Saturday, 08 October 2022 09:41

ካፑችኖ፣የዮሐንስ ሐሳቦች

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(0 votes)


      “እኛ የግዮን ጥንስሶች - የወይን ፍሳሽ ባለቤቶች - - ጠጥተን - ሰካራም ሳይሆን ራሱን ስካርን ነዉ የምንሆነዉ … ስካርን ስንሆን ደግሞ
      - መርሳት የሌለብንን ዘንግተን - መርሳት የሚገባንን አስታዉሰን - - ማወቅ የማይገባንን አዉቀን እንገኛለን …”
          
          (ክፍል ሁለት)
፪. የዮሐንስ ሐሳቦች
ልብወለድን የመጻፍ ተግባር የላቀ ክህሎትን ብቻ የሚጠይቅ ተግባር አይደለም፣ የላቀ ምናብንም የሚፈልግ እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ደራሲ በእዉቀት የመጠቀ ፈላስፋ መሆን አለበት፡፡ ድርሰት የመጻፍ ተግባር ምሁራዊ ተግባር (intellectual actvity) ነዉ። ዮሐንስ የላቀ ምናብን የታደለ (genius) ደራሲ ነዉ። የዮሐንስ ፍልስፍናዊ ሐተታዎች ፍፁማዊ አድርገን የተቀበልነዉን እዉነት የሚያፈርሱ ናቸዉ፣ የድንቁርናችን መጋረጃ የጋረደብንን እዉነት ገልጠዉ የሚያሳዩ፣ እንደ ህዝብ የገባንበትን የሞራል ዝቅጠት ጥልቀት የሚያሳዩን፣ የተጣባንን ዳተኝነትና ድንቁርና ነቅሰዉ ሐቁን የሚግቱን፡፡ መንገደ ሰማይ በተሰኘ ሥራዉ ዮሐንስ እንዲህ ጽፏል፡
የዛሬዋ ገነት - ጥንተ - ጥንት - ያኔ ድሮ … የሳጥናኤልና የጭፍሮቹ ከተማ ነበረች፡፡ መናገሻ ከተማቸዉ በክብር ሳሉ አለምልመዋታል - - ተራሮቿን ፈልፍለዉ - ያምልኮ ቤተ-ገነቶችን አንፀዉባታል፡፡
አራቱን ተራሮቿን ፈልፍለዉ -ቦርቡረዉ - - ሰርጥ በማበጀት - - አራቱን ወንዞች - ከማህፀኗ መንጭተዉ - ወደ ምድር እንዲዘቀዝቁ አድርገዋል፡፡
(እኛ ኢትዮጵያኖችም - ባለ ወይን ፍሳሹ ግዮን ደርሶናል)
እናመስግን ይሆን- ?
“ደግሞ ከይሲ እናመስግን ትላለህ?” አለች ፀሐፊ ጓደኛዬ፡፡ ይቅርታ - ቢራ አጣጪ ወዳጄ፡፡  
“የምትጠጪዉ ኢትዮጵያዊ ስለሆንሽ እንጂ - ደራሲ ስለሆንሽ አይደለም - - - ወይን - እንደ ኢትዮጵያዊያን - የየትኛዉንም ዓለም ሰዉ - ከልብ አያረካም፡፡”
“ከጠጣንስ በኋላ?”
“እኛ የግዮን ጥንስሶች - የወይን ፍሳሽ ባለቤቶች - - ጠጥተን - ሰካራም ሳይሆን ራሱን ስካርን ነዉ የምንሆነዉ … ስካርን ስንሆን ደግሞ - መርሳት የሌለብንን ዘንግተን - መርሳት የሚገባንን አስታዉሰን - - ማወቅ የማይገባንን አዉቀን እንገኛለን …”
“… የማይጠቅመንን አዉቀን እንወደዉና - ከእርሱ ጋር ወይን በልተን - ወይን ጠጥተን - በወይን ተጠምቀን - ወይን ለብሰን … ቅንዝር ምንዝር እንሰራለን …”
“ኢትዮጵያዊ መሆን ደስ ሲል … ማንንም ስረ መሠረቱ ድረስ ማወቅ ስለማይቻል - ይሄ መልካም የኑሮ ዘይቤ ነዉ” አለች እየተዝናናች፡፡
“በኩርናሽን እስካለወጥሽ ወይም እስካልሸጥሽ ድረስ ማንንም ታዉቂያለሽ - ማንም ያዉቅሻል፡፡”
“ባክህን አትዘባርቅ - ኢትዮጵያዊ መሆን ያምራል!”
“በጣም እንጂ! በስካር የጠነሰሰዉን - የጥበብ አሀዱ - - ከስካሩ ሳይነቃ - አተላ ማድረግ የሚችል ኢትዮጵያዊ ብቻ ነዉ፡፡ በስካር ያቀፈዉን - ታላቅ ፀሐይ - - ከስካሩ ሳይነቃ - ወደ ድጉልጉል ደመና የሚቀይር ኢትዮጵያዊ ብቻ ነዉ…” (ዮሐንስ፣ 2009፡ ገጽ 161-63)፡፡
     የዮሐንስ ልብወለድ ጭብጦች እጅግ ጠጣር ናቸዉ፡፡ ካፑችኖ መድበል ዉስጥ የቀረበዉ ከማዕረግ ወደ ማዕረግ የተሰኘዉ ትረካ ጭብጥ ሜታፊዚካዊ (the existence of good, the problem of evil) ነዉ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ እና ሰዉ ሰራሽ ሰዉ የተሰኙት ትረካዎች ጭብጥ ደግሞ ኤቲካል (justice, injustice, good, evil) ነዉ፡፡  
፪. ፩. ኤቲዝም (atheism)
ዮሐንስ ከማዕረግ ወደ ማዕረግ በተሰኘዉ አጭር ልብወለድ ፈጣሪን (God) በሰዉ ልማድ (የሰዉ ልጅ ባዳበረዉ የአገዳደል ቴክኒክ) በፍጡሩ የሚገደል አካል አድርጎ አቅርቦልናል፡፡ ፈጣሪ በባሕሪዉ መንፈስ ስለሆነ ይህ ድርጊት ተአማኒ ላይሆን ይችላል። መንፈስን በሰዋዊ ልማድ (አንገት በመቁረጥ፣ በማነቅ፣ በካራ በመዉጋት… ወዘተ) መግደል ፍፁም አዳጋች ነዉና፡፡ ዮሐንስ የሚነግረን ቁምነገር ግን ሌላ ነዉ። ዮሐንስ በዚህ ትረካዉ የሚያሰማን ኤቲስቲክ ድምፁን ነዉ፡፡ የዚህ ልብወለድ ስዉር ጭብጥ ኤቲዝም ነዉ። እንደ ጀርመናዊዉ ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ ሁሉ ለዮሐንስ ፈጣሪ የሚሞተዉ በሰዉ ልጅ ልብ ዉስጥ ነዉ፣ በእሱ ላይ የነበረ ፅኑ እምነት በሌላ አካል (በሳይንሳዊ እዉቀት ማለቱ ነዉ ኒቼ) ሲናድ፣ ሲገረሰስ፣ ሲተካ፣ የምክንያት እና ዉጤት ስሌት (causality) የምልዓተ ዓለሙን (universe) አሠራር እንቆቅልሽ ሲፈታ፡፡ በዚህ ትረካ ዮሐንስ እንደሚነግረን፣ ፈጣሪ እና ሰይጣን ሰዉ በልቡናዉ የፈጠራቸዉ ፍጡራን ናቸዉ፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ትረካ ከኤቲዝም በተጨማሪ በዘመናችን የምንመራበት የሞራል እሴት ላይ ብርቱ ጥያቄን (ethical dilemma) የሚያነሳ ነዉ፡፡ ዮሐንስ በዚህ ሥራዉ የሰዉ ልጅ የእግዜርን ሞት በምን አይነት የግብረገብ መርህ ሊዳኘዉ እንደሚችል ብርቱ ጥያቄን ይሰነዝራል። በዚህ ትረካዉ ዮሐንስ የሜታፊዚካዊ ትልቅ ጥያቄ የሆነዉን የአርነት እና የተወስኖሻዊነት ጥያቄንም (the problem of free will and determinism) ይዳስሳል። እንደ ዮሐንስ አቋም፣ የሰዉ ልጅ ሙሉ አርነቱን መጎናፀፍ የሚችለዉ ልቡናዉ ዉስጥ የተፈጠረዉን ፈጣሪዉን በሥልጣኑ ሲገድል ብቻ ነዉ፡፡ ዮሐንስ እንዲህ ጽፏል፡
“ስምህ ማን ነዉ?” አለዉ ሾጣጣዉ ፖሊስ፡፡
ዝም ብሎ አየዉ፡፡ ስሙ የጠፋበት አይነት ሆኖ - ስሜን አስታዉሰኝ ባይ ሆኖ፡፡ ዝም ብሎ አፈጠጠበት፡፡ ስም የሌለዉ አይነት ሆኖ። ዝም ብሎ ዐይኑን ሰነቀረበት፡፡ ‘እንዴት አታዉቀኝም?’ የሚል አይነት ጥያቄ አዝሎ፡፡
“አትናገርም እንዴ?”
“ቦዘኔዉ - ዘባተሎዉ - ደነዙና አረመኔዉ አለሙ አያልቅበት እባላለሁ፡፡”
“ማሾፍህ ነዉ …?” አለ ሾጣጣዉ ፖሊስ ግልፍ እያለዉ፡፡ ከተቀመጠበት ወንበር ተሽቀንጥሮ ተነሳ፡፡ ወደሱ እየተንጠራራ - በመካከላቸዉ ያለዉን ጠረጴዛ አሻግሮ እጁን ላከ፡፡ ለሰላምታ አልነበረም … ዳጎስ ላለ ቡጢ ነበር፡፡ አፍንጫዉ አፈለቀ … ንፍጥ ሳይሆን አወራረዱ ጢስ አባይን የሚያስንቅ ደም፡፡
በዚህ መሃል ነበር - ከዉጭ እነሱ ወዳሉበት ክፍል ሌላ ዱልዱም ፖሊስ የገባዉ፡፡ ቆም ብሎ ያሉበትን ሁኔታ አስተዋለ፡፡ ሁሉ መልካምና እንደተለመደዉ እንደሆነ ተገነዘበ፡፡
“አይ ኮማንደር … ልፋ ብሎህ እንጂ ይሄንን ደነዝ አይደለም በቡጢ በመብረቅም ብትመታዉ የሚሰማዉ እኮ አይደለም …” ወደ ዓለሙ አያልቅበት ዞር እያለ “ … እህ! ዛሬ ደግሞ በምን መጣህ?” በማለት ጠየቀዉ፡፡
“ገድየዉ!”       
“ማንን?” - ቀላል ጥያቄ፡፡ የድርጊት ፈፃሚን ማንነት አንጥሮ ከማወቅ የመነጨ ጥያቄ፡፡
“እግዜርን!”
“ምን?” - ግራ መጋባትና መደናገጥ የወለዳት ጥያቄ፡፡
“ምንም አያገባችሁም፡፡ ልቀቁኝ፡፡ እግዜርን ለገደልኩ ሰዎች ምን አግብቷችሁ ነዉ የምታስሩኝ?”
“ደግሞ አበድክ - ጎሽ - እሱ ነበር የቀረህ” አለዉ አምስተኛ ማዕረጉን እየሰጠዉ በሚመስል አንደበት፡፡
“ልታከብሩኝ - ልታወድሱኝ - ልትቀድሱኝ - ልታነግሱኝ ነዉ የሚገባችሁ፡፡ ማንም የማይችለዉን እኮ ነዉ የቻልኩት፡፡ ፍጡርን አኑሬ ፈጣሪን እኮ ነዉ የገደልኩት - - በሶሰተኛዉ ቀን አይይለም ለዘላለም እንዳይነሳ አድርጌ ነዉ ፀጥ ያደረኩት … አክብሩኝ! ካቴናችሁን ከእጄ አዉልቁና ዉሰዱ፡፡”  
“ከዚህ በፊት ታዉቀዋለህ እንዴ!” አለዉ ሾጣጣዉ ለዱልዱሙ ፖሊስ፡፡ ለካንስ ሾጣጣዉ ለጣቢያዉ አዲስ ነበር፡፡  
“ታዉቀዋለህ … ? እናትና አባቱ ወለዱት እንጂ እኛ እኮ ነን እዚህ ፖሊስ ጣቢያ ያሳደግነዉ። ከአርባ ሁለት ዓመቱ ዉስጥ ሰማንያ አራት ዓመቱን በመታሰር እኮ ነዉ የጨረሰዉ። ተወለደ፡፡ ታሰረ፡፡ አደገ - ተማረ - ተመረቀ … ምናምን አይነት ታሪክ ለሱ አይሰራም፡፡ ይታሰራል - ይፈታል - - አፍታም ሳይቆይ ደግሞ ይታሰራል … ከዚህ ሌላ ሞያም የለዉ እኮ፡፡”
ወደ ፖሊስ ጣቢያዉ ራሱ ነዉ የመጣዉ። ያለማንም እርዳታ እርጋታዉን ተከናንቦ ነዉ የመጣዉ፡፡ ሁለቱም እጆቹ በደም ተነክረዉ - ተዘፍዝፈዉ - ተጨማልቀዉ፡፡ ጎራዴ ሊያክል - ሰንጢ ታክል እርዝመት የጎደለዉ - በደም የተነከረ ካራ ይዞ፡፡ ቀጥ ብሎ ገብቶ እጁን ሰጠ፡፡
“ምን አድርገህ መጣህ ደግሞ?” አሉት፡፡
“ገድየዉ!” አለ፡፡
“ማንን?” አሉት ለፈረደበት እያዘኑ፡፡
“እግዜርን!” አለ በሰዉ ልጅ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ቆራጥነት፡፡ ሁሉም እርስ በርስ ተያዩ፡፡ አንዳቸዉም ከአንዳቸዉም አኳኋን መልስ መስጠት መልስ ማግኘት ባይሆንላቸዉ ወደ ጉደኛዉ እሱ አንድነት ዞሩ፡፡ ግራ እንደተጋቡ፡፡        
 “ምንድን ነዉ እያወራህ ያለኸዉ?” አሉት በእኩል አንደበት፡፡   
“በሰዉ ልጅ ታሪክ ተፈፅሞ የማያዉቅ ወንጀል መፈፀም ፈለግሁ፡፡ እናም አሳካሁት፡፡”
እያዘኑ፤ “ምን አደረክ?”    
“ገደልኩት! እግዜርን ክልትዉ አደረኩት፡፡” (ዮሐንስ፣ 2009፡ ገጽ 182-183)     
በዚህ ትረካ ዮሐንስ የሰዉ ልጅ በሐሳቡ የፈጠረዉን ፍጡር መግደልም ማስነሳትም ይችላል ይለናል፡፡ እንደ ዮሐንስ እሳቤ፣ ሳይንስ የእግዜር ሔምሎክ ሲሆን እምነት ደግሞ ትንሳኤዉ ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፤ የፈጣሪ ህልዉናን የሚወስነዉ እምነት ነዉ፡፡ ፈጣሪ አለ ካልክ ፈጣሪ አለ፤ ህልዉናዉን ከካድክ ግን ፈጣሪ ሟች ነዉ፡፡ የእግዜር መንበር የሰዉ ልጅ ልቦና ነዉ፡፡      
፪. ፪. ዮሐንስ እና ነገረ ፆታ
ካፑችኖ በተሰኘዉ የአጫጭር ትረካዎች መድበል ዉስጥ የቀረቡት መንገደ ሰማይ፣ የመናፍስት ማኅሌት፣ ቁጥር እና ፊደል እና “ወንድ አፍራሽ” “ሴት ገንቢ” የሚል ይዘት ያለዉ የቀዉጢ ሰዓት ፍልስፍና የተሰኙት ሥራዎች ነገረ ፆታን የሚዳስሱ በመሆናቸዉ ከልብወለድ ሂስ አቀራረቦች (literary critical approaches) መካከል አንዱ በሆነዉ በነገረ ፆታ ሂስ (gender criticism) አንፃር የሚፈከሩ ሥራዎች ናቸዉ። ከነገረ ፆታ ሂሶች መካከል አንዱ እንስታዊነት ሂስ (feminist criticism) ነዉ፡፡ ነገረ ፆታ ሂስ በሁለት የተከፈለ ነዉ፡ ፌሚኒስት ሂስ እና ኪዉር ቲዮሪ (lesbian and gay criticism) ተብለዉ (ባርኔት፣ ቡርቶ፣ ኬን እና ስተብስ፣ 2003፡ ገጽ 590)፡፡ ዮሐንስ ሴት ከወንድ የሚልቁ ብዙ ተፈጥሯዊ ፀጋዎች አሏት ብሎ የሚሞግት ጸሐፊ ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ዮሐንስ ሴትን አሞጋሽ ወንድ መራሽ ኅብረተሰብን (patriarchal society) ነቃሽ ነዉ፡፡  ለዮሐንስ ሴት ዉበት ነች፣ ፍቅር ነች፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ለዮሐንስ ሴት ሰላም እና ፍቅርን ሰባኪ ስትሆን ወንድ ግን ጦረኛ፣ ደም አፍሳሽ እና ነዉጠኛ ነዉ (ዮሐንስ፣ 2009፡ ገጽ 284-286)፡፡ ለዮሐንስ ሴት ከወንድ በበለጠ ህልዉናን በጥልቀት ተረድታ የምትኖር ሊቅ (የዮሐንስ ሴት ገጸባሕሪያት እንደ ፈላስፋ የሚቃጣቸዉ ናቸዉ) ናት (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 140)፡፡ ዮሐንስ እንዲህ ጽፏል፡
“ሥራሽ ምንድን ነዉ?”   
“መፃፍ ነዉ፡፡”
“ደራሲ ነሻ … ”
ዝም አለች፡፡ ዝምታዋ - - ልሆንም እችላለሁ- ወይም አይደለሁም፡፡ አልያም - ፈጽሞ አልሆንም - ይመስላል፡፡
“የሴት ደራሲ ደስ ትለኛለች፡፡ በመፃፍ ሴት ልጅ - ከወንድ ትበልጣለች የሚል መምህር ነበረኝ - ልክ ይመስለኝም ነበር፡፡”
“ምን በመፃፍ ነዉ ሴት ከወንድ የምትበልጠዉ?”
“ድርሰት ነዋ!”
“ድርሰት በመፃፍ ማንም ከማንም አይበልጥም፡፡ ድርሰት አርቴፊሻል ነገር ነዉ፡፡ ማንም እንደፈለገ እያበጃጀ እያሽቀረቀረ ሊዋሽህ ይችላል፡፡”
“ምን እያልሽ ነዉ?”
“ለመጻፍ የተነሳ ሁሉ ድርሰት ይጽፋል - - - መመዘኛዉ የሃያሲያን የሰመረና ቀርነት ያለዉ - - የማለት ፍርድ አይደለም፡፡ ሕይወት ግን - - ማንም ተነስቶ እንደፈለገ ሊያቃናትና ሊያወነጋግራት አይችልም፡፡ እናም መምህርህ - - ሕይወትን በመፃፍ - - - ሴት ከወንድ ትበልጣለች ካለ ትክክል፡፡ ምክንያቱም - - ሕይወት ዉስጥ - - - መኖር ዉስጥ - - ሴት ልጅ እጅግ የበረከተ ድርሻ አላትና ነዉ፡፡” (መንገደ ሰማይ፣ 2009፡ ገጽ 139-140)  
ቀራጮች ለምን የሴትን ራቁት ብቻ አይቀርጹም - ሁሉም ያልተገለፀላቸዉ ደነዞች ናቸዉ፡፡ እንዴት በጡንቻ ያበጠ - ዥርግጉን ያንጠለጠለ - እንሰሳዊ ወንድ ቀርጸዉ በአደባባይ ያኖራሉ -? ዐይን ማረፊያዉን ሲያስስ - እፎይታን የሚለግሰዉ ዉበት ይፈልጋል - - - ሴት ላይ ያረፈ ዐይን ሐሴት ተጠምቆ ይዉላል (የመናፍስት ማኅሌት፣ 2009፡ ገጽ 74)፡፡  
 ሶስና ዉበት ነች፡፡ ሦሥና ገነት ነች፡፡ ዉበት እያለቀሰች ነዉ፡፡ ዉበት እየተማፀነችዉ ነዉ። እሱም ይወድዳታል፡፡ እንዳልተረዳችዉ ቢያዉቅም ቅሉ - ይወድዳታል፡፡ ወንድ ነዉ - የሚፈተን ወንድነቱ ሲታይ ግን - ሦሥና በሦስተኛ ደረጃ የሚኖርላትና ኩራት የሚሆናት ሰብዕና ነች (ቁጥር እና ፊደል፣ 2009፡ ገጽ 91)፡፡  
በጦር ዉሎ መሐል - መኖር ብቻ አሳስቶ - የጣት ቀለበት ሳይቀር ሸክም ሆኖ በሚከብድበት ሰዓት - የሬሳ ክምር ተንተርሶ ሥጋዉን ሊጠግብ - ከበላዩ የሚያንዣብብን አሞራ - ሽቅብ ስጋት ባንሳፈፈዉ ዓይኑ እያማተረ - እንዲህ የሚል ነገር ይጽፍላት ጀመር - - -
ወንድ በብዛት ይዘምታል፡፡ ‘ከወንድ እኩል ነን’ ብለዉ የሚያስቡ ወይም ጥቂት ወንዳወንድ ሴቶች ይዘምታሉ፡፡ ሴትነት የሞላባት - እናት የምትሆን ሴት ግን አትዘምትም፡፡ ለምን? ደም ምን ማለት እንደሆነ ታዉቃለች፡፡ ለደም ቅዠት ሳይሆን - ለደም ንግር በየጦርነቱ ሳይሆን በየወሩ ቅርብ ነች፡፡ የምተኩሰዉ ጥይት ከሀገሬ መሬት አይወጣም፡፡ ተኩሼ የማሞተዉ ጠላት ሳየዉ ቁርጥ እኔኑ ነዉ [ሟች የገዳይ ወንድም የሆነዉ አምሳለ ሰዉ በመሆኑ ነዉ (አፅንኦቱ የእኔ ነዉ)] - - - ድሮም በሄደበት መዉለድ የወታደር አባት መታወቂያም አይደል - - -
እኔ ደሜን ለማፍሰስ እርምጃ ስወስድ - የሌላዉን ደም - እኔ ደመ ከልብ አደርጋለሁ፡፡ ሴት ልጅ ግን ደሟ እንዳይፈስስ ስትወስን በሆዷ ዉስጥ ሕይወትን መገንባት ትጀምራለች፡፡
አርግዘሽልኛል፡፡
ፍቅር ብቻ ለምን ይሰማኛል? እንዲህ በመላከ -ሞት መዳፍ መሀል ላይ ተቀምጬ - እንዲህ ከበላዬ የሚያንዣብብ አሞራ ሲሳዩን እስክወድቅለት እየጠበቀ ባለበት - በዚህ ቅፅበት - ምስኪንሽ አጠገብሽ መሆንን ተመኘሁ፡፡ አንቺ አጠገብ እኮ ሞት የለም፡፡ በየቅፅበቱ ትንሣኤ ብቻ- በየሽርፍራፊዉ ሰከንድ ሐሴት ብቻ- - -
እያለ ሲጽፍ - - - አንድ ሕይወት ነበረ እንዲህ ያከተመ - - -
እርግዝናሽ ሴት ሰዉ ያብቅል፡፡ በፈጠረሽ!
ወንድ ቢሆን እንኳን የሴት ልብ ይኑረዉ፡፡
አልያም ሴታ ሴት አድርገሽ አሳድጊዉ፡፡
የሴት ልጅ ተብሎ ማደጉ ላይቀር -- ሴታ ሴት ቢሆን ምኑ ላይ ነዉ ጭንቁ፡፡
ይኼም መጫት እንዳይመስልሽ፡፡
የዓለም ወንዶች ሁላ - እባካችሁን አጥንታችሁን ብቻ ሳይሆን - ደማችሁንም ለዓለም ሴቶች ገብሩ፡፡
ምክንያቱም …
እያለ ሊቀጥል ሲል…
ለምክንያት ባዕድ የሆነች ሕይወት ቁጭቷ ተፈታ፡፡ ዉሏ ላላ፡፡ መጻፊያ ብዕሩም - ወረቀቱም ከእጁ አመለጡ (“ወንድ አፍራሽ” “ሴት ገንቢ” የሚል ይዘት ያለዉ የቀዉጢ ሰዓት ፍልስፍና ፣ 2009፡ ገጽ 284-286)፡፡     
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዉን በቴሌግራም አድራሻው፡- @ MekonnenDefro77 ማግኘት ይቻላል፡፡Read 1124 times Last modified on Friday, 14 October 2022 06:48