Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 20 October 2012 10:51

የትዕግስት ማሞ “ቁጭት”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ሰሞኑን ወደኋላ ሄጄ የግጥም መጽሃፍትን ሳገላብጥ የትዕግስት ማሞ ግጥም እጄ ገባና ደጋግሜ አነበብኩት፡፡
መጽሃፉን የገዛሁት ገና የወጣ ሰሞን ነበር፡፡ገጣሚዋን አንዴ ባህል ማዕከል ውስጥ ስታነብ አይቻት ስለነበር ብዙ አልፈራሁትም ፤ይሁንና ቤት መጥቼ ሳነብበው ያን ያህል ስላላሰከረኝ አስቀመጥኩት፡፡ከዚያ በኋላ እንደዚሁ አውጥቼ አነበብኩት፡፡አሁንም ይኸው አነበብኩት፡፡
እናም አሁን ሳነብበው ለምን ትንሽ ነገር አልልም ብዬ አሰብኩ፤ምክንያቱም ልጅቷ ጥሩ ነገሮች አሏት፤ይህ ጥሩ ነገር ቢነገራት፣ ምን ላይ እንደደከመች ብታውቅ አሻሽላ ጥሩ ግጥም ልታስነብበን ትችላለች፡፡ እውነት ለመናገር ትዕግስት አሁን አደባባይ ላይ በድፍረት “ገጣሚ ነን” ከሚሉት በጣም የተሻለ ስራ ሰርታለች፡፡የቃላት አጠቃቀምዋ ራሱ ጥሩና የተሻለ ነው፡፡

የርሷ ችግር ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸውን ግጥሞች አንድ ላይ መሰብሰቧ ነው፡፡ግጥሞቹ ተመሳሳይ ድምጽና ስሜት ብቻ ሳይሆን አንድ ጊዜ ላይ፣በአንድ ስሜት የተጻፉ መሆናቸው የፈጠረው ችግር አለ፡፡ ተመሳሳይ ቃላትም ተስተውለውባቸዋል፡፡
በተለይ 1998 ዓ.ም የተጻፉት ግጥሞች በሙሉ ስለከሸፈ ፍቅር የሚተርኩ ናቸው፡፡ከመጽሃፉ አጠቃላይ ግጥሞች 23 ያህሉ ስለፍቅር ሲሆን፣ከነርሱ ውስጥ 90 ፐርሰንት ያህሉ ስለከሸፈ ፍቅር የሚያወሩ ናቸው፡፡እነዚህ የከሸፉ ፍቅር ግጥሞች ደግሞ በአንድ አይነት ዜማ ፣በተመሳሳይ ቃላት የታሰሩ ናቸው፡፡ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ በዚያ ሰቀቀን ድምጽ ውስጥ እንኳ ይጣፍጣሉ፡፡ያምራሉ፡፡
ገብቶኛል ውዴ ነገርህ …
መውደድህ ሊሰባበር ነው፤
ትህትናህ በይሉኝታ ታንቋል፤
በማስመሰልህ አትጋርደኝ ፤የኔ ልብ ማፈግፈግህን፣
መጉደሌን ካይኖችህ አውቋል፡፡
ፍቅር በአይን እንደሚነበብ ብቻ ሳይሆን ማስመሰልን ጠልቆ እንደሚያይ ጠቆመችን፡፡
ግጥም ሰባኪ አይደለም፡፡ “ስንብት” ከሚለው ግጥሟ ነው የወሰድኩት፡፡ ይሉኝታ አይያዝህ ሂድ እያለች ነው ገጸ-ባህሪዋ፡፡ አንሼብሃለሁ የሚለውን ሃሳብ ደስ በሚል መንገድ ገልፃዋለች፡፡
ትካዜ፣ሃዘን፤ማንከስ፣ተስፋ መቁረጥ፣ጽልመት ወዘተ የሚሉት ቃላት እጅግ በዝተዋል፡፡ይህም ግጥሞቹ የተጻፉበት ጊዜ ተቀራራቢነት ሊሆን ይችላል፡፡ ግጥምን አቆይቶ ደጋግሞ ማየት ጥሩ መሆኑን ሁለት ተመራማሪዎችን ጠቅሼ ለመጻፍ ሞክሬ ነበር፡፡ግድ የላችሁም ደጋግመን ብናነባቸው ያላየነውን ነገር ማየት እንችላለን፡፡ግጥም ስበከት አይደለም ደስታ ፈጣሪ ነው፡፡ደስታ ደግሞ በደስታ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሃዘን ስሜት ውስጥ ሊመጣ ይችላል ይላሉ ምሁራኑ! እንዲያውም የግጥም ተዓምሩ ይህንን ማድረጉ ነው፡፡ትዕግስት ይህንን ተመሳሳይነት ልብ ብትል ግጥሞችዋ እምባ እየፈሰሳቸው የሚያስደንቁ ነበሩ፡፡እያሳዘኑ የማያስመርሩ!
“ባይተዋር ማለት” ከሚለው ግጥሟ የሚጣፍጡ ስንኞች እንውሰድ፡-
ሰው በሞላው ሀገር፤
በሰው ጠኔ ታንቀው፣
ባዘን ጩኸታም ድምፅ ብቻ መደንቆሩ
ኦና ቤት ታቅፈው ፣
ጠረጴዛ ፣ወንበር፣ጣራ ፣እየቆጠሩ ፤
ለብቻ ማደሩ፤
ብቻ መዘመሙ፤
አይደለም ስሌቱ አይደለም ትርጉሙ፡፡
“ላንተ አይደለም” የሚለው ግጥም ስሜት ይይዛል፡፡ውበትም አለው፡፡
የሀዘን ጅራፍ ገምጄ፣
ለጋ ሰውነቴን ብተለትል ነፍሴንም፣
በሲቃ ባርደው፤
አሻግሬ ለምቀላውጥ ፤መጣ ቀረ እያልኩ፤
አካሌን በጭንቀትም ባስቃትተው፤
ውዴ ሙት ስላንተ አይደለም፡፤
በቸልታህ ካራገብከው ፍም ላይ፣
ነፍሴን ያለስስት የጣድኩት፣
“የኔ ሁኝ”ከሚለኝ ሁሉ …
አንተን ከርቀት የመረጥኩት፤
ሆዴ ሙት ስላንተ አይደለም፡፡
…እያለ ይቀጥላል፡፡ የትዕግስት ግጥሞች ተመሳሳይነት ቢታይባቸውም ድንቅ ውበትና አገላለጽ ግን አላቸው፡፡ ዜማቸው፣ማዕከላዊ ሃሳብ ጠብቀው መጓዛቸው ሁሉ ጥሩ ነው፡፡ምትና የምጣኔ ችግር አይታይባቸውም -ከአንዳንድ ቦታዎች በቀር፡፡
“ኑዛዜ” ከሚለው ግጥምዋ ልዋስ፡-
ከፀሃይ መድመቂያ አንስቶ ፤እስከ ሰማይ፤
ጥቁረት ድረስ፤
የምናፍቀውን ታውቃለህ መቼ ነው የልቤ ሚደርስ?
ሕይወተ ቢስ መሆኔ፤ለርሱ ምን ይፈይዳል?
ትዕግስትን የሰነቁ ለት አንድ እንጨት ብቻውን ይነዳል፡፡
ጥሩ የቃላት አጠቃቀም ለግጥም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ግጥሞቻችን የቃላት ድህነት አጥቅቷቸዋል፡፡
“የመለየት ትርጉም”ውስጥ ደስ ያሉኝን ስንኞች እናንብብ፡-
በዚያ የደስታችን ማድመቂያ ጊዜ፣
በዚያች ሽራፊ የሕይወት ብልጭታ፣
አካልህ ከኔ ተጋድሞ፣
ነፍስያህ ከተሰደደች፣ለትናንትህ ቀን ሞታ፤
በትናንት ትዝታ ዶፍህ፣
ተስፋችን ውርጭ አዝሎታል፣
ተንጋዷል አብሮነታችን፣
ምን ልብህ ከኔ ቢሆንም…
ያለፈ ኑረት ትዝታህ፣የኋሊት የጎተተህ ዕለት፣
ያን ጊዜ ተለያይተናል፤
ሳቃችን ባዶ ጩኸት ነው፤
ፍቅር ፊት የምናስመስል፣
ራቁት ቋሚ ሆነናል፡፡
በአጠቃላይ ሲታዩ የትዕግስት ግጥሞች ጥሩ ናቸው፤ ትልቁ ስህተት አንድ አይነት ድምጽ መሆኑ ነው፡፡ ስለፍቅር፤ ደግሞ የወደቀ ፍቅር!! አንድ ዜማ! ከዚያ ውጭ ትዕግስት ወጣትም ናት፤ ጎበዝም ናት፡፡ ለወደፊቱ በጣም የተሻለ ነገር እንደምትሰራ ግጥሞችዋ ይናገራሉ፡፡
“ግድ የለም” የሚለው ግጥምዋ መግቢያ እንዲህ ነው፡-
በወጣትነቴ ዋዜማ ዕለት …
ሮጦ ያልጠገበው እግሬ፣ለዕይታህ ተደናበረ፣
ሽንፈት ዘማሪው ልቤ፣የሩቁን አድሮ ሲያሰላ፣
ቸልታህ ከቅርብ አስቀረው፤
በሃዘን ጽልመት ታጠረ፡፡
ፅሁፌን “ድንቄም” በሚለው ግጥሟ ልዝጋ መሰለኝ፤
የተስፋዬን ክታብ አሻራ ፣
በስህተት ዱልዱም ቢላ ገዝግዘህ እያከረርከው፤
የሚያምንብህ ልቤን ቆፍረህ፤
ከስጋት መንደር እያኖርከው፤
ፅናት ከየት ሊመጣ ብለህ?
ድንቄም የሩቅን ማለም!
ድንቄም ነገን ማስታከክ!
ድንቄም ወግ ወጉን መያዝ፤
ድንቄም ምኞትን ማኘክ!
ስለ ትዕግስት ካነሳን አይቀር ስርዐተ-ነጥብ አጠቃቀምዋን ማድነቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ድርብ ሰረዝ፣ ነጠላ ሰረዝ፣ ቃለ አጋኖ፤ የጥያቄ ምልክት ሳይቀር በሚገባ ተጠቅማለች፡፡ ትዕግስት ግጥም ለመጻፍ ጥሩ አቅም አላት ብዬ አምናለሁ፤ ስለዚህ አትቁሚ! አትጥፊ! ብዬ እጨርሳለሁ፡፡


 

br /

Read 7998 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 10:57