ይበልጣል። ክብደታቸውና ግዝፈታቸው ከምድር ይለያልና። የስበት ኃይላቸውም እንደዚያው ይበላለጣል። ከከፍታ የተለቀቀ ጠጠር ወይም አሎሎ ወደ ወለል የሚደርስበት የፍጥነት ግስጋሴም የዚያኑ ያህል ይለያያል - በጨረቃ፣ በምድር፣ በፀሐይ አጠገብ።
ያለ በቂ ጉልበት፣ ያለ በቂ ፍጥነት ሽቅብ የተወነጨፈ ሮኬት፣ ግማሽ መንገድ ተጉዞ ቁልቁል ተመልሶ ይወርዳል። አወዳደቁ አይጣል ነው። የምድር ስበት ኃይለኛ ነው።
15 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ ደርሶ ነዳጅ ያለቀበት ሮኬት፣ ወደ ምድር ተመልሶ ለመፈጥፈጥ አንድ ደቂቃ አይፈጅበትም። ከምድር ጋር የሚላተምበት ፍጥነት “በአንድ ሰዓት ከ1500 ኪሎ ሜትር በላይ የመክነፍ” ያህል ነው።
በዚህ ፍጥነት ከአለት ጋር የተላተመ ሮኬት፣ ለምልክት ያህል ከተረፈ ተዓምር ነው። መነሻ ቦታና መነሻ አቅምን ሳያውቁ ሽቅብ መዝለል፣ ይህን የመሰለ መዘዝ ያስከትላል።
በትክክል ለመምጠቅስ?
ከጨረቃ ላይ መምጠቅ ቀላል ነው። ከምድር ላይ ደግሞ ይከብዳል። እንደ ስበት ኃይላቸው ነው ልዩነቱ። በሌላ አነጋገር፣ የማምጠቂያና የማምለጫ ፍጥነት፣ እንደ መነሻው ቦታ ይለያያል።
ይህም ብቻ አይደለም። መድረሻውም ልዩነት ያመጣል።
ከምድር፣ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚሽከረከሩ ሳተላይቶች አሉ። በየቀኑ ምድርን ከ5 ጊዜ በላይ ይዞራሉ።
በ20 ሺ ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ በቀን ሁለቴ ምድርን የሚዞሩ “የጂፒኤስ ሳተላይቶችም” አሉ።
ከምድር በ35 ሺ ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኙ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማሰራጫ ሳተላይቶች ደግሞ፣ በየቀኑ አንዴ ምድርን ይዞራሉ።
ምን ማለት ነው? ከምድር ያላቸው ርቀት ይለያል። እንደ አገልግሎታቸውና እንደ አላማቸው መድረሻቸው ይራራቃል።
ወደ ጨረቃ የሚመጥቅ መንኮራኩር ደግሞ፣ ከምድር ተነስቶ ከ350 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛል።
እነዚህን ሁሉ ከምድር ለማምጠቅ፣ የተለያየ የጉዞ ፍጥነት ወይም ጉልበት ያስፈልጋል። ጨርሶ ከምድር ስበት ለመላቀቅና ለማምለጥ ደግሞ፣ ተጨማሪ ፍጥነት መኖር አለበት።
ከምድረ ገፅ ተነስቶ፣ 11 ሺ ሜትር በሴኮንድ መምዘግዘግ ከቻለ፣ ከምድር ስበት አምልጦ፣ ወደ ሌሎች ዓለማት መጓዝ ይችላል። በሰዓት 40ሺ ኪሎ ሜትር እንደ መጓዝ ነው ፍጥነቱ።
መነሻው ታውቆ፣ መድረሻው ደግሞ ተመርጦ፣ ከኒውተን በመነጨው ቀመር ሲሰላ ይሄን ይመስላል - የማምለጫና የማምጠቂያ ፍጥነት።

Read 9238 times