Saturday, 08 October 2022 09:39

“በህግ አምላክ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ከፈረንጅ መጽሐፍ ላይ የተገኘችን ታሪክ እዩልኝማ! አቃቤ ህግ ከሳሽን እያነጋገረ ነው፡፡ ሰውየው ተደብድቤያለሁ ብሎ ነው የክስ ፋይል የከፈተው፡፡
“ክስህ ላይ ተከሳሽን ጨካኝ ነው፣ ጨከነብኝ ትላለህ፡፡ ምን አደረገህ?”
“ደበደበኝ፣ ነከሰኝ፡፡”
“በምንድነው የደበደበህ?”
“በዱላ፡፡”
“በምንድነው የነከሰህ?”
እሰይ! እና የአንዳንድ ጋዜጠኞች አጠያየቃችን እንዲሁ ነው፡፡ እንግዲህ ዘንድሮ የማይደረስበት ‘አዳዲስ ግኝት’ የለም አይደል! የሰው ልጅ ‘መንከስ የሚቻል’ን (አሁን ደግሞ በተለይ እኛ ዘንድ ደግሞ ‘መንከስ የማይቻልን’) ነገር ሁሉ ከጥርስ የተለየ ሌላውን ‘መንከሻ ምን መሳሪያ’ እንዳለው እውቀቱ የተገለጠላቸው ይንገሩንማ! ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ዘብረቅ ማድረግ የሚመስል ነገር ውስጥ ዘው የምንለው ለምን ይመስለኛል መሰላችሁ...በቃ ‘ስማርት’ ለመሆን ስንሞክር ሳናውቀው እያዳለጠን!
የእኛ ነገር እኮ...አንዳንድ ጊዜ...አለ አይደል...ስታንድአፕ ኮሜዲ ምናም ነገር ይመስላል፡፡
“የዛሬው እንግዳችን ከመንግሥት ሥራ ለቅቀው ወደ ኢንቬስትመንት የገቡ ናቸው። በአሁኑ ጊዜም የሦስት ሆቴሎች ባለቤት ናቸው፡፡” በአምስት አባዝቶ አሥራ አምስት ያደርግላቸውማ! እንግዲህ እህታችን ዋናውን መረጃ ከነገርሽን በዘመኑ ቋንቋ ይመችሽማ! አሁን ደግሞ እንግዳው ሞዴል ስድስትን ለመውሰድ ከመሰለፍ እንዴት አድርገው አንድ ብለው የሆቴል ሰልፍ እንደጀመሩ ጠይቂልንማ፡፡
“እንግዳችን ወደ እርሶ ልመለስና በአሁኑ ጊዜ ስንት ሆቴል አለዎት?”
በህግ አምላክ! እንዴት ነው ነገሩ? ምናምን ሺዎችን ጠብ አድርገን (በአራድኛ “ሆጭ አድርገን” ነው የሚባለው አይደል!) ለሸመትነው ቴሌቪዥናችን ስክሪን ሊዝ የምትከፍሉን ይመስል እንደፈለጋችሁ አትሁኑብና፡፡ “ይሄኔ ነበር የፖሊስ ያለህ አትሉም ወይ! የዳኛ ያለህ አትሉም ወይ!” የሚለው ዘፈን የሚያስፈልገን!
እንግዳው ሆቴልም ከፈተ፣ ወፍጮ ቤትም ከፈተ፣ ‘ጭኮ ቤትም’ ከፈተ (አዲስ የቢዝነስ ‘አይዲያ’ ነው! ቂ...ቂ...ቂ....) አንዲት የማትቀር ጥያቄ አለች...
“የሆቴል ቢዝነስ ለመጀመር ያነሳሳዎት ምንድነው?” (በረጅሙ ስተነፍስ ሰማችሁብኝ እንዴ!) እዚህ ላይ ምን መሰላችሁ... እንግዳው በቃለ መጠይቁ ድራማ ውስጥ ከአጃቢ ተዋናይነት አስደናቂና፣ አስደንጋጭ እድገት አሳይቶ ወደ ዋና ገጸ ባህሪይነት ሊሸጋገር ይገደዳል፡፡ (በነገራችን ላይ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...ለጠቅላላ እውቀት እንዲረዳ ያህል፣ ‘አስደናቂ’ እና ‘አስደንጋጭ’ ቃላት በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ለመጠቀም የሆነ ‘ልዩ ታለንት’ ሳይጠይቅ አይቀርም፡፡ አሁን፣ አሁን -- ምናልባትም ዜናዎች እና መረጃዎች ተብለው በሚቀርቡት ‘ሰስፔንስ’ የሚባለውን ነገር ለመፍጠር -- እንዲህ የሚመሳስሉ ነገሮች ደጋግመን ስለምናይ ነው፡፡) 
“ምን መሰለሽ፣ እንዲህ አይነት ሀሳብ በውስጤ ሲፈጠር ምናልባት የአምስትና የሦስት ዓመት ልጅ ብሆን ነው፡፡”
እንደገና እርሶም ራስዎም በህግ አምላክ! እንዴ ለእኛም አስቡልና! ‘ግሎባል ወርሚንግ’ ነው ምናምን የሚሉት መከራ ያበላናል፡፡ እናንተ ደግሞ “ወርም” የሚሉትን መቻል አቅቶን ጭርሱን ብረታብረት ፋብሪካ ልታደርጉን ነው እንዴ! የተከበሩ እንግዳ...ከባቅላባና ከዘቢብ ኬክ ካፌዎች እመርታን አሳይተው ለመጀመሪያ ጊዜ ሆቴል ሲገቡ እኮ እጮኛዎን ‘ኢምፕሬስ’ ለማድረግ ነው ሲባል ሰምቼ ስለነበር ነው፣ ቂ...ቂ...ቂ...፡፡  
የምር ግን ፊት ለፊታችን ካሜራ ስለተደቀነ የግድ ልዩ ምናምን መሆን አያስፈልግም እኮ፡፡ በቃ “በአሁኑ ጊዜ የሆቴል ኢንደስትሪው በጣም አትራፊ እየሆነ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ ቢዝነስ ነው ብዬ የገባሁበት ነው!” አለቀ፣ ደቀቀ፡፡ (ፈረንሳይ ነው ፊሊፒንስ “ሴ ፊኒ!’ ይላሉ የሚባለው? ልጄ...ማን ልብ አንጠልጥሎ ማን ይቀራል! አንዱ ቡቲክ ሲከፍት ሌሎች ሀያ የሚሆኑ እንደሚከፍቱ ሁሉ አምስቱ ‘ልብ ማንጠልጠል’ ሲጀምሩ ሁለት መቶ ሀምሳችን የማናንጠለጥልሳ!)
ይቺን ስሙኝማ...ወጣት ገና ሥራ የጀመረ የፈረንጅ ጠበቃ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ... ገና ከጅምሩ...በቃ “ጥይት እኮ ነው!” ለመባል ፈልጎ ነበር፡፡ ወይም ‘ኢምፕሬስ’ ለማድረግ የሚባለው አይነት ማለት ነው፡፡
እናላችሁ...ከሳሽ ጠበቃ ሆኖ እየተከራከረበት የነበረው ጉዳይ አንዱ ከብት አርቢ በእርሻ ስፍራው አጠገብ ከሆነ ባቡር በኩል ሲያልፍ ሀዲድ በመሻገር ላይ የነበሩ ሀያ አራት አሳማዎችን ይገድላል፡፡ ‘ትኩሱ’ ጠበቃው አስራ ሁለት አባላት ለሚገኙበት የፍርድ ሸንጎ ፊት ለፊት እየተናገረ ነበር፡፡
“ሀያ አራት አሳማዎች፣ ክቡራንና ክቡራት! እስቲ አስቡት፣ በአንድ ጊዜ ሀያ አራት አሳማዎች!” ቆም ካደረገ በኋላ ምን ብሎ ቢቀጥል ጥሩ ነው... “እዚህ ያላችሁትን እጥፍ ማለት እኮ ነው!” ብሎ እርፍ አለላችሁ፡፡ ግዴላችሁም... ይቺ “ፈረንጅ ቅኔ አይችልም፣ የምንላት ነገር...አለ አይደል...እንፈትሻትማ! አሀ ልክ ነዋ... ባቡር የጨረሳቸውን አሳሞች ቁጥር ጠቅሶ ከሰዎች ቁጥር ጋር ንጽጽር መፍጠር ‘የፈረንጅ ቅኔ’ ካልሆነ ምን ሊሆን ነው!
“እንግዳችን እንግዲህ አሁን መንገድ ላይ ነው ያገኘንህ፡፡ አትሌቶቻችን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው  በመግባታቸው  ምን ተሰማህ?”
“ምን ልበልሽ! ምን ልበልሽ!...በደስታ ብዛት በቃ ሌሊቱን ሳልተኛ ቁጭ ብዬ ነው ያደርኩት። (ኸረ እባክህ... አንተስ ይሁን እሺ፡፡ እንደው ለዘመዶችህና ለጓደኞችህ አስብላቸው! በኋላ እኮ...አለ አይደል... ደስ ሲለው እንቅልፍ በዓይኑ የማይዞረው ሰውዬ ወዳጆችና ዘመዶች” ሊባሉ ነው እኮ! አለማድነቅ ግን አይቻልም፡፡ ሰው ጭንቀት ሲይዘው እንቅልፍ ያጣል፣ አጅሬ ደግሞ አትሌቶች ሲያሸንፉ በደስታ ብዛት እንቅልፍ ያጣል! ተፈጥሮማ የሆነ የምትጫወትብን የካርታ ‘በጨ ጠቆረ’ አይነት ነገር ሳይኖር አይቀርም! ) እናላችሁ...”እነእንትና” የሚባሉት ሰዎች አይነት ካልሆነ በስተቀር  በአትሌቶች ድል ከደስታ ሌላ ምን ሊሰማው ይችላል! ታዲያላችሁ...እንግዲህ ተጠያቂው መንገድ ላይ የተገኘ የእኛ ቢጤ ‘ተራ ሰው’ ነው፡፡ ጥያቄውም ይቀጥላል፡፡
“በእውነቱ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ ድል በአንተ እንዴት ይገለጻል?”
አንቺም ራስሽ በህግ አምላክ! አሀ...እኛስ የ‘ኔይል ፖሊሽ’ ቀለም አይነት ምናምን በማድነቅ ብቻ ይሞታል እንዴ! የምር ግን ስማቸውን የማናውቃቸው ‘ቀለሞች’ እየበዙብን ስለሆነ እንዴት ብለን እንደምንገልጽ ግራ ይገባናላ!
“በቃ፣ እንትን በሚባለው ካፌ አምስት ሰዓት ላይ ትጠብቅሀለች፡፡ እና አመስግነህ ይህንን ስጥልኝ፡፡”
“እንዴት ነው የማውቃት! ማለቴ እሷ መሆኗን በምን እለያታለሁ?”
“አጠር ያለች፣ ጠይም፣ ጸጉሯ እዚህ ትከሻዋ ድረስ...”
“ቆየኝማ፡፡ ይህን ሁሉ ከምትዘረዝርልኝ ለምን ምን አይነት የጥፍር ቀለም እንደምትቀባ አትነግረኝም!” ቂ...ቂ...ቂ... (ምን መሰላችሁ...የ‘ኔይል ፖሊሽ’ ቀለም ለመግለጽ ምን ያህል ‘ኮምፕሊኬትድ’ እንደሚሆን በማሰብ አምልጦ የወጣ ‘ጄኒዩን’ ሳቅ እንደሆነ ለማሳወቅ ያህል ነው፡፡)
የምር...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ተሯሩጠውም ‘ትኩስ ዜና’ የሚባል ለማሰማት የሚደረግ ሙከራ ነገር አሪፍ ነው፡፡ ግዴላችሁም ‘ትኩስ ትኩሱን’ ለማድረስ የምንሞክረው መብዛታችን ክፋት የለውም፡፡ ግንማ... ያለመነሻ በስሜት ብቻ የሚሠሩ ነገሮች ሲበዙ...ጥሩ አይሆንም፡፡
“ሰበር ዜና! አሁን ስቱድዮ ከገባን በኋላ የደረሰን ዜና...” ይልና የሆነ ዜና ወይም መረጃ የተባለው ይለቀቃል፡፡ ከዛ ቀጥሎ ምን ቢባል ጥሩ ነው... “ዜናው ህዝብን በስፋት እያነጋገረ ነው፡፡” ቆይ...ቆይማ! የለም...“ቆይማ” ሳይሆን፣ “በህግ አምላክ!” አንድ ቀን እንኳን ሳያድር እዛው በዛው! አሀ...መረጃ አቅራቢዎቹም፣ እኛም እኮ እጅ ለእጅ ተያይዘን አንድ ላይ ስቱድዮ የገባን አስመሰለብና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1361 times