Saturday, 24 September 2022 16:57

32ኛው ዋና አሰልጣኝ ውበቱና የ22ኛው ዓለም ዋንጫ 32 አሰልጣኞች አመታዊ ደሞዝ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)


       ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን  ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በሃላፊነት ይዘው እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡  የብሄራዊ ቡድን ሃላፊነቱን ከሁለት ዓመት በፊት መስከረም 18 ላይ ይዘው የነበሩት አሰልጣኙ በመጀመርያ ስራ ዘመናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በካሜሮን በተስተናገደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ይዘው የቀረቡ ሲሆን፤  ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ደግሞ በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ  ወይም የቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚያበቃውን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባከናወነው የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈፃሚ ምርጫ  የዋና አሰልጣኙ ኮንትራት የማራዘሙ  ጉዳይ ዘግይቶ ነበር፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ  ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ብሄራዊ ቡድኑን ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በሃላፊነት ይዘው እንዲቆዩ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ለሶስት ጊዜያት ባካሄዳቸው ስብሰባዎች የዋና አሰልጣኙን ያለፉት ዓመታት የስራ ተመክሮ ገምግሟል፡፡ የሚከፈላቸውን ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም የሚያሳድግበትን ውሳኔም አሳልፏል፡፡ የፌደሬሽኑ ዋና ፀሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በብሄራዊ ቡድን ሃላፊነታቸው የተጣራ ወርሃዊ ደሞዛቸው 250 ሺ ብር (57980 ዩሮ በዓመት) ብር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከሚያገኟቸው  ጥቅማ ጥቅሞች የቢዝነስ በራራ፤ የትምህርትና የስልጠና ክፍያዎችን በፌደሬሽኑ ሊሸፈንላቸው ስምምነት መደረጉን ተመልክቷል። የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ  በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ብሄራዊ ቡድኑ በቻን በሚያደርገው ተሳትፎ ካለፈው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብና በ2023 ኮትዲቯር ላይ በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  ላይ እንዲያልፍ መስራት እንደሚኖርባቸውም አሳስቧል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሁለት ዓመት በቆዩበት የስራ ዘመናቸው ከፍተኛ ፈተና የሆነባቸው ጉዳይ ለካፍ እና ለፊፋ ጨዋታዎች የሚመጥኑ ስታድዬሞች ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመኖራቸው የተፈጠሩ ሁኔታዎች ናቸው።   ‹‹ከተጫወትናቸው 19 የነጥብ ጨዋታዎች አራቱን ብቻ ነው በሜዳችን የተጫወትነው። 15 ጨዋታዎች ከሜዳ ውጭ መጫወት ቀላል አይደለም፡፡ ተጨዋቾች ከሜዳቸው ውጭ በልበሙሉነት የሚጫወቱበትን ልምድ ማዳበር ችለናል፡፡›› በማለት ፈተናው ቡድኑን ሊያጠነክረው መብቃቱን  ገልፀዋል፡፡
ከዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በፊት
በኢትዮጵያ  ብሄራዊ ቡድን 64 ዓመታት ታሪክ 31ኛው ዋና አሰልጣኝ እንዲሁም 19ኛው ኢትዮጵያዊ  አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ከዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በፊት ብሄራዊ ቡድኑ በታሪኩ 18 ኢትዮጵያዊና 13 የውጭ  አሰልጣኞች በሃላፊነቱ ሰርተዋል፡፡ ከዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩ 31 አሰልጣኞች ከዚህ በታች የቀረቡት ናቸው፡፡ (የስራ ዘመናቸው የተቀመጠው እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር ነው)
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩ 18 ኢትዮጵያ  አሰልጣኞች  የሚከተሉት ናቸው፡፡ ይድነቃቸውተሰማ  (1961–1962) እና (1963)፤ ሉችያኖ ቫሳሎ (1969–1970)፤ አዳሙ አለሙ (1970)፤ መንግስቱ ወርቁ (1977–1978)፣ (1980–1982) እና (1987)፤ ጥላሁን ተስፋዬ (1984)፤ ካሳሁን ተካ (1992–1993)፣(1994–1995) እና (1997)፤ ጌታሁን ገብረጊዮርጊስ (1993) ፤ ስዩም አባተ (1996)፣ (1998–2000) እና (2006)፤ ኦኮ ኢዲባ  (1997)፤ አስራት ሃይሌ (2001)፣ (2003)እና  (2004)፤ ስዩም ከበደ (2003–2004)፤ ሰውነት ቢሻው (2004–2006) እና (2011–2014)፤  ተስፋዬ ፈጠነ (2007)፤  ፀጋዬ ደስታ (2007)፤  አብርሃም ተክለሃይማኖት (2008–2010) ፤ ዮሃንስ ሳህሌ (2015–2016)፤ ገብረመድህን ሃይሌ (2016)፤ አሸናፊ በቀለ (2017) እና  አብርሃም መብራቱ  (2018–2020) ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ  ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩ ከ10 አገራት የተውጣጡ 13 የውጭ አአሰልጣኞች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው። ኤድዋርድ ቪርቪሊስ ከግሪክ 1950–1954)፤ ጆርጅ ብራውን ከኦስትሪያ (1954–1956)፤ ጂሪ ስታሮስታ ከቼክስሎቫኪያ (1959)፤ ስላቫኮ ሚሎሶቪች ከዩጎዝላቪያ (1961) እና (1962)፤ ፈርኔክ ስዙኩስ ከሃንጋሪ  (1968–1969)፤ ፒተር ሽናይትገር ከምዕራብ ጀርመን (1974–1976)፤ ክላውስ ኢቢጋውሰን ከጀርመን፤ (1987–1989)፤ ጆሃን ፊገ ከጀርመን(2002–2003)፤ ዲያጎ ጋርዚያቶ ከጣሊያን (2006–2007)፤ ኢፊ ኦኑራ ከስኮትላንድ (2010–2011)፤ ቶም ሴንትፌይት ከቤልጅዬም (2011) እንዲሁም ማርያኖ ባሬቶ ከፖርቱጋል ናቸው፡፡

Read 1195 times