Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 20 October 2012 11:06

ሐሳብን የሚፈራ ጠቢብ…

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በሀገራችን ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ስለ ሐሳብ አዲስነት፣ ስለሞጋችነት፣ ስለአፈንጋጭነት፣ እያነሣን ብንወያይ አብዝተን የምንጠቅሳቸው በመንፈሳዊ ትምህርት አልፈው ጻድቅነታቸው ስለሚነገርላቸው ጸሐፍት ይሆናል፡፡ ከዘመነ ጽድቅ ተሸቀንጥረን አሁን ወደ ተነከርንበት ዘመነ ሉላዊነት መጥተን ብንጠይቅስ? ጉንጭ ከሚያለፋና ነጭ ላብን ከሚያመነጭ ሙግት ጋር ከጣቶቻችን ቁጥር ያልዘለሉ ፈጠራዎችን እንጠራ ይሆናል፡፡
እንደመስከንተሪያ
ብዙው ደረቁን ጠጅ ግፎ እየሰከረ
የሰማይ የምድሩን እየቀባጠረ
የሆነ ያልሆነ ነገር ተናገረ
ከበደ ሚካኤል
በኪነ ጥበብ ዘርፍ አለን የምንል ብዙዎቻችን የመብት ጥያቄ ስንሰነዝር ኪነ ጥበባችን ለዚች ሀገር የደም ሥር መሆኗን ለማሳመን አወቃቀሩ የሰመረ ንግግር እንተረትራለን፡፡ የትኛዋ ኪነ ጥበብ ለሀገር ደም ሥር እንደሆነች ብንጠየቅ ለመመለስ ዐይናችን የሚፈጥ ጥቂቶች እንዳይደለን ሳንዘነጋ!

ብዙዎቻን ኪነ ጥበብን ውስጧ ገብተን እየዋኘን እያቦካናት እንድንጠቀምባት፣ ከዚህ ሲዘል ኪነ ጥበብ ስለሚኖራት ውለታ እየቀበጣጠርን የምንፈልገው ይፈጸምልን ዘንድ እንማልላለን፡፡ ይህ ታዲያ በጎ ነው ጎበዝ?
በእርግጥ ኪነ ጥበብ ሐሳብን ማራመጃ ስትሆን የሀገር ደም ሥር ትሆናለች፡፡ ሐሳብም ሲባል አዲስ ዕይታ አዲስ መንገድ አዲስ ሕይወት ማለት ነው፡፡ በመሠረቱም ኪነ ጥበብ የሰዎች ክህሎት አናት፣ የሰዎች ስሜት የደም ጠብታ፣ የሰዎች እርካታ ቁንጮ፣ የሰዎች አንድነት መተሳሰሪያ ገመድ ናትና የሀገር የደም ሥር ናት ቢሏት ቢያንሳት ነው፡፡
በደም ሥራችን የሚሯሯጠው አዲስ ደም (በኦክስጅን የበለጸገ ) ሲሆን እንጅ ያደፈ (በካርቦን ዳይ ኦክሳይድ የተበከለ ) ደም ቢሆን ጤና ሊሆን እንደማይችል ልባችን ይነግረናል፡፡ ለዚህም ነው ከፍ ብዬ ኪነ ጥበብ በአዲስ ሐሳብ ካልታጀለች በስተቀር አጉል ነው ያልኩት፡፡
ተስከንትረን እዚህ ከደረስን ወደዋናኛ ነጥባችን እንመለስ፡፡ ሐሳብን የሚፈራ (የማይፈጥር) ደራሲ ማንን ይመራል? ሐሳብን የማይፈልግ ማኅበረሰብስ የት ይደርሳል?
ስለ ምዕራባዊያን ስልጣኔ ሲወራ ቀድሞ የሚመጣልን አንባቢነታቸው እንደመሆኑ፣ የሚያነቡት ምንነትም አብሮ ሳይታሰብ አይቀርም፡፡ ዘመናዊ ጽሕፈትን እና የኅትመት ጥበብን ስንወርስ የሐሳብ ፈጠራን እና ምጥቀትን እንደዘነጋነው መገመት እንችላለን፡፡
‹‹የፈረንጅ ቋንቋ የተማረ ሰው ለሥራ ሲፈለግ እና ሲከበር ስለታየ የቋንቋ ትምህርት በዚያ ዘመን ተፈላጊ ሆነ፡፡
(1913)›› እንዲሉ መርስኤ ኀዘን ወ/ ቂርቆስ፣ አወሳሰዳችን የገረፍታ አይነት በጨረፍታ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎቻችን ውስጥ ካርቶኑን እየተቀበልን ብስኩቱን የምናሽቀነጥረው፡፡
ፊደሎች….
የኢትዮጵያ ፊደሎች ይህም ሲባል ነባሩ ግእዝ እና ተተኪው አማርኛ የሚጠቀምበት ፊደል ከ1750 ዘመናት በላይ ያስቆጠሩ ስለመሆናቸው ማንበቤን አልዘነጋም፡፡
በዚህ ጽሑፍ ስለፊደል አመጣጥና አፈጣጠር የማንሳት ዓላማ የለኝም፡፡ በእነዚህ ፊደሎች ምን ሠራን የሚለውን እንድናነሣ ብቻ ነው ፍላጎቴ፡፡
የክርስቶስን ልደት ተከትሎ ምናልባም ከዘመንና ዕለተ ጥምቀቱ አስቀድሞ ፊደል የተቀረጸባት ሀገር በፊደሎቿ ስለተደረሱ ድርሰቶች ሊወራ ቢቻልላት እንኳ፣ ስለ ድርሰቶቹ ሐሳብ ምጥቀት እያወጋን ሁለት ምእራፍ የሚሆን አንጓዝም፡፡
በሀገራችን ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ስለ ሐሳብ አዲስነት፣ ስለሞጋችነት፣ ስለአፈንጋጭነት፣ እያነሣን ብንወያይ አብዝተን የምንጠቅሳቸው በመንፈሳዊ ትምህርት አልፈው ጻድቅነታቸው ስለሚነገርላቸው ጸሐፍት ይሆናል፡፡ ከዘመነ ጽድቅ ተሸቀንጥረን አሁን ወደ ተነከርንበት ዘመነ ሉላዊነት መጥተን ብንጠይቅስ? ጉንጭ ከሚያለፋና ነጭ ላብን ከሚያመነጭ ሙግት ጋር ከጣቶቻችን ቁጥር ያልዘለሉ ፈጠራዎችን እንጠራ ይሆናል፡፡
የሆነው ሆኖ በርካታ መጻሕፍት በአንድ ሣምንት ውስጥ እየታተሙ ባሉባት ሀገር ሀሳብ ምን ቦታ እየተሠጠው ነው? ለመሆኑስ ሐሳብ ሐሳብ የምለው ምን ስለሆነ ነው?
የጥበብ ሁሉ የጥበብነት መገለጫ አዲስ ዕይታን፣ አዲስ ሐሳብን፣ አዲስ አቅጣጫን ማመላከት መቻል ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ‹ፈጠርኩ የፈጠርኩትንም በጽሑፍ አቀረብኩላችሁ› የሚል ደራሲ ነኝ ባይ የፈጠረውን ነገር አዲስነት ሊገልጥልን ይገባል የሚል ብርቱ አቋም ስላለኝ ነው፡፡ ያለዚያ ከ ‹‹ፈጠርኩ›› በፊት ‹‹ዘገብኩ›› ን ሊነግረን ይገባል የምትል ግብረገባዊነትን ለማስታወስ ነው፡፡
ልብወለዶች በፈጠራ ሥራዎች ሥር ናቸው፡፡ አዲስ ዕይታን አዲስ ሐሳብን ሊያመጡ ይገባቸዋል እንጅ ከነበርንበት ማኅበራዊ ትንከክ ስንዝር ካላንቀሳቀሱን ስለምን ተደጉሰው ይቀርቡልናል? በግሌ ደራሲው ስለፈጠራቸው ገጸባህርያት የእለት ከዕለት ኑሮ የማወቅና የመስማት ጉጉት የለኝም፡፡ ደራሲው ፈጠርኩት ያለውን ሐሳብ የማወቅ እንጅ የእርሱ ገጸባሕርያት የሚያደርጉትን እሰጥ አገባ፣ የውርስ ፉክክር፣ የመጠፋፈት አለዚያም የመለማማት ጉጉት እያነበብኩ ጊዜና ገንዘብ እንዳባክን የሚያውጅ የጥበብ ሕግ ያለ ስላልመሰለኝ መቀናጣት አይሆንብኝም፡፡
በሀገራችን ስለስነጽሁፍ ሲወራ እንደብርቅ የሚወራ የስነጽሑፍ ውለታ ግብረገባዊነትን መስበክ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ወጣ ያለ ሐሳብ ያላቸው የውጭ መጻሕፍት እንደ እርኩስ መንፈስ መድረክ የሚቆጠሩት፡፡ የእገሌን መጽሐፍ ያነበባችሁ ጸበል ተጠመቁ እስከመባል የተደረሰው ለአዲስ ሐሳብ ካለን ግድ የለሽት ይመስላል፡፡
ይህ ሲባል አዳዲስ የጋጠወጥነት መርሆዎች እየወጡ በሥነ ጽሑፍ ይሰነዱ ማለት አይደለም፡፡ ጥሩ ስነጽሑፍ የግብረገብ መማርያ ብቻ የሆነለት ማኅበረሰብ መጥፎ ስነ ጽሑፍ ጋጠወጥነትን የሚሰብክ መሆኑን በማመን ነው፡፡
የዚህ ፀሐፊ መሟገቻ ግን ስነ ጽሑፍ የአዲስ ሐሳብ መድረክ እንጅ የምክር እና የተግሳጽ ብቻ አይደለም የሚል ነው፡፡ ሰዎችን መለወጥ፣ ዓለምን ማሰናዳት፣ ሁነትን መፍጠር የሚቻለው አዳዲስ ሐሳብን በማመንጨት እና ዕይታን በማመላከት እንጅ በምክር እና በተግሳጽ ብቻ አይደለም ፡፡ ተግሳጽና ምክር ብቻ የሰውን ሕይወት የሚቀይር ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉም ምሉዕ አልነበረምን? Nooman የተባሉ ጸሐፊ ያሉትን እዚህ ላይ እንደምሳሌ መጥቀስ ሳይበጅ አይቀርም ፡፡
,,the bible helped to form opinion against usury, but its influence was not predominant..,, ‹‹ መጽሐፍ ቅዱስ አራጣን የሚያጣጥል አስተምህሮ ይኑረው እንጅ ለአቅመ ቅድመ ቁጥጥር የሚበቃ ተጽእኖ ግን አልፈጠረም፡፡›› ስለዚህ ነው አዳዲስ ሐሳብን በሥነ-ጽሑፋችን ውስጥ የምንፈልገው፡፡ ፊደሎች ተፈጠሩ የተባሉበትን ረዥም ዘመን አቆይተን፣ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ተጀመረ የተባለበትን ያለፈውን አንድ መቶ ዓመት እየመላለስን ብንመለከት አዲስ ሐሳብ በመፍጠር ላይ የተጉ ደራስያን እና ድርሰቶቻቸውን ማግኘት ይጨንቀናል፡፡
ሐሳብን የማይፈጥር ደራሲ ደግሞ ጠቢብ ነኝ ብሎ ሊናገር ይከብደው ሐሳብን የማይፈልግ አንባቢም አንባቢ ነኝ ሊል ይከብደው ይገባ ይመስለኛል፡፡
መነሻዬ ኪነጠቢብ ነኝ የሚሉትን መውቀስ መሆኑ ከዚህ ከፍ ብሎ የሚታይ ሐቅ ነው፡፡ በኪነ ጥበቡ ምን አገለገልኩበት ብሎ መጠየቅ ግብረገባዊነት ነውና!
ያሬዳዊነት..
ኢትዮጵያ የራሷ የሆነውን ቅኝት የፈጠረችው ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት መሆኑን ሳንከራከር እንስማማለን፡፡ መቼም በስማ በለውም ቢሆን ስለቅዱስ ያሬድ ያልሰማ አይኖርምና፡፡ ይህኛው የኪነጥበብ ዘርፍም እንደፊደሎች ምን ተሠራበት የሚል ጥያቄን እናነሳበት ይመስለኛል፡፡
የዘመናዊ ሙዚቃን እሳቤ ከተቀበልንበት ጊዜ ጀምሮ (የሙዚቃ ዕውቀቴ አጀማመሩን እንኳ ለማወቅ የሚያበቃ ባለመሆኑ ይቅር በሉኝ) ዘመናዊ ባልነው ሙዚቃችን ምን ሠራን?
ከፍ ዝቅ በሚለው ሙዚቃ መድረካችን (ኢንዱስትሪ?) አወዛጋቢ ታሪኮችን እና እውነታዎችን እናገኛለን፡፡ አደገ አላደገም የሚለውን ሙያዊ ሙግት ለቀደሙት እና አሁን ለመጡት የሙያው ሰዎች ትተን ይህኛው የኪነጥበብ ዘርፍስ ምን ተሠራበት ብለን እንጠይቅ፡፡
ለምለሚቱ አገሬ ብሎ መዝፈን ለአንድ ዜጋ ልብን ደስ የሚያሰኝ መሆኑ የማያጠያይቅ ቢሆንም እተራቆተች እና በድህነት ውስጥ እየዳከረች ላለች ሀገር ለምለሚቱ አገሬ ብሎ መዝፈኑ ምን ይፈይዳል? የሚለውም ሙግት ለባለሙያዎቹ ሊተው ቢችልም በዚህኛው ሙግት ውስጥ ግን የእኔን ሐሳብ የሚደግፍ ነቀፌታ አይጠፋውምና እንመንዝረው፡፡ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ግብረገባዊነት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ሁሉ ሙዚቃ ውስጥም ስለሀገር መዝፈኑ ወላዊ የሆነ ቅቡልነት ያለው ይመስላል፡፡ ከመዝፈኑ ላይ ጥያቄ ማንሳት ቢቸግርም አዘፋፈኑ ላይ መጠየቅ ግን ይቻላል፡፡
አዎ! ስለሀገር መዘፈኑ ሳይሆን ስለሀገር ምን ተዘፈነ የሚለው ያነጋግራል፡፡ ደግሞስ ስለሀገር የትኛው ተዘፈነና? ስለጎንደር ቢዘፈን ከቴዎድሮስ ውጭ ሌላኛውን የጎንደር ገጽታ የሚያሳይ አይደለም፡፡
ስለጎጃም ቢዘፈን ከበላይ ውጭ ሌላኛውን ገጽታ የሚያሳይ አይደለም፡፡ ስለጉራጌ ቢዘፈን ከክትፎ ውጭ ሌላኛውን ገጽታ የሚያሣይ አይደለም ወዘተ. አዲስ ሐሳብን ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ይመስለል፡፡
ተሠርተው ካደመጥናቸው ሙዚቃዎች ወይም አሁን እየተሠሩ ያሉ ሙዚቃዎችን ስናዳምጥ ተደጋጋሚ ነገሮችን እንሰማለን፡፡ አዲስ ሐሳብ ግን ለምን አጠረን?
ሙዚቃዎቻችን ውስጥ አዳዲስ ዕይታ እያየንባቸው ነው ወይ? ለዚህ አዎንታዊ መልስ ለመስጠት የሚደፍር ያለ አይመስለኝም፡፡ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያሥደፍር ደረጃ በተለይ ዘመናዊ ሙዚቃችን ባህር ተሻግሮ የሄደ ይመስላል፡፡ ይህ ክፋት አይደለም እንኳ ቢባል ባህር ተሻግሮ ምን አመጣ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ካርቶኑን ተሸክሞ ብስኩቱን አሽቀንጥሮ ዐይነት ነው፡፡ ከከበርቻቻው እና ዳሌን ከማንቀጥቀጡ ባለፈ ከሙዚቃ ኢንዱስትሪው የተገኘው አዲስ ነገር ምንድን ነው? የገበየነው አዲስ እውቀት ምንድን ነው? ባለሙያ መልስ ይስጥበት፡፡
በጠቅላላው በኪነ ጥበባችን ውስጥ አዲስ ሐሳብ ማግኘት ያዳግታል፡፡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በኪነጥበብ ምን ሠራን ብሎ ለመጠየቅ ድፍረት ያላቸው አይመስሉም፡፡
ኪነጥበብ ያላትን ጥቅም ማብራራት ብቻውን የኪነጥበብ ባለሙያ የሚያሰኝ አይመስለኝም፡፡ ግን ኪነጥበብ ያላትን ሚና ማብራራት የመምህራን ተግባር፤ ኪነጥበብን ከፍተኛ ሚናና ፋይዳ ያላት ማድረግ ደግሞ የኪነ ጥበቡ ኃላፊነት ነው፡፡ መስከንተሪያ ያደረግሁት የከበደ ሚካኤል ግጥም ያለንበትን ዘመን እና ኪነ ጠቢብ ነኝ የሚለውን ይገልጥ ይመስለኛል፡፡

 

Read 3496 times Last modified on Saturday, 20 October 2012 11:20