Saturday, 15 October 2022 11:10

ካፑችኖ፣ የዮሐንስ ሐሳቦች

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(0 votes)

  “ወንድ ትወድዳለች፡፡ የመዉደዷን ያህል ግን የተሳካለት የሚባል የፍቅር አጋጣሚ የላትም፡፡ የቀረቧት ወንዶች ሁሉ ባለአሮጊት እናቶች -
አፍቃሪነት ሳይሆን የዘር ግንድ የማወፈር ተስፋ የተጣለባቸዉ፡፡ ያለሳቅ - ያለዕንባ - ያለፍቅር ልጅ የመፈልፈል ሕልም የሰነቁ፡፡--”
       
      ክፍል ሦስት
የእንስታዊነት ሂስ አንድ ማኅበረሰብ እንስታዊነትን (feminine) እና ተባዕታዊነትን (masculine) አስመልክቶ የገነባዉን የተዛባ አተያይና ትርክት (prejudice) የሚፈትሽ ሂስ ነዉ፡፡ በነገራችን ላይ፣ የእንስታዊነት ንቅናቄ (feminism) ዋናዉ መነሻ የዣን- ፖል ሳርተር ኤግዚስቴንሻሊዝም መሆኑን የሚያዉቁት ጥቂት ምሁራን ብቻ ናቸዉ፡፡ የታዋቂዋ እንስታዊነት ንቅናቄ መስራች ፈረንሳዊቷ ደራሲና ፈላስፋ (እስከ ሞት ያልተለየችዉ የሳርተር ፍቅረኛ) ሲሞን ደ ቡቯር ፍልስፍና መነሻ የሳርተር ፌኖሜኖሎጂካል ኦንቶሎጂ (የሳርተርን ልጨኛ የፍልስፍና ሥራ ቢንግ ኤንድ ነቲንግነስን ተመልከት) ነዉ፡፡ እንደ እንስታዊነት ሃያሲያን እሳቤ፣ ማኅበረሰባችን የሚመራበትን የሴትነት እና የወንድነት መገለጫ ባሕርይ የደነገገዉ ወንድ መራሽ ኅብረተሰብ ነዉ፡፡ በመሆኑም፣ ሴትነት እና ወንድነት የምንለዉ ፆታዊ ሚና (masculine and feminine behavior) ተፈጥሯዊ ሳይሆን ወንድ መራሽ ኅብረተሰብ ያበጀዉ ነዉ፡፡ ተፈጥሯዊዉ የሆነዉ ነገር ፆታ (sex) ነዉ (ሜየር፣ 2005፡ ገጽ 2044)፡፡ እኛ ሐበሾችም እምነታችን በአብዛኛዉ የነጮች ዉርስ (አይሁዶችን እና አረቦችን ከማምለክና በጭፍን ከመዉደድ የተነሳ የተቀዳ) በመሆኑ ሴትን አንኳሳሽ ወንድን አሞጋሽ ነን፡፡ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች አስተምህሮ፣ የሴቶች ጭቆና እና ቀንበር ዋና ምንጮች ናቸዉ። የእኛ ማኅበረሰብ ሴትን አንኳሳሽነት በዋናነት ከሚያንፀባርቁት አሉታዊ እሳቤዎች ዋነኞቹ ምሳሌአዊ አነጋገሮች ናቸዉ፡፡ “ሴትን ያመነ ጉም የዘገነ”፣ “ሴት በዛ ጎመን ጠነዛ”፣ “በሴት ይጀመር በወንድ ያልቅ” … ወዘተ ሴትን የሚያንኳስሱ አሉታዊ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ናቸዉ፡፡ ዮሐንስ የሳላቸዉ ገጸባሕሪያት እንደ ሌሎቹ ደራሲያን ሴት ገጸባሕርያት መደዴዎች (ርጥብ ምኞትን እና የመናፍስት ማኅሌትን ተመልከት) አይደሉም፡፡
፪. ፫. ኀልዮ (existence)
ለዮሐንስ ሕይወት የፀናችዉ በሁለት ተቃራኒ ፅንፎች ነዉ፡፡ ዉልደት እና ሞት፣ ሐዘንና ደስታ፣ ፍቅር እና ወረት፣ ሲሳይ እና እጦት፣ ቸርነት እና ስስት ..ወዘተ ተቃራኒ የሕይወት መልኮች ናቸዉ (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 179)፡፡ ዮሐንስ ሰዉ ደስታን የሚሸምተዉ እነዚህን ተቃራኒ መልኮች ሳያጉረመርምና ሳይመረር በይሁንታ ሲኖር ነዉ ይለናል (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 3)፡፡
፫. የዮሐንስ የአጻጻፍ ይትባህሎች
፫. ፩. ድንክ ትረካ (sketch story)
የዮሐንስ ካፑችኖ በዛ ያሉ ድንክ ትረካዎች (sketch stories) የቀረቡበት መድበል ነዉ። ድንክ ልብወለድ (ስያሜዉ የግሌ ነዉ) በጥቂት ቃላት የተጻፈ ነገር ግን ምልዓት ያለዉ ትረካ ነዉ። ሦስት ሰዉ (ግለኝነት (egoism) እና ክብካቤ (caring) የተሰኙትን የግብረገብ ፍልስፍናዎች የዳሰሰ መቸት (seting) አልባ ታሪክ ነዉ)፡፡ በዚህ ሥራ ዮሐንስ፤ ሰዉ ግለ አምልኮዉን ማሸነፍ አለበት ይለናል፡፡ እንዲህም ጽፏል፡
ሦስት ነን፡፡
ሦስት አካል፡፡ ሦስት አምሳል፡፡
እኔ ‘ነጭ’ ስል … እሱ ‘ጥቁር’ ይላል … እሷ ደግሞ ‘ቀለም ምን ያደርጋል?’ ትላለች፡፡ ወደድኳት፡፡ መዉደዴንም ነገርኳት፡፡ ሳትከፋም ሳትደሰትም አብራኝ ሆነች፡፡ አብረን መሆናችንን ነገርነዉ፡፡ ሰምቶን ሲያበቃ የፌዝም ይሁን የቁም ነገር ሐሳቡን ነፈገን፡፡
ዕልህ አለበት …
ወደዳት፡፡ መዉደዱንም ነገራት፡፡ አብራዉ ሆነች፡፡ አብረዉ እንደሆኑ ነገረችኝ፡፡ ሰምቼ ሳበቃ አብሮኝ ቀንድ ያወጣዉን ዳተኝነቴን እየታቀፍኩ ክፉም ደግም ሳይወጣኝ ቀረ፡፡
ሦስት ነበርን፡፡
ሦሰት አካል፡፡ ሦስት አምሳል፡፡
‘ሰዉ መሆን ማለት የራስን መስቀል በራስ መሸከም ነዉ፡፡’ እኔ ስል  
‘ሰዉ መሆን ማለት የመጣን ሁሉ ልሂድ ሲል በሙሉ ልብ መልቀቅ ነዉ’ … ባይ እሱ ነዉ፡፡
እሷ ደግሞ
‘በአንድ ነን ባይነት ዉስጥ ከሚመጣ ቅናት ማምለጥ ነዉ፡፡’ ትላለች (ዮሐንስ፣ 2009፡ ገጽ 63-64)፡፡
የዮሐንስ ሦስት ሰዉ ሌላዉ ስዉር ጭብጥ አንፃራዊነት ነዉ (relativism) ነዉ፡፡ ለዮሐንስ እዉነት (truth)፣ እሴት (moral and aesthetic value) እና የሕይወት ትርጉም (meaning) ከግለሰብ ግለሰብ የተለያየ ነዉ፡፡ ቀለማቱ ተምሳሌትነታቸዉ (symbolism) የእያንዳንዱ ግለሰብ ግላዊ የሕይወት ፍልስፍና ወይም ንፅረተ ዓለም ነዉ፡፡    
ካፑችኖ፣ ዘቢብ እና “ወንድ አፍራሽ” “ሴት ገንቢ” የሚል ይዘት ያለዉ የቀዉጢ ሰዓት ፍልስፍና ሌላኛዎቹ የዮሐንስ ግሩም ድንክ ትረካዎች ናቸዉ፡፡
፬. ድህረ ዘመናዊ ጸሐፊዉ ዮሐንስ
በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ዮሐንስ ከጊዜያችን ድህረ ዘመናዊ ልብወለድ ጸሐፍት አንዱ ነዉ፡፡ ብዙዎቹ ሥራዎቹም ይኸን የቅርብ ዘመን የአጻጻፍ ይትበሀል የተከተሉ ናቸዉ፡፡ ዮሐንስ በሥራዎቹ ዉስጥ የተገበራቸዉ አራት ድህረ ዘመናዊ የአጻጻፍ ይትበሀሎች ከዚህ በታች የዘረዘርኳቸዉ ናቸዉ፡፡
፬. ፩. ድቅል ታሪክ (a story within a story)
ድቅል ታሪክ ከድህረ ዘመናዊ ልብወለድ አጻጻፍ ቴክኒኮች መካከል አንዱ ነዉ፡፡ ድቅል ታሪክ በዋናዉ ትረካ ዉስጥ ተሰፍቶ የሚቀርብ ትረካ ነዉ፡፡ መንገድ ሰማይ እና እኔ እና የጓደኛዬ ትዕንግርት እና የመናፍስት ማኅሌት ዮሐንስ፤ ድቅል ታሪክን ያቀረበባቸዉ ሥራዎቹ ናቸዉ፡፡ ዮሐንስ እንዲህ ጽፏል፡
“ተረት አዉራልኝ?” አለች፤ ድንገት በወሬዬ መሐል ገብታ፡፡
“ተረት ተረት?”
“ቀጥል …”
“በሥነ ተረቱ አካሄድ መልሽልኝ፡፡”
“የላም በረት - - ወይም - - የመሠረት - - -”
“ሆድሽ ይተርተር በጋለ ብረት - - የፈላ ዉሃ ይጨመርበት - - አርባ ጋንኤል ይታሰርበት - - - ቀን ቀን ቃልቻ - - ማታ ባለዛር ይጨፍርበት - - እናልሽ - - - በጥንት ዘመን አለቃ ገብረሀና የሚባሉ የኔ የዘር ግንድ የነበራቸዉ ቀልደኛ - - - ቁምነገረኛ ባለቅኔ በቃ ምን አለፋሽ አንድ የሆነ ህዝብ የሆኑ ሰዉዬ ነበሩ - - -
“ከዛማ - - -  ሲኖሩ - - - ሲኖሩ - - - ሲኖሩ - - - ሲኖሩ - - - ሲኖሩ - - - ሲኖሩ - - - ሲኖሩ - - - ሲኖሩ - - - ሲኖሩ - - -”
“ከሲኖሩ ቀጥሎ ምን?” ይህቺ ሴት በሽቃለች። ተጋባዥነቷን ሁሉ ረስታ ደንበኛ ጋባዥ መሰለች፡፡
“መጀመሪያ መኖራቸዉን አጥርተሽ እወቂ። የት ለመድረስ ነዉ እንዲህ መጣደፍ፡፡ እናልሽ ሲኖሩ - - ሲኖሩ - - ሲኖሩ - - ሲኖሩ - - ሲኖሩ - -”
“መኖራቸዉን አዉቄያለሁ -ከዛስ?” ልጅቱ ከነብሽቀቷ ሰፊ ጨዋታ ፈልጋለች፡፡
“ከዛማ ኖረዉ ሲያበቁ ሞቱ፡፡ ሞተዉ ሲሰነብቱ ታሪካቸዉ ለተረትነት ቦታዉን ለቀቀ - - - ለነገ ተተራች ለዛሬ ተረት ነጋሪ አፋም - - - በወሬ ቀላጭ ቅቤ ሆነዉ አረፉት - - - ተረቴን መልሺ አፌን ባአፍሽ አብሺ - - - ከንፈሬን በከንፈርሽ አስሺ - - ምላሴን በምላስሽ አራርሺ - - - ጥርሴን በጥርስሽ ንከሺ - - -”
“አንተ ሰዉ ግን ማን ነህ?”
“ያለቃ ገብረሀና - - - የዘር ግንድ ያለኝ ከዛገዉ - - - ይቅርታ ከዛጉኤ ማለቴ ነዉ - - -”
“እሱን አዉቄያለሁ - - - የማላዉቀዉን አንተን ንገረኝ?” (መንገደ ሰማይ፣ 2009፡ ገጽ 142-143)፡፡
“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች . . .” ከብሉይ እስከ ዛሬዋ ሐዲስ ኪዳናዊ እለት ድረስ የተዘረጋ እጅ!
እና ፈጣሪ እጇ ላይ ምን አስቀመጠ?
ፀጋዉስ?
በረከቱስ?
ደገኛ ቀኑስ?
መቼ ነዉ ከነአኗ በእጇ የሚገባዉ? መቼስ ነዉ ኢያሪኮዋ በጭብጨባዋ ድምቀት አመድ የሚሆነዉ? ኧረረረረረ መቼስ ነዉ አስጨናቂ ጎልያዷ በዳዊታዊ ወንጭፏ ቅንድቡን ተብሎ መሐል መዳፏ ላይ የሚዘረገፈዉ …
እንዲህና እንዲያ ያሉ ታሪኮችን ከእስራኤል ምድር ወርሼ ለኢትዮጵያ ኩነት ማሳያ ሳደርግ ጓደኛዬ እርር እያለ እንዲህ ይለኛል፡፡
“… እኔ እኮ ግርም የሚለኝ - - ሲያንስ የሦስት ሺህ ዓመት - - ከተፈለገም ከኖህ እስከ ኢህአዴግ - - ኧረረረረ ወላ የመጀመሪያዉ ሰዉ አዳም ኢትዮጵያ ነዉ … የሚል የታሪክ ድርሳን የምንመዝ ፉፈኛ ህዝቦች … ለዛሬ ኩነታችን ማሳያ የሚሆን የኛዉ ታሪካዊ ማነፃፀሪያ እንዴት እናጣለን? ከኛዉ አብራክ ተፈልቅቆ ለአረመኔነትም ሆነ ለቅድስና ማሳያ የሚሆን ሰዉ እንዴት አይኖረንም?  
“በአይሁድ ታሪክ መማለል ለችግራችን መፍትሄ አይሆንም፡፡ ሃይማኖት ሌላ ታሪክ ሌላ፡፡ የእስራኤል ታሪክ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ትረካ ከመሆን የዘለለ ሚና አይኖረዉም …
“ደርግ ቀይሽብሩን አፋፍሞ … ያለምንም ደም ትቅደም ያላትን ኢትዮጵያ በደም ማዕበል ሲያሰጥማት … ሄሮድስ የተባለ ‘ጋንግስተር’ እየሩሳሌምን በሁለት ሺህ ህፃናቶቿ ደም የዋጀበትን ታሪክ ማንፀሪያ ማድረግ ምን ርባና አለዉ?
“ወያኔ ከነአጋዚዋ ከአፍ እስከ ገደፏ ታጥቃ እየጠበጠበችን፣ መፅናኛ ምሳሌያችን ፈርኦን ከእነሰራዊቱና ባሪያ አይሁዳዉያን ለምን ይሆናሉ?”
“… አየህ - የሰዉ ልጅ ትልቁ ትምህርት ቤት በገዛ ራሱ የመዉደቅና የመነሳት ዕጣ ፈንታዉ ላይ የተገነባ ነዉ፡፡ የሕይወት ትልቁ ጥበብም የሻገተ ማንነትና አፍርሶ አዲስ ሰዉ መሆንን ለመገንባት ከገዛ ራስህ ትላንትና፣ ዛሬን ማስተካከል ማለትም ከታሪክ በማር ላይ የተገነባ ነዉ… የራሳችንን ታሪክ መርምረን እዉነቱን ካልተረዳን አንዳች ጠብ የሚልልን አዲስ ሕይወት የለም” … ይለኛል፡፡
በሀሳቡ ብስማማም - - የንግግሩ እዉነትነት ቢጎላብኝም ያዉ ያደገብኝ ነዉና - - ያዉ የዘሬ ያንዘረዝረኛልና የአይሁዳዉያንን ታሪክ መጥቀሴን አልተዉም፡፡
ስለ አይሁድ ሀገር መንደርና ሰፈር - - ተራራ - -ወላ ኮረብታ ሳይቀር ያለኝን እዉቀት አስቤ … ለገዛ ምድሬ ታሪክ ያለኝን ምህረት አልባ መሀይምነት መፋቅም አልችልምና ባልባሌ መዘንጋት ተጀቡኜ በለበጣ ድዴን እገሸልጣለሁ።
እንጂ… ሳኦል አልያም ናቡከደነፆር ከምንል አፄ ዮሐንስ ወይም አፄ ንብለ ድንግል ብንል … ቤተ ሳይዳ ወይም ሞርያም ከምንል ሰገሌ ወይም አድዋ ብንል … ኦርዮን ወይም ሶምሶን ከምንል አሉላ ወይም አብዲሳ አጋ ብንል የትኛዉ ነዉ ቅርባችን?  የትኛዉስ ነዉ የእኛ?
ንጉሱንና ቅዱሱን ዳዊት በንጉሳችንና በቅዱሳችን ላሊበላ … ጠቢቡ ሰሎሞንን በአባ መላ … የአብረሃምና የሳራን ጋብቻ በአለቃ ገብረሀናና በእመት ማዘንጊያ ትዳር ተክተን ብናየዉስ?
በየምኩራቡና በየስብከት አደባባዩ በክርስቶስ ዉድቀት ላይ ያሴሩ የነበሩትን ጸሐፍት ፈሪሳዉያን … በየቤተ ክርስትያኑ ተሰግስገዉ የቴዎድሮስ ራዕይ እዉን እንደዳይሆን ቀን ተሌት ይታትሩ፣ መርዛቸዉን ይረጩ በነበሩት ደብተራና ቀሳዉስት ተክተን ብናየዉ እዉነቱ ፍንትዉ ይልልን አልነበረም? ለመዉደቃችንም ለመነሳታችንም ሩቅ ሳንሄድ መፍትሄ አናገኝም ነበር?
ከራስ ሕፀፅ መማር ይከብዳል … ራስን መገሰፅና መዉቀስ ሸክም ነዉ … ቢሆንም አማናዊ እዉቀትና ግንዛቤ የሚገኘዉ ከራስ መማር ሲቻል ነዉ፡፡
(ኧኧኧኧረረረረረረ ኢትዮጵያና እጆቿስ …?)   
እና ፈጣሪ እጇ ላይ ምን አስቀመጠ?
የማይመጣ ግን ሲናፈቅ የሚኖር ነገ የሚባል ጉም ነዉ ያስቀመጠዉ? ወይስ በከባድ ጥድፈት ዛሬዉኑ የምንገዳደርበትና የምንዋደቅበት ጦር መሳሪያ ይሆን ያቀበላት?
ታዲያ መቼ እፎይ ብለን እናዉቃለን … ታዲያ ፋታ እንጂ መቼ እረፍት ወስደን እናዉቃለን … እኛ እኛኑ የጨረስነዉን ያህል እርስ በእርሱ የተጫረሰ ሌላ ሀገር በታሪክ ይገኝ ይሆን? እምነት እንዳንል እምነት አላነሰን፡፡ ታሪክ ላይ እንዳናላክክ ታሪክ አልኮሰሰብን፡፡ መዋለድስ ቢሆን ከኛ በላይ ላሳር፡፡ ታዲያ ከኛ በላይ ለኛዉ ጠላት ያጣንበት ምክንያቱ ምን ይሆን? (እኔ እና የጓደኛዬ ትዕንግርት፣ 2009፡ ገጽ 272-275)
“ዓለም ሸርሙጣ ብሎ አንቅሮ የተፋትን ሴት - በቀን ከአሥር በላይ ወንዶች እንደ ቁርበት እየለፋች - እንደ ጀንዲ እየቀዘቀዘች - ለስሜት ሳይሆን ለገንዘብ የምታስተናግድን ሴት ታዉቂያለሽ?”
“አላዉቃትም፡፡”
“የገዛ ራስሽን አለማወቅሽ ዉርደትሽ እንጂ ፀጋሽ አይሆንም፡፡”
ሳታዉቀዉ በፊት ስለእሱ ብዙ ሰምታለች፡፡ አብላጫ ስሚዎቿ የታላቅነቱ ዉዳሴዎች ናቸዉ፡፡ ጓደኛዋ ሰሎሜ - ስለታላቅነቱ የምትቦተልካቸዉ ገድላት አያልቁባትም - ከነገድላዊ ይዘታቸዉ፡፡
“ይህን ሰዉዬ ወደሽዋል ልበል?” - ጥርቅም ወሬዎቿ ሌላ ሲያሳስቧት፡፡
“ግጥም አድርጌ!”
“አስራትስ? ባልሽ እኮ ነዉ?”
“የማይረቡ አርቲ ቡርቲዎችን እየቀበጣጠርሽ ትኩስ የፍቅር ስሜቴ ላይ በረዶ መጋገር አይፈቀድልሽም፡፡”
የእስከዛሬዋ ባለጭንብል ሰሎሜ ወለቀች - ወይስ - ዝና ፈላጊዋ ጓደኛዬ - ወይስ - እርቃኗ እና ባለጭንብሏ ሰሎሜ ጠብ ገጠሙ - - - ግራ የገባዉ ነገር ሆነባት፡፡  
ዘላለም -
“የምር - ከነፍስ የሚመነጭ ሳቅ - - - ከአንጀት - ከስምጥ እየፈነቀለ የሚለቀስ ዕንባ - እነዚህ ሁለቱ ይመቹኛል” ትላለች፡፡ ስቆ ማልቀስ - አልቅሶ መሳቅ ከልብ ከሆኑ የኔ ናቸዉ ባይ ነች፡፡
ወንድ ትወድዳለች፡፡ የመዉደዷን ያህል ግን የተሳካለት የሚባል የፍቅር አጋጣሚ የላትም። የቀረቧት ወንዶች ሁሉ ባለአሮጊት እናቶች - አፍቃሪነት ሳይሆን የዘር ግንድ የማወፈር ተስፋ የተጣለባቸዉ፡፡ ያለሳቅ - ያለዕንባ - ያለፍቅር ልጅ የመፈልፈል ሕልም የሰነቁ፡፡ ጨቅላህን ታቅፌ - በሽንቱ - የቀዘቀዘ ጭኔ ሞቆ - በእፎይታ ወደተማሰልኝ ጉድጓድ ልግባ - ተባዮች - - - ፍቅር መፈለጓን ለማወቅ ጊዜ የላቸዉም - የልጅ መፈልፈያ ማሽን - ኢንኩቤተር አድርገዉ እንደሚቆጥሯት ስታስብ ትበግናለች (የመናፍስት ማኅሌት፣ 2009፡ ገጽ 67-68)፡፡
፬. ፪. ሕፅናዊነት (intertextuality)  
ዮሐንስ ሕፅናዊነትን (an allusion of another text) በብዛት የሚጠቀም ጸሐፊ (ሄራን፣ ገጽ 3፤ ሽንቁሬን በካንሰር ገጽ 10፣ 12፤ ርጥብ ምኞት ገጽ 25፣ 40፣ 41፤ ሦስት ሰዉ ገጽ 64፤ ከመስከረም ጷግሜ ገጽ 99፣ 104) ነዉ፡፡ እንደ ካርተር (2006) ኒኮል (2009) ገለፃ፣ ከድህረ-ዘመናዊ የአጻጻፍ ቴክኒኮች አንዱ ሕፅናዊነት ነዉ፡፡ ሕፅናዊነት አንዱን ሥራ ከሌላ ሥራ ጋር አዛምዶ ማቅረብ ቴክኒክ ነዉ። በሕፅናዊነት ቴክኒክ አንድ ደራሲ የራሱን ትረካዎች እርስ በእርስ አስተሳስሮ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ዮሐንስ ሄራን (ይህ አጭር ልብወለድ በአንደኛ መደብ የትረካ አንፃር (first-person point of view) የተተረከ ሥራ ነዉ) በተሰኘዉ አጭር ልብወለዱ ዉስጥ የተሳለችዉን ዋና ገጸባሕሪ ሄራን ካፑችኖ በተሰኘዉ ሌላኛዉ የልብወለድ ሥራዉ ዉስጥ ከስቶ፣ ሌላኛዉን የታሪኳን ምዕራፍ ያስነብበናል፡፡ እንደገናም ይቺዉ ገጸ ባሕሪ መንገድም ሕይወትም  በተሰኘዉ ትረካ ተስላ እናገኛታለን (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 1-8፤ 128-132፤ 287-296)፡፡       
ስምሽ ባሕሪሽ ነዉ፡፡ ስምሽ ሲጠራ ብርሃን ዓለምን ሊሞላ ይራወጣል፡፡ ሙሉ ብርሃን! በዓለም ላይ ሰፍኖ - ብጣቂ ጨለማ እንኳን ያልተወ ብርሃን፡፡ ስምሽ ዉስጥ ሰላም - ፍስሃ - ሐሴት ሞልተዉ ገንፍለዋል (ሄራን፣ 2009፡ ገጽ 1)፡፡
ሰዉ ጠልቼ ነበር፡፡ ራሴን ከግርግር አግልዬ - ብቻነቴን አግዝፌ - ለራሴ እያወራሁለትና በሚደልል ፈገግታ እያወፈርኩት ስኖር - - በሆነ ቀን እሷ ወደ ብቸኝነቴ ዉስጥ ለመግባት መጣች (ካፑችኖ፣ 2009፡ ገጽ 128)፡፡
ብቻየን ነኝ፡፡ ግን ትሞቀኛለች፡፡
በተደጋጋሚ በተገናኘንባቸዉ ጊዜያት - እሷ ሌላ ነገር ስታዝ እኔ ካፑችኖ እጠጣለሁ፡፡ ስጠጣ ትስቃለች፡፡ ስትስቅ ሳቄን ከተሸሸገበት ዋሻ ታወጣዋለች፡፡ የሷን ሳቅ ካላየሁ መሳቄ ተራ ማግጠጥ ነዉ የሚሆንብኝ! (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 129)፡፡   
ስምሽን ከሰብዕናሽ አስተባብረሽ - ሁለመናሽን ከፍቅር ጋር አዋህደሽ - እንደተወርዋሪ ኮከብ - በብርሃን ተደፍቀሽ - መንገዴን ባትሞይዉ ኖሮ ሕይወቴ ምነኛ ከንቱ በሆነ ነበር … (መንገድም ሕይወትም፣ 2009፡ ገጽ 295)፡፡
ስምሽ ባሕሪሽ ነዉ- - ስምሽና አካልሽ - አንዳቸዉ ከአንዳቸዉ አይቀዳደሙም- - ስምሽን ስጠራ ትመጫለሽ- - ዓለሜም ዘጠኝ ትሆናለች - አላልኩሽም ነበር! (ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 296)፡፡
ከአዘጋጁ፡- መኮንን ደፍሮ፤ ገጣሚ፣ ልብወለድ ጸሐፊ፣ ሃያሲና በዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን የአዲስ አድማስ ጸሐፊም ነው፡፡Read 5622 times