Saturday, 24 September 2022 17:37

የጎጆ ብሪጅ ሀውስ ቤት እጣ አወጣጥ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከዳሽን ባንክ ጋር የሁለትዮሽ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል



         ጎጆ ብሪጅ ሃውሲንግ  ትሬዲንግ ባለፈው ማክሰኞ መስከረም 10 በወዳጅነት አደባባይ ባዘጋጀው ልዩ መርሃ ግብር  ላይ ከዳሽን ባንክ ጋር የሁለትዮሽ መግባቢያ ሰነድ የተፈራረመ ሲሆን ጎጆ ብሪጅ ሀውስ ላደራጃቸው የተለያዩ ማህበራትም የካርታ ርክክብ አድርጓል።
በተጨማሪም ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ  ከ7 ሺህ 400 በላይ አባላትን መዝግቦ ለ95 የሀገር ውስጥ ሮስካ ባለዕድለኞች  ዕጣ የማውጣት ሥነሥርዓት  ለማካሄድ መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ አንዳንድ ደንበኞች ስማቸው በዕጣ ዝርዝር ውስጥ ባለመካተቱና  በቴሌግራም በተላከው  መልዕክት ላይ ስማቸው ባለመኖሩ ምክንያት ከባለዕቁብተኞች/ከደንበኞቹ/ በተነሳ ቅሬታ መሰረት ላልተወሰነ ቀን የዕጣ ማውጣት ሥነሥርዓቱ ተራዝሟል። ይህም አሰራሩን የበለጠ ግልፅና ታማኝ ያደርገዋልም ተብሏል ።
የጎጆ ሮስካ እቁብ ሞዴል ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲችል ቀጣዩን 20 ሺህ አባላት ያለበትን መደብ ቤት ፈላጊዎችን ለመድረስ ጎጆ ብሪጅ አንድ ስልት የቀየሰ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ለዚህም በመጀመሪያ ዙር ለዕጣ የቀረቡ 7438 አባላት የጎጆ ብሪጅ ሀውስ አምባሳደሮች ሆነው ተሹመዋል። ይህም ለቀጣዩ ምዝገባ ቤት ፈላጊዎችን ለሚያመጡ አባላት ክፍያ ለመፈፀም የተዘጋጀ ነው ተብሏል። አባላቱ ተግተው ከሰሩ ከወርሃዊ ቁጠባ ነፃ ሊያደርጋቸው ስለሚችል የተሰጣቸውን የአምባሳደርነት ዕድል በመጠቀም ራሳቸውንና ቤት ፈላጊ ማህበረሰቡን እንዲጠቅሙ ጥሪ ቀርቧል።
የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓቱን ግልፅና  ፍፁም ታማኝ ለማድረግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ እንደሚሰራ የተገለፀ ሲሆን፤ በቀጣይም ለበርካታ ቤት ፈላጊ የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎታቸውን ለማርካት በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።


Read 11640 times