Saturday, 01 October 2022 12:30

የነዳጅ ዋጋ በ16 በመቶ ጨምሯል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)


በደመወዝ ማሻሻያ ችግሩን መፍታት አይቻልም ለምን?የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ የተደረገ ሲሆን፤  ቤንዚን በሊትር 57 ብር ከ05 ሳንቲም፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 59 ብር ከ90 ሳንቲም፣ ኬሮሲን በሊትር 59 ብር ከ90 ሳንቲም መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።  
የአውሮፕላን ነዳጅ ፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣና ከባድ ጥቁር ናፍጣ ባሉበት እንዲቀጥሉ መወሰኑን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
በሌላ በኩል፤ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ በተዘረጋው የታለመ ድጎማ አሠራር ታቅፈው ሕዝቡን እንዲያገለግሉ የተመረጡት የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በሚጠቀሙት ነዳጅ ላይ በሁለተኛው ምዕራፍ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አልተደረገም ተብሏል።
ሚኒስቴሩ ከነዚህ ተሽከርካሪዎች በሐምሌ ወር በተወሰነላቸው ዋጋ ፦ ቤንዚን በሊትር 41ብር 26 ሳንቲም፣  ነጭ ናፍጣን በሊትር  40 ብር ከ86  እየገዙ እንዲቀጥሉ ብቻ ሳይሆን ከእጥፍ በላይ ያደገ ድጎማ ከመንግሥት እንዲያገኙ የተደረገ ስለሆነ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ አይደረግም ብሏል።
የነዳጅ የዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ የሚመጣውን ማህበራዊ ቀውስ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ ሲናገሩ፣ ከመንግስት በኩል እየተሰጠ ያለው መግለጫ ሁለት ዓይነት መልክ ያለው መሆኑን ጠቁመው አንደኛው በጎረቤት ሀገራት ካለው የነዳጅ ገበያ ጋር ሲነጻጸር የኛ ዋጋው ዝቅተኛ በመሆኑ ከፍተኛ የነዳጅ ፍላይት አለ የሚል ሲሆን፤ሁለተኛው ደግሞ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ባለው የነዳጅ ዋጋና በኢትዮጵያ መካከል ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑ መንግስት ያንን ክፍተት በድጎማ ሲሞላ ስለነበር፣ አሁን ድጎማውን ልቋቋም አልችልም ወይ ድጎማው በህዝቡ ኪስ መሞላት አለበት የሚል አቋም ነው ይላሉ።
ከዚህ መሰረተ ሃሳብ ስንነሳ የዓለም አቀፍ ገበያ በሚባለው ደረጃ ከፍተኛ ከሆነና ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ወደ ጎረቤት ሀገር ነዳጅ የሚወጣ ከሆነ፣ የነዳጅ ዋጋ ለመጨመር መነሻ ሊሆን ይችላል ብለዋል። ሁለተኛውና አንገብጋቢው ግን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ  የሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ ምን ይመስላል የሚለው ነው። ይህ ጥያቄ ሲነሳ ነው ትርጉም የሚኖረው ያሉት አቶ ሙሼ፣ መንግስት የዓለም የነዳጅ ዋጋ ይሄ ነው፤ ይሄ መከፈል አለበት ካለ፣ በመጀመሪያ እስከዛሬ ድጎማ ያስፈለገበት ምክንያት ምን ነበር የሚለውን ጥያቄ ያስከትላል ይላሉ።
እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ እስከዛሬ ለምን ነበር ድጎማ ሲደረግ የነበረው? ወይስ ያለምክንያት ነው ድጎማው ሲደረግ የነበረው? ወይስ ለድጎማው ምክንያት የነበሩት ሃሳቦች ተለወጡ? የሚሉት ጥያቄዎች በደንብ መብራራት አለባቸው። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም መንግስት ነዳጅን የሚደጉመው ነዳጅ በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦና ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ስለሚረዳ እንዲሁም ህዝቡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ስለሚኖር ማህበረሰቡን ለመደገፍ እንደነበር ይገልጻሉ።
“አሁን መንግስት ከነዳጅ ላይ ድጎማ አንስቻለሁ ካለ ከዚህ በፊት ድጎማ ማድረጌ ስህተት ነበር ብሎ አስቧል ማለት ነው” የሚሉት ባለሙያው፤ ይህ ማለት ደግሞ ማህበረሰቡ በኢኮኖሚ አድጎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ የመግዛት አቅሙን አሳድጓል ማለት ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ አሁን በሀገሪቱ ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደዚህ አለመሆኑንና ማህበረሰባችን በተለይ ደሞዝተኛው ላለፉት በርካታ ዓመታት የደሞዝ ማሻሻያ ሳይደረግለት መቆየቱን አስታውሰው የኑሮ ግሽበቱም ቢሆን ባለፉት ሶስት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ መናሩንና እነዚህ ተደራራቢ ሁኔታዎች ባሉበት መንግስት የነዳጅ ጭማሪውን ወደ ማህበረሰቡ ሲያወርደው ይህንን መሸከም የሚያስችል ትከሻ አለው ወይ የሚለው ግምት ውስጥ መግባት አለበት ብለዋል።
የጎረቤት ሀገራትን በማንጸሪያነት ያነሱት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ጎረቤት ሀገር ኬኒያን ብንወስድ በዓለም ዓቀፍ የግብይት ዋጋ ነዳጅ ሲሸጡ መነሻ ሃሳብ የሚያደርጉት ማህበረሰቡ ዋጋውን መሸከም ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ነው ያሉ ሲሆን፣ የኬንያ አንድ መካከለኛ ገቢ ያለው ሰው ከእኛ አገር መካከለኛ ገቢ ካለው ሰው ጋር ሲወዳደር የኬንያው  ወይም የሌሎቹ የጎረቤት ሀገራት ገቢ ከእኛ አገር በሶስት እጥፍ እንደሚበልጥና እነሱ በዓለም አቀፍ ገበያ ነዳጅ ቢሸጡ ህብረተሰባቸው ሸክሙን መቋቋም የሚያስችል አቅም ስላለው በቀላሉ ጉዳት አይደርስበትም ብለዋል።
ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን የማህበረሰቡ ደሞዝም ሆነ ኑሮው አለመሻሻሉን ገልጸው፤ በተጓዳኝ የመሰረታዊ ፍጆታ አቅርቦትና ፍላጎት ካለመመጣጠኑም በላይ የብራችን የመግዛት አቅም ከማሽቆልቆሉ ጋር ተዳምሮ የኑሮ ሁኔታው መሸርሸሩን አብራርተዋል። በነዚህ ተደራራቢ ጫናዎች ላይ መንግስት የነዳጅ ጭማሪውን ሲደርግ፣ ማህበረሰቡ ተቀማጭ ገንዘብ ስለሌለው ከተቀማጩ አውጥቶ ችግሩን ለመቅረፍ እንደማይችል የማህበረሰቡ ደሞዙ ባላደገበትና ገበያ ላይ ያለው እቃ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ በናረበት ሁኔታ ነዳጅ ሲጨምር ማህበራዊ ቀውሱን ያባብሰዋል ይላሉ።
አቶ ሙሼ አክለውም፤ መንግስት ከዚህ በፊት ያለው ክርክር “ከየት አምጥቼ ልደጉም” የሚል ነበር፤ መንግስት ከየት አምጥቼ ልደጉም ካለ ህዝቡ ከየት አምጥቶ ጭማሪውን ይሸከም የሚለው ጥያቄ አብሮ ይነሳል” ብለዋል።
ነዳጅን በተመለከተ ከተማ ውስጥ የሚኖረው 15 በመቶው ህዝብ ብቻ ነው የሚጠቀመው የሚል የተሳሳተ አመለካከት እንዳለ የሚገልጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከእርሻ እስከ ገበታ ነዳጅ የማይጠቀም የማህበረሰብ ክፍል እንደሌለም አስረግጠው ይናገራሉ። በውሃ ፓምፕ፣ ትራክተር፣ ማጓጓዣ ትራንስፖርት፣ ኩራዝ የሚያበራውም ሆነ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቀጥታም ሁን በተዘዋዋሪ ነዳጅ እንደሚጠቅምም ያስረዳሉ። የሆነ ሆኖ መንግስት አቅምና ስልጣን ስላለው ድጎማውን አንስቶ ክፍተቱ በህዝቡ ኪስ ይሞላ ካለ ህብረተሰቡስ ከየት አምጥቶ ክፍተቱን ይሙላ የሚለው በመሰረታዊነት መታየትና የመፍትሄ ሃሳብ መፈለግ አለበት ሲሉ በአጽንኦት አሳስበዋል።
መንግስት አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ለማህበረሰቡ ለምን የደሞዝ ማሻሻያ አያደርግም በሚል ላነሳነው ጥያቄ፤ የደመወዝ ማሻሻያ መፍትሄ ሊሆን አይችልም ይላሉ። የደመወዝ ማሻሻያው መፍትሄ የማይሆንበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤ በጣም የተደራረበና ለዘመናት የቆዩ ክፍተቶች ስላሉ ይህን ክፍት በፍጥነትና በአጭር ጊዜ ሞልቶ የማህበረሰቡን የመግዛ አቅም ማጎልበት አይቻልም ባይ ናቸው።  ለምን ቢባል መንግስት ደሞዝ ሲጨምር ነጋዴውም በዚያው ልክ  ዋጋ ይጨምራል በማለት ያብራሩት አቶ ሙሼ፤ ከዚህ ይልቅ መፍትሄ ያሉትን ሃሳቦች ጠቁመዋል።
መንግስት የነዳጅ ዋጋን ሲጨምር ህዝቡ ያለአግባብ የሚያባክነውን ነዳጅ ወደ መቆጠብና ሁለት ጊዜ ወደ ማሰብ እንዲገባ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሙሼ፤ በዚህ ጊዜ ለነዳጅ የሚያወጣውን ዶላር በማትረፍ አቅርቦት ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ማዋል አለበት-ብለዋል። በሌላ በኩል፤ ያልተገባ ጥቅም ፍለጋ ገበያ ላይ ያለውን አቅርቦት በመደበቅና ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር ችግር የሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ፣ ገበያው ተረጋግቶ እንዲሄድ ማድረግ የመንግስት ግዴታ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፣ የንግዱ ማህበረሰብ ወደ ህዝብ መጓጓዣ ማስመጣት እንዲገባና እንዲበረታታ ያለ ታክስ የማስገባት ዕድል በመስጠት መለዋወጫ እቃዎችን ከታክስ ነጻ በማድረግ፣ ከግብር  ከአሰራር ቢሮክራሲ ጋር ያለውን ችግር በመቅረፍና ማበረታቻዎችን በማድረግ የብድር አቅርቦትን በማመቻቸትና መሰል አሰራሮችን በመዘርጋት ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል ብለዋል።
ዋናው ነገር፤ መንግስት የነዳጅ ዋጋን በመጨመርና ህዝቡ የነዳጅ ፍጆታውን በመቀነስ ለነዳጅ የሚያወጣውን ሃብት በመቆጠብ በዚህም ሀብት በማትረፍ አቅርቦቱን በማሻሻል ገበያውን ማረጋጋትና የህዝቡን የኑሮ ጫና መቀነስ መሆኑን አስረግጠው የተናገሩት አቶ ሙሼ፤ እንደዚህ አይነት ፖሊሲዎች ሲወጡ የሚያስከትሉትንም ነገር አብሮ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ሁሉን ያማከለ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል።
መንግስት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የሚያገለግሉ ትራንስፖርቶች በነበረው ዋጋ እንዲቀጥሉ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ድጎማ አድርጌላቸዋለሁ ቢልም፤ እነዚህ አሽከርካሪዎች በአንድም በሌላም መንገድ ማህበረሰቡን  ከታሪፍ ውጪ እያስከፈሉ መሆኑ ይነገራል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ ብለን ለጠየቅናቸው አቶ ሙሼ ሲመልሱ፤ መንግስት ታሪፍ ሲተምንላቸው የነዳጁን ዋጋ ብቻ ግምት ውስጥ በማስገባት  ነው ይሁን እንጂ መለዋወጫ፣ የሰርቪስና የተለያዩ ወጪዎች ስላለባቸው አያዋጣንም እያሉ ነው ያሉት አቶ ሙሼ፤ ከዚህ ይልቅ የፐብሊክ ትራንስፖርት አስመጪዎችን የሚያበረታታ አሰራር በመዘርጋት ነጋዴው ሚኒባስ፣ አውቶብስና ሌሎች የትራንስፖርት አቅርቦቶችን ማሳደግ ላይ ማተኮር አለበት ሲሉ ይመክራሉ። የሜትር ታክሲ ትርፍ ማራኪ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ከ100 ሺህ በላይ መኪኖች ገበያውን መቀላቀላቸውን እንደ ሰሙ የጠቆሙት ባለሙያው የህዝብ ትራንስፖርት ቀረጡና፣ ትርፉ ማራኪና አበረታች  ባለመሆኑ ብዙ ባለሃብት ወደ ዘርፉ እየገቡ አይደለም ብለዋል። መንግስት ወደዘርፉ ለሚገቡ ባለሃቶች ብድር  በማመቻቸት፣ መኪኖቹንም ሆነ መለዋወጫዎቹን ከታክስ ነጻ በማድረግ ቢያበረታታቸው የሚገዙበት ዋጋ ቀለል  ስለሚልና ሰርተው ቶሎ ብድር ለመክፈል ስለሚቀላቸው በርካታ የህዝብ ትራንስፖርት አስመጪዎችን ማግኘት ይቻላል ብለዋል በምክረ ሃሳባቸው።

Read 21989 times