Saturday, 24 September 2022 17:48

የጆሽዋ ሽልማት

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(1 Vote)

 (Life is Beautiful የሚለው ፊልም እንደ አጭር ልብወለድ)
                  ኢዮብ ካሣ


        ግሪዶ እና ልዕልት ዶራ ከጋብቻ በፊት ረዥም የፍቅር ጊዜ አሳልፈዋል ቢባል የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ትውውቃቸው የአጭር ጊዜ ነበር፡፡ በግሪዶ ኪሚክነትና ጨዋታ አዋቂነት ልዕልቲቱ ተማርካለች፡፡ አለዚያማ ሁለቱን በትዳር የሚያስተሳስር ተመሳሳይ የዘር ሀረግ የላቸውም፡፡ ልዕልቲቱ ያው ልዕልት ነች፤ የንጉስ ዘር! እናም ደረጃዋን የሚመጥን ባል መጥቶላታል፡፡ ቤተሰቡ ልጃችን ለወግ ማዕረግ በቃች ብሎ ቢደሰትም በልዕልቷ ልብ ውስጥ ቤቱን ሰርቶ የተቀመጠው የግሪዶ ፍቅር ነው። ቤተሰቡ ልዕልት ልጃቸው ከአንድ መናጢ ድሀ ጋር የጀመረችው ምስጢራዊ ግንኙነት ብግን ቢያደርጋቸውም የሚዘይዱት መላ ጠፍቶባቸዋል፡፡ እናም የሰርጉን ቀን ማፍጠን ብቻ ነው ያለው አማራጭ ተብሎ ተወስኗል፡፡
ልዕልቲቱ ወደደችም ጠላች የሰርግ ዕለቱ ይፋ በሚሆንበት የዳንስ ምሽት ላይ መገኘቷ ግድ ነበር። የዳንስ በዓሉ የተደረገው ግሪዶ በአሳላፊነት በሚሰራበት ትልቅ ሆቴል ነው፡፡ ድግሱ ድንገተኛ ነበርና ግሪዶ ወሬውን አልሰማም። ድንገት ልዕልቲቱን ፍቅረኛውን ባየ ሰዓት የልብ ምቱ ጨመረ፤ የሚሰራው የሚያደርገው ጠፋው፡፡ በእጁ የያዘውን መድፋት፤ መገልበጥ ብቻ ሆነ ሥራው፡፡ የፍቅረኛውን ዓይን ለማየት ሲያጮልቅ ድንገት ዓይን ለዓይን ተገናኙ። እጁ ላይ የነበረው ትሪ ከእጁ አመለጠውና ብስኩታ-ብስኩቶቹ ወለሉ ላይ ተገለበጡ። የተገለበጠውን ለመሰብሰብ ጠረጴዛው ስር ባጎነበሰ ጊዜ ልዕልት ዶራ ከወንበሯ ተንሸራታ ጠረጴዛው ስር አገኘችው፡፡ አዳራሹ በሳቅና ሁካታ በተሞላባት በዚች ቅፅበት፤ ሁለቱ የስርቆሽ የፍቅር ዓለማቸውን ፍለጋ ላይ ነበሩ። ጠረጴዛው ሥር በእንብርክካቸው እንዳሉ ተሳሳሙ፡፡ ልዕልት ዶራ ግሪዶ ከዚህ አዳራሽ ይዟት ይጠፋ ዘንድ ተማፀነችው፡፡ “እባከህ ከዚህ ይዘኸኝ ጥፋ!” አለችው፡፡
ልዕልት ዶራ ሀብት፤ ማዕረግና ዘር ለምኔ ብላ ኑሮዋን ከግሪዶ ጋር መሰረተች፡፡ ፍቅር ጮቤ ረገጠ፡፡ ትዳራቸው ሞቀ፡፡ የሁለቱ ሥምረት ሙቀት ደግሞ የአብራካቸው ክፋይ የሆነውን ህፃን ፈጠረላቸው፡፡ ጆሹዋ የቤተሰቡን ቁጥር ወደ ሶስት ከፍ አደረገው፡፡ በዚህ ደስታና ፍቅር በሰፈነበት ቤት የሚመቀኝና ዓይኑ ደም የሚለብስ፣ ልዕልቲቷ ትገባኛለች ባይና ከወላጆቿም የልብ ልብ ያገኘ አንድ የዘመኑ ሀብታም ነበር። ይህ ሰው የሚመኛትን ሴት ባለማግኘቱ ቂም በሆዱ አረገዘ። ግሪዶን ማጥፊያ፣ ትዳሩን ማፍረሻ፣ ፍቅሩን ማርከሺያ ተንኮል መተብተብ ጀመረ።
ግሪዶ ፈቃድ ለማግኘት ረዥም ጊዜ የወሰደበት የመጽሐፍ መደብር ተከፍቶ ስራ ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል። ገበያው ደርቷል። ጆሽዋ በእድሜና በቁመት ከፍ ብሏል። አንዳንዴ ከአባቱ ጋር በብስክሌት እየተፈናጠጠ ወደ መደብሩ ይሄዳል፡፡ ማታ ተሰባስበው ወደ ቤት ይገባሉ። በዚህ መሀል አንድ ድንገተኛ ሁኔታ ተፈጠረ። ግሪዶ በማያውቀው ምክንያት ትፈለጋለህ እየተባለ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መጠራት ከጀመረ ሁለት ሶስት ጊዜ ሆነው። አንዳንዴ አንድ ሁለት የማይረባ ጥያቄ ይጠይቁትና ሂድ ይሉታል። ሌላ ጊዜ ፖሊስ ጣቢያ ብቻ አድርሰው ይመልሱታል። በእርሱ መንገላታት የሚደሰትና “አገኘሁህ!” የሚል ሰው ያለ ነው የሚመስለው።
***
ዛሬ የጆሽዋ ልደት ነው። የግሪዶ አጎት ሊዮ ከሆቴሉ ለልደቱ የሚያስፈልጉ የምግብ ዘሮችን አምጥቷል። አንድ ልጃቸው ነውና ድግሱ ሞቅ ደመቅ ብሏል። ጆሽዋ የአሻንጉሊት ታንክ ተገዝቶለታል። ወደዚህ ቤት ዝር ብለው የማያውቁት የልዕልቷ እናት እንኳ ዛሬ ይህን ቤት ይጎበኛሉ። ልጃቸው በሰረገላ ይዛቸው ለመምጣት  ወደ ቤታቸው ሄዳለች።
 ልዕልት ዶራ ከእናቷ ጋር ቤት በደረሰች ጊዜ በአይኗ ያየችውን ማመን አልቻለችም። የተዘጋጀው የምግብ ቡፌ ተገለባብጧል፣ ዕቃዎች ተሰባብረዋል። ቤቱ የሀዘን ድባብ ወርሶታል። “ሌላ ማንም አይደለም እነሱ ናቸው?” አለች ዶራ ጭንቅላቷን በሁለት እጆቿ ይዛ። እናት ግራ ገብቷቸው ተደናግጠዋል።
***
ትልቅ የጦር ሰራዊት መኪና ከፊት ለፊት ተገትሯል። በፖሊስ ሀይል በውዳጅም ሆነ በግዳጅ ተሰባስበው የተያዙ ሰዎች ቆመዋል። ብዙዎቹ አይሁዳውያን ናቸው። አንዳንዶቹ በከፊል የአይሁድ ዘር ያለባቸው ጥቂቶቹ ደግሞ አይሁዳውያን ባይሆኑም ተጠርጣሪዎች ናቸው። የጀርመን መንግስት ዘር የማጥራት ዘመቻውን እንቅስቃሴ ከጀመረ ጥቂት ወራት አልፈዋል። ሰዎች አይሁዳውያን መሆናቸውን ለመጠቆምና ለማስፈራራት ልዩ ልዩ ዘዴ ሲጠቀሙ ሰንብተዋል። የአጎት ሊዮን ፈረስ በቀለም አዥጎርጉረው “የአይሁድ ፈረስ” የሚል ጽሁፍ በቀለም ጽፈውበታል። አጎት ሊዮ በዚህ አቅላቸውን አጥተዋል፣ ተናደዋል። ግሪዶ ጉዳዩ ብዙም የሚያስጨንቅ እንዳልሆነ ነበር የነገራቸው። አጎት ሊዮን ግን “ግዴለህም ይች ነገር፣ ነገር አላት! ምን አለህ በለኝ ግሪዶ፣ በመጨረሻ ወደ አንተ ይመጣሉ!” አሉት። የተናገሩት መሬት ጠብ አላለም።
“ወዴት ነው የምንሄደው?” አለ ህጻኑ ጆሽዋ መኪናው ላይ ከተሳፈሩ በኋላ፤ “ሽርሽር ነዋ! ልደትህ እኮ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ለብዙ ወራት ሳስብ ነው የቆየሁት” አለና መለሰ ግሪዶ። ልጅን የሚያየውን ነገር፣ አንተ ያየኸው አይደለም፤ እኔ የምነግርህ ነው ልክ ብሎ ማሳመን እጅግ ከባድ ነው። ቀጠለና “አይዞህ ጆሽዋ ይህ መኪና በቅድሚያ የያዝነው ነው” አለ።
የጦር ሰራዊቱ መኪና በተሳፋሪ ተጨናንቋል። ፖሊሶቹ ተሳፋሪውን እየገፉ በደንብ ከጠቀጠቁ በኋላ መኪናው ተንቀሳቀሰ። ግሪዶ ራሱ የት እንደሚወስዱት አንዳች የሚያውቀው ነገር የለውም። በየደቂቃው ህፃኑ ጆሽዋ የሚጠይቀውን መመለስ ደግሞ ግድ ነው። አንዳንዴም የተናገረው እውነት እንዲመስልለት “አይደለም አጎት ሊዮ?” ብሎ ይጠይቃል። “ትክክል ነው ጆሽዋ” ይላሉ፤አጎት ሊዮ፡፡ ጆሽዋ ብዙም ሳይጓዝ በአባቱ እቅፍ እንዳ እንቅልፍ ይዞት ጭልጥ አለ። አይ የልጅ ነገር! መኪናው ያለ አንዳች እረፍት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቆራረጠ።  አንድ የባቡር ጣቢያ ሲደርስ ቆመና የተጫኑት ሰዎች ሁሉ ወረዱ።
ብዙም ጊዜ ሳይፈጅ ወዲያው ወደ ባቡሩ እንዲገቡ ትዕዛዝ ተላለፈ። ወንድ፣ ሴት፣ ህፃን፣ አሮጊት፣ ሽማግሌ ሳይል ሁሉም በአንድ ላይ ተሰገሰጉ። አሁን ጉዞው የአይሁዶች ማሰሪያ ወደሆነው ካምፕ ነው። አጎት ሊዮ፣ ግሪዶና ጆሽዋ የሽቦ መስኮት ባለው የባቡር ፉርጎ ነው የተሳፈሩት። የአዛዡ “ሂድ” የሚል ቃል እየተጠበቀ ነው። ባቡሩ ጭሱን እያንቦለቦለና እየተንዶቀዶቀ ነው። ወዲያው ባቡሩ እንዲሄድ ትዕዛዝ ተላለፈ። ባቡሩ ሊንቀሳቀስ ድምጹን አጓራ። ወዲያው ደግሞ እንዲቆዩ የሚል ትዕዛዝ በእጅ ምልክት ተሰጠው። አንዲት ውብ ሴት ወደ ባቡሩ ለመግባት ስትራመድ ታየች። የተሳፋሪውን ስሜት የቀሰቀሰውና ትኩረት የሳበው የጆሽዋ ጩኸት ነበር።
“እማማ! እማማ ያቻት!” አለ።  ብዙዎቹን አስገርሟል የልዕልቷ ድርጊት። በዚህ ባቡር የተሳፈሩ ሁሉ ታድነው የተያዙ ናቸው። በመንግስት የሚፈለጉና አይሁዶች የተባሉ ናቸው። ልዕልቲቷን ግን የፈለጋት የለም! አዛዦቹ “አልተፈለግሽም” ቢሏትም በጄ የምትል አልሆነችም። ባሏን፣ ፍቅሯን፣ ልጇን ተከትላ መምጣቷ ነው። ግሪዶ እጇን ያዘና ወደ ባቡሩ እንድትወጣ ረዳት።
“ባቡሩን አልወደውም!” አለ ጆሽዋ፤ ወደ እስር ቤት ለመግባት ተሰልፈው ሳለ፡-
“እሽ አውቶብስ እንይዛለን” አለ ግሪዶ።
“ወዴት ነው የምንሄደው አባባ?”
እንግዲህ ችግሩ ጀመረ። ህፃናት ማወቅ ይፈልጋሉ። ባወቁት አይቆሙም፤ጥያቄያቸውን ይቀጥላሉ። እውነት ያለችው በህፃናት አፍ ጫፍ ላይ ነው ይላሉ ፈረንሳዮች።
“ጨዋታ ልንጫወት ነዋ! ውድድር አለ! ጨዋታውን የተሸነፈ በፍጥነት ወደ ቤቱ ይላካል። ያሸነፈ ግን አንደኛ ሽልማት ያገኛል”
“ሽልማቱ ምንድን ነው?” ጠየቀ ጆሽዋ በጉጉት።
“ታንክ ነው!” አሉ አጎት ሊዮ።
“ታንክማ አለኝ!”
“ይሄኛው የመጫወቻ አይደለም! የእውነት ነው! የእውነት ታንክ!”
ሰልፉ በቀስታ እየተጎተተ ሄዶ ሄዶ ሁሉም በየክፍሉ ገባ። ልዕልት ዶራ ወደ ሴቶቹ የእስር ክፍል፣ አጎት ሊዮ ወደ አዛውንቶቹ ክፍል። ግሪዶና ጆሽዋ ደግሞ ወደ አንድ ሌላ ክፍል አመሩ። ጆሽዋ በሁኔታው የተደሰተ አይመስልም። የሽልማቱ ነገር እንዳልተዋጠለት የፊቱ ገጽታ ይመሰክራል።
“አባባ እኔ እርቦኛል” አለ ጆሽዋ።
“ቆይ ይመጣል! አሁኑኑ፣ ዳቦና ማርማላት ከች ይላል!” አለ ግሪዶ። ወዲያው በዚያው ክፍል ወደቆየው እስረኛ ዞር አለና “ለእናንተ መጥቶላችኋል?” ብሎ ጠየቀው። ኮስማናው እስረኛ ጭንቅላቱን በአዎንታ ነቀነቀ።
“በቃ በሁለተኛው ዙር ይደርሰናል” ብሎ ሊያባብለው ሞከረ። ግሪዶ ከእስሩ ስቃይና የጉልበት ሥራው በበለጠ ልጁ ጆሽዋ እስር ቤት ስለመኖሩ እንዳያውቅ ለማድረግ ብዙ ልፋት፣ ብዙ ጭንቀት የሚጠይቅ ነበር። እስሩን እንዲረሳ፣ በከፍተኛ ሙቀት ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላኛው እየተሸከሙ የሚያደርሱትን ከባባድ ብረቶች እንዲዘነጋ የሚያደርገው ሃይል ቢኖር የጆሽዋ በዚህ እስር ቤት መኖር ነበር። ሁሌም እዚያ የመጡት ለሽርሽርና ለውድድር መሆኑን ህጻኑን ማሳመን ይጠበቅበታልና በየጊዜው የባጥ የቆጡን ይቀባጥራል።
“አባባ አሁን ስንት ነጥብ አለን?” ይጠይቃል ጆሽዋ። ልጅና ወረቀት የነገሩትን አይረሳም!
“ስድስት መቶ ሰማኒያ”
“ታንኩን ለመውሰድ ስንት ነጥብ ነው የሚያስፈልገን?”
“ዘጠኝ መቶ ስልሳ”
“ከዚያ ታንኩ ይሰጠናል?”
“አዎ ግን መበርታት፣ ጎበዝ መሆን አለብህ”
የእስር ቤቱ ኃላፊ ጄኔራል ከሌሎቹ ጋሻ ጃግሬዎቹ ጋር ሆነው፣ እነ ግሪዶ ወዳሉበት ክፍል መጡ። ለአዳዲሶቹ የእስረኛ አባላት የእስር ቤቱን ደንብና ስርዓት ለማሳወቅ ነው የመጡት። ከጀርመንኛ በቀር እንግሊዝኛ ጆሯቸውን ቢቆርጧቸው አይሰሙም። ጀርመንኛን ወደ እንግሊዝኛ ማስተርጎም የሚችል እንዳለ ተጠየቀ። ግሪዶ እጁን ለማውጣት ማሰብ እንኳን አላስፈለገውም። ወዲያው ከጄነራሉ ጎን ቆሞ ጆሽዋን በአይኑ ጠቀሰው፡፡
“ማንም እስረኛ ከጠዋቱ 1 ሰዓት በኋላ መኝታ አይፈቀድለትም።” አሉ ጄነራሉ።
“ጨዋታውን ያላሸነፈ ሽልማቱን አያገኝም” አለ ግሪዶ የእንግሊዝኛ ትርጉሙን ሲሰጥ።
“የጉልበት ስራው ላይ ማላገጥ አይቻልም” የጄነራሉ ንግግር ነበር።
“ተወዳዳሪው ነጥቦቹን ማሟላት አለበት” ግሪዶ ጆሽዋን እያየ ነበር ትርጉሙን የሚሰጠው።
በዚህ ሰዓት ጆሽዋ በጉጉት ስሜት አባቱ የሚያስተረጉመውን ሲሰማ በዚያ የእስር ካምፕ በደስታ የተዋጠ ብቸኛ ሰው ሆነ። ሌላው እስረኛ ሁሉ ግን በነገሩ ግራ ተጋብቶ ነበር። ምልአተ እስረኛው ፊት የመወነባበድ ስሜት ይነበባል።
ጄኔራሉ፤ “ለማምለጥ የሞከረ ወዲያው ይገደላል!”
ትርጉም፤ “ትናንት የተሸናፊዎቹን ሃያ ስምንት ከረሜላ እኛ በላነው”
በዚህ ጊዜ ጆሽዋ አፉን ይዞ ሳቅ ጀመረ።
ጄኔራሉ፤ “በእንግሊዝኛ ብዙ ማውራት አይቻልም”
ትርጉም፤ “ሽልማቱን፣ ታንኩን ለማግኘት ጠንክር”
ጄነራሉ ንግግራቸውን ጨርሰው ወጡ። በክፍሉ ጉምጉምታ ነገሰ። እስረኛው ግሪዶ በተረጎመው ነገር ግራ ተጋባ።
“ምንድነው ነገሩ?...” አለ አንዱ የቆየ እስረኛ ለግሪዶ።
“አይ እኔን ተዉኝ፤ እኔ አፌን ቢቆርጡኝ አንዲት ጀርመንኛ አልናገርም። ጀርመንኛ አላውቅም እኮ!” አላቸው።
***
የእስር ቤቱ ኑሮው ጥቂት ወራትን አስቆጠረ። ጆሽዋ በእናት ናፍቆት ተንገበገበ። በየጊዜው “እማማ! እማማ” ማለቱ አልቀረም። ግሪዶ ማባበሉንና ማታለሉን አልተወም። ግሪዶ ደስ ባይለውም ጆሽዋ ከሌሎች የእስር ቤቱ ህፃናት ጋር መገናኘቱ ግድ ነበር። ከልጆቹ ጋር በዋለ ቁጥር ደግሞ ለብዙ ጊዜ ሲነግረው የከረመውን የሚያፈርስ ነገር ነው ሰምቶ የሚመጣው።
“አባባ ማንም ስለሽልማቱ የሚያውቅ ልጅ የለም። ውሸት ነው!”
“አውቀው ነው የለም የሚሉህ፤ ሊወስዱብህ”
“አላምንህም ውሸትህን ነው!”
“ነገርኩህ ጆሽዋ፤ ሲያታልሉህ ነው”
አንድ ቀን ግሪዶ ከእለቱ እልህ አስጨራሽ የጉልበት ስራ ሲመለስ ጆሽዋን ከአልጋው ላይ ያጣዋል። “ጆሽዋ ጆሽዋ” ብሎ ጠራው። መልስ የለም። አጎንብሶ በየስርቻው ሲፈልገው ድምጹን አጥፍቶ በአንዱ ስርቻ አገኘው። ውጣ ቢለው አሻፈረኝ አለ፤ አኩርፏል፤ ከብዙ ልመና በኋላ ወጣ።
“ምን ሆነህ ነው ጆሽዋ?” አለ ግሪዶ።
“አቃጥለው ሳሙና ሊያደርጉን ነው አይደል?” አለ ጆሽ በፍርሃት ስሜት።
“ማነው እንዲያ ያለው? ዝም ብለህ ታምናቸዋለህ እንዴ?”
“ሁለቱ እስረኞች ሲያወሩ ሰማሁ”
“…በቃ ሁሉንም አልፈልግም፤ ወደ ቤታችን እንሂድ” አለ ጆሽዋ።
“ታንኩን አትፈልግም?”
“አልፈልግም!”
“ግንኮ ዝናብ እየዘነበ ነው?”
“ይዝነባ!” አለ ጆሽዋ።
“እሺ እንሂድ” አለና ግሪዶ ቦርሳቸውን ይዞ ተነሳ።
“የታንኩ ጎማ እምቢ እንዳይልህ ዘይት ቀባው፤ በደንብ ያዘው እሺ” እያለ ግሪዶ ለአንዱ እስረኛ ስለታንኩ ማስጠንቀቅ ጀመረ።
“ቆይ ስንት ነጥብ አለን እስካሁን?” ጆሽዋ ጠየቀ።
“ነግሬሀለሁ 680 ነጥብ” አለው ግሪዶ።
ግሪዶ ቦርሳውን ይዞ ውጭ ወደ ዝናብ ወጣ።
“ና እንሂድ እንጂ!” አለው።
“ሲያባራ እንሄዳለን!” ብሎ ጆሽዋ እየሳቀ አልጋው ላይ ወጣ። የታንኩ ነገር ሳያጓጓው አልቀረም።
***
በግቢው ውስጥ የጥይት እሩምታ በሰዓታት ልዩነት ይሰማል።
“ጦርነቱ እኮ አልቋል” ይላሉ በየበሩ ላይ የተደረደሩት እስረኞች እርስ በርሳቸው።
ግሪዶ አሁን መውጣት አለብኝ ሲል አሰበ። የእስር ቤቱ ጥበቃ ላልቷል። አንድ ተቃራኒ ሃይል እየገፋ ለመምጣቱ ብዙ ምልክት እየታየ ነው። ሁሉም ቢሆን ፈርቶ እንጂ መውጣቱን አልጠላውም። በቅርቡ ግን ነጻነት እንደሚታወጅ ሁሉም በልቡ ተስፋ ሰንቋል። በብርድ ልብሱ አንዳንድ ነገሮችን ቋጥሮና ጆሽዋን ይዞ ከክፍሉ ወጣ። የወንዶችና ሴቶች ክፍል የሚለያይበት ስፍራ አንዲት አነስተኛ የብረት ሳጥን ትታያለች።  ሳጥኗን ከፍቶ ጆሽዋ እዚያ ውስጥ እንዲደበቅ ነገረው።
“ነገ ጠዋት ጨዋታው ያልቃ እሺ?” አለው።
“ስንት ነጥብ አለን?”
“940 አለን፤ 960 ሲሆን ይጠነቀቃል” አለ ግሪዶ።
“አካባቢው ጭር እስኪል ከዚህ እንዳትወጣ፤እሺ!”
“እሺ አባባ”
ግሪዶ ብርድልብሱን እንደ ቀሚስ አገልድሞ ወደ ሴቶቹ ክፍል አመራ፡፡ “ዶራ! ዶራ! ዶራ!” ሲል ተጣራ። መልስ የሰጠው አልነበረም። የሴቶቹ ክፍል ኦና ሆኗል፡፡ ብዙ ሴት እስረኞችን የጫነ መኪና ሲንቀሳቀስ አየና በሩጫ ደረሰበት።
“እዚህ ውስጥ ዶራ የምትባል አለች?” ብሎ ጮኸ።
አንዷ ዶራ ተብዬ ብቅ አለች፤ የእሱ ዶራ አልነበረችም። ለብዙ ጊዜ ያላያትን ፍቅረኛውንና ሚስቱን አይኗን ለማየት ጓጓ። መኪናው ውስጥ ከሌለች ብሎ በህንፃ መስኮት እየተንጠላጠለ ሚስቱን ፍለጋ ጀመረ። ብዙ ጊዜ ከተቆጣጣሪው መብራት ለማምለጥ ሞክሮ ተሳክቶለታል። አሁን ግን ያ መብራት እላዩ ላይ አነጣጠረ። እጅ ከፍንጅ ያዘው። ሮጦ ለማምለጥ አልሞከረም። ወዲያው ጠመንጃ የታጠቀ ወታደር አጠገቡ ደረሰ። ፊትና ኋላ ሆነው ተከታትለው ሲሄዱ፣ ጆሽዋ ከትንሿ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ሲያሾልቅ ከግሪዶ ጋር አይን ለአይን ተገጣጠሙ። ግሪዶ ምንም እንዳልተፈጸመ በኩምክና አካሄድ እየተራመደ ጆሽዋን ሊያስቀው ሞከረ። ወታደሩና ግሪዶ ከእይታ ጠፉ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ተከታታይ የጥይት እሩምታ ተሰማ።
***
አሁን በእርግጥም አካባቢው ጭር ብሏል። እስረኞቹ እንዳሻቸው እየወጡ ነው። ከፊሉ ተቃቅፎ ከፊሉ ተደጋግፎ ነው የሚራመደው። ግማሹ ያነክሳል። ሁሉም ላይ ድካም ይነበባል። ሆኖም ግን በነጻነት እየተራመዱ ነው። የሰዎቹ ሰልፍ እንደ ሰንሰለት የተሰላሰለ ነው። ጆሽዋ የአባቱን ትዕዛዝ አክብሮ ጭር ሲል ከተደበቀበት ወጣ። ዙሪያ ገባውን ተመለከተ። ማንም አይታይም። መሃል መንገድ ላይ ቆሞ ሲመለከት አንድ የአሜሪካ ወታደር ታንኩን እየነዳ ወደ እርሱ ሲመጣ ተመለከተ። ታንኩ ጆሽዋ አጠገብ ሲደርስ አቆመ። የነፃነት ባንዲራ እላዩ ላይ ይውለበለብበታል።
“እውነት ነው! ሽልማቱ እውነት ነው” አለ ጆሽዋ፤ ታንኩን በጉጉት አፍጥጦ እያየው።
“ብቻህን ነህ?” አለና ወታደሩ ጆሽዋን ይዞ ታንኩ ላይ ወጣ። ትንሽ እንደሄዱ የእስረኞች ሰልፍ ጋ ደረሱ። ከእስረኞቹ መሃል በዝግታ መጓዝ ጀመሩ።
“እማማ! እማማ!” አለ ጆሽዋ፤ ከሰልፈኞቹ መሃል ወደ እናቱ እያመለከተ።
ጆሽዋና ዶራ ተቃቀፉ፡፡ የእናትና ልጅ ፍቅራቸውን ናፍቆት ተወጡ።
“አሸነፍን! አሸነፍን! ጨዋታውን አሸነፍን አይደል?!” አለ ጆሽዋ በልጅነት ወኔ ተሞልቶ።
“አዎ አሸንፈናል!”  አለች እናት፤ ከልጇና ከሚውለበለበው ባንዲራ ጋር በሀሴት እየተውለበለበች።
“የኔ ስጦታ አንተ ነህ! ከአባትህ ያገኘሁህ” የሚለውን የሹክሹክታ መልዕክቷን ለእኛና ለቤተሰቦቿ ያደርስ ዘንድ ለንፋሱ ሰጠችው።
(አዲስ አድማስ፤ መጋቢት 6 ቀን 1995 ዓ.ም)


Read 266 times