Saturday, 01 October 2022 12:42

ዝክረ - ማዲንጎ አፈወርቅ “ሥራዬ የወርቃማውን ዘመን ደረጃ እንዲይዝ ጥሬአለሁ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

(ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሦስተኛ አልበሙን ሲያወጣ የዛሬ 7 ዓመት ከአዲስ አድማስ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ)


በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከ15 ዓመታት በላይ በምሽት ክበቦች
ሰርቷል፡፡ “ስያሜ አጣሁላት” በሚለው የመጀመሪያ አልበሙ ከህዝብ ጋር
የተዋወቀው ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ፤ሦስተኛ አልበሙን (ስወድላት) ሰሞኑን
ለቋል፡፡ በአዲሱ ስራውም ስለ ሃገር፣ስለ ፍቅር፣ ስለ ታማኝነት፣ ስለ ጎንደር፣
ስለ ወሎና ምንጃር ብዙ አቀንቅኗል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት
ዮሴፍ፤ ከድምፃዊ ማዲንጐ ጋር በአዲሱ አልበሙና በሙያው ዙሪያ ተከታዩን
ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

የመጀመሪያ ስራህ “ስያሜ አጣሁላት” የሚል ነበር፡፡ በሁለተኛው “አይደረግም” ብለህ መጣህ፡፡ አሁን ደግሞ “ስወድላት” እያልክ ነው…
የመጀመሪያው አልበሜ የልጅነት ስራዬ ነው፡፡ ያኔ ጠቆር ያልኩ ነበርኩኝ፤ እንዳሁኑ አልገፈፍኩም ነበር፡፡ አሁን እንደ እባብ ቆዳ ቀይሬያለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ “ስያሜ አጣሁላት” በልጅነት እድሜ ከህዝብ ያገናኘኝ ስራ ነው፡፡ ወቅቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ነበር፡፡ ታዲያ “ስያሜ አጣሁላት” እና “አማን ነው ወይ ጎራው” የተሰኙት ሁለት ዘፈኖች በተለየ መልኩ ተወደውልኝ ነበር፡፡ ሁለተኛው ስራዬ የትዝታ ዘፈን ያለበት “አይደረግም” በሚል ስያሜ የወጣው ነው፡፡ አሁን “ስወድላት”ን ይዤ ወደ አድማጭ ቀርቤያለሁ፡፡
በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት “ስያሜ አጣሁላት” እና “አማን ነው ወይ ጎራው” የተወደዱበት ምክንያት ምንድን ነው? ከጦርነቱ ጋር የተገናኘ ሃሳብ ይዘዋል እንዴ?
በተለይ “ስያሜ አጣሁላት” ከኤርትራ ጠብ አጫሪነት ጋር ሳይያያዝ አይቀርም፡፡ እኔ በወቅቱ እንደነገርኩሽ ልጅ ስለነበርኩ ጉዳዩ አይገባኝም ነበር፡፡ ግጥሙን የፃፈው አንጋፋው የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ይልማ ገ/አብ ነበር፡፡ ይልምሽ ደግሞ ወቅታዊ ፈጠራዎችን በመስራት አይታማም፡፡ አሁን ነው የሚገባኝ፡፡ እኔ ከሴት ልጅ ፍቅር ጋር ብቻ ነበር አገናኝቼ የዘፈንኩት። በነገራችን ላይ አሁንም ቢሆን ግጥሙ ከወቅቱ ጦርነት ጋር እንዲሄድ ሆን ተብሎ ይሰራ አይሰራ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግምቴን ነው የነገርኩሽ፡፡
ሁለተኛው አልበምህ “አይደረግም” የሶስት አራት ድምፃዊያንን ትዝታ አፈራርቀህ የሰራህበት ሲሆን የትዝታው ዘፈን ድምፅህ የተፈተነበትና ወደ አድማጭ በደንብ የቀረብክበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ እውነት ነው?
በጣም ትክክል ነው፡፡ እኔም ባለውለታዬ የምለው ዘፈን ትዝታው ነው፡፡ የእኔ የመዝፈን ብቃት ምን ያህል እንደሆነ ለህዝብ ግልፅ ያደረገ ስራ በመሆኑ በሚባለው ነገር መቶ በመቶ እስማማለሁ፡፡
“አይደረግም” ከወጣ ረዘም ያለ ዓመት ሆኖታል… ባልሳሳት ሰባት ዓመት አካባቢ… ለምን እንደዚህ ቆየህ?
ተቃርበሻል! ስምንት ዓመት አልፏል፤ አልበም ሳልሰራ፡፡ በመሃል ግን የተሳኩና የተወደዱ ነጠላ ዜማዎችን ሰርቻለሁ፡፡ ለምሳሌ “የበላይ ዘለቀ”፣ “አንበሳው አገሳ”፣ ለ“አባይ ወይስ ቬጋስ” ፊልም የሰራሁት ማጀቢያ ሙዚቃ “አባይ ወይስ ቬጋስ”---ህዝቡ ስምንት ዓመት አልበም አለመስራቴን እንዳያስታውስ አድርገውታል፡፡ ከህዝብ ጆሮ አልጠፋሁም ነበር ማለት ነው፡፡ በዚያ ላይ ኮንሰርቶች እሰራለሁ፤ የሰርግ ስራዎችንም እንደዚሁ፡፡ ይህን ስታይው ስምንት ዓመት ሙሉ የጠፋሁ አይመስልም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን እንደዚህ አልጠፋም፤ በየሁለት አመቱ አልበም ይኖረኛል፡፡
አዲሱ አልበምህ በግጥማና ዜማ የነማን አስተዋፅኦ አለበት? ምን ያህል ጊዜስ ወሰደ?
በመጀመሪያ ደረጃ የአልበሙን ስራ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የወሰድኩት እኔ ነኝ፡፡
ምን ማለት ነው?
ይሄ ማለት ግጥምና ዜማ የመምረጡን ስራ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የተወጣሁት እኔው ነኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ሙዚቃ ውስጥ እንደመሆኔ፣ ግጥምና ዜማን በማስተዋል በኩል ጥሩ ተሰጥኦ አለኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ የአልበሙን ግጥምና ዜማ የመረጥኩት ራሴ ነኝ፡፡ ነገር ግን ግጥምና ዜማ እንዲሰሩ ትልልቅ የሚባሉና የካበተ ልምድ ያላቸውን ሰዎች አሳትፌአለሁ። ይልማ ገ/አብ፣ ጸጋዬ ደቦጭ፣ አበበ ብርሃኔ፣ አማኑኤል ይልማ፣ ታመነ መኮንን፣ አህመድ ተሾመ (ዲንቢ)፣ መኮንን ለማ (ዶክተሬ) እና መሰል ታዋቂዎች ተሳትፈዋል፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት የተለያዩ ግጥምና ዜማዎችን ስሰበስብና ስመርጥ ነው የቆየሁት፡፡ 30 ዘፈኖች መረጥኩና ስቱዲዮ ተቀረፅኩ፤ ከ30ው ግን 14ቱን ነው የመረጥኩት፡፡ 14ቱም ዘፈኖች አንዱ ከአንዱ እንዳይበልጥና በጥሩ ሁኔታ እንዲደመጥ ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ እነዚህ ዘፈኖች የቀደመውን (የወርቃማውን ዘመን) የሙዚቃ ደረጃ እንዲይዙ ነው የፈለግሁት፡፡
የወርቃማው ዘመን ድምፃዊያን የሚባሉት እነማን ናቸው? የአሁኑ አልበህም ያስቀመጥከውን ደረጃ አሳክቷል ብለህ ታስባለህ?
ኤፍሬም ታምሩ፣ ንዋይ ደበበ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ ያሉበት ዘመን  ለእኔ ወርቃማውና የምወደው ዘመን ነው፡፡ እኔም ያን ዘመን ሊያስታውሱ የሚችሉ በሳል ዘፈኖችን ከአሁኑ ትውልድም እንዳይርቁ አድርጌ ሰርቻለሁ፡፡ አልበሙ ሰሞኑን ነው የወጣው፤ በእነዚህ ጥቂት ቀናት ውስጥ የደረሰኝ የአድማጮች አስተያየትና ምላሽ ያለምኩትን ግብ እንደመታሁ አመላካች ነው ብዬ አምኜያለሁ፡፡
በአንድ ወቅት አልበም ማሳተም ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ አሁን አሁን ዘፋኞች ደፈር እያላችሁ የመጣችሁ ትመስላላችሁ?
ልክ ነው፤ የአልበም ስራ የተኛበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሄ የቅጂ መብት ጉዳይ ዘፋኙንም አሳታሚውንም ተስፋ አስቆርጦት ነበር፡፡ አሁን እነ ሸዋንዳኝ፣ እነ ሚካኤል በላይነህ፣ እነ ታምራት ደስታ፣ እነ አብነትና ሌሎችም ደፍረው አልበም በማውጣታቸው ሌሎቻችንን አበረታተውናል። አሁን ሰውም ኦሪጂናል አልበም የመግዛት ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣቱን ያወቅሁት፣ የእኔ አልበም በወጣ በሶስተኛው ቀን እንኳን በጥሩ ሁኔታ በመሸጥ ላይ መሆኑን ስመለከት ነው፡፡
አልበሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ በትክክል ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?
ግጥምና ዜማ መምረጥ የጀመርኩት ከስምንት ዓመት በፊት ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ስቱዲዮ መግባትና ስራውን በደንብ መስራት የጀመርኩት ከአምስት ዓመት በፊት ነው፡፡ ያልገባሁበት ያልወጣሁበት ስቱዲዮ የለም፡፡
ለምንድነው በየስቱዲዮው እየገባህ የወጣኸው?
ያሉትን ግጥምና ዜማዎች ይዤ ስራውን እጀምራለሁ፤ ነገር ግን መርካት አልቻልኩም። አንድ ስራ ይዤ እገባና አያስደስተኝም ትቼ እወጣለሁ፡፡ ይህን ሳደርግ በራሴ የገንዘብ ኪሳራ ነው፤ ዛሬ አንድ ዘፈን ለመስራት ከ20 ሺህ ብር በላይ ይጠይቃል፡፡ ቅንብር 10 ሺህ ብር፣ ግጥምና ዜማ በቀላሉ 10 ሺህ ብር ወጪ ይጠይቃሉ። ሌሎች ጥቃቅን ወጪዎችን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጋር የዛሬ ስድስት ዓመት ነው የተፈራረምኩት። ስንፈራረም ግን በራሴ ስራውን አጠናቅቄ ማስተሩን ላስረክበው ተስማምተን ነው፡፡ ይሄ ማለት ዜማ፣ ግጥም ቅንብር… እያንዳንዱ ወጪና ልፋት በእኔ ላይ ነበር፡፡ ታዲያ ከስድስት አመት በፊት የነበረው ዋጋና የአሁኑ ልዩነቱ ሰማይና ምድር ነው፡፡ በዚያ ላይ ስቱዲዮ ገብቼ ጀምሬ የተውኳቸው አሉ፡፡ ያ ኪሳራ በራሴ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ 30 ዘፈን ሰርቼ፣ 14ቱን ብቻ ነው የመረጥኩት፡፡ 16ቱ ቀሩ ማለት ነው፡፡
ታዲያ ምን ያህል ወጪ ወጣበት አዲሱ አልበምህ?
ያለማጋነን ከ500 ሺህ ብር በላይ አውጥቻለሁ፤ ሆኖም ለህዝብ ጆሮ የሚመጥን ስራ እንደሰራሁ ይሰማኛል፡፡ ራሴን በጣም አስደስቶኛልና፡፡
ከአንተና ከእህትህ ትዕግስት አፈወርቅ ሌላም ታናናሽ ድምፃዊ እህትና ወንድሞች አሉህ ይባላል፡፡ እንደነ አምስቱ እርጎዬዎችና እንደነ ጃክሰን ፋሚሊ “የአፈወርቅ ቤተሰቦች” ለመባል እየተቃረባችሁ ነው ወይስ?
እኛ እንኳን የአፈወርቅ ቤተሰቦች ለመባል አልበቃንም፤ ምክንያቱም በሙዚቃው ነጥረን የወጣነው እኔና ትዕግስት ብቻ ነን። አንድ ወንድሜ ፍላጎት ስላለው በመሞከር ሂደት ላይ ነው፡፡ ካናዳ ነው የሚኖረው፡፡ ጂጂ የምትባለው የታናሼ ታናሽ በጣም የሚገርምና የሚመስጥ ድምፅ አላት፤ ነገር ግን ዘማሪ መሆን ነው የምትፈልገው፡፡ አሁን እንግሊዝ ነው የምትኖረው፤ ስለዚህ የአፈወርቅ ቤተሰቦች ለመባል አልደረሰንም፡፡ እኔና  ትዕግስት ግን ወደፊት አስተዳደጋችንን፣ ባህላችንን የሚያሳይ አንድ ዘፈን የመስራት ሃሳብ አለን፡፡
ብዙ አድናቂዎች እንዳሉህ ይታወቃል፡፡ አንተስ የማን አድናቂ ነህ?
ኢትዮጵያ የቅዱስ ያሬድ አገር ናት፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስትቀርቢ ዜማ ማህሌትና የመሳሰሉት ያስደምሙኛል፡፡ ወደ ዘፈኑ ስትመጪ አገራችን ብዙ አንጋፋና ተሰጥኦ ያላቸው ድምፃዊያንን አፍርታለች፤ ከእነ ጥላሁን ገሰሰ ጀምሮ፡፡ እኔ ሞዴል ብዬ የያዝኩትና ወደ ሙዚቃው እንድገባ የተሳብኩት በኤፍሬም ታምሩ ነው፤ በጣም ነው የምወደው፡፡ ሙሉቀን መለሰን፣ ቴዎድሮስ ታደሰን፣ እነ ጸጋዬ፣ አረጋኸኝ… እንዲሁም ቀደም ሲል ወርቃማው ዘመን ላይ የነበሩ ብዬ የገለፅኩልሽን በሙሉ አደንቃለሁ፡፡ ቀደም ካሉት ፍሬው ኃይሉ የቤተ-ክህነት አይነት ድምፅ ስላለው እወደዋለሁ፡፡ ከወጣቶች ጎሳዬ፣ ብዙአየሁ፣ አብነት፣ ቴዲ አፍሮን አደንቃለሁ፡፡
ግጥምና ዜማ ድርሰት ላይ እንዴት ነህ?
ባለፈው አልበም ላይ “አፋር” የተሰኘውን ዜማ ሰርቻለሁ፡፡ “ማን እንደኔ ንገሪኛ”፣ “አባይ ወይስ ቬጋስ” እና “አንበሳው አገሳ” የኔ ዜማዎች ናቸው፤ ዜማ ላይ ምንም አልልም። ግጥም ግን ሰርቼ አላውቅም፡፡ በአሁኑ አልበሜ ላይ በዜማም አልተሳተፍኩም፤ ሁሉንም በሌሎች ባለሙያዎች ነው ያሰራሁት፡፡
በአዲሱ አልበምህ እስካሁን ከመጡት አስተያየቶች በጣም ያስደመመህ አለ?
ያው ብዙ አስተያየቶች ይመጣሉ፡፡ በአብዛኛው አድናቆትና ማበረታታት ናቸው። አንድ ሰው ግን ደውሎ “ለገና ለበግ መግዣ ያስቀመጥኩትን ብር የአንተን ሲዲ እየገዛሁ ለወዳጅ ዘመድ አድዬበታለሁ፤ በጉን አንተ ግዛልኝ” ብሎኛል፡፡ በጣም ገርሞኛል፡፡ አንዳንዴ ሰው ሲወድሽ እንዲህ ሁሉ ያደርጋል፡፡ ሌላው ችሎታህን በአሁኑ አልበም ላይ በአግባቡ ተጠቅመሃል የሚል አበረታች አስተያየት ነው፡፡
ታዲያ ምን አሰብክ… በጉን ትገዛለታለህ?
 እገዛለታለሁ፡፡ ይሄ ሰው እኮ ሲዲውን ሲገዛ ገንዘቤ በተዘዋዋሪ እኔው ኪስ ገብቷል፡፡ ስለዚህ ደስ እያለኝ እገዛለታለሁ፡፡
በመጨረሻስ….
በመጨረሻ እንግዲህ ይሄ አልበም እንዲህ አምሮ እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉት የግጥምና ዜማ ደራሲዎች አመሰግናለሁ። የተለያዩ ጉዳዮችን በማስጨረስ ድካሜን ሲያቀልልኝ የነበረው የአቻሬ ጫማ ባለቤት (አቻሬ) ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡ አቀናባሪ ሙሉጌታ አባተና ኤልያስ መልካ፣ እህቴ ትዕግስት አፈወርቅን፣ ማርታ ዘለቀን፣ አህመድ ተሾመንና ሌሎችም በመዘንጋት ስማቸውን ያላነሳሁትን ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ በደከመበት በአሁኑ ወቅት ከጎኔ ሆኖ የክብር ስፖንሰር የሆነኝን ዳሽን ቢራንና የኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ባለቤትን አቶ ተሾመ ፀጋዬን እንዲሁም በአስተያየት እየኮተኮተ ያሳደገኝን የኢትዮጵያን ህዝብ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ለሁሉም ብድሩን ይክፈልልኝ እላለሁ፡፡ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን የገናን በዓል በሰላም አሳለፋችሁ፤ መጪው የጥምቀት በዓል የምትደሰቱበት ይሁን እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡

Read 3909 times