Sunday, 09 October 2022 00:00

እየተጣራ እያማረ፣ ወይም እየደፈረሰ እየጎደፈ ይሄዳል - ዘመን!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

   “የተረትና ምሳሌ” ግዛት ውስጥ፣ ትክክለኛው የጥበብ መንገድ፣ ከተረት ይጀምራል። እየተበጠረ እየተለቀመ ይጠራል። እየተነጠረ ኩልል ብሎ ይፀዳል። ወደ “ምሳሌያዊ ዘይቤ” ይሸጋገራል።
በሌላ አነጋገር፣ ከተረት ማህፀን ውስጥ ምሳሌያዊ ብሒል ይወለዳል ማለት ይቻላል። እንዲህ ስንል ግን፣ ተረትን ዝቅ፣ ምሳሌን ከፍ ለማድረግ አይደለም። በጥምረት “ተረትና ምሳሌ” ተብለው የተሰየሙት አለምክንያት አይደለም።
ተረት፣ ራሱን የቻለ ጥበብ ነው። ምሳሌም ሌላ የጥበብ ማዕረግ ነው - ከተረት የሚወለድ የጥበብ ማዕረግ።
በእርግጥ፣ ሁሉም ምሳሌያዊ አገላለፆች፣ “የተረት ልጆች” ናቸው ማለት አይደለም። በጭራሽ። እንደ ምድር አሸዋ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት ለስፍር ለቁጥር የሚያስቸግሩ አብዛኞቹ ምሳሌያዊ አገላለፆች፣ በትውልድም በጉዲፈቻም ከተረት ጋር አይዛመዱም።
ሃር ከመሰለ ዞማ ፀጉሯ ጀምሮ እስከ ሎሚ ተረከዟ ድረስ የፍቅረኛውን ውበት ለማድነቅ የወደደ ወጣት፣… ተረት እያቀለጠ ሲያነጥር አይውልም። ጥርሶቿን ከወተት፣ ፈገግታዋን ከወጋገን፣ ድምፅዋን ከሙዚቃ ጋር እያመሳሰለ ውበቷን ለማወደስ፣… ተረት አያስፈልገውም።
እሷም በተራዋ፣ “ድምፁ እንደ ነጎድጓድ ልብን የሚያስደነግጥ፣ ንግግሩ እንደ ፀሐይ ሁለመናን የሚያሞቅ፣ አረማመዱ እንደ አንበሳ የሚያኮራ”… ብላ ወዳጇን ለማሞገስ፣ ተረቶችን አታጠናም። በሕዝብ መሃል ግርማ ሞገሱ ከሩቅ ይጣራል፣ እንደ ዘውድ ገንኖ ይታያል… ትላለች። ጠመንጃው ዓይን አለው ብላ ልትዘፍንለትም ትችላለች - አልሞ ተኳሽነቱን ለመግለፅ።
ምናለፋችሁ! ለፍቅር ትኩሳት የሚስማሙ እልፍ አእላፍ ምሳሌያዊ አገላለፆችን መጠቀም ይችላሉ። አዳዲስ አባባሎችን ለመፍጠር ከሞከሩም ይቅናቸው - አቅሙ ካላቸው።
ነገር ግን፣ ከምሳሌያዊ አገላለፆች ባሻገር፣ ተጨማሪ መልዕክት በውስጣቸው አምቀው ያዘሉ ወይም የሕይወትን ምስጢር በጨረፍታ ለማሳየት የሚችሉ ምሳሌያዊ አባባሎች ደግሞ አሉ። እነዚህ ምሳሌያዊ ብሒሎች፣ በመንፈስና በአካል፣ ትውልዳቸው ከተረት ጋር የተዛመደ ነው። ማድነቂያ ወይም ወውቀሻ፣ ማስረጃ ወይም ማፍረሻ፣ ማበረታቻ ወይም ማስጠንቀቂያ፣ መመሪያ ወይም መገሰጫ የሕይወት መልዕቶችን ወይም ምስጢሮችን የያዙ ምሳሌያዊ ብሒሎች፣… የተረት ልጆች ናቸው።
በእርግጥ፣ ምሳሌያዊ ብሒል ሁሉ፣ “ስሙን ከነአባቱ” ፅፎ የትውልድ ሐረጉን እየዘረዘረ ይመጣል ማለት አይደለም። እንዲያውም በሰፊው የሚታወቁ በርካታ ምሳሌያዊ ብሒሎች፣ ከየትኛው ተረት መቼ በአካል እንደተወለዱ በግልፅ አይታወቅም።
“መኖር ደጉ ይላሉ አበው!” ብሎ ዛሬ ይናገራል። በማግስቱ ደግሞ፣ “አለሁ ማለት ከንቱ!” የሚል ምሳሌያዊ ብሒል ይመጣበታል። ምን ከሚሉት ተረት፣ ወይም ከየትኛው ገጠመኝ እነዚህ አባባሎች እንደተፈጠሩ አናውቅ ይሆናል። ነገር ግን፣ ከገጠመኝ ወይም ከተረት ጋር የተዛመዱ ብሒሎች እንደሆኑ ይገባናል። ምን ገጥሞት ይሆን? ብለን እናስባለን። ለመገመት እንሞክራለን። ወይም ደግሞ፣ ከየትኛው ተረት እንደተወለዱ ለማስታወስ እንጥራለን።
ይህም ባይሳካ ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ የተረት መንፈሳቸውንና ተረትኛ ዝምድናቸውን መገንዘብ አያቅተንም። ምሳሌያዊ ብሒል ከሰው ስንሰማ፣ “ተረተ፣… ተረተች”፣ “ተረተብን፣… ተረተችብን” እንል የለ!
ሰው ብርቱ!... ወይም ሰው ሞኙ!… የሚሉ ብሒሎች፣ ምንም ተቃራኒ ቢሆኑም እንኳ፣ የተረት ልጆች መሆናቸው ያመሳስላቸዋል። ታዲያ፣ ከአንድ ተረት የመጡ ናቸው ማለት አይደለም። “የእናት ሆድ ዥጉርጉር” ብለን ካልተረትን በቀር፣ ከአንድ አይነት ተረት ውስጥ ተቃራኒ መልዕክት የያዘሉ ምሳሌያዊ ብሒሎች ሊወለዱ አይችሉም። ይችላሉ?
“የአነጋገር ለዛ፣ የብረት መዝጊያን ያስከፍታል” የሚል መልዕክት እናገኛለን - ከአንዱ ተረት። ከሌላኛው ተረት ደግሞ፣ “በአነጋገር ለዛ፣ የብረት መዝጊያ አይታዘዝም” የሚል ምሳሌያዊ ብሒል ይወለዳል። የየራሳቸው “እናት ተረት” ቢኖራቸው ይሆናል። ምንም ሆነ ምን፣ የተረት ልጅነታቸው አያከራክርም። ቢያከራክርም ግን፣ በአካል ሲወለዱ ባናይ እንኳ፣ በመንፈስ የተረት ልጆች መሆናቸው አያጠራጥርም።
ከሐተታ ወይም ከትንታኔ በኋላ የሚመጡ የሃሳብ ድምዳሜዎች እንዳልሆኑ ይገባናል። የሕይወትን ሐዲድ መርምረው፣ የኑሮን ዱካ አገናዝበው፣… እንዴት ወደ ምሳሌያዊ ብሒል እንደደረሱ በትንታኔና በሐተታ እንዲያስረዱን አንጠብቅም።
ይልቅስ፣ በስጋና በአጥንት ሁሉ የሚሰራጭ፣ ደምና ነፍስ ውስጥ የሚሰርፅ ጥልቅ ትርጉም ያዘለ ልዩ ገጠመኝ ወይም አንዳች ተረት የሚተረኩልን ይመስለናል። ባይተርኩልን እንኳ፣ “ምን ገጥሟቸው ይሆን?”፣ “ምን አይተው፣ ምን ሰምተው ይሆን?” ብለን የገጠመኝ ሃሳብ ወይም የተረት መንፈስ በአእምሯችን ይመጣልናል፣ ወይም ይመጣብናል።
ገጠመኛቸውን ሲተርኩልን፣ ተረቱን ሲነግሩን፣… “ሰው ብርቱ፣… መኖር ደጉ!” ያስብለናል። ወይም ደግሞ፣ “አየ የሰው ነገር፣… አለሁ ማለት ከንቱ!” የሚያሰኝ ይሆናል።
በእርግጥ ብዙውን ጊዜ፣ ምሳሌያዊ አባባሉን ብቻ እንጂ፣ ከየትኛው ተርት እንደተወለደ ላይታወቅ ይችላል። “ከራስ በላይ ነፋስ” የሚለው ምሳሌያዊ ብሒል፣ ከየትኛው ተረት የመጣ ይሆን? “ፍሬያማ ዘለላ ጎንበስ ይላል” የሚለውስ?
የተረት መንፈስ እንዳላቸው ባይካድም፣ የተረት ልጅነታቸውን በእርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል።
አንዳንድ ምሳሌያዊ ብሂል ግን፣ በአካል ተጸንሶ በግላጭ ይወለዳል።
ምሳሌው ከነተረቱ ይታወቃል። ሊታወቅ ይችላል ማለቴ ነው። የማያውቁ ይኖራሉና።
“ለምን ኬክ አልበሉም አለች”… ተብሎ ሲነገር ሰምታችሁ ይሆናል።
ምሳሌያዊ አባባል ነው። ነገር ግን፤ የተረት ልጅ እንደሆነ፣ ራሱ ምሳሌያዊው አባባል ይናገራል፤ በራሱ አንደበት ይናዘዛል፤ ወይም ያውጃል። የተረት ቀለሙ ገና ያልለቀቀ ምሳሌያዊ አባባል ሲገጥመን፣ “ተረተባቸው፣ ተረተብን”… እንደምንልም አስታውሱ።
ያው፤… “ለምን ኬክ አይበሉም?” የሚለው ተረት፣ የየዘመኑን መንግስት፤ የየአገሩን ንጉሳዊ ስርዓት ለማብጠልጠልና ለማጥላላት አገልግሏል። የንጉስ ቤተሰቦች ላይ ለማላገጥ፤… እንደ አዲስ እየተተረተ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ እውነተኛ ታሪክ፣ እንደ ትኩስ መረጃ እየተቆጠረም ተተርኳል።
እንዲያውም፣ እንደ እውነተኛ ታሪክ ከመቆጠሩ የተነሳ፣ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ታሪክ መስሎ ሊታየን ይችላል። ነገሩ እንዲህ ነው።
ጊዜው፣ የዛሬ 50 ዓመት ነው።
ንጉሣዊ አስተዳደርን ለማጥላላት ተኝቶ የማያድር “የአመፅና የአብዮት ትውልድ” ከተፈጠረ በኋላ፣ አፍላ የጉርምስና እድሜ ላይ እየደረሰ ነበር - በ1965 ዓ.ም። ያኔም ነው፣ አመፀኛው የአብዮት ትውልድ… ነባሩን ጥንታዊ ተረት፤ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ላይ ያሳረፈባቸው። ለዚያውም፣ እንደ ማላገጫ ተረት ሳይሆን፣ እንደ መወንጀያ ታሪክ ነበር የተቆጠረው።
ክፉቱ ደግሞ፤ ያኔ ክፉ ረሃብ የተከሰተበት ጊዜ ነበር። እና፣ አብዮተኞቹ የአመፅ ወጣቶች ምን ብለው ተረኩ?
የተራቡ ሰዎች፣ የሚበሉት የሚቀምሱት አጥተው፤ “ዳቦ ዳቦ” ብለው ይጮሃሉ። ወደ ቤተ መንግሥት እጃቸውን እየዘረጉ ይማፀናሉ። ይህን የተመለከተችና የሰማች ወጣት ልዕልት ግራ ገብቷታል። “ለምንድ ነው ዳቦ ዳቦ እያሉ የሚጮኹት?” ብላ ጠየቀች።
ርቧቸው ነው ብለው ነገሯት።
“ታዲያ ዳቦ ከሌለ ለምን ኬክ አይበሉም” አለች።
የያኔዎቹ አመፀኛ ወጣቶች፤ ይህን ተረት እንደ እውነተኛ ታሪክ ሲያወሩ፤ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየደጋገሙ ወሬ ሲነዙ፤ ትልቅ ቁምነገር የሰሩ እንደሚመስላቸው አትጠራጠሩ። ንጉሣዊውን ሥርዓት ማጥላላት፤ ዋና አላማቸው ሆኗልና።
ዘወትር ንጉሡን መወንጀል መደበኛ ስራቸው መስሏል። እውነተኛ መረጃ መሆን አለመሆኑን ማጣራት አያስፈልጋቸውም። ለአላማ እስካገለገለ ድረስ፤… እውነተኛ መረጃም፤ የውሸት አሉባልታም… ይፈቀዳል። በደስታ ተቀብለው በሆታ ያስተጋቡታል።
እንዲያውም፤ ነባሩን ሥርዓት በውሸት መወንጀል፤ ተቃዋሚን በአሉቧልታ ማንቋሸሽ፣… የዓላማ ፅናትን እንደማስመስከር ሆኖ ይታያቸዋል።
ወይ አለማወቅ! ለታሪክ ደንታ የሌላቸው፣ ለመጪው ዘመን በቅጡ ማሰብ የማይፈቅዱ አላዋቂዎች፤ ለእውነታ የመታመን መልካም ስነ-ምግባርን የመከተል መርህ አይኖራቸውም። ከዛሬዋ እለት፤ አሁኑዋ ቅጽበት አልፈው ማየት ባይችሉ ነው። ወይም ለማየት ባይፈልጉ።
የሚቃወሙትን ከማንቋሸሽ የሚጠሉትን ከማፍረስ ውጭ፤ ነገ ከነገወዲያ ምን ለመገንባትና ምን ለመስራት እንደሚፈልጉ በወጉ ለመረዳት፤ በቅጡ ለመምረጥና ለመወሰን የማሰቢያ ጊዜ የላቸውም። ማሰብ እንደሚያስፈልግ አይታያቸውም።
ነባሩን ስርዓት ሲያፈርሱ ወይም ተቀናቃኛቸውን ሲያጠፉ ሁሉም ነገር የሚሳካና የሚያምር ሆኖ ይሰማቸዋል። በቃ፣ የማፍረስና የማጥፋት ሃሳብ ብቻ እንጂ፣ ምንን እንዴት እንደሚገነቡ፣ ምን ዓይነት መርህ እና ብቃት፣ የቱን ያህል ጥረትና ጊዜ እንደሚያስፈልግ አያገናዝቡም። ማሰብና ማሰላሰል እንደ ትልቅ ቁም-ነገር አይቆጥሩትም።
አመጽን ለማጥፋት ብቻ የሚጓጓ መንግስት፣ ወይም ነባሩን ስርዓት ለመገንደስ ብቻ የሚያሰፈስፍ አመፀኛ፣ ለስነ-ምግባርና ለመርህ፣ ለህግና ለስርዓት ብዙም ግድ የማይኖራቸውም በዚህ ምክንያት ነው። አመፅን የማጥፋት ወይም መንግስትን የመናድ አላማ ብቻ ነው የሚታያቸው።
ለጊዜው እና ለዛሬ፤ “ለአላማ እስካገለገለ ድረስ” ደግሞ፤ የሀሰት ውንጀላን የአሉቧልታ ዘመቻን በደስታ ያስተናግዳሉ። ያደንቃሉ። እየተቀባበሉም ያዛምታሉ። ነባሩን ስርዓት ቢያፈርሱና ቢሳካላቸው፣ ነገ እርስ በርስ ለመወነጃጀልና ለመጠፋፋት ተመሳሳይ ዘዴ እንደሚጠቀሙ አይገባቸውም።
አዲስ ግንባታ መጨመር ሳይሆን ነባሩን ማፍረስ እንደ ቋሚ አላማ ቆጥረው ዛሬ ሲዘምቱ፤ ነገ ገሚሶቹ ባለስልጣን ገሚሶቹ ተቃዋሚ ሆነው አንዱ ሌላውን ለማፍረስና ለማጥፋት እንደሚዘምቱ አላወቁም።
የዛሬዋን የቅፅበቷን ብቻ ነው የሚያዩት።
ወደ ነገ አሻግረው ላለማየት ዓይናቸውን ጋርደዋል።
ለነገሩ፤ ነገን በዓይነ ህሊና ለማየት ይቅርና፣ ትናንትን ለማስተዋል፣ ከታሪክም ክፉና ደጉን ለመማር አልቻሉም።
ጥንታዊው ተረት ወቅታዊ ዜና መስሎ የታያቸውም በአላዋቂነት ሳቢያ ነው። አልያም በጭፍንነት ወይም፣ ለእውነትና ለእውቀት ደንታ ቢስ በሆነ ክፉ መንፈስ ሳቢያ ሊሆን ይችላል።
እናም የየዘመኑ አመጸኛ አብዮተኞች፣ “ለምን ኬክ አይበሉም?” የሚለው አባባል፤ ምዕተ ዓመታትን ያስቆጠረ ጥንታዊ ብሒል መሆኑን ለማወቅ አይፈልጉም። ትኩስ ዜና ይመስላቸዋል።
የዛሬ ሁለት መቶ ዓመት በፈረንሳይ አብዮት ዘመን፤ ተመሳሳይ ተረት እንደ ጉደኛ ዜና እንደ ወረት ይናፈስ ነበር። ንጉሳዊውን ስርዓት ለመወንጀል አገልግሏል።
ታዲያ የዘመኑ የፈረንሳይ አመጸኞችና አብዮተኞች፣ ንጉሳዊውን ስርዓት ካፈረሱ በኋላ፣ እርስ በርስ እንደ አውሬ መተላለቃቸው ይገርማል?
እውነትን መተማመኛው፣ እውቀትን መንቀሳቀሻው፣ መልካም አላማና የስነ-ምግባር መርህም የእለት ተእለት መመዘኛውና የጉዞ መመሪያው ሲሆን ነው፤ ነገር የሚያምረው አላማ የሚያዛልቀው።
መርህ  የሌለው፣ … ማለትም፣  በማንኛውም ዘዴ ተቀናቃኙን ለመደምሰስ ወይም ነባሩን መንግስት ለማፍረስ ታስቦ የተወጠነ አላማ ግን ቢሳካ እንኳ፣ እንደገና ሌላ ዙር ትንቅንቅና መጠፋፋት ከመፍጠር ያለፈ ውጤት የለውም።
ሌባን ሌባ ቢሰርቀው ምን ይደንቀው ተብሎ የለ!
ይህ ምሳሌያዊ አባባል፣ ከየትኛው የተረት መነሻ የመጣ ይሆን? ለማንኛውም፣ መልዕክቱ ግልጽ ነው።
ለዛሬ፣ ለአሁን፣ ለጊዜው ተማምለው፣ ተቀናቃኛቸውን በውሸት ለመወንጀል ወይም ለመስረቅ የተስማሙ ሰዎች፣ ነገ ሲሳካላቸው እርስ በርስ አንዱ ሌላው ላይ መዝመቱ አይቀርም። የፈረንሳይ ዓመጸኛ አብዮተኞችም ከዚህ መመዝ አላመለጡም።
ለነገሩ፣ ከ1500 ዓመታት በፊት ጥንታዊው የሮም ሥርዓት ለማጣጣልና ለማፍረስ አገልግሏል- “ለምን ኬክ አይበሉም?” የሚለው ተረት እንደ እውነተኛ ታሪክ እየተተረከ፣ እንደ ውንጀላ አንቀጽ እየተጠቀሰ በዘመኑ ተለፍፏል።
ትክክለኛው የጥበብ መንገድ፣ ከእውነተኛ ገጠመኞች ወደ ፈጠራ ታሪኮች ወይም ወደ ተረት፣… ከተረት ደግሞ ወደ ምሳሌያዊ ብሒል የሚወስድ የውበት የእውቀት የብስለት መንገድ ነው።
በተቃራኒው፣ ነጥሮ የተጣራው ምሳሌያዊ ብሒል ተረስቶ፣ የኋሊት ወደ ተረት ሲመነዝር፣ እና እዚያው በብትኑ ሲቀር፣… ጥበብንና እውቀትን የሚያራቁት፣ መንፈስን የሚሸረሽር የብክለት መንገድ ይሆናል።
ይባስ ብሎ፣ ምሳሌዊ ብሒልነቱ ተዘንግቶ፣ የተረት ጥበብ እንደሆነም ተረስቶ፣ እንደ እውነተኛ ታሪክ እንደ አዲስ የዜና መረጃ መወራት ሲጀመር ግን፣… ለዚያውም ለሀሰት ውንጀላና ለዘመቻ ማቀጣጠያ ሲያገለግል፣… ያኔ፣… ከሰውነት ወደ አውሬነት እያንጋጋ የሚነዳ ዘመን ተፈጥሯል ማለት ነው።
ከተጣራ ጥበብ ወደ ድፍርስና ግርድፍ፣ ከዚያም ወደ አስቀያሚ የቆሻሻ ፍሳሽና ወደ ጉድፍ እንደ መውረድ ቁጠሩት።


Read 14289 times