Monday, 03 October 2022 00:00

ከቢያፍራን ጦርነት ምን እንማራለን?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞው የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

“--ጦርነቱ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ረሃብም የአብዛኞቹን ናይጄሪያውን ህይወት ቀጥፏል። በህወሃት
ተለዋዋጭ ስግብግብ ፍላጎት በተቀሰቀሰው ጦርነት፣ ሀገራችን ከናይጄሪያ የባሰ መመሰቃቀል
እየደረሰባት መሆኑን መገመት ነብይነትን የሚጠይቅ አይሆንም፡፡--”

እ.ኤ.አ በ1960 ናይጄሪያ ከዩናይትድ ቅኝ ግዛት ኪንግደም ነፃ ሆነች። እንደ ሌሎች ብዙ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ አዲስ የአፍሪካ ሀገራት፣ የሀገሪቱ ድንበሮች ቀደም ሲል የነበሯቸውን የጎሳ፣ የባህል፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ ድንበሮችን አልያዙም። በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ሙስሊሞች የሚበዙበት ሲሆን በዋነኛነት ግዛቱ ነባሩን የሰኮቶ ኸሊፋ ግዛት ያካተተ ነበር። የደቡቡ ህዝብ በአብዛኛው ክርስቲያን ነው፡፡ በስተምዕራብ የዮሩባ እና በስተምስራቅ የኢቦ ጎሳ ግዛቶች ይገኛሉ። ከነጻነት በኋላ፣ ናይጄሪያ በዋነኛነት በጎሳ ድንበር ተለይታ ነበር፡፡ ይህም በሰሜን ሃውሳ እና ፉላኒ እንዲሁም ዮሩባ በምእራብ እና ኢቦ በምስራቅ ይዋሰኑ ነበር።
በናይጄሪያ የነጻነት ሂደት ላይ ውይይት እየተደረገ ባለበት ወቅት የጎሳ ውጥረት ነግሶ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ የጎሳ እና የሃይማኖት አመፆች መከሰት ጀመሩ። እ.ኤ.አ. በ1945 ጆስ በተባለ አካባቢ የሃውሳና ፉላኒ ጎሳዎች በኢቦ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ሁከት ተቀሰቀሰ። በዚህም ብዙ ሰዎች የሞቱበትና የቆሰሉበት የጎሳ ብጥብጥ ተቀጣጠለ። የአካባቢውን ጸጥታ ወደነበረበት ለመመለስ ከካዱና የፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት ኃይሎች መጡ፡፡ ይህንን ክስተት በወቅቱ የታተመ አንድ ጋዜጣ እንዲህ ገልፆታል፡-
“እ.ኤ.አ. በ1945 ጆስ በተባለ አካባቢ በሰሜን ተወላጆች የተፈጸመ ድንገተኛና አረመኔያዊ ጥቃት ምስራቃውያንን ሙሉ በሙሉ ያስገረመ ሲሆን፤ ጉዳዩ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት የምስራቅ ሴቶች፣ ወንዶችና ህጻናት አስከሬኖች በየጎዳናው ተጥለው በሺዎች ፓውንድ የሚገመት ንብረታቸው ተበታትኗል”
ጆስ በተባለው አካባቢ በተቀሰቀሰው ግርግር ሶስት መቶ የኢቦ ጎሳ አባላት ሞቱ። በ1953 በካኖ አካባቢ ተመሳሳይ ሁከት ተፈጠረ። ከአሥር ዓመት በኋላ በ1964 በምዕራቡ ግዛት ሌላ ግጭት ተቀሰቀሰ፡፡ በዚህ የፖለቲካ ቀውስ ምዕራባዊው የናይጀሪያ ግዛት ለሁለት ተከፈለ። በወቅቱ ተካሂዶ የነበረው ምርጫ ተጭበርብሯል የሚሉ በርከት ያሉ ዘገባዎች ምርጫውን ህጋዊነት አሳጡት። የምዕራብ ግዛት ነዋሪዎች በተለይ በሰሜን ህዝቦች ኮንግረስ ፓርቲ የፖለቲካ የበላይነት ተማረሩ፣ ብዙዎቹ እጩዎች በምርጫው ያለምንም ተፎካካሪ ተወዳደሩ። ሁከት በመላ አገሪቱ ተስፋፋ፡፡ ህዝቡ ፈለሰ፡፡ አንዳንዶቹ ወደ ሰሜን እና ምዕራብ፣ አንዳንዶቹ ወደ ዳሆሚ ግዛት ተሰደዱ። የፖለቲካ ሥርዓቱ በሰሜኖች ብቸኛ የበላይነት መያዙና በመላ አገሪቱ የተፈጠረው ትርምስ በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ አካላት እርምጃ እንዲወስዱ አነሳሳቸው። በሰሜን ናይጄሪያውያን የበላይነት የተያዘው የፌደራል መንግስት ቀውሱ እንዲባባስ ዝም አለ፡፡ ይህንንም ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅና ምዕራባዊያን ግዛት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ለማስተዳደር በማሰብ ነበር።
ይህም የናይጄሪያን ፌዴራላዊ መንግሥት አስተዳደር ብልሹነት ያጋለጠ ተግባር ነበር። በጥር 1966 ሁኔታው የከፋ ደረጃ ላይ ደረሰ። በአብዛኛው የኢቦ ጎሳ ወታደራዊ መኮንኖች ያሉበት ሁሉንም ለማካተት የሞከረ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዶ፣ አቡበከር ታፌዋ ባሌዋንና የሰሜን ተወላጅ የሆነውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር አህመዱ ቤሎን ጨምሮ 30 የፖለቲካ መሪዎችን ገደሉ። በዚሁ መፈንቅለ መንግስት የሰሜን ተወላጆች የሆኑ አራት ከፍተኛ መኮንኖችም ተገድለዋል። ከባለስልጣናት ውስት የኢቦ ጎሳ ተወላጅ የሆኑት ናምዲ አዚኪዌ እና የምእራብ ግዛት ፖለቲከኛው ኦባፌሚ አዎሎዎ ብቻ አልተገደሉም። የሠራዊቱ አዛዥ ጄኔራል አጉይ ኢሮንሲ በጥር 1966 ሥልጣኑን ተቆጣጠሩ።
በሐምሌ 1966 የሰሜኑ መኮንኖች እና የሰራዊት ክፍሎች ሌላ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ጄኔራል አጉይ ኢሮንሲ እና በርካታ የደቡብ መኮንኖችን ገደሉ። አብላጫዎቹ ሙስሊም የሆኑት መፈንቅለ መንግስት አድራጊ መኮንኖች በማዕከላዊ ናይጄሪያ ከሚገኘውና አነስተኛ ከሆነው ከአንጋስ ጎሳ ጄኔራል ያኩቡ ዳንዩማን (ጃክ ጎዎንን) የፌዴራል ወታደራዊ መንግስት መሪ አድርገው ሰየሙ። ሁለቱ መፈንቅለ መንግስቶች የናይጄሪያን የጎሳ ግጭት አባባሱት። በመስከረም 1966፣ በሰሜን ናይጄሪያ ግዛት የሚኖሩ ወደ 30,000 የሚጠጉ የኢቦ ጎሳ ሲቪሎች ሲገደሉ፤ በምስራቃዊ የሀገሪቱ ከተሞች የሚኖሩ የሰሜናዊ ግዛት ተወላጆች በአጸፋው ተገድለዋል።
በጥር 1967 የጦር መሪዎቹ ጄኔራል ያኩቡ ጎዎን፣ ቹክዌሜካ ኦጁኩ እና ከየግዛቱ የተውጣጡ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች በጋና አቡሪ ከተማ ተገናኝተው የተማከለ የክልል አስተዳደሮችን ህብረት ለመመስረት ተስማሙ። የሰሜኑ ተወካዮች “የአቡሪ ስምምነት” ተብሎ በሚጠራው በዚህ ስምምነት አልተደሰቱም። የመገንጠል ስሜት አሳዩ፡፡ የምዕራቡ ግዛት መሪ ኦባፌሚ አዎሎዎ ምስራቃዊው ክልል ከተገነጠለ ምዕራባዊው ክልልም እንደሚቀጥል አስጠነቀቁ። ሰሜኖቹ ይህንን አባባል ተቀበሉት።
የምስራቁ ተወካይ እንዲህ የሚል ሃሳብ ነበር ያቀረበው፡- “እኔ ሌተናል ኮሎኔል ቹክዌሜካ ኦድሜጉ ኦጁኩ፣ የምስራቅ ናይጄሪያ ወታደራዊ አስተዳዳሪ፣ ባለኝ ስልጣን መሰረት እና ከላይ በተገለጹት መርሆዎች መሰረት፣ የምስራቃዊ ናይጄሪያ ተብሎ የሚጠራው ግዛትና ወሰን ከአህጉራዊ ድንበርና የውሃ ወሰን ጋር አንድ ላይ ከአሁን በኋላ “የቢያፍራ ሪፐብሊክ” በሚል ስም ነጻ የሆነች ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን እገልጻለሁ” አለ፡፡
ወደ ናይጄሪያ ከተመለሰ በኋላ የፌደራል መንግስቱ የአቡሪውን ስምምነት በመሻር በቢያፍራ የሚገኙትን ኢቦዎችን የሚከፋፍልና በርካታ አዳዲስ ግዛቶች መፈጠራቸውን የሚገልጽ አዋጅ አወጣ። በግንቦት 26 ኦጁኩ ከምስራቃዊ ክልል የተውጣጡ የማህበረሰብ መሪዎች ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ ከናይጄሪያ ለመገንጠል ወሰነ። ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ በተፈጠረው ሁከት የተገደሉትን ኢቦዎች በምክንያትነት በመጥቀስ ከአራት ቀናት በኋላ ኦጁኩ የቢያፍራ ሪፐብሊክን ነፃነት አወጀ፡፡
የቢያፍራውን ጦርነት ከቀሰቀሱት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ይህ እንደሆነ ይታመናል። የናይጄሪያ ኢኮኖሚ ዋና ምንጭ የሆነውና በአካባቢው የተገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ዘይት ለቢያፍራ ጦርነት ሌላው ምክንያት ነው። ቢያፍራ ለጦርነት ያልተዘጋጀ ነው፡፡ ከናይጄሪያ መንግስት ጦር ያነሰ የጦር ሰራዊትና መሳሪያ ነበር ያለው፡፡ ነገር ግን በትውልድ ቀያቸው መዋጋታቸውና የብዙዎቹን ቢያፍራውያን ድጋፍ ማግኘት መቻላቸው ከናይጄሪያ መንግስት የበላይነት ፈጥሮላቸዋል፡፡
የናይጀሪያ ፌዴራል መንግስት በጁላይ 6 ቀን 1967 ቢያፍራን አጠቃ። የናይጄሪያ የመጀመሪያ ጥረቶች የተሳካ አልነበረም። ቢያፍራዎች የራሳቸውን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ ጀመሩ፡፡ በነሀሴ 1967 ጥቃታቸውን በማስፋፋት በመካከለኛውና በምዕራባዊ የናይጀሪያ ግዛት በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጠሩ። ይሁን እንጂ በብሪታንያ፣ በአሜሪካና በሩሲያ መንግስታት ድጋፍ ናይጄሪያ የጦርነቱን ማዕበል ቀየረቸው። በጥቅምት 1967 የናይጄሪያ ፌዴራል መንግስት ከጠንካራ ውጊያ በኋላ የተወሰዱበትን መሬቶች ማስመለስ ቻለ። በመስከረም 1968 የፌደራል ጦር ጎዎን “የመጨረሻው ማጥቃት” ሲል የሰየመውን እቅድ አወጣ። መጀመሪያ ላይ የመጨረሻው ማጥቃት በቢያፍራ ወታደሮች ተመክቷል። በኋላ ላይ፣ በደቡባዊ ቢያፍራ የተሰለፈው የፌዴራል መንግስት ጦር ምከታውን ጥሶ ማለፍ ችሏል።
አሁን የህወሃትና የኢትዮጵያ አደራዳሪ ሆነው የቀረቡት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎ ኦባሳንጆ በቢያፍራው ጦርነት በመሳተፍ ሀገራቸውን ከመገንጠል እንደታደጉ ይነገራል። እ.ኤ.አ ከ1967 እስከ 1970 ዓ.ም በናይጄሪያ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በጦርነት፣ በዘር ማፅዳት ሕይወታቸውን አጥተዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ጦርነቱ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ረሃብም የአብዛኞቹን ናይጄሪያውን ህይወት ቀጥፏል። በህወሃት ተለዋዋጭ ስግብግብ ፍላጎት በተቀሰቀሰው ጦርነት፣ ሀገራችን ከናይጄሪያ የባሰ መመሰቃቀል እየደረሰባት መሆኑን መገመት ነብይነትን የሚጠይቅ አይሆንም፡፡
Read 9097 times