Saturday, 08 October 2022 09:28

“አሁን ለምንድነው ፈሪ ማቀንቀኑ ቅጠል አይበጠስ ካልደረሰ ቀኑ!”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዕለታት አንድ ቀን ልክ እንደ ደራሲ ስብሐት ልብ ወለድ ባሕሪ፤ እንደ አጋፋሪ እንደሻው፤ ሞትን የሚፈሩና የሚሸሹ አቶ መርኔ የሚባሉ ባላባት ነበሩ፡፡ የሰፈሩ ሰው አብዬ መርኔ እያለ ነው የሚጠራቸው፡፡
አቶ መርኔ ሞትን ለማሸነፍ ሲሉ ወደፊት የሚሆነውን ነገር የሚተነብዩ ኮከብ ቆጣሪዎች ዘንድ ሄደው ያውቃሉ፡፡ ኮከባቸውን አስቆጥረዋል፡፡ የወደፊታቸው ሁኔታ፣ ፍፃሜያቸው ምን እንደሚሆን ለማወቅ ከጅለው፡፡
የመዳፍን መስመር እያዩ የሰውን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚናገሩ መዳፍ አንባቢዎች ዘንድም ሄደዋል፡፡ ዕጣዬን እዩልኝ ብለው የተለያዩ አዋቂዎችን  ጠይቀው አስነብበዋል።
ሞራ ገላጮች የሚባሉ የሰው መፃዒ ዕድል ተናጋሪዎችም ጋ ሄደው የወደፊት ፍፃሜ ሕይወታቸውን ለማረጋገጥ ሞክረዋል፡፡ የቡና ስኒ አይተው ስለ ዕድል የሚናገሩ ሰዎች ቤትም ሄደው “መጨረሻዬን ንገሩኝ እባካችሁ?” ብለው ተማጥነዋል፡፡
በየመፅሐፍ - ገላጩ ሰፈር እየዞሩ የነገ ሕይወታቸውን አላፊ ዕድሜ ሊያስጠኑ ጥረት አድርገዋል። አብዬ መርኔ ያልሄዱበት ቦታ የለም፡፡
ሁሉም አዋቂዎች የሚሞቱባትን ሣምንት ጠቅሰው፣ ”የፈለጉትን ጥንቃቄ ቢያደርጉም፤ የሚሞቱት በእሾህ ተወግተው ነው!” ሲሉ ነገሩዋቸው፡፡
አብዬ መርኔም በልባቸው፤
“እንዲያማ ከሆነ እኔ እሾክ የደረሰበት አልደርስም! እንዲያውም ከእነአካቴው ከቤቴ አልወጣም” ይሉና በነዚያ በተጠቀሱት ቀናት እቤታቸው ክትት ብለው ሰነበቱ፡፡
ከተባሉት አንድ ቀን ብቻ ነው የቀራቸው፡፡ ቤታቸው በረንዳ ላይ ተቀምጠው አላፊ አግዳሚውን የሰፈራቸውን ሰው ሰላም እያሉ፣ “እንዴት ሰነበትክ ?” ሲሉ አመሹ፡፡
ወደ ቤታቸው ሊገቡ ጥቂት ሲቀራቸው፣ የከብት እረኛቸው፣ ላሞችና በጎች እየነዳ መጣ፡፡
አብዬ መርኔ ከግልገልነቱ ጀምሮ ያሳደጉትን በግ አዩ፡፡ በጣም ደስ አላቸው፡፡ በጉ ያውቃቸዋልና እየሮጠ ወደሳቸው መጣ፡፡ እያሻሹ ሲያጫውቱት ድንገት በፀጉራም ቆዳው ውስጥ የነበረ አንድ እሾክ መዳፋቸውን ጠቅ አደረጋቸው! ደማቸው ክፉኛ ፈሰሰ፡፡ ቁስሉ አልሽር አለ፡፡ ለካ ያ እሾክ መርዝነት ያለው ኖሮ፣ ብዙም ፋታ ሳይሰጣቸው ለሞት አበቃቸው!
“ዓለም አላፊ ነው
መልክ ረጋፊ ነው
ፎቶግራፍ ቀሪ ነው!”
ይላሉ የጥንት ሰዎች፡፡ ከተፃፈልን ቀን አናልፍም፡፡ የዕጣ-ፈንታችን ነገር ነው፡፡ በሕይወት የምንኖርባትን እያንዳንዷን ደቂቃ እንጠቀምባት እንጂ ነገን አንጠብቅ፡፡ በእጃችን ያለውን ወርቅ ቀን ሳንውል ሳናድር እጥቅም ላይ እናውለው፡፡
ሀገራችን የጦር አውድማ ከሆነች አያሌ ዓመታት  ተቆጥረዋል። ስደት እንደ አዘቦት ቀን ልብስ ከተዘወተረ ከራርሟል። መፈናቀልና ቀዬን ለቅቆ መሄድ ወረት መሆን ከተወ ቆይቷል። ይሄም ያልፋል እያሉ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ሞኝነት ሆኗል። መንግሥትም፤ “የበላችው አቅሯታል፣ በላይ በላዩ ያጎርሳታል!” እንደሚባለው፤ ነጋ ጠባ የማይፈጸም ቃል መግባቱን ቀጥሎበታል። “ለምን አልፈጸምክም?” ብሎ መንግስትን አፋጥጦ ለመጠየቅ ህዝብ ወኔ አጥቷል። አሊያም በተደጋጋሚ በደረሰበት ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል፣ ቁምስቅሉን እያየ፤ ያረገው ነገር ቸግሮታል። አንገቱን ደፍቷል!
ያውቃሉ የተባሉት ምሁራንም ዱሮ ይባል እንደነበረው፡-
“እናውቃለን። ብንናገር እናልቃለን!” የሚሉ ይመስላል። ወይም ፍርሐት ቤቱን ሰርቶባቸዋል። ረዥም ዕድሜን ከዘለዓለማዊነት እያምታቱ (They took longevity for eternity እንዲሉ)፣ ያልፍልናል እያሉ ራሳቸው ያልፋሉ! የእርግማን እስኪመስልባቸው ድረስ አድር-ባይነትን፣ ስግብግብነትን፣ ሁሉን ለእኔነትን ተያይዘውታል! የሩቅ ምስራቅ ጠበብት፤”የአንድ ህብረተሰብ ጥንካሬ በምሁሩ መዓዛ ሽታ ይለካል” የሚሉት ብሂል፣ ለሀገራችን ምሁራንም መጠቀስ ያለበት ሀቅ ነው ብንል ከማጋነን አይጣፍብንም፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከተፈጥሮም ጋር ትግል ይጠበቅብናል። ጎርፍ፤ ድርቅና የአየር መዛባት በተደጋጋሚ አባዜው አልለቀን ስላለ ለከባድ ቸነፈር እና ርሀብ መጋለጣችን በየአስርት ዓመቱ የምናየው ክፉ እጣ መስሎብናል፡፡ ይህን የሚቋቋም ብርቱ ጫንቃ ያለው ትውልድ ከመፍጠር ይልቅ፤ “ጦርነቱ አገርሽቷል” የሚል ዜና የሚያዳምጥ ማህበረሰብ አቅፈንና አዝለን፤ መቀመጥን ሥራዬ ብለን ረዥም መንገድ ዳክረናል!
አሁን፤ያለፈው ይበቃን ዘንድ ወደፊት ለመራመድ መቁረጥ አለብን፡፡ የመለወጥ/ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል፡፡ ድህነትንም ሆነ ድህነትን የሚያመጣብንን ሁሉ ለመቋቋም መነሳት ግድ ነው። በአንድ በሀገር ጉዳይ ሁላችንም ተጠያቂ መሆናችንን አንርሳ። ያየነውን አይተናል ለማለትና እንከንም ካለበት ለመጠቆም፤ ለመዋጋት ወደ ኋላ አንበል፡፡ እንድፈር፤ እንነጋገር፡፡
“አሁን ለምንድነው፤ ፈሪ ማቀንቀኑ
ቅጠል አይበጠስ፤ ካልደረሰ ቀኑ!”
ያሉ አባቶች ያቆዩዋት አገር እንደሆነች አንርሣ! መንገድ ካልጀመሩት አይገፋም፤ ወንበር ካልያዙት የማንም መቀመጫ ነው! ለሁሉም በዚህ ዘመን፤ ልብና ልቦና ይስጠን!

Read 12221 times