Saturday, 01 October 2022 12:08

የተናቁ መረጃዎች!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

ጎጃም ውስጥ በተለይ በምዕራብ ጎጃም፤ እርባብ ጠለዛሞ የታወቀ አካባቢ ነው። መሪጌታ ስመኝ (ስመኝ ዘጠለዛሞ) የታወቁ የቅኔ መምህር ነበሩ። አንድ ቀን እምብዛም ከማይታወቁበት ደብር ሄደው እያገለገሉ እያለ አንድ ቅኔ ይቀኛሉ። በቦታው የነበሩት ካህናት እንደነገሩ አይተው ይበል ሳይሏቸው ይቀራሉ። ይህንኑ ቅኔ መልሰው ሌላ ቦታ ላይ ይነግራሉ። የሰሙት በቅኔው ሚስጥር ተመስጠው ይበል ብለው ወረቡን ያደምቁታል። መሪጌታም ቅኔያቸውን የሚረዳ በመገኘቱ ደስ ብሏቸው በወረቡም መድመቅ ተገፋፍተው “ባሏት የተገፋች ናት” አሉ ይባላል።
መገፋት የሚደርስበት ብዙ ነገር አለ፤ ከእነሱ አንዱ መረጃ ነው። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አባል የነበሩት ገብሩ ገብረ ማርያም በተለያየ ጊዜ ለመንግስትና ለህዝብ የሰጧቸው መረጃዎች የሚሰማቸው፣ የሚረዳቸው፣ ወደ ተግባር የሚያሻግራቸው አጥተው፣ ሕዝብና አገር አብዝተው ዋጋ ሲከፍሉ ሳይ ለምን ማለት ጀምሬያለሁ።
ትሕነግ መራሹ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃንና የመንግስት ባለስልጣናት ከፍተኛ ስራ አድርገው የተጠመዱበት ጉዳይ፣ የአማራን ህዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት አድርጎ መሳልና አማርኛ ቋንቋንም ለመግባቢያ የሚያገለግል መሳሪያ አድርጎ ከማየት ይልቅ የመጨቆኛ መሳሪያ አስመስሎ ማቅረብ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በአማርኛ ቋንቋ የሚተላለፉ ሃሳቦችና መልዕክቶች ሰሚና የሚረዳ እያጡ መሄድ ጀመሩ። ይህን የተገነዘቡት አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም በአንድ ስብሰባ ላይ “ዛሬ በአማርኛ ብትነግረው የሚሰማህ የኦሮሞ ልጅ የለም። ለኦሮሞው በኦሮምኛ ልትነግረው ግድ ነው” እንዳሉ አስታውሳለሁ። ይህ ሃሳባቸው በኦሮምኛ ተናጋሪዎች ዘንድ ብቻ የተወሰነ ነው ብዬ አላምንም። በሁሉም ብሔረሰቦች ዘንድ ያለ ችግር ነው። ስለዚህም በአማርኛ ቋንቋ የሚዘጋጁ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችም ሆኑ መንግስታዊ መግለጫዎች ፈጥነው ወደየአካባቢው ቋንቋ መተርጎም ወይም በአካባቢው ቋንቋ መቅረብ  ይኖርባቸዋል። የዚህን አስፈላጊነት መረዳት ምልዓተ ሕዝቡን በኢትዮጵያ ጉዳይ በጋራና በአንድነት ለመቀስቀስ ይበጃል። የሚመለከታቸው ክፍሎች ይህን ጉዳይ ስራዬ ብለው ቢያስቡበትና ቢያዩት  ድካማቸውን እንደሚቀንስላቸው አምናለሁ። ይህን የተናቀ መረጃ አንድ በሉት።
የተናቀው መረጃ ሁለት የሚጀምረው በደርግ ዘመን በድርቅ ምክንያት ከተካሄደ ሰፈራ ፕሮግራም ነው። ደርግ ከሰሜን፣ ከትግራይና ወሎ፣ ከደቡብ፣ ከወላይታና ከሌሎችም ቦታዎች ወስዶ በወለጋና በሌሎችም አካባቢዎች ህዝብ ማስፈሩ ይታወቃል። ትሕነግ የኢትዮጵያ መንግስት ፈላጭ ቆራጭ በነበረበት ጊዜ ከትግራይ የመጡ ሰፋሪዎች በየአካባቢው በልዩ ልዩ መንገድ የተለየ ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበርም ስለ ጉዳዩ በቅርበት የሚያውቁ ይናገራሉ። ይህ የቆየ የማደራጀት ስራ እያመጣ ያለውን ውጤት በአግባቡ የተከታተሉት አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም፣ የኔታ በተባለ ማህበራዊ መገናኛ ላይ ቀርበው “በየቦታው በአማራ ላይ ለሚደረገው ጥቃትና ግድያ ዋና አቀናባሪዎችና ፈጻሚዎች ከትግራይ መጥተው ኦሮሚያ ውስጥ ያደጉ የትግራይ ልጆች ናቸው። ከሌላው ብሔረሰብ በአንዳንድ ምክንያት ወደ እነሱ የገባ ኦሮሞ፣ ወላይታ ወይም ሌላ ሊገኝ ይችላል። ዋናዎቹ ግን ኦሮሚያ ውስጥ ያደጉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው” በማለት አስረግጠው ተናግረዋል።
ይህን መረጃ ወለጋ ውስጥ ተወልዶ ባደገው የኦነግ ሸኔው መሪ በኩምሳ ድሪባ (ጃልመሮ) እና በጀኔራል ጻድቃን መካከል በትግርኛ ቋንቋ ካደረጉት ውይይት ጋር አዛምዶ ማየት በኦሮሚያ ክልል በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በሌሎቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች በአማራው ላይ የሚደርሰው ዘር ተኮር ግድያ መነሻና መድረሻውን ለመገንዘብ የቀለለ ያደርገዋል። መፍትሔውም ሊገኝ የሚችለው ከዚህ ከችግሩ ማህጸን ውስጥ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።
ከኦነግና ከኦፌኮ ጀምሮ ሌሎችም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና ልሂቃን ይህን ጉዳይ ሳያውቁት ቀርተው ሳይሆን እያወቁትም ሊሆን ይችላል፣ለትህነግ የነፍስ ገዳይ ቡድን የሚያገለግል ብዙ ቅስቀሳዎች እያደረጉ ያሉት ብዬ አምናለሁ። አንዳንድ መግለጫዎቻቸው የሚያሳዩት በአካባቢው እየተገደለ ስለአለው አማራ የሚሰማቸውን ሀዘን ሳይሆን በስሙ ደባ እየተሰራበት ስለአለው ኦሮሞ መጨነቃቸውን ነው።
በኦሮሞ ስም የሚነግደውንና የትህነግን መልዕክተኛ ኦነግ ሸኔን ከኦሮሞ ህዝብ ለመነጠል መነሳት ለአካባቢው ህዝብና በዚያ አካባቢ ለሚኖረው አማራም ሰላም ማምጣት እንደማይችል ሊታመንበት ግድ ነው።
ሰሚና ተግባሪ ያጡት የአቶ ገብሩ ገብረ ማሪያም መረጃዎች ወደ ተግባር ተሻግረው ለማየት ያለኝ ጉጉት ከፍተኛ መሆኑን የምገልጠው ጠበቅ አድርጌ ነው።

Read 1891 times