Sunday, 02 October 2022 00:00

የህፃናቱ ግድያ ከሥነልቦና አንፃር ሲታይ

Written by  ከአልታ ካውንስሊንግ
Rate this item
(0 votes)

“የአዕምሮ ህመምና ግድያ  እንዲሁም የአመፅ ባህርያትና ግድያ ግንኙነት አላቸው?”
 “በአለማችን ውስጥ የግድያ እንዲሁም የአመጽ ድርጊቶች አብዛኛውን ጊዜ የአዕምሮ ጤናቸው በታወከ ሰዎች ነው ወይስ ጤነኛ በተባሉት  ነው የሚፈፀሙት?”
 “ምን አይነት የሥነ ልቦና ህመሞች ናቸው ሰዎችን ወደ አመፅ ባህሪያቶች የሚገፉት?”


ክፍል - 2
በዚህ የክፍል 2 ፅሑፋችን  የአእምሮ ጤንነት ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ እና የአዕምሮ ጤንነት ማሳያዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥቂት ከዘረዘርን በኋላ በህፃናት ግድያ ዙሪያ ያለውን ስነልቦናዊ ትንታኔ እናያለን፡፡
የአዕምሮ ጤንነት ምን ማለት ነው?
ሳይኮሎጂን ለብዙ ችግሮች መፍትሔ እንዲሆን ከሚጠቀሙ ተቋማት መካከል የአሜሪካ ሳይኮሎጂካል አሶሴሽን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ማህበር ከአንድ መቶ ሰላሳ ሶስት ሺህ አባላት በላይ ያለው የሙያ ማህበር ነው (በነገራችን ላይ በዚህ ፅሑፍ ተሳታፊ የሆነው አቶ ወንድወሰን ተሾመ ለበርካታ አመታት የማህበሩ ተባባሪ አባል ነው)። የአሜሪካ ሳይኮሎጂካል አሶሴሽን የዲክሽነሪ ፍቺ የአዕምሮ ጤናን ሲገልፀው፤ “ስሜታዊ ደህንነት፣ ባህርይን የማረቅ አቅም፣ አንፃራዊ ከጭንቀትና አቅም ማጣት ነጻ የመሆን ሁኔታ፣  ጥሩ ግንኙነትን የመመስረት አቅም እና የህይወት የእለት ተዕለት ጥያቄዎችንና  ጫናዎችን መቋቋም መቻል” ይለዋል፡፡
“a state of mind characterized by emotional well-being, good behavioral adjustment, relative freedom from anxiety and disabling symptoms, and a capacity to establish constructive relationships and cope with the ordinary demands and stresses of life. See also flourishing; normality.” ይላል፡፡
 የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ስለ አዕምሮ ጤንነት የሚከተለውን ያብራራል፡- የአዕምሮ ጤንነት የአጠቃላይ የሰው ደህንነት እና የግለሰብ ውጤታማነት መሠረት እንደሆነ፤ የአዕምሮ ጤንነት ከአእምሮ እክል አለመኖር ያለፈ ትርጉም እንዳለው እና የማሰብ ችሎታ፣ የመማር ችሎታ እና የራስን ስሜት መረዳት እና የሌሎችን ምላሽ ከመገንዘብ ጋር የተያያዘ  እንደሆነ ይገልፃል። ከራስና ከአካባቢ ጋር ሚዛናዊ መስተጋብር ማድረግም እንደሆነ ያብራራል፡፡ ሚዛናዊ ለመሆንም የአካል፣ የስነልቦና፣ የማህበራዊ፣ የባህላዊ፣ የመንፈሳዊ እና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ መስተጋብሮች ይህንን ሚዛናዊነት ሊያመጡት እንደሚችሉ ይገልፃል፡፡
አንዳንድ የስነልቦና ሳይንስ ምሁራን የአዕምሮ ጤንነት መለኪያዎች ወይም አመላካቾች  (Indicators)  ብለው  የሚጠቅሷቸው የተለያዩ መለኪያ መስፈርቶች ወይም አመላካቾች ያስቀመጡ ሲሆን ለምሳሌ የስነልቦና ምሁር ከታች የተዘረዘሩትን ዘጠኝ የስነልቦና ጤንነት መለኪያዎች (አመላካቾች) በዝርዝር አቅርቧል።
ራስን መውደድ(በመጠኑ ሲሆን) (Self-love but not self-infatuation)-ይህ ራስን ከመቀበል እና ለራስ ክብር ከመስጠት  ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ራስን ማወቅ (Self-knowledge) ጠንካራና ደካማ ጎንን ከመረዳት፣ ስሜትንና ፍላጎትን ከመገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በራስ መተማመንና ራስን መግዛት (Self-confidence and self-control)
ግልፅ የሆነና መጠነኛ ተስፋ ያለበት የተጨባጭነትን እይታ (A clear (though slightly optimistic) perception of reality)
ድፍረትና ነገሮችን መቋቋም መቻል (Courage and resilience)
ሚዛናዊነት (Balance and Moderation)
ሌሎችን መውደድ (Love of others)
ህይወትን መውደድ (Love of Life)
በዓላማ መኖር (Purpose of life)
ከላይ የተጠቀሱትን መለኪያዎች ዝርዝር ትርጉም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የታተመውንና እ.ኤ.አ. በ30 July 2014 በኦን ላይን የወጣውን ጽሑፍ ማየት ይቻላል፡፡ “የስነ ልቦናዊ ጤንነት መለኪያዎች” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ጎግል ቢያደርጉ ያገኙታል፡፡
በአጠቃላይ የአእምሮ ጤና ማለት በስሜት እና በባህሪ ደህንነት የሚገለፅ የአእምሮ ሁኔታ ሲሆን በአንፃሩም ከጭንቀት እና ከሌሎች አሰናካይ (አሉታዊ)  ሁኔታዎች ነፃ መሆንን የሚወክል ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ የአእምሮ ጤና  ማለት ገንቢ የሆኑ  ግንኙነቶችን የመመስረት እና የዕለት ተዕለት የህይወት ጭንቀቶችን እና ተግዳሮቶችን የመቋቋም ችሎታ ነው።
ወደ ዋናው ጉዳያችን እንግባ፡-
ጥያቄዎችን በመጠየቅ እንጀምር፡-
“የአዕምሮ ህመም እና ግድያ  እንዲሁም የአመፅ ባህርያትና ግድያ ግንኙነት አላቸው?”
 “በአለማችን ውስጥ የግድያ እንዲሁም የአመጽ ድርጊቶች አብዛኛውን ጊዜ የአዕምሮ ጤናቸው በታወከ ሰዎች ነው ወይስ ጤነኛ በተባሉት ሰዎች ነው የሚፈፀሙት?”
 “ምን አይነት የስነ ልቦና ህመሞች ናቸው ሰዎችን ወደ አመፅ ባህሪያቶች የሚገፉት?”
የአዕምሮ ህመም ስንል በአስተሳሰብ፣ በስሜት መቆጣጠር ወይም በባህሪ ላይ ከፍተኛ መዛባቶችን ወይም ቀውስን የሚያስከትሉ ህመሞች ናቸው፡፡
ላለፉት በርካታ አስርት አመታት የስነ አዕምሮ እንዲሁም የስነ ልቦና ልሂቃን ከላይ የተጠቀሱትን ሃሳቦች መልስ ለማግኘት ሰፋ ያሉ ጥናቶችን አካሂደዋል፤ እስከአሁንም እየተካሄደባቸው ይገኛል። በአሜሪካ በተደረገ ጥናት መሰረት ከሚፈጸሙ የአመፅ እንዲሁም የግድያ ድርጊቶች ውስጥ የአዕምሮ ህመም ባለባቸው ሰዎች የሚፈጸሙት ከ3 እስከ 5በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ ያስረዳል። በተመሳሳይ ሁኔታ በአዕምሮ ህመም እና በአመጽ እንዲሁም በግድያ ድርጊቶች መካከል ባለ ግንኙነት ዙሪያ በተደረገ ጥናት፣ በአዕምሮ ህመም የተያዙ ሰዎች  በአደገኛ እና ሱስ አስያዥ በሆኑ ንጥረ ነገሮች ተጽእኖ ስር ካልሆኑ በስተቀር ከሌሎች “ጤናማ ናቸው” ተብለው ከሚታሰቡ ሰዎች  የበለጠ በአመፅ  ድርጊት ውስጥ እንደማይሳተፉ ያትታል።  ነገር ግን በእነዚህ አደገኛ እና ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮች ተፅእኖ ስር ያሉ ሰዎች ከበድ ያሉ እንዲሁም አሰቃቂ ወንጀሎችን የመፈጸማቸው ሁኔታ ከፍተኛ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በተለያየ የአዕምሮ ህመም ውስጥ ያሉ ሰዎች እነዚህን ንጥረ ነገሮች የመጠቀም ልማድ ስለሚኖራቸው በወንጀል ድርጊቶች ውስጥ የመሳተፍ ዕድላቸው ሊጨምር እንደሚችል የጥናት ውጤቱ ይጠቁማል፡፡
ምን አይነት የአዕምሮ ህመሞች ሰዎችን ወደ አመጽና የግድያ ባህሪዎች ይመሯቸዋል?
ሳይኮሲስ  በተለይ ደግሞ ስኪዞፍሬኒያ (schizophrenia)- ሰዎችን ከእውነታው በወጣ መልኩ እንዲያስቡ የሚያደርጉ ህብር የአዕምሮ ህመም ስብስቦች ሲሆኑ ሰዎች ከእውነታው የራቀ እምነት እንዲሁም አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። ለምሳሌ “ሌሎች ሰዎች እያሳደዱኝ ነው”፣ “ሊገሉኝ ይፈልጋሉ”፣ ወይም ደግሞ “እየተከታተሉኝ ነው” ብለው እንዲያስቡ ስለሚሆኑ ሰዎችን ወደ ከፋ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ሊጨምሩ ይችላሉ። ሌላው ምልክት ኮማንድ ሃሎሲኔሽን ሲሆን በእነዚህ ከባድ የአዕምሮ ህመም የተጠቁ ሰዎች ለሌላ ሰው የማይሰማ ነገር ግን ለነሱ ብቻ በጆሯቸው የሚሰሙት ትእዛዝ አዘል የሆነ ድምጽ ጥቃት እንዲፈጽሙ ሊያዛቸው ይችላል። በመሆኑም የሰሙትን ትእዛዝ ተከትለው ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ።  
ለምሳሌ፡ ሪቻርድ ቼዝ የተባለ በስኪዞፍሬኒያ የአዕምሮ ህመም የተያዘ ግለሰብ ካሊፎርኒያ ውስጥ ስድስት ሰዎችን በመግደል ደማቸውን መጠጣቱ ይነገራል። ይሄ ግለሰብ ከልጅነቱ ጀምሮ አልኮል፣ ማሪዋና እንዲሁም ኤል. ኤስ. ዲ (LSD) የተባሉ ከባድ የአደንዛዥ እጾችን ይጠቀም እንደነበር እና እ.ኤ.አ  ከ1973 ዓ.ም እስከ 1976 ዓ.ም ድረስ በአዕምሮ ህክምና መስጫ ሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ ይታከም እንደነበር ተጠቅሷል። የግድያ ወንጀሎቹን የፈጸመው  ሰዎች ሊመርዙት እንዲሁም ሊገድሉት እየሞከሩ እንደሆነ ስለሚያስብ እንደሆነ ለመርማሪዎቹ ተናግሯል። እ.ኤ.አ ከ1977 ዓ.ም  እስከ 1978 ዓ.ም ድረስ 6 ሰዎችን የገደለው ቼዝ፤ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት እስር ቤት ውስጥ የታዘዘለትን መድሀኒት ከልክ በላይ በመውሰዱ እ.ኤ.አ በ1980 ዓ.ም ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል።
 ባይፖላር ዲስ ኦርደር፡-  ሌላው ሰዎችን ከባድ ወንጀል ለመፈጸም የሚያጋልጣቸው ህመም Bi-polar disorder ሲሆን በዚህ ህመም የተጠቁ ሰዎች፣ ሁለት ጽንፍ ለጽንፍ የሆኑ ስሜቶች በተለያየ ጊዜ ይፈራረቁባቸዋል። በጣም ከፍተኛ የሆነ ምክንያት የለሽ የደስታ ስሜት እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የመደበት ወይም የማዘን ስሜት ይሰማቸዋል። በተለይ ከፍተኛ የሆነ ምክንያት የለሽ የደስታ ስሜት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ በሁሉም ነገር ከሌሎች ሰዎች እንደሚሻሉ እና እንደሚበልጡ ስለሚያስቡ እንዲሁም እሱን ችሎታቸውን ማሳየት ስለሚፈልጉ ለሌሎች ሰዎች ማሰብም ሆነ ማዘን ያዳግታቸዋል። ይህም ሁኔታ ከበድ ያሉ የወንጀል ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ሊገፋፋቸው ይችላል።  
አንቲ ሶሻል ፐርሰናሊቲ ወይም ጸረ-ማህበረሰብ ሰብዕና፡- ያላቸው ሰዎችም በአመጽ እንዲሁም በግድያ ወንጀሎች ውስጥ የመሳተፍ እድላቸው ከፍተኛ ነው። የዚህ የሰብዕና እክል ተጠቂ የሆኑ ሰዎች የሌሎች ሰዎችን መብት መርገጥ፣ ማታለል፣ ለግል ጥቅማቸው ሌሎች ሰዎችን መጨቆን፣ እንዲሁም ራሳቸውን በሌሎች ሰዎች ቦታ ተክተው የሰውን  ስሜት መረዳት ስለማይቻላቸው እንዲሁም ለሰሩት ጥፋት ጸጸት ስለሌላቸው ከሌሎች የአዕምሮ ህመም ተጠቂዎች በላይ በከባድ ወንጀል ውስጥ ሲሳተፉ ይታያሉ፡፡  
ለምሳሌ፡ ቲዎዶር በንዲ (ቴድ በንዲ) የተባለ አሜሪካዊ ግለሰብ አንቲ ሶሻል ወይም ጸረ ማህበረሰብ ሰብዕና አላቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ሰዎች ግንባር ቀደም የሆነ ሰው ነው። ይሄ ግለሰብ ፈጽሟቸዋል ተብለው ከሚገመቱት የግደያ ወንጀሎች ውስጥ ሰላሳ የሚሆኑትን እሱ እንደፈጸማቸው ሲያምን፣ ምንም አይነት የጥፋተኝነት እንዲሁም የመጸጸት ሁኔታ አይታየበትም ነበር።
በንዲ የሚታወቅባቸው ወንጀሎቹ ወጣት ሴቶችን ማገት፣ መድፈር እንዲሁም መግደል ሲሆን አልፎ አልፎም ከገደላቸው ወጣት ሴቶች አስከሬን ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ይፈጽም ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ጥቃት የሚፈጽመባቸውን ሴቶች የሚቀርበው የሆነ የአካል ጉዳት እንደደረሰበትና እርዳታ እንደሚያስፈልገው ሰው አስመስሎ ሲሆን ወደ መኪናው ውስጥ ካስገባቸው በኋላ ሰው ወደ ማይደርስበት አካባቢ በመውሰድ ከደፈራቸው በሁዋላ ይገላቸዋል። በንዲ በጣም በሰዎች የሚወደድ እንዲሁም ተግባቢ የሆነ ባህሪ እንደሚያሳይ ነገር ግን ትንሽ ቆይቶ አረመኔ እንዲሁም ደመ ቀዝቃዛ የሆኑ ባህሪዎቹን እንደሚገልጥ በህይወት ታሪኩ ዙሪያ የተጻፉ መዛግብቶች ያትታሉ።
እዚህ ላይ ግን ልብ ሊባል የሚገባው ነገር አንድ ሰው የአዕምሮ ህመም ስላለበት ብቻ ወንጀል ይፈጽማል ማለት አይደለም። ይልቁንም ተጨማሪ ደባል ችግሮች  ለምሳሌ እንደ አደገኛ ሱስ አስያዥ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም፣ አስቸጋሪ የሆኑ የልጅነት ጊዜያትን ማሳለፍ፣ በተለያዩ አሰቃቂና ከባድ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ፣ ብስጭት፣ ድህነትን የመሳሰሉ ሌሎች አጋላጭ የሆኑ ነገሮችም እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ወደ ውስኑ ርዕሰ ጉዳያችን ማለትም፣ ህፃናትን ለመግደል ወደ ሚገፋፉ ስነልቦናዊ ምልከታዎች ስናመራ ስለ ህፃናት ግድያ ወይም Pedicide ማስገንዘብ ይኖርብናል፡፡ Pedicide (ፔዲሳይድ) የሚለው ሕጻናትን መግደል፣ ልጅ መግደል፣ ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሰው ላይ የሚፈፀምን ማንኛውም ግድያ የሚወክል ቃል ሲሆን፤ በዚህ ፅሁፍ አውድ Pedicide የሚለው ቃል እንዳንድ የቤት ሰራተኞች በህፃናት ላይ የሚፈፅሙትን ግድያ የሚወክል ቃል ይሆናል፡፡
ሰዎች ሰዎችን ለምን እንደሚገድሉ የሚተነትኑ በርካታ ጥናቶች ቢኖሩም ሰዎች ለምን ህፃናትን እንደሚገድሉ ብዙ የተጠና ጥናት ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ እንድ ጥናት በተደጋጋሚ ልጆችን ስለሚገሉ ሰዎች ጠቅለል ያለ ምክንያት ሲሰጥ፤ “ልጆችን ብቻ የሚገድሉ ግለሰቦች በአንፃራዊነት ዝቅተኛ የማሰብ ችሎታ፣ ደካማ የመግባባት ችሎታና ችግር የመፍታት ችሎታ ያላቸው እና ብዙ ጊዜ የአእምሮ ህመምተኞች ናቸው።” ይላል፡፡
ሆኖም በአንዳንድ የቤት ሰራተኞች የሚፈፀመው የግድያ ምክንያት ከአዕምሮ ህመም ይልቅ ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ መለስተኛ ምክንያቶች ከሚባሉት የሚከተሉት ይገኙበታል፡-በቀጣሪዎቻቸው የሚደርስባቸውን በደል ለመበቀል (Revenge)፤ የደመወዝ ክፍያ መከልከል፤ ወርሃዊ እረፍት አለማግኘት፤ ከፍተኛ የስራ ጫና፤ ንቀት፣ ስድብ፣ ሰራተኛን እንደ ባሪያ ማየት፤ አካላዊ ቅጣት፤ ፆታዊ ጥቃት፤ ውስን የሆነ የስራ ሰዓት አለመኖሩ፤ በቂ የሆነ የምግብ አቅርቦት በቤት ውስጥ አለመኖር የመሳሰሉት ገፊ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተሞክሮዎችና አንዳንድ ፅሑፎች ይጠቁማሉ፡፡  
ይህንን ክፍል ለመጠቅለል የአዕምሮ ህመም ካለባቸው ሰዎች እጅግ ጥቂቶቹ ብቻ ግድያ እንደሚፈፅሙ፤ አብዛኞቹ የግድያ ምክንያቶች ከአዕምሮ ህመም ጋር እንደማይገናኙ ለማየት ይቻላል፡፡ በመሆኑም በሚቀጥለው ሳምንት በክፍል ሶስት ፅሑፋችን ግድያ በሚፈፅሙ አካላት ላይ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች፤ ወላጆች፤ ማህበረስብ፣ የድለላ ስራ የሚሰሩ፣ የህግ አካላት ወዘተ ምን አይነት ሃላፊነትና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የአለም አቀፍ ተሞክሮን ጨምረን እናቀርባለን፡፡ ቸር እንሰንብት!
አልታ ካውንስሊንግን በኢ-ሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡
ማስታወሻ፡- በዚህ ጽሁፍ ሃዊ ሽጉጥ- ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት፣ ብሩክ ገ/ማርያም- ዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂስት፣ ወንድወሰን ተሾመ- ካውንስሊንግ ሳይኮሎጂስት ተሳትፈዋል።

Read 2375 times